August 6, 2019

Source: https://mereja.com/amharic/v2/135235

ወይዘሮዋ ጥፋት ምንድነው ? (ምንሊክ ሳልሳዊ )

አፈር ልሶ ለመነሳት የሚንደፋደፈው ሕወሓት ካድሬዎቹን የጭቃ ጅራፍ አሸክሞ የዘር ፖለቲካ ካርዱን ስቦ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ ላይ አዝምቷል ። ፌዴራል መንግስቱ ይህንን ለማርገብ የኢንሳውን ቢኒያምን ጨምሮ የሕወሓት ወንጀለኞችን በዋስ እንደሚለቅ ተሰምቷል። ምን ያለበት ዝላይ አይችልም እንደተባለው አውራ ወንጀለኞችን የደበቀው የትግራይ ክልል ሕወሓት የሕግንና የፍትሕ ግንዛቤ ማስጨበጫ ላይ ወይዘሮዋ የተናገሩት ንግግርን ፖለቲካዊ እደምታ በመስጠት አላስፈላጊ እሰጥ አገባዎችን እየፈጠረ ነው።

በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሙስና የሚፈለጉ የሕወሓት ቱባ ባለስልጣናት ጉዳይን ሕወሓት ፖለቲካዊ አድርጎ ማስቀመጡ የሞራል ዝቅጠትን ያሳያል ። ወይዘሮ መአዛ ሕግን የማስከበር ስልጣን እስከተጣቸው ድረስ ወንጀለኞችን የመያዝ መንግስታዊ ግዴታ እንደሆነ መግለፃቸው ትክክለኛ ናቸው ። ወይዘሮዋ ይህንን የተናገሩት ከተሳታፊዎች የፍርድ ቤትን ትእዛዝ መከበርና ውሳኔ አፈፃፀም አስመልክቶ የቀረበ ጥያቄ ለመመለስ የጠቀሱትን የአሜሪካንን ተሞክሮ አስታኮ ሕወሓትና ጭፍሮቿ እያለቃቀሱ መታየታቸው ለሕግ ተገዢ ላለመሆን ያላቸውን ፍላጎት ከማሳየቱም በላይ ወንጀለኞችን ታቅፈው ለመኖር ያላቸውን ፍላጎት ያሳያል።

ሕወሓት ከላይ በኤርትራ ከታች በፌዴራል መንግስቱ መንጋጋ ስር በመግባቷ የትግራይ ሕዝብን ድጋፍ ለማግኘት የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም። ሕወሓት የፍርድ ቤት ውሳኔዎች እና ትእዛዞች እንዲፈፀሙ የሚያዘውን ሕግ ሳታከብር ወይዘሮ መአዛን መተቸት አትችልም ። የወይዘሮዋ ንግግር ሁሉንም ክልሎች የሚመለከት እና ግልፅ ነው ። የፍትሕን ጉዳዮች በተመለከተ የበለጸጉ አገሮች ያሳለፉትን ተግዳሮቶች ለተሞክሮ ማንሳት ተገቢ ነው ። የወይዘሮዋ ጥፋት አይታየኝም ።

MinilikSalsawi