‹‹ትውልድ አይደናገር እኛም እንናገር›› ቅፅ 1

(አዲስ አበባ፣ አንድ ቤተሰብ፣ አብዮቱ እና ኢህአፓ (1877- 1970) አንዳርጋቸው ፅጌ)

መፅሐፍ፡- ‹‹ትውልድ አይደናገር እኛም እንናገር›› ቅፅ 1
ደራሲ፡- አንዳርጋቸው ፅጌ)
ገጽ፡-  644
ሃያሲ፡- ፀ/ትፂዮን ዘማርያም

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጊዜውን ስውቶ ያውም በእስራት ላይ እያለ የጻፈውን መጽሐፍ ሳነብ ደስ አለኝ፣ ደስ ያለኝም መጽሐፉ መጥፎ ነው ጥሩ ነው ከሚል ሳይሆን መፈታቱን እንኳን የማያውቀው ደራሲ ለመጭው ትውልድ የሚሆን ትረካ ትቼ ልለፍ በማለቱ ነው፡፡ በድጋሜ ለዚህ ለቁርጠኛ ሃሳቡ ምስጋና ሊሰጠው ይገባል ብዬ ኣስባለሁ፡፡ ይህንን ካልኩ በኋላ አቶ አንዳርጋቸው በእስራት ላይ እያለ ሁሉን ያስታውሳል ማለት ግን የነበረበትን ሁኔታ አለመረዳት ይመስለኛል፡፡ መጽሐፉን በስሜት አነበብኩት፡፡ ለምን ቢባል? ታሪኩ የዛን ጊዜ ወጣቶች ታሪክን ያካተተ ስለሆነ ይህም እኔንም እንደገለሰብ አካባብዬ ያሉትን እንደ ቤተሰብ የሚመለከት ሆኖ ስላገኘሁት ነው፡፡

አቶ አንዳርጋቸው በዚህ መጽሐፍ በገጽ 71 እስከ 82 ድረስ ባለው ‹‹ምዕራፍ 2. አዲስ አበባ የወታደሮች፣የባሪያዎች እና የሴተኛ አዳሪዎች ከተማ›› በሚል ርዕስ በሚል የፃፈው ታሪክ ከታሪክ እውቀት አንፃር Inductive Reasoning ከደቂቅ ወደ ልሒቅ/ ከተናጥል ወደ አጠቃላይ ማለትም ከኢትዮጵያ ወደ ዓለም ታሪክ የባሪያ ንግድ ዘመን የነበረውን ዘግናኝ ታሪክ ነጮቹ ባሪያ ፈንጋዬች በአፍሪካ ያመጡት የጊዜ ቦንብ መሆኑን አስረግጦ መግለፅ ነበረበት እላለሁ፡፡

የባርያ ንግድ ዘመን Slave trade ከምዕራብ አፍሪካ የባህር ዳርቻ አገራቶች ይኖሩ የነበሩ ዜጎችን አስገድዶ በባርነት በመፈንገልና በመሸጥ የባርነት ንግድን ጀመሩ፡፡ የአውሮፓ አሕጉር በዛን ዘመን በአገራቸው ውስጥ ሰፋፊ የግብርና እርሻ ልማት ሠራተኞች በማሰማራት ለኢንዱስትሪ ዘርፍ ግብዓት (ጥጥ ምርት ለጨርቃጨርቅ ፋብሪዎች) በማድረግ የሰው ኃይል ከአፍሪካ አሕጉር በመውሰድ የባርያ ንግድ አስፋፉ፡፡ በዓለማችን በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ በባሪያ ንግድ ፍንገላና ሽያጭ የተሰማሩ የአውሮፓ አገራቶች ቀንደኞቹ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ፖርቹጋልና ዴንማርክ ነበሩ፡፡ በዴንማርክ የባርያ ንግድ በ1802 እኤአ በሕግ ተሻረ፡፡ በሃገረ እንግሊዝ የባርያ ንግድ በ1807 እኤአ በሕግ ተሰረዘ፡፡

ዘር = በሥነ-ሕይወት ትምህርት የሰው ልጆች በሥነ ፍጥረት ፀባያቸው ልዩ ልዩ ዘርፎች አላቸው፡፡ የሰው ልጆች የዘር ዓይነቶች በአካል ቅርፅ በጭንቅላት ቅርፅ፣ በአፍንጭ ቅርጽና መጠን እንዲሁም በቆዳ ቀለምና በዓይን ቀለም ልዩነቶችን ውጫዊ (External) በማጥናትና ውስጣዊ (Internal) ጥናትን በማግለል በተገኘው ግኝት መሠረት የሰው ልጅ ዘር በአራት ዋነኛ ዘርፎች ተካተቱ፡፡ እነሱም

(1) ካኬይዥየን ዝርያዎች (ነጭ የሰው ዘር ፈነንጅ/ የአውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ምዕራብ ኢሲያ)
(2) ሞንጎሎይድ ዝርያዎች (የሞንጎላዊ ዝርያ ያላቸው ሰዎች ጃፓን፣ ቻይና፣ህንድ፣ ኮርያ፣ቬትናም፣ ካንቦዲያ)
(3) ኔግሮይድ ዝርያዎች (የጥቁር ሰው ዝርያ/ የአፍሪካ አገራቶች ህዝቦች/ ደቡብ አሜሪካ፣ ጃማይካ / ካሪቢያን ወዘተ)
(4) አውስትራሎይድ ዝርያዎች (በአውስትራሊያ አህጉር የሚገኙ ህዝቦች)

በሥነ-ሰብ ትምህርት ጥንታዊ የሰው ዘር ክፍፍሎች በአራት መከፈሉ በስፋት ሲሰበክ ቆይቶል፡፡ በዚህ ጥናትና ምርምር መሠረት ምርጡ ዘር ኮኬዬዥያን ዝርያዎች ወይም ነጭ የሰው ዘር መሆኑ ከዛም በመቀጠል በሁለተኛ ደረጃ አውስትራሎይድ፣ በሦስተኛ ደረጃ ሞንጎሎይድ፣ በአራተኛ ደረጃ ኔግሮይድ (የጥቁር) ዘር መሆኑን አጥኝዎቹ ሳይንቲስቶች አበሰሩ፡፡ በተለይ ኔግሮይድ ዝርያ ያላቸው ትንሽ ከዝንጀሮ ዝርያ ከፍ እንደሚሉ በአብዛኛው ግን የአፍንጫቸው ቅርፅ፣ የመንጋጭላቸው ትልቅነት፣ የእጃቸው መዳፍና እግራቸው ትልቅነት እንዲሁም የቆዳቸው ጥቁር ቀለም፣ የአይናቸው ጥቁር ቀለምና የፀሩራቸው ከርዳዳነትና ጥቁር መልክ ተደማምሮ የቀድሞ ሳይንቲስቶች የሰው ዝርያን ከውጫዊ (External) ትንተናና ግኝት በመነሳትና የውስጣዊ (Internal) የዲኤን ኤ ;የህብለ በርሄ፣ የደም ዓይነት፣ የአካል ብልቶች ዓይነት ሣንባ፣ ልብ፣ ጉበት፣ወዘተ ጥናትን ሳያካትቱ የኔግሮይድ የጥቁር ሰው፣ ከሰው ዘር ተራ እንዲወጣ ታላቅ አስተዋፆኦ አድርገዋል፡፡ በዚህም ኢሳይንሳዊ ዘረኛ ነጮች ጥናት ምክንያት የጥቁር ህዝብ በባሪያ ንግድ እየፈነገሉ እንዲሸጡ ተዳረጉ፡፡ የዚህ ጥናት ውጤትም በዓለማችን የዘረኝነት አመጣጥ መንስዔ ሆነ፡፡

ዘረኝነት፡- የዘረኝነት ርእዮተ ዓለም ማጠንጠኛው የሰው ዝርያ በአራት ልዩ ልዩ የዘር ግንድ እንደሚከፈልና የዘር ግንዱም የበላይና የበታች ዘሮችን በየፈርጃቸው በቆዳ፣በዓይንና በፀጉር በቀለም፣ በአፍንጫና መንጋጋ በአካል ቅርፅ፣ እንደሚሸነሽን፣ እንዲሁም በእውቀት ክህሎት በችሎታቸው፣ በግብረገብነታቸው ወዘተ የሰው ልጆች ዘር አንዱ ከአንዱ ይበልጣል የሚል እምነት ተከታይ ዘረኛ ይባላል፡፡ የሰውን ልጅ በውጫዊ ቅርፁ ብቻ በማጥናት የውስጣዊ ተፈጥሮውን ሳያጠኑ የተካሄደ ኢሳይንሳዊ አመለካከት የነገሠበት የዘረኝነት ዘመን ነበር በሚል ከአጠቃላ የዓለም ታሪክ ወደ አፍሪካ ታሪክና ኢትጵያ ታሪክ ቢያወርደው የታሪክ አወራረዱን ጥራት ይኖረው ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የባርያ ንግድ ዘመን በፊታውራሪ ተከለ ሃዋርያት ተክለ ማርያም፣

ልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ፣ ሪቻርድ ፓንክረስት፣ አዶልፍ ፓርለሳክ፣ ጄስፔንሰር ትሪሚንግሃም እንደፃፉት ከእራስህ መፅሃፍ ተርከሃል፡፡ ሌሎችም የቀረቡ ብዙ ጹሑፎች እንደሚኖሩ ሳስብና ስገነዘብ ያንተ ግን መሸፋፈን ያለበት ነው ብዬ ስለማምን ያልከው ሁሉ በማስረጃ የተደገፈ አይደለም እላለሁ ፡፡ በሃገሪችን የባርነት ታሪክ በሁሉም ‹‹ብሔር በሔረሰቦች›› ላይ የደረሰ እና የባሪያ ፈንጋዬቹም አስተዋፅኦ ይብዛም ይነስ እንጂ በሁሉም መፈጸሙን የታሪክ ማስረጃ መዛግብት መመልከት ያሻል እላለሁ፡፡ ይህንን አንተ ያለፍከው ይመስለኛል፡፡

በገጽ 82 ላይ ‹‹ይህን የሃገራችንን የባርነት ታሪክ ሰፋ አድርጌ ጽፌዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ብዙ ያልተጻፈበትና መሸፋፈን አለበት ብዬ ስለማላምን፡፡ ይህ ማለት ግን የባርነት ታሪካችንን ከታሪክ ማቀፍ ውጭ እያወጣን በእዛን ዘመን ታሪክ ከሂስ ሂደት ውጭ ሊሄዱበት የሚቻል ልብወለዳዊ የታሪክ አማራጭ ነበር ለማለት አይደለም፡፡… በዓለማችን የባርያ ጠባሳ ታሪክ የሌለው ሀገርና ህዝብ የለም፡፡ በርካታ ሃገሮች ይህን አይነቱን ታሪክ ትርጉም ያሳጣ፣በተሳካ ሁለንተናዊ የዘመናዊነትና ስልጣኔ ደረጃ ደርሰዋል፡፡ በዚህ የተነሳ እንዲህ ዓይነቱ ታሪክ ስሜት ቀስቃሽ፣ በዜጎችና በማህበረሰቦች መሃል መናቆሪያ ፈጣሪነቱ አብቅቶል፡፡ በዘመናዊነትና በስልጣኔ ማደግ ባልቻለችው ሃገራችን ኢትዮጵያ ግን፣ ባርነት፣ ጭስኝነት፣ ገባርነት የመሳሰሉት ሌሎች ታሪካዊ ኩነቶች፣ ያለፉ የታሪካችን ገጽታዎች ቢሆኑም እነዚህን የታሪካችንን ሃቆች እየመዘዙ ስሜት ለማስቀስቀስ ለሚፈልጉ ሃይሎች የተመቸ ሁኔታ ፍጥሮላቸዋል፡፡ በበኩሌ ‹‹ ይህን አይነቱን የታሪክ እስረኛነት ማለፍ የማይችል ለልጆቹ የሚያወርሰው ሀገር ከአያቶቹ ከወረሰው የከፋ ሲሆን ይችላል፡፡የሚል ትልቅ ስጋት አለኝ፡፡›› ይላል አቶ አንዳርጋቸው ከአጠቃላይ ወደ ተናጥል ማለትም ከዓለም የባርያ ንግድ ዘመን ወደ አፍሪካ ብሎም ወደ ኢትዮጵያ ታሪኩን ከሽኖ ቢያቀርብ ኖሮ ምንም ስጋት ባልኖረው ነበር፡፡ ለምን ይህንን አስገባው ስል? አንድም ተራማጅ ለመሆን ካልሆነም ያገራችን ታሪክ የባሪያ ፈንጋይ ታሪክ ነው ለማለት ከሆነ ከመነሻው ችግር አለበት፡፡ ፈረንጆች የነበረውን የባሪያ ንግድ ወንጀላቸውን ለማጥፋት የዛሬውን ጥቁር አሜሪካዊ “ኒግር” ብለው እንደማይጠሩ ሁሉ የሃገራችን ብሔረሰቦች ይህ መጠሪያችን አይደለም ያሉትን የተለምዶ መጠሪያ ትተን በፈቀዱት ስማቸው እንደምንጠራቸው ሁሉ እራሱን ከጥቁርነት ነጥሎ እቤታቸው የነበሩትን ሰራተኞች ባሪያ ማለቱ አላስፈላጊ ነው ብዬም አምናለሁ፡፡ በታሪክ ትረካ አፍሪካውያን የቀለም ጭቆና የተደረገብን ነንና፡፡ ይህንንም ጸሐፊው በለንዶን ቆይታው የደረሰበትም ይመስለኝል፡፡

አቶ አንዳርጋቸው በመጽሐፉ ገፅ 240 እንዲህ ይላል ‹‹ ቀኑ የሥራ ቀን ነበር፡፡ ጥላሁን፣ የአባቴን ጓደኞች ‹ዘፈን ምረጡ› እያለ እያስመረጠ ነበር የሚዘፍነው፡፡ አቶ ወርቄ ደምሴ፣ ‹‹እኔ ልሁን እንጂ የማልጠቅም እርካሽ፣ ምንም ጊዜም ቢሆን አንቺን ክፍ አይንካሽ›› የሚለውን ዘፈን እንደመረጡ አስታውሳለሁ፡፡ እጅግ ደግና ቆንጆ ባለቤታቸውም ወ/ሮ ዘውዲቱ መሸሻ እዛው ነበረች፡፡ ከብዙ አመታት በኃላ እንደሰማሁት ያ የዘፈን ምርጫቸው ‹ከሚስታቸው ውጭ ከሌላ ሴት ጋር በነበራቸው ግንኙነት ተጸጽተው የመረጡት ነው› ይባላል፡፡ ለእኛ ለልጆቹ፣ ያምሽት ከማንኛውም ጸጸት የጸዳ ነው፡፡›› ይላል ስለ አቶ ወርቄ ደምሴ ስለ ግል ታሪካቸው በመጽሐፉ ውስጥ በይመስለኛል ለመናገር መነሳት አስፈላጊነቱ አልታየኝም፡፡ ቤተሰቦቻቸውን ከማስከፋት በስተቀር ለአሁኑ ወጣት የሚሰጠው ትምሕርትም ምን እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ይህንን የሚነግረን ከያሲ ስሌላው የይሆናል ትረካ ሲነግረን የራሱን የፈረሰ ትዳር አስመልክቶ ግን የቀድሞ ባለቤቱን (PRIVACY) አከብራለሁ በሚል ሲያልፈው ይስተውላል፡፡ እርግጠኛ ሳይሆን መጠቀሱ አግባብም አልነበረም፡፡ ለባለቤታቸው፣ ለልጃቸው፣ ለወንድምና እህቶቻቸው ሁሉ ያስቀይማቸዋል ተገቢ አልነበረም፡፡ እንዲሁም ስለ ኑኑ፣ ስለ የሺ የግል ህይወት የተጠቀሰው አስነዋሪ ትረካ ነው ለምን ተካተተ ብሎ መጠየቅ እንደ ቤተሰብ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ አቶ አንዳርጋቸው በሚቀጥለው መፅሃፉ ስለ ሚስቶቹ እና ስለልጆቹ እውነቱን እንደሚተርክልን እንጠብቃለን፡፡ እኛ ከዛ ትረካ የምናገኘው ትምህርት ግን መኖሩን እጠራጠራለሁ፡፡ስለ ራሱ ስብዕና ስለ ሴቶች እኩልነት፣ ስለ ትዳሩ መፍረስ፣ ስለ ታማኝነቱ፣ ልጆቹን ጥሎ በርሃ ስለመውረዱ ከልጆቹ ፍቅር “የሃገር ፍቅር ትኩሳቱ” አላስቀምጥ ብሎት እንደሆነ ሃቁን ማስረዳት ይጠበቅበታል፡፡ ግን ልጆቹንና ሚስቱን የማይወድ ባል ሃገር ይወዳል! የሃገር ፍቅር ብሎ ነው የሚል ተረት ተረትስ እንዴት ያየዋል ይግለጠው ብለን እናልፈዋለን፡፡

በ1969 ዓ/ም አንዳርጋቸው እንዲህ ይላል፤- ‹‹ የዘውዱ ከኢህአፓ ጋር የነበረው ግንኙነት የተመሠረተው የትምህርት ቤቱ ልጅና ጎደኛው በነበረው ናደው በሚባል ወጣት በኩል ነው፡፡ ናደው ከእውቁ የተፈሪ መኮንንና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ከኤልያስ ወልደማርያም ጋር በኢንተር ዞን ደረጃ ተመድበው ለኢህአፓ ሲሰሩ መርካቶ ውስጥ ተይዘው ከዋናው ቀይ ሽብር ቀደም ብሎ በመስከረም ወር በ1969 ዓ.ም በደርግ ከተገደሉት ወጣቶች አንዱ ነው፡፡ የመጀመሪያዋን ዴሞክራሲያ የሰጠኝ ልመነው በአንድ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ከነሱ በፊት በወታደሮች ተገድሎል፡፡ ናደውና ዘውዱ 1966 ዓ/ም ላይ የ12 ኛ ክፍል ተማሪዎች ነበሩ፡፡ በዕድሜም ይሁን በተመክሮና ዕውቀት ደረጃ ብስለት ያልነበራቸው ልጆች ናቸው፡፡ በተለይም የአብዬታዊ ንድፈ ሃሳብ እውቀታቸው በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ለአንድ በከፍተኛ ጥንቃቄና በሚስጥር ስራ መስራት ለነበረበት ድርጅት የሚመጥን ዲሲፕሊን ይጎድላቸዋል፡፡ ናደው በአዲስ አበባ የፓርቲው የዞኖች አስተባባሪነት በኢንተር ዞን ኮሚቴ ደረጃ ተመድቦ ይሰራ እንደ ነበረ ክፍሉ ታደሰ ያ ትውልድ በሚባለው መጽሃፉ ገልጾታል፡፡ ዘውዱም በዞን መሪነት ደረጃ ተመድቦ ይሰራ እንደ ነበረ ለማወቅ ችያለሁ፡፡ በዚህ ደረጃ ከላይ የጠቀስኳቸው ድክመቶች የነበሩባቸውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች መመደብ የቻሉት በ1964 ቦተር ከሚባለው ስፍራ የተወሰኑ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከነግርማቸው ለማና ሌሎች ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር በታሰሩበት ወቅት በመሰረቱት ግንኙነት ነው፡፡›› (ገፅ 432)

አቶ አንዳርጋቸው ስለ ዘውዱ ወልደአማኑኤልና ናደው ኃይሌ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው እውቀት የላቸውም በሚል ያጣጥላቸዋል፡፡ ነገር ግን ዘውዱ በ1966 ዓ/ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መግባቱና እንደ አቶ አንዳርጋቸው በመጀመሪያው ሴሚስተር በፈተና ወድቆ አለመባረሩን ግን አይተርከንም፡፡ አንዳርጋቸው በበሪሁን ተክሌ በኩል የመኢሶን የፖለቲካ መስመር ትክክል ነው ብሎ ወጣቶች ይሰብክ ከነበረበት አውጥቶ ወደ ኢህአፓነት የመለመለው ዘውዱ እንደሆነ ከፃፈው መረዳት ይቻላል፡፡ ‹‹ጌታ ሆይ እንዴት አንተ ጌታዬን እኔ አጠምቅሃለሁ!›› ብሎ ዮሐንስ መጥምቁ እየሱስን እንዳለው መጽሃፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡ ታዲያ በወቅቱ ነቅቶ የሚያታግል የነበረውን ጓደኛውን ብሎም እንደሱ አባባል “ጓዱን” እንዴት በንቃትና በዲሲፕሊን ጉድለት ሊወቅሰው ተነሳ? ይህ ወጣት እኮ ሌሎች ጓዶቹን ላለማስበላት ትልቁን ውሳኔ የወሰነ ሕይወቱን አሳልፎ የሰጠ ነው፡፡ ያንድ ሰው ንቃትስ እራስን ለዓላማ ከመሰዋት ሌላ ምን ሊሆን ይችላል፡፡ ፈረንጆች “ጀግኖች ለዓላማ የተሰው ናቸው” ይላሉ፡፡ ዛሬ አንዳርጋቸው ሰነበተና የነቃ እነዘውዱ Hይወታቸውን ገበሩና ያልነቁ ሆኑ? በአንድ አገር ንጉሱ የሚያስተዳድረውን ሕዝብ ለመተዋወቅ ቅዳሜ ገበያ ቀነ ቀጠሮ ተሰብሰቡ ብሎ አዋጅ ያስነግራል፡፡ በእለተ ቀኑ ሕዝቡ አዋጁን አክብሮ ወደ ገበያ ተመመ፣ ከመንገድ ዳር የተኛ የኔ ብጤ ትልቅ ሰው ሞቶ ዘኬ ያመለጠው መስሎት አንዱን ፈረሰኛ ‹‹ማነው የሞተው፣ አዳሜ ወዴት ነው የሚተመው›› ብሎ ጠየቀው ለካ ፈረሰኛው ንጉሱ ኖሮ ‹‹ አልሰማህም እንዴ አዲሱ ንጉሥ ቅዳሜ ገበያ ዛሬ ሕዝቡ እንዲሰበሰብ አውጇል ›› አለው፡፡ የኔ ብጤውም እባክህ ንጉሱን አይቼው ልሙት ውሰደኝ ብሎ ፈረሰኛውን ጠየቀው፡፡ ንጉሱም በጥያቄው ተገርሞ ንጉሱን ለማየት እንደዚህ ከፈለግህ ና ተፈናጠጥ ብሎ ከፈረሱ ላይ አፈናጠጠው፡፡ በመንገዳቸው ላይ ሁሉ ሕዝቡ ባለፉ ቁጥር እጅ ይነሳቸው ጀመር፡፡ ለሰላምታው የኔ ብጤውም ንጉሱም አጠፋውን እየመለሱ በኩራት ሲጎዙ ቆዩ፡፡ ፈረሰኛው ንጉስ ወደ ተፈናጠጠው መለስ ብሎ በፈገግታ ተሞልቶ ‹‹አሁን ንጉሱ ማን እንደሆነ አወቅህ?›› ብሎ የተፈናጠጠውን ሰው ሲጠይቀው ተፈናጣጩ የኔ ብጤ ጠረጠርኩ ‹‹ወይ አንተ ነህ ፣ ወይ እኔ ነን›› ብሎ መለሰለት ይባላል፡፡

አቶ አንዳርጋቸው ‹‹ እኔ ከማህተመ ጋር ዘውዱን ጨምሮ የአካባቢያችን የሪጅን ኮሚቴ አባላት ሆነን እንደምንስራና ሌሎችም ሁለት ተጨማሪ ሰዎች እንደሚቀላቀሉን ዘውዱ ነገረን፡፡ በሪጅን ኮሚቴ አባልነት የተሰበሰብኩት ግን ሁለት ጊዜ ብቻ ሆነ፡፡ ዘውዱ የኢህአፓን አመራር ወይም ከበላዩ ያሉትን የድርጅት ሰዎች ‹‹የበላይ አካል›› እያለ ነበር የሚጠራቸው፡፡›› ይላል (ገጽ 457) ጸሐፊው ካልተሳሳትክ በስተቀር በኢህአፓ አሠራር በአንድ ጊዜ በተመለመልክ በሳምንትህ የህዋስ እንጂ የሪጅናል ኮሚቴ አባል እንዴት ልትሆን ቻልክ? የናደው ኃይሌ፣ የዘውዱ ወልደአማኑኤል፣ ተገርፈው ተቀጥቅጠው ብዙ ጎዶቻቸውን አንተን ጭምር እንዳዳኑ መዘንጋትህ ግን የሚያሳዝን ነው፡፡ የናደው ኃይሌ፣ የዘውዱ ወልደአማኑኤል፣ የቢኒያም ቦጋለ፣ የጃርሶ ኪሩቤል ገድልን በመጽሐፍህ በደንብ ተርከሃልና ግርማቸው ለማ ጥሩ ጎዶች በማፍራቱ ከእራስህ ትረካ ጋር እውነተኛ ታሪካቸው ገልፀሃል ብለን እንቀበል፡፡ በሹፌርነትም ናደው ኃይሌ፣ ዘውዱ ወ/አማኑኤል፣ ሳምሶን ለገሰ፣ ሱራፌል ካባ፣ ብርሃኑ ነጋ፣ ሰይፉ ይርጋ፣ የዓየር ኃይልና የዓየር ወለድ የድርጅቱ አባላቶች ሁሉ በሹፌርነት ድርጁቱን ያገለግሉ እንደነበር ግን አልገለፅክም፡፡ ለምን ቢባል መኪና አሽከርካሪ በወቅቱ እኔ ብቻ ነበርኩ ልትለን የከጀለህ ይመስላል፡፡ የሹፍርና ገድልህ በጣም የተጋነነ አንድ ሹፌር ሁሉንም የኢህአፓ ፖሊት ቢሮ ሰዎችን እንደሚያውቅ ተደርጎ የተሳለው ተክለ ሰውነትህ ያለህ የገዘፈ የእኔነት/ የኢጎ ስሜት የጥንቱንና የዛሬውን የታሪክ ክስተት በአንድ ላይ ሰፍተህው ‹‹ስራዬ እሱንና ሌሎችንም በይፋ መንቀሳቀስ የማይችሉ የኢህአፓን አመራር አባላትን መሾፈር እንደሆነ ተገነዘብኩ፡፡ በዚህ ስራ የተነሳ መደበኛ የህዋስ ተሳትፎዬ አበቃ፡፡ ብዙ ጉድ ውስጥ የጨመረኝ የኢህአፓ የመኪና ነጅነት ስራዬ ተጀመረ፡፡›› (ገፅ 458) ይላል፡፡ አንዳርጋቸው ከአንድ ገጽ በኃላ ደረጃውን በመናዘዘ በእራሱ ፁሁፍ አረጋግጦልናል እላለሁ፡፡

አንዳርጋቸው ናደው ከእውቁ የተፈሪ መኮንንና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ከኤልያስ ወልደማርያም ጋር በኢንተር ዞን ደረጃ ተመድበው ለኢህአፓ ሲሰሩ መርካቶ ውስጥ ተይዘው ከዋናው ቀይ ሽብር ቀደም ብሎ በመስከረም ወር በ1969 ዓ.ም በደርግ ከተገደሉት ወጣቶች አንዱ ነው፡፡ ያለው ስህተት ነው፡፡ አቶ አንዳርጋቸው፣ ታሪክ ያለማስረጃ አይፃፍም፣ ትውልድ አይደናገር እኛም እንናገር እያልክ አደናገርከን፡፡ ናደው ኃይሌ የተያዘው በመስከረም ወር በ1969 ዓ/ም ሳይሆን በጥቅምት 1968 ዓ/ም ነው፡፡ የእኛ ማስረጃ ከቀይ ሽብር አቃቢ የህግ ጥሰት የቀረበው እንደሚከተለው ነበር፡፡

‹‹ Count Eight Statement of the offense

An offense committed in violation of article 522 of the 1957 Ethiopian penal code
PARTICULARS OF THE OFFENCE
As of Sept 12,1974, the accused, having established the P.M.A.C. or government and while ruling the country collectively and exclusively, committed a crime intentionally with premeditation and motive and, are therefore charged for the violation of Arts.32 (1) (a) (b)and 522 (1) (a) of the penal code in that they caused, under the guise and in the name of court, in a manner contrary to law and in such conditions of exceptional cruelty and manifest abuse of power, the execution of:

1. Ato Teka Amare
2. Ato Samson Legesse
3. Ato Tesfagiorgis Haile
4. Ato Nadew Haile
5. Ato Yoseph Arefayne who were under their custody in October 1976 in Addis Ababa, at an unidentified place and with an unidentified weapon by arbitrarily designating them as reactionaries, anti-revolutionaries, anti-people and subversive anarchist members of E.P.R.P. ›› PART ONE, GENOCIDE AND CRIMES AGAINST HUMANITY, October 1994, PAGE 115)

አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ዘውዱንና ናደውን ‹‹በዕድሜም ይሁን በተመክሮና ዕውቀት ደረጃ ብስለት ያልነበራቸው ልጆች ናቸው፡፡በተለይም የአብዬታዊ ንድፈ ሃሳብ እውቀታቸው በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡›› በሚል ሲያጣጥላቸው ይታያል ብለናል፡፡ ያንተ መለኪያ የዩኒቨርቲ ተማሪ መሆን ከሆነ ተሳስተሃል ልበልህ፡፡ በጊዜው የነበረው መለኪያ የማርክሲዝም ሌኒኒዝም ርዕዬተ ዓለም ፖለቲካን ማወቅና አለማወቅ እንጂ የዩኒቨርሲቲ የሳይንስና ሶሻል ሳይንስ የትምህርት እውቀት ስላለህ አልነበረም፡፡ ብዙ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችንና ሰራተኞችን የማርክሲዝም ሌኒኒዝም ርዕዬተ ዓለም ፖለቲካን እያስጠኑ ወደ ኢሕአፓ ድርጅት በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዬታዊ ወጣቶች ሊግ ቀጥሎም ወደ ፓርቲ አባልነት ይመለምሉ እንደ ነበር ይታወቃል፣ ወንድሜ አሰራሩ እንደዛ ነው ልበልህ፡፡ ስለሆነም የላብ አደሩ እረእዮት ስንል የዩንቨርሲቲ ምሁራን ስብስብ፣ የገበሬው ትግል ስንል የሊቃውንት ቅንጅት ማለት ነው ብለህ ተቀብለህ ካልሆነ የወጣቱን ትግል በትምህርት ደረጃ ማጣጣል ወንጀል ነው ብለህ ተቀበል፡፡ እንዴው ለማስታወስ ያክል ስንቶች የታወቁ የሃገር መሪዎች ናቸው ዩንቨርሲቲ ያልጨረሱ? ብለህ ጠይቀህ ታውቅ ይሆን? መንግስቱ ሃይለማርያምም አገር መርቷል አይደል?

በ1983ዓ/ም አንዳርጋቸው እንዲህ ይላል፤- ‹‹ትዝታ በፖስታ ልኬልሃለሁ፣ መልሱን በቶሎ እጠብቃለሁ፡፡›› ዘፋኟ እንዳለችው በ1983ዓ/ም ህወሓት ኢህአዴግ አዲስ አበባን እንደ ተቆጣጠረ ከሃገረ እንግሊዝ ከሎንዶን ከተማ ስልክ ተደወለልኝ፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ነበር፣ ቅርብ ቀን እመጣለሁ አዲስ አበባ አለኝ!!፣ ‹‹ወንድሜ አትምጣ፣ እኛም መሄጃ አጥተናል፣ አሲንባ ስለራቀን፣ መንዝ ብንሸፍት ይቀርበናል ተባባልን!!!›› የከሸፈ ኮድ ነበር፡፡ በሳምንቱ አቶ አንዳርጋቸው የባህር ኃይል መኪና ታርጋ የሌላት ይዞ ቤቴ ሰተት ብሎ መጣ፡፡ ቀጥሎም በተለያየ ጊዜ፣ ይዞኝ ሄዶም ጎደኞቹን የኢትዩጵያ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢህዴን) አባላት መኃል እሱ በፍልስፍና ዲግሪ ይዞ ተኮፍሶ ገድላቸውን እንደ ጠጠር ወርዋሪው ዳዊት አግዝፎ፣ አንዴ የባንክ ዘረፋቸውን፣ አንዴ እስረኛ ከመቐለ እስር ቤት እንዴት እንዳስፈቱ፣ አንዴ እንደ ሲሊቨስትሪ ስታሊየን የራንቦ ፊልም ‹‹የደርግን ሠራዊት›› በቆረጣና በደፈጣ እንደረፈረፉት እንደ ሆቺሚኒህ፣ ቼጉቬራና ካስትሮ ፣ እንደማረኩ ገለፁልን፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ከኢህዴን ታምራት ላይኔ፣ በረከት ስምኦን፣ አዲሱ ለገሰ፣ ተፈራ ዋልዋ፣ ህላዊ ዬሴፍ፣ ታደሰ ጥንቅሹ፣ ከኦህዴድ ኩማ ደመቅሳ፣ አባ ዱላ ገመዳ፣ ከህወሓት ሳሞራ ዮኑስ፣ ኃያሎም አርአያ፣ ስዬ አብርሃ፣ ወዘተርፈ ከደኢህዴን ካሱ ኢላላ፣ አባተ ኪሾ፣ ወዘተርፈ ተከቦ የተማረ ሰው ያለህ!!! ብለው ምሁር ሊመለምሉ አሴሩ ከኢህአፓ በኋላ የፖለቲካ ደቀ መዝሙር አንሆንም በማለታቸው ምሁራን በጥቁር መዝገብ ከተቦቸው፡፡ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የአቶ ተፈራ ዋልዋ ከንቲባ፣ አቶ አንዳርጋቸው ምክትል ሆነው የመንግሥት ቤት ተሰጥጦቸው፣ የመንግሥት መኪና እና የወር ደሞዝ ቀለብ ተሠፍሮላቸው ሲሰሩ በሎንዶን ከተማ ሚኒ ካብ ይነዱ እንደነበረ እረስተውት ነበር!!! አንዳርጋቸው ‹‹ብዙ ጉድ ውስጥ የጨመረኝ የኢህአፓ የመኪና ነጅነት ስራዬ ተጀመረ፡፡›› አቶ አንዳርጋቸው ፅጌና ዶክተር ብርሃኑ ነጋ በእፀመሰውር ከሹፌርነት ወደ ኢህአፓ ፖሊት ቢሮነት እንደጠለቁ ብዙ ጊዜ ሲደሰኩሩ ይሰማሉ፡፡ የኢህአፓ ፖሊት ቢሮ አባሎችና ከፍተኛ አመራሮች ለሹፌሮቻቸው ግልፅ ሆነው ሚስጢር ያወራሉ ለማለት መድፈሩ ግን አንባቢን መናቅ ይመስለኛል፡፡ በጆሮ ጠገብትነት ዘመን ከተሸጋገረ በኋላ በስሚ ሰሚ ሁሉም ሰው ከፍተኛ አመራር ቦታ ላይ እንደ ነበረ ሲያወራ መስማት ደግሞ እየተለመደ እየመጣ ነው፡፡ ታጋይ ሹፌር ነበርኩ ብሎ የሚሸልልበት አገር፣ የቀድሞ የኢህአፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ነበርኩ ብሎ የሚፎክርበት ሀገር ተወልደን በመኖራችን ‹‹እንበል አስራሁለት›› ከማለት ሌላ ምን ይባላል? የህወኃት ኢህአዴግ አስራአንደኛ ክፍል ተማሪዎች አንዴት ሚኒስቴር፣ አንዴት ጀነራል መኮንኖችና አንዴት አንባሰደር ሆኑ ብሎ ያልጠየቀው አንዳርጋቸው በመለስ ዜናዊ ዘመነ መንግስት የነበረውን መርሳቱ አውቆ እንደሆነ ጥርጥር የለኝም፡፡ በአገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እውቀት አልባ የፖለቲካ ካድሬዎች ባለሥልጣኖች ሆነው የተሸሙባቸው ጊዜ እንደ ነበረ የእሱን የሹመት ድርሻ በሚቀጥለው መጽሃፍህ ብታካትተው ተረት የመሰለ ታሪክ ለሚቀጥለው ትውልድ ታቆያለህ ብለን እንጠብቃለን፡፡

ሌላው ማስረጃ አልባ ተረት ተረት ደግሞ አንዳርጋቸው ፅጌ ‹‹ትውልድ አይደናገር እኛም እንናገር›› የዘለቀው ‹‹ የጌታቸው ማሩ የተቆረጠ ጭንቅላት፣ በአንድ ወቅት እኔ በማውቀው፣ ግርማቸው ለማ ተጠልሎ ይኖር በነበረበት ቤት ውስጥ እንደተገኘ ሰምቻለሁ፡፡ ይህ ቤት የአዲስ አበባው በይነ ቀጠና ይሰበሰቡበት የነበረበት ዘነበወርቅ ት/ቤት አካባቢ የሚገኝ ቤት ነው፡፡ ድርጊቱ የበይነ ቀጠናው ኮሚቴ አባላት እንደሆነ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡›› (ገፅ 597) ተረት ከሃቅ የራቀ ለመሆኑ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል፡፡ የጌታቸው ማሩ በደርግ እንዳይታወቅ ፍቱ ላይ ከሞተ በኃላ አሲድ እንደተደፋበት ኮነሬል አየሁ ጥሩነህ ወታደር ፖሊስ እስር ቤት ውስጥ ለኢህአፓና ለኢህአወሊ ከፍተኛ አመራሮች ፍቶግራፉን አሳይቶቸዋል፡፡ የጌታቸው ማሩ የተገደው ሰሜን ማዘጋጃ ከሚገኝ ቤት ውስጥ እንጅ ዘነበወርቅ ት/ቤት አለመሆኑ የሚያውቁ ያዛን ዘመን ጎዶች አሁንም በሕይወት አሉ፡፡ ዛሬም በአገራችን ጋዜጠኞች ካሉ ኮነሬል አየሁ ጥሩነህ በህይወት ስላሉ ቃለ መጠይቅ በማድረግ የጌታቸው ማሩን አሟሟት ማወቅ ይቻላል፡፡ በ1969 ሰኔ 14 ቀን ግርማቸው ለማ ዘነበ ወርቅ ት/ቤት አጠገብ ከጎደኛው ሃሰን ቤት ለማደር በሄደ ጊዜ እንደተገደለና ጎደኛው ተታኩሶ እንዳመለጠ ኮነሬሉ ግርማቸው ሞቶ ከወደቀበት ያነሱትን ፎቶግራፍ ለዘውዱ ወልደአማኑኤል ባሳዩት ጊዜ በሃዘን ተውጦ የተሰማውን ያጫወታቸው እስረኞች ዛሬም በህይወት አሉ፡፡ የነዚህን ጎዶች የሞት ሚሥጢር የማወቅ ፍላጎት ያላቸው ህይወት ተፈራና አንዳርጋቸው ፅጌ ከቀይ ሽብር ሰማዕታት ሙዚየም የተቀመጠ በኢህአፓ/መኢሶን/ሌሎች ድርጅቶች አባሎቻቸው በደርግ ፅህፈት ቤት፣ በማዕከላዊ፣ በአራተኛ ክፍለ ጦር፣ በቀበሌና ከፍተኛ እስር ቤቶች የተመረመሩ እስረኞች ቃላቸው በአደራ የተቀመጠው ከዚህ ሙዚየም ውስጥ ስለሆነ እውነቱን ማወቅ ቀላል ይሆናል፡፡ በተመሳሳይ ብርሃነመስቀል ረዳ በሰጠው ቃል መሠረት እነ ጌታቸው ማሩ እንዴት በኢህአፓ ውስጥ አንጃ እንደመሰረቱ እጃቸውን ለደርግ እስከሰጡበት ጊዜ ድረስ የሰሩትን ብርሃነመስቀል በእራሱ እጅ ጽሁፍ ዶሴ ሙሉ የፃፈውን እዛው ታገኙታላችሁ፡፡ ይህን ታሪክ ቀጣዩ ትውልድ ‹‹መቼም የትም አይደገም!!!›› ‹‹NEVER AND EVER AGAIN›› ብሎ እንዲማርበት በእኛ ትውልድ መገዳደል እንዲያበቃ፣ ችግራችንን በጠረጴዛ ዙሪያ በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት እንድንሞክር ትምህርት ለመቅስም ያስችላል እላለሁ፡፡

‹‹ተራራውን በአንቀጠቀጠ ትውልድ›› በቀለ መርኔ በመፅሄት ላይ የገደለውን ወታደር በገለፀ ጥቂት ወራቶች ውስጥ የሟች ወታደር ዘመዶች ተከታትለው በመርዝ እንደገደሉት ሁሉ ዛሬ እንትና እንትናን ወለደ እንጂ እንትናን ገደለ ታሪክ ተብሎ አይከተብምና፣ ቂም በቀል ለቀጣዩ ትውልድ እያወረስን ከመሄድ መቆጠብ አዋቂነት ነው እንላለን፡፡ አቶ አንዳርጋቸውም እንዳለ ይመኑ እንትናን ገደለ ብለው መፃፋቸው አግባብ አይደለም የምለውም ለዚህ ነው፡፡፡ ለሌላው መማሪያ እንዲሆን እንትና እንትናን ገደለው እያሉ መተረክ ቂም በቀል እንዲቀጥል ያደርጋልና፡፡ በኢህአፓ ዘመን በስራት ላይ ያሉ መገደላቸው እንደማይቀር የተገነዘቡ አባላት ሌሎቹን ለማትረፍ የእከሌ የእከሌ ገዳይ እኔ ነኝ በማለት የሁለትና ሦስት ሰዎች ገዳይ እነሱ እንደሆኑ በመናገር የብዙ ልጆች ሕይወትን ሊያተርፉ እንደቻሉ በዚህም ከኢሰብአዊ ግርፋትና ድብደባ ለመዳን ብሎም ቶሎ ለመሞት እሽቅድምድ የነበረበት ዘመን እንደ ነበር ማስታወስ ያስፈልግ ይሆን? ከእነዚህ ተጋዳዎች መሃል አንዱ ደግሞ እንዳለ ይመኑ ነበር፡፡

በዚህ 664 ገፆች ውስጥ ያለ የሃገራችን ታሪክ ከጥቂት የምጣኔ ኃብት / ኢኮኖሚ ትንተና የሌለው መሆኑ ሙሉ የፖለቲካ ሰው አያደርገውም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ ሲፃፍ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጉዳዮች እስከነማጣቀሻቸው፣ መረጃው ተሰድሮ ለውይይት እስካልቀረበ ድረስ የታሪክ ድርሳኑ ቅመም የሌለው፣ ምስክር የሌለው የቡና ቤት ወሬ ከመሆን አይዘልም፡፡ በእውነቱ አቶ ክፍሉ ታደሰ (ያ ትውልድ ከቁጥር 1 እስከ 3) የፃፈው እና ቃለመጠይቅ ያደረገላቸው ጓዶች በመጥቀስና ማስረጃ አስደግፎ በመፃፉ ሊመሰገን ይገባዋል እንላለን፡፡ የአቶ ክፍሉ መጽሃፍ ከነእንከኑ የሀገራችንን ምሁራን አይን የገለጠ፣ የታሪክ አፃፀፍ ያስተማረ ለመሆኑ ጠቢብ መሆን አያሻም፡፡

ቀጥሎም To kill a generation እና Red tears የመሳሰሉት የዘውዴ ረታ መጽህፍት፣ የፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ የታሪክ አፃፃፍን መከተል በትምህርትና በእውቀት ብቻ የሚገኝ መሆኑን ያለማስረጃ፣ ያለማረጋገጫ ታሪክ እንደልብ ወለድ እንደማይጻፍ ያስተምራል ብዬ አምናለሁ፡፡ በሃገራችን መንግስቱ ኃይለማርያም፣ ፍቅረስላሴ ወግደረስ፣ ፍስሃ ደስታ መፅሃፍ ሲጽፉ አንዳቸውም የደራሲ በዓሉ ግርማን አሟሟት ሊገልፁልን አልቻሉም፡፡ ታሪክ ፀሃፊዎች የእራሳቸውን ገድል ሳይሆን መፃፍ የሚገባቸው በሚቀጥለው ትውልድ እነሱ

የሰሩት ስህተት እንዳይደገም ለማስተማር በኃጥያታቸው መፀፀታቸውንና ንስሃ መግባታቸውን ለማስተማር መሆን አለበት እላለሁ፡፡ ካለበልዚያ ማስረጃ የሌለው ወሬ እንደ ሰማሁት ብሎ ታሪክ አይፃፍም፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪዎች የታሪክ አፃፃፍ ዘዴን ለእነዚህ ወፈ ሰማይ ተራኪዎች ሀ፣ሁ ውን ማስተማር ይጠበቅባችኋል እላለሁ፡፡ ወፈ ሰማዬቹም የታሪክ መፅሃፍ ከማለት ይልቅ ‹‹ታሪካዊ ልብ ወለድ›› ማለቱ የተሻለ ይሆናል ልበል፡፡ ለማስረጃ ያክል አንተ እንዳልከው ጥበበ በንቲ በሜኖሶታ ኖሮም እንደማያውቅ ሰምቻለሁ፡፡ የትግል ስሙም አንተ እያብራራህ ትርጉም እንደሰጠኽው አላዛር ሳይሆን አዛርያ እንደ ነበረ ለወደፊት ማስታወሻ ያዝ ብዬ ነው የምጠቁምህ፡፡ በነገራችን ላይ ጆሮ ጠገብ ነህና ሲያትል ነዋሪ እንደሆነም ልንገርህ፡፡ ገጽ(553)፡፡ ታሪክ ተራኪ ሳያጣራ አያወራም፡፡

የህቡዕ/ ሚስጢራዊ ድርጅቶች አሰራር በዴሞክራቲክ ሴንትራሊዝም/ ማዕከላዊ እዝና ስንሰለት የድርጅቱን ዴሞክራሲያዊ አስራር የውይይትና ክርክር ባህል በማቀጨጭ ኢ,ዴሞክራሲያዊ አንባገነናዊ አመለካከትና የውስጠ ድርጅት አፈናና ጭቆና እንዲጎለብት በር ይከፍታል፣ ፍርሃት ያንዣብባል፣ የፈጠርከው ድርጅት ሊገድልህና ሊያሳድድህ ይችላል፡፡ በእኛ ትውልድ ሚስጢራዊ ፓርቲዎችና ድርጅቶች የእራሳቸውን አባላቶች የገደሉ እንደነበሩ እናስታውሳለን፡፡ ሰላይ ሳይሆኑ ሰላይ ተብለው፣ ምንም ሳያውቁ የተገደሉ ወገኖች ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ ስለዚህ የእኛ ዘመን የህቡዕ ድርጅታዊ አሰራር መወገድ ይገባዋል እንላለን፡፡ ይህ ህቡእነት ደግሞ እንዳት ያሉ ደፋሮች ሲመለመሉ አመራር ነበርን እንዲሉ እድል ሰጥቷቸዋል፡፡ እነዚህ ሚስጢራዊ ድርጅቶች በአንድ ቤተሰብ ግንኙነት ውስጥ የተለያዩ የፖለቲካ መስመር ተከታይ በመመልመል የአንድ ቤተሰብ ወንድምና እህቶች በፍቅር እንዳይኖሩና አንዱ አንዱን እንዲሰልል በማድረግ ማህበራዊ የቤተሰባዊ ህይወትን ያጨለሙ የክፉ ዘመን ጥቁር ጠባሳ አስከትለው አልፈዋል፡፡ ለምሳሌ

• የአክሊሉ ህሩይ፣ ቲቶ ህሩይ፣ ፍቅሩ ህሩይ በኢህአፓነት፣ ታላቅ ወንድማቸው ህሩይ በመኢሶንነት ወላጆች ያሳለፉት ዘመን
• ቢኒያም አዳነ፣ ዬሴፍ አዳነ፣ በኢህአፓነት፣ ዶክተር ንግስት አዳነ በመኢሶንነት ወላጆች ያሳለፉት ዘመን
• ይደነቁ ተክሌ በኢህአፓነት፣ በሪሁን ተክሌ በመኢሶንነት ወላጆች ያሳለፉት ዘመን
• ናደው ኃይሌ በኢህአፓነት፣ አበበ ኃይሌ በመኢሶንነት ወላጆች ያሳለፉት ዘመን ዳግም እንዳይደገም እንላለን፡፡

እነዚህ ሚስጢራዊ ድርጅቶች ስርጎገብ (ኢንፍልትሬተር) በሌሎች ድርጅቶች ውስጥ በማስረግ፣ በእራሳችን ድርጅት ውስጥ ሰላዬች እንዳሉ በማስመሰል ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ በማጨለም ፈላጭ ቆራጭ አንባገነናዊ መሪዎች እንዲነግሱ አድርገዋል፡፡ በፓርቲው ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ውይይትና ክርክር እንዲጨናገፍ አድርገዋል፡፡ መሪዎቹ የእድሜ ልክ መሪ በመሆን ተቀናቃኛቸውን እያስወገዱ ዝንተ ዓለም መግዛት ይሻሉ፡፡ የፓርቲዎቹ መሪዎች በአባሎቻቸው ያልተመረጡ፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ያልተመረጡ፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት የማይመለከታቸውና መብትና ግዴታቸውን የማያውቁ ዘመን የተገላበጠባቸው የስልጣን ሱሰኞች መሆናቸውን ለማወቅ የህቡዕ ድርጅቶች ሚስጢርን መገንዘብ በቂ ነው እንላለን፡፡

መቼም የትም እንዳይደገም (Never Ever Again ) በኢትዮጵያ ሃገሬ የተፈጠሩ ጉግማንጉጎች፣ የፖለቲካ ካድሬዎች ሁሉም ያለፍርድ ገዳዬች ነበሩ፡፡ ሁሉም የታሪክ እስረኞች ናቸው፡፡ ሁሉም አላዋቂ ፖለቲከኞች፣ የውሸትና የተውሶ ማርክሲስቶች ናቸው፡፡ የሁሉም የስልጣን ጥማት ታሪክ ብዙ ወጣቶችን ለሞት ዳርጎል፣ እናቶች አልቅስዋል፣ ሴቶች ተደፍረዋል፣ ወጣቶች በግርፋትና በርሸና አልቀዋል፡፡ ከሃገር ተስደዋል፣ በሃገራችን የማያባራ ጦርነት የተቀጣጠለው በነዚህ የስልጣን ጥመኞች መሆኑን ታሪክ ተመራማሪዎች ሁሉ በመመስከር መቼም የትም እንዳይደገም በማለት ቀጣዩ ትውልድ ካለፈው ስህተተኛ ትውልድ እንዲማር፣ ያሉ የፖለቲካ ችግሮች በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት ብቻ እንዲፈቱ ማስተማር የምሁራን ኃላፊነት ነው፡፡ ታሪክ ፃፍን እያሉ ካድሬዎቹ ስህተታቸውን ላለመቀበል ‹‹መጀመሪያ ማን ተኮሰ! ማን ገደለ! በደፈጣ ነው በቆረጣ! ›› እያሉ ሲያናፉና ሲፅፉ አራት አስርት ዓመታት ተቆጠረ፡፡ የፖለቲካ አመራሮቹ ሁሉ የታሪክ እስረኞች ናቸው!!!! የታሪክ እስረኞች!!! ካድሬዎች ዛሬም ገድላቸውን በመጻፍ የጠለሸ ታሪካቸውን ያለ አንዳች ማስረጃ ለማደስ ይሻሉ፡፡

‹‹ትውልድ አይደናገር እኛም እንናገር›› መልካም ጎኖችን በሚቀጥለው ፁሁፍ ለማካተትና በሚቀጥለው ቅፅ ደራሲው ታሪክ ሲፅፍ ማስረጃዎች በመጥቀስ መጠንቀቅ እንደሚገባው ለመምከር ሲባል ገንቢ ሂስ ለማቅረብና ከንቱ ዝናን፣ ውዳሴና ገድልን በዚህ በ60ኛና 70ኛ ዓመታችን ኃጢዓታችንን ተናዘን ንስሓ ለመግባት ካልሆነ፣ ታሪክ ተራኪው አባት ህጻኑ ከመተኛቱ በፊት አባቱ በማንቀላፋታቸው ህፃኑ አባባ ‹‹መሸ ደህና ደሩ›› የሚለውን ይመስለኛል፡፡ ለወደፊቱ የጨበጥከውን ጡት የተመኘኸውን ገላ ታሪክ አትንገረን፡፡

ለሃገርና ለወገን ስትሉ በሃቀኝነት ለተሰው ሰማዕታት ክብርና ምስጋና መስጠት ይገባችኋል እንላለን፡፡

መቼም የትም እንዳይደገም!
NEVER EVER AGAIN!