Aug 5 at 9:40 PM
በአንድ መጽሀፍ ዉስጥ በጨቋኝነት አለ የተባለዉ አማራ እንደገና የለም ይባላል
——————
ፕሮፌሰር መስፍን አገዛዝን : ባህልን: አምባ ገነንነትን እና ዲሞክራሲን በአንድ ላይ አዳብለዉ ፋይዳቸዉን ለመተንተን በሞከሩበት መጽሃፋቸዉ ዉስጥ አንድ ማጣቀሻ የምርምር ጽሁፍ ተጠቅመዋል::ይሄም ማጣቀሻ የምርምር ጽሁፍ የራሳቸዉ ስራ ነዉ::ማጣቀሻ ጽሁፉን ሲያትቱት እንዲህ ይላሉ” በ1950ቹ ዉስጥ በሶማሌ ክልል አንድ ምርምር አንድርጌ ጽሁፍ አሳትሜ ነበር::በጽሁፌም በግልጽ እንዳስቀመጥኩት የአማራ ገዥዎች ሶማሌዎችን እየጨቆኑ ስለሆነ ሶማሌዎች በጣም ቅሬታ አላቸዉ::ይሄ ነገር ካልተስተካከለ ለሀገሪቱ አስጊ ነዉ” ሲሉ ያትታሉ:: እናም እዚህ ጋ ፕሮፌሰር መስፍን አማራን አገኙት::አማራ አለ::ከመኖርም ዘሎ ተደራጅቶ መንግስት ተቆጣጥሮ ሌሎች ነገዶችን የሚጨቁን ሀይል ነዉ::ዋናዉ ነጥብ በራሳቸዉ በፕሮፌሰር መስፍን አንደበት አማራ አለ ማለት ነዉ::ከዚሁ አገዛዝን : ባህልን: አምባ ገነንነትን እና ዲሞክራሲን በሚያትተዉ መጽሃፋቸዉ ጋር ደግሞ ሌላ መጽሃፍ አዳብለዉ አሳትመዋል::በጀርባዉ አንድ መጽሃፍ ከፊቱ ደግሞ አንድ መጽሃፍ በአንድ ጥራዝ አድርገዉ አሳትመዋል:: እናም ሌላዉ መጽሃፍ ደግሞ የክህደት ቁልቁለት የሚል ነዉ::ይሄ መጽሃፋቸዉ ደግሞ በ1984 ከመለስ ዜናዊ ጋር ቁጭ ብለዉ የተከራከሩትን ክርክር ለማምብራራት የሚፍጨረጨር ነዉ::በዚህኛዉ መጽሃፋቸዉ በ1984 ዓም አማራ የለም ብለዉ እንዳተቱ ሁሉ አሁንም አማራ የሚባል ህዝብ የለም ብለዉ ይከራከራሉ::
————————
በ2011 ዓም በዘወርዋሬ አማራ ማንነታቸዉን የነገሩን ፕሮፌሰር መስፍን
—————————-
ፕሮፌሰር መስፍን ስለማንነታቸዉ ምን አሳስቧቸዉ እንደሆነ ባይታወቅም ሰሞኑን ባሳተሙት ጽሁፍ እራሳቸዉን በማስተዋወቅ ጀምረዋል::
“ይድረስ ለሰብአ ትግራይ” በሚል ርዕስ በጻፉት ጽሁፍ ስለ ማንነታቸዉ ሲያብራሩ “በመጀመሪያ ራሴን ላስተዋውቅ፡ የተወለድሁት አዲስ አበባ ስድስት ኪሎ አካባቢ ነው፤ ዘመኑም 1922 ዓ. ም. ነው፤ የአገዛዝ የመንግሥት ለውጥ የተደረገበት ዘመን ነበር፤ አባቴ አቶ ወልደ ማርያም እንዳለ (ከአንኮበር፣ ሸዋ፤) ፣ እናቴ ወይዘሮ ይመኙሻል ዘውዴ (ከየጁ፣ ወሎ፤) ናቸው፤ ሚስቴ የነበረችው በአባትዋ ሸዋ (መርሐቤቴ) በእናትዋ ትግራይ (አድዋ፣ እንትጮ፤) ነች” ሲሉ ሀተታ አቅርበዋል::እንግዲህ በራሳቸዉ አባባል ፕሮፌሰር መስፍን የአንኮበር እና የጁ ማንነት መሰረታቸዉ ከትዉልድ አዲስ አበባ ከባቢያዊ እሴት ጋር ተጣምሮ ያገኙት ማንነት አለ ማለት ነዉ::ጥያቄ እንጠይቅ? ለመሆኑ ፕሮፌሰር መስፍን አባታቸዉ አማራ መሆናቸዉን ሳያዉቁ እንዴት አድርገዉ አንኮበሬ መሆናቸዉን እንዴት አወቁ? ስላቁ የሚጀምረዉ እዚህ ጋ ነዉ:: ለመሆኑስ በመጽሃፋቸዉ የሶማሌ ነገድን ይጨቁናሉ: ያሏቸዉ የአማራ ገዥ ሲሉ የፈረጇቸዉ ሰዎች በብዛት ከአንኮበር እና ከቀሪዉ ሸዋ ናቸዉ የሚለዉን ትርክት የተቀበሉት ፕሮፌሰር መስፍን ሶማሌን የጨቆኑ አማሮች ማንነት ሳይጠፋቸዉ እንዴት የራሳቸዉ ማንነት ጠፋቸዉ? ነገሩ ስላቅ ነዉ:: ነገሩ ከስላቅም በላይ ፕሮፌሰር መስፍን የራሳቸዉን አማራ ማንነት በገደምዳሜ እና በዘወርዋሬ መግለጻቸዉ ነዉ:: እኔም አማራ ነኝ::አማራ የለም ብለሃል አትበሉኝ ማለታቸዉ ነዉ::————————
ፕሮፌሰር መስፍን ኢትዮጵያዊነትን ለመስበክ የተከተሉት መንገድ
————————–
ፕሮፌሰር መስፍን ኢትዮጵያዊነትን ለመስበክ የተከተሉት መንገድ የመነጨዉ በ1984ዓም ከትግራይ የበቀሉት ህዉሃታዉያን ኢትዮጵያዊነትን ክደዉ ኢትዮጵያ የሚባለዉ ሀገር 100 አመት ታሪክ ያለዉ ህዝብ ነዉ የሚል ክርክር ይዘዉ ሲመጡ ያንን የሀሰት አስተሳሰብ ለመቃወም አስበዉ ያደረጉት እንደሆነ መገመት ይቻላል::ግን ቀጥታ ኢትዮጵያዊነትን ከመስበክ ይልቅ የተከተሉት አጓጉል መንገድ እና ጠመዝማዛ መንገድ መሳለቂያ አድርጓቸዋል::———————————-
ኢትዮጵያዊ ማንነት በማባበል አይሰበክም
——————————–
እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ሁሉ ሴረኞችን: ኢትዮጵያዊነት ጠሎችን ለማሳመን የራስን ንኡስ ማንነትን በመካድ ማሳመን ይቻላል ብለዉ እንዘጥ እንተፍ የሚሉ የአማራ ምሁራን ቁጥር ብዙ ነዉ::ኢትዮጵያዊነትን ማንንም በማባበል ማሳመን ወይም መስበክ አያስፈልግም::ምክንያቱም ኢትዮጵያዊነትን ለኢትዮጵያዊ ሁሉ የሰጠዉ እራሱ እግዚአብሄር ነዉና::የሚቀበለዉ ኢትዮጵያዊ መልካም አደረግ::የማይቀበለዉም ኢትዮጵያዊ መብቱ ነዉ:: ከእዉነቱ ስትቆረጥ ይዘህዉ የምትመጣዉ ትንታኔ ሁሉ ሀስት እና እርስ በርሱ የሚምታት ነዉ::ኢትዮጵያዊነት ተፈልጎም የማይገኝ ማንነት ነዉ::ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለዉ ህዝብ እንኳን ቢጥለዉ ሌላ ወገን ያነሳዋል::ጥቁሩ አለም የነጻነት: የ እኩልነት: በእግዚአብሄር መንፈስ መወደድን እና በ እግዚአብሄር አይን የታወቀ ህዝብ መሆኑን ማረጋገጫ ቢፈልግ የሚያገኘዉ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ነዉ::ስለዚህ ዛሬ ኢትዮጵያ የተባለዉ ህዝብ ኢትዮጵያዊነትን አዉልቆ ቢጥለዉ ሌላዉ ወገን አንስቶ ይልብሰዋል::ስለዚህ የማንንም ዘረኛ እና ጎጠኛ ከማባበል ይልቅ ኢትዮጵያዊነትን ቀጥ አድርጎ መስበክ ይገባል::ይሄም ኢትዮጵያዊነት የ እግዚአብሄር ልጅነት ነዉ::ይሄም የ እግዚአብሄር ልጅነት ለክርስቲያን ወይም ለ እስላም አለዚያም ለኢ አማኝ የተሰጠ ሳይሆን ለኢትዮጵያዊ ሁሉ የተሰጠ ነዉ::ይሄም ማለት ኢትዮጵያዊነት ነጻነት እኩለነት እና ወንድማማችነት ማሳያ ነዉ::ኢትዮጵያዊነት የ እግዚአብሄር ልጅነት ነዉ ሲባል ማጠዬቂያ እና ማሳያ ነዉ እንጂ ሌላዉ የአዳም ልጅ የ እግዚአብሄር ልጅ አይደለም ማለት አይደለም::ጠማማ ህሊና ያላቸዉ እና ኢትዮጵያዊነትን የሚጠሉ ሰዎች ይሄ ሁሉ ቢነገራቸዉ አይገባቸዉም እና እንደ መሰላቸዉ እንዲሄዱ መተዉ ይገባል::ኢትዮጵያዊነትን ለመስበክ ይሄን ያህል ግራ የሆነ ነገር የለዉም ::ኢትዮጵያዊነትን እግዚአብሄር እራሱ ነዉ “ኢትዮጵያዊ ልጄ” ያለዉ::ኢትዮጵያዊ የእግዚአብሄር ልጅነቱ ተገልጾ: መልክዓ ምድሩ በግልጽ ተጠቅሶ: መልኩ ተነግሮ: የታቦተ ጺዮን መሪ ህዝብ መሆኑ ተነግሮ: እነ ሙሴን አመራር ያስተማሩ ካህናት መሪዎች ያለዉ ህዝብ መሆኑ ተተርኮ በታላቁ መጽሃፍ ተቀምጧል::ኢትዮጵያዊ በፍትህ አዋቂነቱ ሳይቀር በነቢዩ መሃመድ ሳይቀር ተተርኮለታል::ኢትዮጵያዊ ማንነት የታወቀ እና የሁሉም ኢትዮጵያዉያን የጋራ ማንነት ነዉ::ይሄም ሆኖ ግን እያንዳንዱ ነገድ የየራሱ ንኡስ ማንነቶች አሉት::እነዚህም በቋንቋ: በባህል: በእምነት ልዩነቶች የኢትዮጵያዊዉ ዝንጉርጉርነት የሚገለጸበት መገለጫዉ ናቸዉ:: ፕሮፌሰር መስፍን ይሄ አይጠፋቸዉም::የሆነ ሆኖ አክራሪ ቡድኖች ይሄን በግልጽ እና በገሃድ የተቀመጠ ኢትዮጵያዊ ማንነት እንዳይክዱት በመስጋት ዋናዉን ጭብጥ የለቀቀ ህሳቤ ማራመድ የትም እንደማያደርስ ከፕሮፌሰር መስፍን መማር መልካም ነዉ::አለዚያ በ1950ቹ አማራ አለ: በ1980ቹ አማራ የለም: በ2011 ዓም ደግሞ አባቴ አንኮበሬ እናቴ የጁ ናት ብሎ በዘወርዋሬ እኔም አማራ ነኝ ማለትን ያስከትላል::ቁምነገሩ አማራ መሆን ወይም አለመሆን አይደለም::አማራነት: ትግሬነት: ኦሮሞነት ወይም የየትኛዉም ነገድ አባል መሆን ቁም ነገር አይደለም::ሌላዉ ቀርቶ ኢትዮጵያዊ ወይም ጋናዊ አለዚያም አሜሪካዊ መሆን ቁም ነገር አይደለም::ሰዉ አንድ ነዉ::አንድ ነገድ ነዉ::እግዚአብሄር ለዚህ አንድ የሰዉ ነገድ ” አንተ ትንሽ ነገድ አትፍራ” የሚል ማጽናኛን የሰጠዉ የሰዉን ነገድ አንድነት እና በጋራም በምድር የመኖር እድል ሲያጠይቅ ነዉ:: ሰዉ አንድ ነገድ ነዉ::ዋናዉ የዚህ ጽሁፍ አላማ ግን እናዉቃለን የሚሉ ሰዎች እንዴት ነገሮችን እንደሚያበለሻሹ ለማሳዬት ነዉ::በ1950ቹ: 60ቹ:70ቹ:80ቹ:90ቹ እንዲሁም እስካሁን በአማራ ነገድ ላይ በተደረገበት የቅኝ ገዥ ነዉ : ጨቋኝ ነዉ የሚሉ ቅስቀሳዎች ይሄ ነገድ አምስት ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ እንዲያልቅበት ተደርጓል::ለዚህ ቅስቀሳ እና ክስ ደግሞ ፕሮፌሰር መስፍን የራሳቸዉን ሚና እንደተጫወቱ በራሳቸዉ አንደበት መስክረዉልናል:: ሆኖም አማራዉ በተደረገበት ቅኝ ገዥ ነዉ: ጨቋኝ ነዉ በሚለዉ ቅስቀሳ ዘሩ እየተለቀመ መታረድ እና መፈናቀል መሳደድ ሲደረግበት ፕሮፌሰር መስፍን አማራ የሚባል ህዝብ የለም ማለት ጀመሩ::አሁን ደግሞ በመጨረሻ እድሜያቸዉ እራሳቸዉም ከአማራ ወገን መሆናቸዉን በተዘዋዋሪ አስተዋወቁን:: ይሄ ሁሉ ዙሪያ ጥምጥም ምን ማለት ይሆን?—————–
ማጠቃለያ
———————–
ፕሮፌሰር መስፍን አገዛዝን : ባህልን: አምባ ገነንነትን እና ዲሞክራሲን በአንድ ላይ አዳብለዉ ፋይዳቸዉን ለመተንተን በሞከሩበት መጽሃፋቸዉ ዉስጥ አንድ ማጣቀሻ የምርምር ጽሁፍ ተጠቅመዋል::ይሄም ማጣቀሻ የምርምር ጽሁፍ የራሳቸዉ ስራ ነዉ::ማጣቀሻ ጽሁፉን ሲያትቱት እንዲህ ይላሉ” በ1950ቹ ዉስጥ በሶማሌ ክልል አንድ ምርምር አንድርጌ ጽሁፍ አሳትሜ ነበር::በጽሁፌም በግልጽ እንዳስቀመጥኩት የአማራ ገዥዎች ሶማሌዎችን እየጨቆኑ ስለሆነ ሶማሌዎች በጣም ቅሬታ አላቸዉ::ይሄ ነገር ካልተስተካከለ ለሀገሪቱ አስጊ ነዉ” ሲሉ ያትታሉ:: እናም እዚህ ጋ ፕሮፌሰር መስፍን አማራን አገኙት::አማራ አለ::ከመኖርም ዘሎ ተደራጅቶ መንግስት ተቆጣጥሮ ሌሎች ነገዶችን የሚጨቁን ሀይል ነዉ::ዋናዉ ነጥብ በራሳቸዉ በፕሮፌሰር መስፍን አንደበት አማራ አለ ማለት ነዉ:: ዞረዉ ግን አማራ የሚባል ህዝብ የለም ሲሉ ተናገሩ::በ2011 ዓም ግን የራሳቸዉን አማራነትም ፈልገዉ አገኙት::