ኢትዮጵያ፡ የዛፍ ችግኝ የመትከል ዘመቻ ታሪካዊ ዳራ ምን ያሳያል?

ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ‘አረንጓዴ አሻራ’ በሚል ዘመቻ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድን ጨምሮ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የተለያዩ አካባቢ ነዋሪዎች በአገር አቀፍ ደረጃ ችግኝ ተክለዋል።
በዚህ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻም በአንድ ጀምበር ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል በሕንድ ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረ ወሰን ኢትዮጵያ መስበሯ ተዘግቧል። ለመሆኑ ችግኝን በዘመቻ መትከል መቼ፣ እንዴት እና በማን ተጀመረ?
ችግኝን በዘመቻ መትከል በሕዝቡ ነው የተጀመረው የሚሉት በአካባቢ ጥበቃ ላይ በርካታ ምርምሮችን ያደሩት ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገ/እግዚአብሔር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ከአንድ ሺህ ዓመታት በፊት ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ የዛፍ ችግኞችን የመትከል ልማድ ነበረው።
“የዛፍ ጠቃሚነትን ከማንም በላይ ሕዝቡ ይረዳ ነበር” የሚሉት ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ከዚያ በኋላ የዛፎች መቆረጥ በመብዛቱ እነርሱን የመተካት ጥረት ተጀመረ ይላሉ። ያ- ጥረትም እየተፋፋመ መጥቶ ዘንድሮ በስፋት የችግኝ ተከላ መካሄዱን ይገልጻሉ።
“ሕዝቡ አካባቢውን ያውቃል፤ ተነግሮት አይደለም አካባቢውን እንዲያውቅ የሚማረው፤ የአካባቢ እንክብካቤ ለዘመናዊው ትውልድ የተላለፈው ከሕዝቡ ነው። በመሆኑም ሕዝቡ ድሮም ቢሆን መትከል ባያስፈልገው ዛፎችን ይንከባከብ ነበር፤ አስፈላጊ ሆኖ ሲታየውም ችግኞችን ይተክል ነበር። መሬቱ እንዳይሸረሸርም እርከኖችን ይሰራ ነበር፤ ይህም አዲስ ነገር አይደለም” ብለዋል።
ይሁን እንጂ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ይኸው ባህል በዘመናዊነት ምክንያት መዳከሙን ገልፀው ወደፊት ወደ ነበረው ባህል የመመለስ ጥረት መጀመሩን ይናገራሉ።
በሺህዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የቆየን ባህል በዚህ ጊዜ ተጀመረ ማለት ባይቻልም በተለያየ ጊዜ እና ዘመናት ተመሳሳይ የችግኝ ተከላ ዘመቻዎች ይካሄዱ እንደነበር ግን ያስታውሳሉ- ዶ/ር ተወልደ ብርሃን።
“ከሺህዎች ዓመታት በፊት ሕዝቡ በራሱ ተነሳሽነት ነበር የሚተክለው ዘመቻውም ከታች ወደ ላይ ነበር፤ ከዚያ በኋላ ግን ዘመቻው ከላይ ወደታች ሆኗል” ይላሉ።
በዘመነ መሳፍንት ከነበረው የሥልጣን ሽኩቻ በኋላ ማዕከላዊ መንግሥት የጥንቱ የዛፍ ችግኞችን የመትከል ባህል እየተዳከመ ሲመጣ ወደነበረበት ለመመለስ ከላይ ወደታች ትዕዛዝ ማስተላለፍ እንደተጀመረ ያወሳሉ።
የተለያዩ ጥናታዊና ታሪካዊ ፅሁፎች ችግኝን በዘመቻ መትከል የተጀመረው በ14ኛው ክፍለ ዘመን በንጉስ ዘረ ያዕቆብ ዘመን እንደሆነ ያስረዳሉ።
ከሁለት ዓመታት በፊት Status, Challenge and Opportunities of environmental Management in Ethiopia በሚል በታተመ ጆርናል ላይ በንጉስ ዘረ ያዕቆብ ዘመን በዘመቻ ከተተከሉና ተጠብቀው ከቆዩ ደኖች ወፍ ዋሻ፣ ጅባት፣ መናገሻ እና የየረር ተራሮች ጥብቅ ደኖች ተጠቅሰዋል።
ከዚያም በኋላ አፄ ምንሊክ “ዘመናዊ” እፅዋትን ለኢትዮጵያ እንዳስተዋወቁ ይነገራል። በአገሪቱ ያለውን የማገዶና የቤት መሥሪያ ቁሳቁስ እጥረት ለመቀነስ የባህር ዛፍ ተክልን ከአውስትራሊያ እንዳስመጡ ይነገራል።
በወቅቱም የደን መጨፍጨፍን ለመከላከል “ሁሉም በግለሰብ መሬት ላይ ያሉ ዛፎች የመንግሥት ንብረት ናቸው” ሲሉ አውጀው እንደነበር በዚሁ ጆርናል ላይ ተጠቅሷል። ይህም ደኖች የህዝብ ሐብት እንደሆኑ በሕብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ ለመፍጠር አስችሏል።

ከዚያም በኋላ ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ መሪዎች የተለያዩ ስልቶችን እየተጠቀሙ ችግኞችን በዘመቻ ያስተክሉ ነበር።
“ቤተክርስቲያንና መስጊዶች ምን ጊዜም ዛፎችን የመጠበቅና የመንከባከብ ልማድ አላቸው፤ በእርሻና በተለያየ መልኩ ቦታው ቢፈለግም ዛፎችን ጠብቆ ማቆየት የተለመደ ነው” የሚሉት ደግሞ የኢትዮጵያ የአካባቢና ደን ምርምር ኢንስቲቲዩት ዳይሬክተር ዶ/ር አብዮት ብርሃኑ ናቸው።
በመንግሥት ደረጃ ችግኞችን አፍልቶ መትከል የተጀመረው ግን በአጼ ልብነ ድንግል ዘመን ነው ይላሉ ። በ16ኛው ክፍለ ዘመን አጼ ልብነ ድንግል ከወፍ ዋሻ ዘርና ችግኞችን ወስደው ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ በሚገኝ መናገሻ ሱባ የሚባል ሥፍራ የሃበሻ ጽድ መትከላቸውን ያነሳሉ።
ከዚያ በኋላ አፄ ምንሊክ ባህርዛፍን ከአውስትራሊያ በማስመጣት ተክለዋል ሲሉ ያወሳሉ። “ምን አልባት አጼ ሚንሊክ ባህር ዛፍን አዲስ አበባ ባያስመጡ ኖሮ አዲስ አበባ አሁን ያለችበት ቦታ ልትገኝ አትችልም ነበር የሚል እምነት አለኝ” ይላሉ።
በወቅቱ የአፄ ሚንሊክ ሠራዊትና በዙሪያቸው የነበሩት ሠራተኞች የማገዶ እጥረትና የቤት መሥሪያ ግብዓት ይገጥማቸው ነበር። ይህንንም ለመፍታት ንጉሡ ባህርዛፍ አስመጥተው ባያስተክሉ አዲስ አበባ ባለችበት ላትቀጥል ትችል ነበር ሲሉ ምክንያታቸውን ያስረዳሉ- በዘመኑ ነገሥታት በተለያዩ ምክንያቶች መናገሻቸውን ይለዋውጡ እንደነበር በማስታወስ።
አፄ ምንሊክ በፍጥነት ማደግ የሚችልና ራሱን በፍጥነት የሚተካውን ባህርዛፍን በአማካሪያቸው አማካኝነት እንደመረጡትም ይነገራል።
በዛፍ ችግኝ ተከላ ታሪካዊ ዳራ ላይ የተሰሩ ጥናቶችን የሚጠቅሱት ዶ/ር አብዮት አፄ ኃይለ ሥላሴ ችግኝን ለመትከልና ለመንከባከብ የደን አዋጅን በማውጣት በርካታ ሥራዎች ማከናወናቸውን ያስረዳሉ።
“አጼ ኃይለ ሥላሴ ችግኝ መትከልን እንደ አንድ የመንግሥት ሥራ አድርገው ይወስዱት ነበር” ይላሉ ዶ/ር አብዮት።

እርሳቸው እንደሚሉት አጼ ኃይለ ሥላሴ ደን መጠበቅና ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ ፓርኮች እንዲቋቋሙ ምክንያት ሆነዋል። አዋሽ ብሔራዊ ፓርክን በምሳሌነት ያጣቅሳሉ።
በደርግ ዘመነ መንግሥትም የአካባቢ ጥበቃን የተመለከቱ ፖሊሲዎች ተቀርፀዋል። ዋነኛ ትኩረታቸው ግን የዱር እንስሳት ጥበቃ ላይ እንደነበር ጥናቶች ያትታሉ።
በተለይ በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 1973/74 (1966 ዓ.ም) በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የተከሰተው ርሃብና ድርቅ፤ አካባቢ ጥበቃ ላይ ጠንክሮ ለመስራት ካነሳሱት ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ።
በአጠቃላይ ደን ሥራ ላይ ከፍተኛና የተቀናጀ ስራ ለመስራት ዝግጅት ተደርጎ፣ ቦታዎች ተመርጠው፣ ችግኞች ተፈልተው፣ ለማህበረሰቡ አነስተኛ ድጎማ በማድረግ፤ በተራቆቱ ቦታዎች ችግኞች እንዲተከሉ በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን ዶ/ር አብዮትም ያረጋግጣሉ።
በተራሮች ላይ በብዛት የሚታዩት ደኖችም በዚያ ዘመን የተተከሉ ናቸው ይላሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት የችግኝ መትከል ዘመቻዎችን ለማካሄድም በዋነኛነት ለሰዎች ማበረታቻዎችን በመስጠት፤ ለምሳሌ እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ቦታዎች የእርዳታ እህል ለመስጠት ችግኝ እንዲተክሉ ይደረግ ነበር።
“ለትምህርት ቤት ደብተር መግዣ ችግኝ ተክለን ገንዘብ ይከፈለን ነበር” ሲሉ የራሳቸውን ተሞክሮ ያነሳሉ።
በጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ጊዜ በተለይ ዋናው የትኩረት አቅጣጫ የአየር ንብረት ለውጥ በመሆኑ ችግኝ መትከልና አካባቢን መንከባከብ እንደ አንድ ትልቅ ሥራ እንዲወሰድ በርካታ ሥራዎች ይከናወኑ ነበር።
ይህ ወቅት የልማትና የአካባቢ ጥበቃ ተቋማት የተመሠረቱበትም ነው። በፖሊሲ ደረጃም ሥነ ምህዳርን፣ አካባቢን፣ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃን በሚመለከት ግብ ተቀምጦለት እንቅስቃሴ የተጀመረበት ነው።
በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያን እየመሩ ያሉት ዶክተር ዐብይ አሕመድም ‘አረንጓዴ አሻራ’ በሚል የተደረገው አገር አቀፍ የችግኝ መትከል ዘመቻ እየተካሄደ ነው።
ዘመቻው በፍላጎት ላይ የተመሠረተ እና በስፋት በርካታ ችግኞች መተከላቸው ቀደም ካሉት ዘመናት ልዩ ያደርገዋል ሲሉ ዶ/ር አብዮት አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
በጥንታዊው ዘመን በሕዝቡ ተነሳሽነት የሚደረገው ችግኝ የመትከል ዘመቻ አሁን ላይ በመንግሥት አነሳሽነት መካሄዱ ብዙዎችን ያነጋግራል። ሕዝቡ ራሱ አውቆ ነው መትከል ያለበት፤ ዘመቻ አያስፈልግም በሚል።
ይህንኑ ያነሳንላቸው ዶ/ር አብዮት “ከከተሞች መስፋፋትና ሥልጣኔ ጋር ተያይዞ ችግሮቹ እየገነኑ ሲመጡ ማህበረሰቡ የባህርይ ለውጥ ማሳየቱ የሚፈረድበት አይደለም” ሲሉ ይመልሳሉ።
በመሆኑም ማህበረሰቡን ማነሳሳትና ወደ ቀደመው ባህሉ ማሻገር እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ።
ባሳለፍነው ሰኞ በአንድ ጀንበር የተተከሉት ከ350 ሚሊየን በላይ ችግኞች በእርሳቸው ሙያዊ ስሌት 80 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን በዚህ ዓመት ሊተከል የታቀደው አራት ቢሊየን ችግኝ ደግሞ አንድ ሚሊየን ሄክታር መሬት ሊሸፍን እንደሚችል ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ችግኙ ፀድቆ ደን መሆን ሲችል የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በአንድ በመቶ ሊያድግ እንደሚችል ይገምታሉ- አንድ በመቶ በደን ሽፋን ሂሳብ ከፍተኛ መሆኑን በመግለፅ።
የደን ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን የሚናገሩት ዶ/ር አብዮት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ባለፉት አምስት ዓመታት 15.5 በመቶ እንደሆነ ያስረዳሉ።
በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በአውሮፓውያኑ 2020 የደን ሽፋንን 20 በመቶ ለማድረስ መታቀዱን አስታውሰዋል።
ከ80 ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 40 በመቶ እንደነበር ጥናቶች እንደሚያሳዩ የሚናገሩት ዶ/ር አብዮት ምን ያህል የደን ሽፋን እንደሚያስፈልግ ጣራ ሊሰራለት እንደማይገባ ይናገራሉ።
በኢትዯጵያ በአጠቃላይ 6027 የእፅዋት ዝርያዎች እንደሚገኙም ዶ/ር አብዮት ነግረውናል።