August 6, 2019
Source: https://mereja.com/amharic/v2/135230

BBC Amharic : የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ አርብ ሐምሌ 26 ቀን 2011 ዓ.ም የሕግና የፍትህ ግንዛቤ ማስጨበጫ ጉባዔ ላይ የጠቀሱት ምሳሌ መነጋገሪያ ሆኗል።
ፕሬዝዳንቷ ምሳሌውን የሰጡት አንድ ግዛት የፍርድ ቤት ውሳኔን አልቀበልም ካለ በኃይል ማስከበር እንደሚያስፈልግ ለመግለፅ ከወደ አሜሪካ አንድ ተሞክሮ በመምዘዝ ነበር።
ምሳሌው፤ በአሜሪካ በ1950ዎቹ የነጮችና የጥቁሮች የትምህርት እድልን አስመልክቶ ከጥቁሮች የቀረበውንና ፍርድ ቤት የወሰነውን ግዛቷ አልቀበልም በማለቷ በወቅቱ አገሪቷን ያስተዳድሩ የነበሩት ፕሬዚደንት ድዋይት አይዘንአወር ውሳኔውን ለማስፈፀም ኃይል መጠቀማቸውን የሚገልፅ ነበር።
ታዲያ ይህ የፕሬዚደንቷ ንግግር የትግራይ ክልል ላይ ያነጣጠረ ነው ያሉ ወገኖች ነበሩ።
በወቅቱ በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የትግራይ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ አማኑዔል አሰፋ ጉባዔው የተጠራው የፍትህ አካላት፤ ፖሊስ፣ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ማረሚያ ቤትና ከፍትህና ከሕግ ዘርፍ ተያያዥ ጉዳዮች የሚሰሩ አካላት የያዘ እንደነበር ያስታውሳሉ።
በተለያየ ጊዜ በክልልም ሆነ በፌደራል ደረጃ እየተገናኙ የሚሰጠውን የፍትህና የሕግ ዘርፍ አገልግሎት እንደሚገመግሙና እቅድ እንደሚያወጡ የሚናገሩት አቶ አማኑኤል የአሁኑ መድረክ ግን ፖለቲካዊ ሃሳቦች የተነሱበት ነው ይላሉ።
የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለ፤ ዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ በሰላም መስራት አይችሉም፤ የሕግ የበላይነት አይከበርም፤ በመሆኑም የራሳችን ሥራ ላይ ትኩረት አድርገን እንወያይ የሚል ሃሳብ ቢቀርብላቸውም ፕሬዚዳንቷ ለመቀበል ዝግጁ እንዳልነበሩ አቶ አማኑኤል ይናገራሉ።
“እንደውም በውይይቱ ላይ መገኘት የሌለባቸው አካላትም ተገኝተዋል” ሲሉ ጥያቄ ሲያቀርቡ ያዩዋቸውን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ የሚመሩትን ግደይ ዘርዓፂዎንን ይጠቅሳሉ።