የኖረጂያን አውሮፕላን

እርካሹ የኖርዌጂያን አየር መንገድ በ737 ማክስ አውሮፕላን እገዳ ሳቢያ በአየርላንድና በአሜሪካ መካከል የሚያደርገውን በረራ ከመጪው ወር ጀምሮ እንደሚያቋርጥ አስታወቀ።

“ይህ የበረራ መስመር በንግዱ አዋጭ እንዳልሆነ ውሳኔ ላይ ደርሰናል” ብሏል አየር መንገዱ።

ቦይንግ ትርፋማነቴ ቀንሷል አለ

ቦይንግ የ737 ማክስ ሶፍትዌርን አሻሽያለሁ አለ

አየር መንገዱ እንዳለው ከደብሊን፣ ኮርክ፣ ሻኖን ወደ አሜሪካ እና ካናዳ የሚደረጉትን ጨምሮ ስድስት የበረራ መስመሮች በመጪው የአውሮፓዊያኑ መስከረም 15 እንደሚቋረጡ ተናግሯል።

ትርፋማ ለመሆን እየታተረ የሚገኘው አየር መንገዱ ባለፈው ወር እንዳስታወቀው ወደ ትርፋማነቱ ለመመለስ በ737 ማክስ አውሮፕላን ላይ ጥሎት የነበረውን እገዳ ሊያነሳ እንደሚችልም ገልጿል።

የአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ምርት የሆነው 737 ማክስ አውሮፕላን የላየን ኤር አውሮፕላን በጃካርታ ባሕር ላይ እንዲሁም ባለፈው መጋቢት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋን አስተናግዷል። በሁለቱ አደጋዎችም በአጠቃላይ 346 ሰዎች ሕይወት አልፏል።

ታዲያ እነዚህን ሁለት አደጋዎች ተከትሎ 737 ማክስ አውሮፕላን በበርካታ አገራት እገዳ ተጥሎበታል። እገዳውን ከጣሉ አገራት መካከልም ኖርዌይ አንዷ ናት።

“ከባለፈው ሚያዚያ አንስቶ አውሮፕላኑን በሌላ አውሮፕላን በመተካት በአየርላንድና በሰሜን አሜሪካ መካከል ባሉ የበረራ መስመሮች ለሚጓዙ ደንበኞቻችን አገልግሎት ለመስጠት ስንጥር ቆይተናል፤ ነገርግን 737 ማክስ አውሮፕላን ችግሩን አስተካክሎ ወደ ሥራ መቼ እንደሚመለስ የታወቀ ነገር የለም። በመሆኑም የሰጠነው መፍትሄ ዘላቂነት ያለው አይደለም” ሲሉ ማቴው ውድ የተባሉ የአየር መንገዱ ባለስልጣን አስታውቀዋል።

ቦይንግ በ 737 ማክስ ምክንያት አምስት ቢልየን ዶላር ማውጣቱ ተገለጸ

አየር መንገዱ አክሎም ለበረራ ቀድመው የተመዘገቡ መንገደኞች በሌላ የኖርዌጂያን አየር መንገድ አገልግሎት ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ በአየር መንገዱ መጓዝ የማይፈልጉ ደንበኞች ካሉም ሙሉ ገንዘባቸውን ተመላሽ እንደሚያደርጉላቸው ገልጸዋል።

ባለስልጣኑ እንዳሉት ከደብሊን ኦስሎ፣ ከስቶክሆልም ኮፐንሀገን ለሚደረጉ በረራዎች የተለመደውን አገልግሎት መስጠታቸውን እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።

ከአየርላንድ ወደ አሜሪካ የሚደረጉ በረራዎችን ለማቋረጥ ያሳለፉት ውሳኔ ግን የመጨረሻ እንደሆነ አስምረውበታል።

“በኖርዌጂያን ዓለም አቀፍ አየር መንገድና በኖርዌጂያን ግሩፕ በጋራ ደብሊን ላይ የተመሰረቱ ሥራዎችን የሚያከናውኑ 80 ያህል ሠራተኞች በበረራ መስመሩ መዘጋት ችግር አያጋጥማቸውም” ሲሉ ውድ ጨምረው ተናግረዋል።

የኖርዌጂያን አየር መንገድ በአውሮፓዊያኑ 1993 ለአገር ውስጥ በረራ የተመሠረተ ሲሆን በ2002 ግቡን በማስፋት ትልቅ አየር መንገድ ለመሆን በቅቷል ።

አየር መንገዱ የሚያስከፍለው ክፍያ ተመጣጣኝ በመሆኑ በፍጥነት ለማደግ እንዳስቻለው እና በአውሮፓ በርካሽነቱ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ አየር መንገድ ለመሆንም ችሏል።

ባለፈው ዓመት ብቻ 35 አዳዲስ የበረራ መስመሮችን የጀመረ ሲሆን ከ37 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን ያጓጉዛል፤ 2000 ተጨማሪ ሠራተኞችንም ቀጥሯል።

ርካሽ በሆነ የበረራ ዋጋም ከእንግሊዝ ወደ አሜሪካ በ2014 በረራ ጀምሯል። አሁን ላይ ግን ከለንደን ጋትዊክ አየር ማረፊያ 12 በሚሆኑ የአሜሪካ መዳረሻዎች ላይ አገልግሎት ይሰጣል።

አየር መንገዱ ትልቅ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ሲሆን በርካታ መንገደኞችን በማጓጓዝ የኒዮርክ ከተማ አካባቢን በማገልገል ከእንግሊዝ አየር መንገድ፣ ኤር ካናዳ ወይም ሉፍታንዛ በላቀ በርካታ መንገደኞችን እንደሚያጓጉዝ የኒዮርክ እና ኒውጀርሲ ባለስልጣናት መረጃ ያመለክታል።

ባለፈው ዓመት ብቻ በነዳጅ ዋጋ፣ ከፍተኛ ውድድር፣ በድሪም ላይነር አውሮፕላኑ ላይ በሚያጋጥሙ የሞተር ችግር አየር መንገዱ 1.45 ቢሊየን ክሮነር (135 ሚሊየን ፓውንድ) አጥቷል።

ባለፈው ሚያዚያ ወር ኪሳራውን ለማስተካከል ከአክስዮን ሽያጭ 1.3 ቢሊየን ክሮነር ማግኘት የቻለ ሲሆን የተወሰኑ አውሮፕላኖችንም ለመሸጥ ተገዷል።