August 11, 2019

የኢዜማ መሪ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ፣ “ፖለቲካና ሀገር የሚለየው በዚህ ነው፡፡ ሀገርን አረንጓዴ ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት ነው። …የኢዜማ አባላት እዚህ መጥታችሁ ችግኝ በመትከላችሁ ትልቅ ነገር ነው ያረጋችሁት፡፡ ወደፊትም አጠቃላይ ሀገራችንን የሚመለከት የጋራ ነገር ከሰላም ጀምሮ ይሄን ዓይነት በረሃማነት ለመከላከል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ በንቃት ትሳተፋላችሁ ብዬ ተስፋ አምናለሁ” ሲል በችግኝ ተከላው ለተሳተፉ የኢዜማ አባላት መልእክት አስተላልፈው ነበር።

ኢዜማ ለአገር በሚጠቅሙ ጉዳዮች ከማንም ጋር አብሮ መስራቱ ሊያስመሰግነው እንጂ ሊያስወqሰው አይገባም።ፖለቲካችን ምክንያታዊ መሆን አለበት። ከአሁን ለአሁን አራት ኪሎ ያሉትን ስለምንቃወም ብቻ፣ ለአገር የሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ፊታችንን ማዞር ተገቢ አይመስለኝም።TIME Leaders: Abiy Ahmedx

ሆኖም ምክንያታዊ ፖለቲካ፣ በምክንያት መደገፍና መተባበርን እንደሚያበረታታው በምክንያት መቃወምን ያካትታል። የችግኝ ተከላ ላይ መሳተፍ በምክንያት ተገቢ እንደሆነው፣ በአገራችን የሰብአዊ መብት ረገጣ ሲፈጸም፣ ዜጎች በጅምላ ሲታሰሩ፣ ሲፈናቀሉ፣ ሀሳብን የመናገርና የመጻፍ መብቶች ሲገደቡ ዝም መባል የለበትም።

ኢዜማ ሰባዊ መብት ሲረገጥ ዝም ማለቱ፣ ድርጅቱ ምክንያታዊ ፖለቲካ አራማጅ ሳይሆን አደርባይና አጨብጫቢ ድርጅት መሆኑን አመላካች ነው። በችግኝ ተከላው እንዳየነው፣ ኦህዴድን ለመደገፍ፣ ለማገዝና ለመተባበር የፈጠነው ኢዜማ፣ የዜጎች መብት ሲጨፈለቅ፣ለዜጎች ለመቆም ድፍረት ማጣቱ በዴሞክራሲያዊ መርህ የሚመራ ድርጅት እንዳልሆነ፣ የሚያሳይ ነው። የኢዜማ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፊ በርዪት ሜድያ ላይ፣ “አምንስቲ ኢንተርናሽናል፣ የአለም አቀፍ ጋዜጠኞች ማህበር ሲፒጂና ሌሎች በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያለውን የጅምላ እስርና የሰብአዊ መብቶች ረገጣ እንዳሳሰባቸው እየግለጹ ነው። ኢዜማ ለምንድን ነው ዜጎች በጅምላ ሲታሰሩ ዝም የሚለው ?” ተብለው ተጠይቀው ነበር። የሰጡትን መለስ አስደንጋጭ ብቻ ሳይሆን አሳፋሪም ነበር። “እኛ የሰብአዊ መብት ተከራካራኢዎች አይደለንም” የሚል ምላሽ ነበር የሰጡት።

በአሁኑ ጊዜ እንደ ባላደራውና አብን ያሉ ሰላማዊ የሆኑ ድርጅቶች፣ የአሃዱ፣ የአስራትና የኢትዮጲስ ጋዜጠኞች፣ “ሽብርተኛ” እየተባሉ በኦህዴዶ እየታደኑ ናቸው። ባላደራው በቦሌና ቃሊት/አቃቂ ክፍለ ከተሞች ህዝባዊ ስብሰባ እንዳያደረግ ታግዷል። በራስ ሆቴል፣ ኢትዮጵያ ሆቴል ፣ ሂልተን ሆቴል …ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳይሰጥ ተደርጓል። ዜጎች በአገራቸው በነጻነት የመሰብሰብና የመናገር መብታቸው እየተረገጠ ነው። ኦህዴድን መቃወም ወንጀል እየሆነ ነው። ዛሬ ባላደራዎች ላይ እየሆነ ያለው ነገር እነርሱ ላይ ሊመጣ እንደሚችል ኢዜማዎች የዘነጉት ይመስለኛል።

ይሄን ብዬ ከስምንት አመታት በፊት የአሁኑ ኢዜማ የቀድሞ ግንቦት ሰባት መሪ ተናግረውት የነበረ አንድ ነጥብ ላንሳና ጽሁፌን ልቋጭ።

ያኔ የመለስ ዜናዊ አስተዳደር የአባይን ግድብ ለመገንባት በተነሳ ጊዜ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ፕሮጀክቱን በቀዳሚነት ከሚቃወሙ ፖለቲከኞች መካከል አንዱ ነበሩ። “ከአባይ በፊት የሰብዓዊ መብት ረገጣ ይገደብ” በሚል፣ አገራዊ ፕሮጀክት ቢሆንም፣ የመለስ ዜናዊ አስተዳደርን ለመደገፍ ፍቃደኛ አልነበሩም። ፖለቲካንና ሀገርን ያኔ መለየት ተስኗቸው ነበር።

ታዲያ የኢዜማ መሪ በችግኝ ተከላው ሲሳተፉ፣ ፖለቲካና አገር ልዩ ናቸው በሚል ሳይሆን በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ደጋፊ ምን አላባት “አካል” ስለሆኑ ነው ቢባል እንደ ስህተት ሊቆጠር ይችላልን ? ትላንትና እነ መለስ ዜናዊ ሰብአዊ መብትን እየረገጡ “አባይ” ሲሉ እየተቃወምንም፣ አሁን ኦህዴዶች እነርሱም ሰብአዊ መብት እየረገጡ “ችግኝ” ሲሉ መደገፍ የስለጠነ ምክንያታዊ ፖለቲካ ሳይሆን የግብዝንነትና የአደባይነት ፖለቲካ አይደለምን ? እንግዲህ የኢዜማ ችግር ይሄ ነው። እንዲህ አይነት መሪ ያለው ድርጅት ነው።

በነ መለስ ዜናዊ ጊዜ ብዙዎቻን ከነ ዶ/ር ብርሃኑ ባልተናነሰ እንደዉም በበለጠ የሕወሃት አገዛዝ እየፈጸመ ያለውን የሰብአዊ መብት ረገጣ ስናጋልጥን ስንታገል ነበር። እኔን ብትወስዱ አንድ አፍታም የዜጎችን መብትና ደህንነት በተመለከተ የተደራደርኩበትና ያጎበደድኩበት ጊዜ አልነበረም።

ሆኖም የሕወሃት አገዛዝ ለሰራቸውም መልካም ስራዎች እውቅና ከመስጠትም አልተቆጠብኩም። በተለይም በአባይ ዙሪያ እነ ዶ/ር ብርሃኑ ያሰሙት የነበረውን ተቃዉሞ አገርን ማስቀደም አይደለም ብዬ ስቃወመው ነበር። ከዘጠኝ አመት በፊት፣
“The Politics of the Niles” በሚል ርእስ ፣ “Surely some of the local policies of the Zenawi regime are not helping to unify Ethiopians for a common cause. In view of the unhelpful track record the regime has domestically, the critical and bitter opposition some are exhibiting against the regime is understandable. However, political differences must not blind us from looking at the long term interests of Ethiopia. Mr. Zenawi will go tomorrow. Ethiopia will be there for generations yet to come” ነበር የጻፍኩት የመለስ ዜናዊ አስተዳደር በአባይ ጉዳይ መደገፍ እንዳለበት በማስረገጥ።

አሁንም የዶ/ር አብይ አስተዳደር ሕዝብንና አገርን ለመጥቀም የጀመረዉን የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ እደግፋለሁ። ብዙ መስተካከል፣ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች አሉ። ቢሆንም ግን ፖለቲካ ከአገር መለየት አለበት። ዶ/ር አብይን ስለምንቃወም ህዝብን የሚጠቅም ስራ ከመስራት መከልከል የለብንም የሚል ጠንካራ አቋም አለኝ። በዚህ በዳያስፖራ ትረስፈንድ ዙሪያ በስፋት ወደፊት እመለስበታለሁ።

http://onethiopia.blogspot.com/…/politics-of-nile-girma-kas…

http://onethiopia.blogspot.com/…/politics-of-nile-girma-kas…

(ስለኢዜማ ስጽፍ፣ እንደ ድርጅት ነው። የኢዜማ አባላትና አመራሮች አሉ፣ በግልሰብ ደረጃ በ ጅምላ እስር ዙሪያ ተቃውሟቸውን የሚያቀርቡ፣ በፍርድ ቤቶች እየተመላለሱ የ እሰረኞችን ጉዳይ የሚከታተሉ …ለነዚህ የኢዜማ አመራሮችና አባላቶች ትልቅ ክብር አለኝ። ግን እንደ ድርጅት ኢዜማ አሳዛኝ ድርጅት ነው)