ትግራይን ከአዲስ አበባ የሚያገናኘው መስመር

የአማራ ክልልን በማቋረጥ ትግራይን ከአዲስ አበባ የሚያገናኘው መስመር ዝግ ነው፤ አልተዘጋም የሚለው መከራከሪያ ከሰሞኑ የመወያያ ርዕስ ሆኗል።

የአማራ ክልል የመንገድና የትራንስፖርት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ወዳጆን ጨምሮ የሚመለከታቸው የዞን ባለስልጣናት መንገዱ አልተዘጋም ሲሉ፤ የትግራይ ክልል ትራንስፖርት ቢሮ በበኩሉ በደህንነት ስጋት ምክንያት ህዝቡ አቅጣጫ ለመቀየር ተገዷል ይላል።

በኢትዮጵያ የመንጋ ፍትህ የሰው ህይወት እየቀጠፈ ነው

በደቡብ አፍሪካ እስር ላይ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ተለቀቁ

የሰሜን ወሎ ዞን የመንገድ ትራንስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጸሃይነው ሲሳይ በአሁኑ ሰዓት ወደ መቀሌም ይሁን ወደ አዲስ አበባ ምንም አይነት የትራፊክ መስተጓጎል እንደሌለና ኃገር አቋራጭ አውቶብሶችም እንደተለመደው እያለፉ መሆኑንም አበክረው ይናገራሉ።

መነሻቸውን ከወልዲያ አድርገው በኮረም በኩል ሰቆጣ የሚሄዱትም መደበኛ ስምሪታቸውን ይዘው እየሰሩ ነው የሚሉት አቶ ጸሃይነው፤ በሰሜን ወሎ ዞን በመንገድ መዘጋት ምክንያት የተቋረጠ የትራንስፖርት አገልግሎት አለመኖሩን ገልፀዋል።

ከዚህ ቀደም በጥቅምት ወር ላይ በአላማጣ ከተማ የታሰሩ ሰዎች እንዲፈቱ በጠየቁ የቆቦ ከተማ ወጣቶች የአላማጣ ቆቦ መስመር ለቀናት መዘጋት፣ እንዲሁም በወልዲያ በኩል ወደ ትግራይ ለበዓል ሲጓጓዙ የነበሩ በጎች በወጣቶች መዘረፍ፣ እንዲሁም ወደ ትግራይ ክልል ይጓዝ የነበረ ተሳቢ አማራ ክልል ውስጥ በወጣቶች እንዲቆም ተደርጎ ጭነቱ የመዘረፍ ሁኔታ ተከስቶ ነበር።

በዚህም ምክንያት የፀጥታ ስጋት በመፈጠሩ ወደ ትግራይ ክልል ለመጓዝ በአፋር በኩል ተለዋጭ መንገዶችን መጠቀም ጀምረዋል የሚሉ ጉዳዮች በማህበራዊ ሚዲያ እየተነገረ ቢሆንም አቶ ጸሃይነው ይህ ከእውነት የራቀ ነው ይላሉ።

አሽከርካሪዎች በአፋር በኩል ያለውን ተለዋጭ አማራጭ መንገድ መጠቀማቸውን አምነው ይህ ግን እንደሚባለው ሳይሆን ደሴ እና ደብረ ብርሃንን አቆራርጦ ከወልዲያ-አዲስ አበባ በሚወስደው መንገድ ላይ ብዛት ያለው የፍጥነት መቀነሻ ግንባታ በመኖሩ ይህን ሽሽት የአፋሩን ተለዋጭ መስመር እንደማራጭ እንዲጠቀሙ አድርጓቸዋል ይላሉ

“ከፍጥነት መቀነሻዎቹ ብዛት የተነሳ ‘በአሽከርካሪዎች፣ በተሽከርካሪዎች እና በተሳፋሪዎች ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው። በሰዓታችን እየደረስን አይደለም’ በማለት የታችኛውን [አፋር] ተለዋጭ መንገድ ሲጠቀሙ ነበር። እኛም ከፌደራል መንገዶች ባከስልጣን ጋር በመነጋገር የፍጥነት መቀነሻዎቹ እንዲነሱ ተደርጎ መንገዱ ክፍት ተደርጓል።” ይላሉ አቶ ጸሃይነው።

የደቡብ ወሎ ዞን የሰላም እና ደህንነት መምሪያ ተወካይ ኃላፊ አቶ እጅጉ መላኬም በአቶ ጸሃይነው ሐሳብ ይስማማሉ ከትግራይም ወደ አማራ ክልል እንዲሁም ከአማራ ወደ ትግራይ ያሉ የተሽካርካሪዎች እንቅስቃሴ በተለመደው ቀጥለዋል ይላሉ።

ከዚህም በተጨማሪ የአማራ ክልልን በማቋረጥ ትግራይን ከአዲስ አበባ የሚያገናኘውን መስመር ዝግ አለመሆኑንና ምንም አይነት የፀጥታ ስጋት እንደሌለም አፅንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።

ከዚህ ቀደም በአንድ ወቅት ለጥቂት ሰዓታት መንገዶች የተዘጉበትን አጋጣሚ አንስተው እሱም ችግሩ ተቀርፎ ወዲያው ተከፍቷል ይላሉ።

“በአንድ ወቅት ብቻ የፌደራል መንገዶች ባለስልጣን የፍጥነት መቆጣጠሪያ መቀነሻዎችን ሲያፈርስ የተቀየሙ ወጣቶች መንገዱ ለጥቂት ሰዓታት ዘግተውት ነበር። ከዚህ ውጪ እኛ የምናውቀው ችግር የለም” ብለዋል።

“በአምስት የዓለም ዋንጫዎች ወርቅ እንዲመጣ ምክንያት ነኝ” አትሌት ገብረእግዚአብሔር

ከዚህ ቀደም ጤፍ እና በጎች ከመኪና ላይ ተወሰዱ የሚባለው ባለፈው ዓመት መጀመሪያ ላይ የተፈጠረና በጣም የቆየ መረጃና የአንድ ጊዜ ክስተት መሆኑንም ገልፀዋል።

ባለፈው አመት ወጣቶች የፍጆታ እቃዎችን የጫኑ መኪኖችን አያልፉም ብለው መንገድ ዘግተው የነበረ ሲሆን በወቅቱም የፀጥታ ኃይሉን በማሰማራት እንዲሁም ከወላጆች፣ ከወጣቱና ከማህበረሰቡ ጋር በተደረጉ ተደጋጋሚ ውይይቶች ችግሮቹን እንደፈቷቸው ያስረዳሉ።

ሁለት መልክ ያለው የጅግጅጋ የአንድ ዓመት ክራሞት

ከዚህም በተጨማሪ ተዘረፍን ብለው አቤቱታ ላሰሙት ገንዘብ እንዲከፈላቸውና ከዚህም በተጨማሪ ጥፋቱን አጠፉ የተባሉ ወጣቶች ህግ ፊት እንዲቀርቡ መደረጉንና አሁንም በህግ የተያዘ ጉዳይ መሆኑን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

“ተከታትለን ያረምነው የአንድ ጊዜ ስህተት ነው። ይሄንን የሚያውክ ምንም አይነት ኃይል የለም። ይሄ ሁኔታ እንዲቀጥል እኛም አንፈቅድም፤ በኛ በኩል ምንም አይነት ስጋት የለም። ነገር ግን የተለየ ስጋት አለን የሚሉና ያላቸው እኛን ሊያናግሩን ይችላሉ” ብለዋል።

የትግራይ ክልል የኮንስትራክሽን፣ መንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ አልማዝ ገብረጻዲቅ ከአቶ እጅጉ የተለየ ሃሳብ ነው ያላቸው። እሳቸው እንደሚሉት ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የደህንነት ስጋቶች በመከሰታቸው ህዝቡ ሳይፈልግ የሚጓዝበትን መስመር ለመቀየር መገደዱን ይናገራሉ።

“ከ2010 መጨረሻ ጀምሮ አንዳንድ የጸጥታ ችግሮች ስለነበሩ እና ኃላፊነት የሚወስድ አካል ስለሌለ ህብረተሰቡ የሚጠቀምበትን መስመር ለመቀየር ተገዷል” ሲሉ ወ/ሮ አልማዝ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአፋር ክልል የሚደረገው ጉዞ በሎጊያ፣ በሰመራ እና በአዋሽ በኩል ተደርጎ አዲስ አበባ እንደሚደርስ የሚናገሩት ወ/ሮ አልማዝ፤ ምንም እንኳ ይህ መስመር ርዝመቱ ቢጨምርም ህብረተሰቡ ይህን አማራጭ ለመውሰድ እንደተገደደ ያስረዳሉ።

ለደህንነታቸው የሰጉና አቅም ያላቸው የህብረተሰቡ ክፍልም የአየር ትራንሰፖርት አማራጭን እየተጠቀሙ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

ችግሩን ለመፍታት ከፌደራል መንግሥቱ እና ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር ውይይት መደረጉን ገልፀው ምንም የተቀየረ ነገር የለም ብለዋል።

“ከነዚህ አካላት ጋር በነበረን ግምገማ መንግሥት ለምን ኃላፊነቱን እንዳልወሰደ አንስተን ነበር። እስካሁን ግን እንደ መንግሥት ኃላፊነት የወሰደ አካል የለም።” ሲሉ ተናግረዋል።

የህዳሴ አውቶብስ ኃላፊዎች ማህበር አቶ ተዓምራት ዮሴፍ ማህበሩ ወደተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የሚያሰማራቸው ከ50 በላይ የሚሆኑ አውቶቡሶች እንዳሉት ገልፀው ከዚህ ቀደም መኪኖቻቸቸው መደበኛ መስመር በነበረው በደሴ በኩል ይጓዙ የነበረ ሲሆን ይህ ግን ከሶስት አመታት ወዲህ ተቀይሯል ይላሉ።

“ባለፉት ሶስት ዓመታት በሀገሪቱ ያለው ሁኔታ ግን ከአዲስ አበባ፣ መተሃራ፣ አዋሽ፣ ከዛም በአፋር አድርገን ነው ወደ መቀለ የምንመጣው። ከአዲስ አበባ ወደ ሽሬ፣ ራማ፣ አድዋ እና አክሱም የሚጓዙ ተሽከርካሪዎችም የአፋርን መስመር ነው የሚጠቀሙት።” በማለት ይናገራሉ።

የሆንግ ኮንግ ፖሊስ፡ «ሰልፈኛ አስመስለን ፖሊስ አሰማርተናል»

በአማራ ክልል በኩል አቆራርጦ የሚያልፈው እና ትግራይን ከመሃል ሃገር ከሚያገናኘው መንገድ የአፋርን መንገድ እንደአማራጭ ከመጠቀም በተጨማሪ ከመቀሌ ወደ ደሴ ይደረግ የነበረው ጉዞ እንዲቋረጥ ከተደረገ አንድ ዓመት ያህል እንደሆነውም ገልጸዋል። ለዚህም እንደ ምክንያትነት የሚያነሱት ጥቃት መድረሱን ነው።

“ከአዲስ አበባ ወደ ትግራይ የሚሄዱ ተሽከርካሪዎች የትግራይ መሆናቸው ስለሚታወቅ እንዲቃጠሉ ይደረጋል አልያም የመኪናው መስታወት ይስበራል።” ይላሉ

ይህም ለኪሳራ እንደዳረጋቸው ገልፀው “የፊተኛው የመኪና መስታወት ዋጋው ከ100 ሺ ብር በላይ ነው። 20 ሺ ብር ለማግኘት 100 ሺ እንከስራለን። የመንገደኞች ድህንነትም አደጋ ውስጥ ነበር። ተጓዦች እንዲወርዱ ይደርጉና መታወቂያቸው እየታየ ይዘረፋሉ።” በማለት የጉዞ አቅጣጫ ለውጥ ወይም የአንዳንድ መስመሮች አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ እንዲቋረጥ የተደረገበትን ምክንያት ያስረዳሉ።