August 15, 2019

ጋዜጠኞች፣የእብን አባላት እና አመራሮች ብቻ ሳይሆን የአዴፓ የአዲስ አበባ የወረዳ አመራሮችም ታስረዋል

የአብን ሊቀመንበር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ኢህአዴግ መፈንቅለ መንግሥት ብሎ የጠራውን የሰኔ 15ቱን ግድያ ሽፋን አድርጎ በአማራ ሕዝብ ላይ የከፈተው ዘመቻ የተቀነባበረ መሆኑን ገልጸው እስሩ ያነጣጠረው ሆን ተብሎ የአማራን ሕዝብ ትግል ለማዳከም መሆኑን ገልጸዋል።የእስር እርምጃው የአብን አመራሮች እና አባላት ላይ ብቻ ሳይሆን ጋዜጠኞች ፣የመብት ተሟጋቾች፣የአማራን ሕዝብ ጉዳይ ያነሱ የመንግሥት ሰራተኞች ፣የሕግ ባለሙያዎች እና የገዢው ፓርቲ አባል የሆነው የቀድሞው ብአዴን የአሁኑ አዴፓ የአዲስ አበባ የወረዳ አመራር አባላት ጭምር ለእስር መዳረጋቸውን ከበረራ ጋዜጣ የትላንት እትም ጋር ባደረጉት ሰፋ ያለ ቃለመጠይቅ ገልጸዋል።

በርካታ ጉዳዮሽች የተዳሰሱበት የአብን የወቅቱ ሊቀመንበር ሙሉ ቃለመጠይቅን ያንብቡት ሼር አድርጉት

Playing Adx

“እነዶ/ር አምባቸዉንና ምግባሩን ከሁላችንም በተሻለ የሚቀርቧቸዉን ክርስቲያንንና በለጠ ካሳን በግድያ ጠርጥሮ ማሰር የአመቱ ታላቅ ምፀት መሆን አለበት!!” ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ የአብን ሊቀመንበር
****
የፓርቲያችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ሊቀመንበር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ የሰኔ 15 የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችና የአገር መከላከያ ሚ/ር ከፍተኛ አመራሮችን ግድያ ተከትሎ በአብን አባላትና አመራሮች፣ በአማራ የመብት አንቂዎች፣ በፀጥታ አካላትና በአዲስ አበባ የባላደራ ም/ቤት አባላት ላይ እየተፈፀመ ስላለው የጅምላ እስርና ወከባ፣ ስለፓርቲው ቀጣይ እርምጃ፣ ስለ ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ እንዲሁም ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ነሐሴ 8 ቀን 2011 ዓ.ም ከወጣችው በረራ ጋዜጣ ጋር ያደረጉትን ቆይታ እንሆ!!
******
በረራ:- ንቅናቄችሁ የወቅቱን ተለዋዋጭና ሴራ-ተኮር ፖለቲካ እንዴት እየተከታተለው ይገኛል?

ዶ/ር ደሳለኝ፡- ከሰኔ 15 ቀን 2011ዓ.ም በኋላ በአገራችን የፓለቲካ ሁኔታ ከፍተኛ ሴራ እየተጠነሰሰ የቀጠለበትና የአማራን ህዝብ ወጥመድ ዉስጥ ለማስገባትና ለማንበርከክ ወደረኞቻችን እረፍት አጥተዉ እየሰሩ ያሉበት ሁኔታ ዉስጥ እንዳለን ንቅናቄያችን ይረዳል፡፡ የሴራዉ ዋነኛ ጭብጥ ሰኔ 15 የተፈጠረዉን የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችና የአገር መከላከያ ሚ/ር ከፍተኛ አመራሮችን ግድያ ተከትሎ የፌደራል መንግስት ምንም አይነት የወንጀል ምርመራ ባልተካሄደበት ሁኔታ ጉዳዩን «መፈንቅለ መንግስት» ነዉ በማለት፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ የአማራን ትግል በተለያየ መስኩ እየመሩ ያሉ የአማራ ህዝብ አብሪ ኮከቦችን ለመምታትና ህዝባችን ያለመሪ ለማስቀረትና ድምጽ አልባ አደርጎ ለመግዛት እየተሞከረ ነዉ፡፡ መንግስት ግድያዉን መፈንቅለ መንግስት ብሎ በሰየመ በማግስቱ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አንድ መግለጫ አዉጥቶ ነበር፡፡ በመግለጫዉ ላይ «ማናቸዉም አማራ ጠል ኃይሎች በወንድሞቻችን ሞት አስታከዉ የተትረፈረፈ የፓለቲካ ትርፍ ለማጋበስ ከሚያደረጉት እኩይ ስራ እንዲታቀቡ» የሚል ነበር፡፡

በኋላ ግልጽ እንደሆነዉም ተለዉጦ ያልተለወጠዉ ኢህአዴግ ግድያዉን መፈንቅለ መንግስት ብሎ በመሰየም፤ አንድም የአማራን ህዝብ በመላ ኢትዮጵያዊያንና በአለም ፊት አንገቱን እንዲደፋ ማድረግ (እነ ኸርማን ኮህን በትዊተር ገጻቸዉ የአማራን የበላይነት እንደገና ለማምጣት የተሞከረዉ ሁኔታ ከሽፏል፤ ለወደፊትም አይሳካም ያለበትን ማስታወስ እንችላለን)፣ አማራ በአለማቀፉ ማህበረሰብና በሌሎች ኢትዮጵያዊያን ፊት ሁሌም በጥርጣሬ እንዲታይ ማድረግ (የተለመደ የአማራ ጠሎች ሴራ መቀጠል)፣ ሁለትም የአማራ የተለያዩ አደረጃጀቶችንና የነቁ አማራዎችን “ከመፈንቅለ መንግስቱና” ከግድያዉ ጋር በተያያዘ ሊያስጠረጥር የሚያስችል ምንም አይነት መነሻ ምክንያት በሌለበት ሁኔታ የጅምላና ዘፈቀደ እስር በመፈጸም አማራን ለማጥቃት ተጠቅሞበታል፡፡ ለምሳሌ፡-
 የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራሮችን፣ አባላትንና ደጋፊዎችን በአዲስ አበባ፣ ኦሮምያና ቤንሻንጉል ጉምዝ “ክልል”፤
 የአስራት ሚደያ መስራች አመራሮችንና ተባባሪ ጋዜጠኞችን፤
 የአዲስ አበባ ባላደራ (ባልደራስ) ምክር ቤት አመራሮችንና አባላትን፤
 የአማራ ልዩ ሃይልና ደህንነት ከፍተኛ አመራሮችንና ለህዝባቸዉ ይቆረቆራሉ ተብለዉ የሚታሰቡ አባላትን፤
 የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ (አዴኃን) አመራሮችን፤
 የአማራ ማህበረሰብ አንቂዎችንና የመብት ተሟጋቾችን፤
 የአማራ ጠበቆችንና የተለያዩ የመንግስት ሰራተኞችን፤
 የአማራ ተማሪዎች ማህበር አመራሮችን፤
 የደራ አማራ ማንነት ኮሚቴ አመራሮችና አባላት፤
 ከአማራ “ክልል” ዉጭ በኦሮምያ፣ በአዲስ አበባና በቤንሻንጉል ጉምዝ የሚገኙ ባለሃብቶችን፣ አርሶአደሮችን፣ የአማራ ዕድሮችና ማህበራት አመራሮች፤
 የኢትዮጲስ ጋዜጣ ጋዜጠኞችና ዘጋቢዎች፤
 የአዴፓ የአዲስ አበባ የክፍለከተማና የወረዳ አመራሮችንና አባላትን ነበሩትን ጨምሮ (የአማራን ጥያቄዎች በመጠየቃቸዉና ማራመዳቸዉ) በጅምላ ታስረዋል፡፡
እነዚህ የፖለቲካ፣ የሙያና የምብት ተሟጋች የሆኑ አካላትን ሁሉ «የሰኔ 15ቱን ግድያ በመፈጸምና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል በማፍረስ» ይሳተፋሉ ብሎ ማሰብ ሁሉም የአማራ ህዝብ በወንጀሉ ተሳትፎ አለዉ ብሎ እንደማሰብ ያለ እብደት ወይም ስካር ነዉ ሊሆን የሚችለዉ፡፡ እነዚህ ሁሉ እስሮች አላማ ያደረጉት ወንጀለኞችን ለፍርድ ማቅረብ ሳይሆን አማራዉንና የአማራ ተቆርቋሪ የሆኑ ወጣቶችን ማጥቃት መሆኑን መላዉ አማራ ህዝብና ሁሉም ቅን ኢትዮጵዊ ይገነዘበዋል፡፡ አሳሪዎቻችን አላማቸዉ ግልጽ ነዉ፡፡ በምንወዳቸዉ የአማራ መሪዎቻችንና ወንድሞቻችን ሞት አማራን መክፈል፣ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ነዉ የመደመር ካልኩሌተሩ ያሰላዉ፡፡ በእርግጥ ይህ መጥፎ አጋጣሚ የአብይ አህመድን አስተዳደር ለኢትዮጵያዊያንና ለአለማቀፉ ማህበረሰብ ራቁቱን ገልጦ ያሳየ ሁኔታም ፈጥሯል፡፡ ስለዚህ ወቅታዊ ፓለቲካዉ በጣም ተለዋዋጭ ቢሆንም ቅሉ የመፃዒዉን ጊዜ ጨለማነትም ቀድሞ ያሳየን በመሆኑ እንደ መልካም አጋጣሚ ወስደን በቀጣይ ማድረግ ስላለብን የመረረ ትግል ከወዲሁ መዘጋጀት እንዳለብን አስገንዝቦናል፡፡ ብአዴን/አዴፓም/ ይህ ሁሉ የአማራ ህዝብ ሲታሰር ድምጹን እንኳ ማሰማት አለመፈለጉ ዛሬም ለአማራ ጥቃት ስሜቱ ስስ ከመሆን ይልቅ የደነደነ ስሜት አልባ መሆኑን ስላመላከተን በረከተ መርገምት ነዉ፡፡ እነ ዶ/ር አምባቸዉና ምግባሩን ከሁላችንም በተሻለ የሚቀርቧቸዉን ክርስቲያንና በለጠ ካሳን በግድያ ጠርጥሮ ማሰር መቼም የአመቱ ታላቅ ምፀት መሆን አለበት፡፡

በረራ፡- በአማራ ህዝብ ጥቅም ዙሪያ ከአዴፓ ጋር አብሮ ለመስራት የጋራ ስምምነት ነበራችሁ። ከሰኔ15ቱ ክስተት በኃላ አዴፓ አሳሪ አብን ታሳሪ ሆኖ ይታያል። የጅምላ እስሩ ንቅናቄውን የማፈረስ ዘመቻ ነው ብላችሁ ታምናላችሁ?

ዶ/ር ደሳለኝ፡- ልክ ነዉ፡፡ አብን ከአመሰራረቱ ጀምሮ ግልጽ አድርጎ ያስቀመጠዉ አንዱ አላማዉ የአማራን ህዝብ ፍላጎት ፣ መብትና ጥቅም ማስጠበቅና ጠንካራ አማራን በመፍጠር የኢትዮጵያን ህልዉናና አንድነት ማስጠበቅ ነዉ፡፡ በዚህ ረገድ ከዉጭ አገር የመጡትንም ሆነ በአገር ዉስጥ ያሉትን በአማራ ህዝብ ስም የፓለቲካ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ድርጅቶችን ቀርበን በማናገር የአማራን ፓለቲካ የማጠናከርና አንድ ርምጃ ወደፊት ለመግፋት ብዙ ጥረት አድርገናል፡፡ ምንም እንኳን ኢህዴን-ብአዴን-አዴፓ አመሰራረቱ የትህነግ የአማራ ክንፍ ሆኖ እንዲያገለግልና የአማራን ህዝብ በነበረከት፣ አዲሱ፣ ህላዌ፣ ተፈራ ሞግዚትነት በእጅ አዙር ለማስተዳደርና አማራን ለመዝረፍ ቢሆንም ቅሉ በተለይ አብን ከተመሰረተ በኋላ ያነሳቸዉን የአማራ ህዝብ መሰረታዊ የህልዉና ጥያቄዎች ተቀብያለሁ፤ የአማራ ህዝብ ከእንግዲህ አንገቱን እንዲደፋ አላደርግም እያለ ይምል ይገዘት ስለነበር ድርጅቱ ሊለወጥ ይችላል ይሆናል የሚል ግምት (benefit of doubt) መስጠት አለብን የሚል ግምገማ ነበረን፡፡ ህዝባችንም ሆነ ንቅናቄያችን ይህን ጥንቃቄ የተሞላበት ተስፋ ለኢህዴን-ብአዴን-አዴፓ መስጠቱም ህዝባችን ለነጻነቱ እያደረገ ባለዉ ትግል ዉስጥ ከመጠፋፋትና ከመጠላለፍ ይልቅ ተቀራርቦና ተረዳድቶ መታገል ለአማራ ህዝብ ዘላቂና ስልታዊ ጥቅም የተሻለ ነዉ በሚል ነበር፡፡ በዚህ ረገድ ሁለቱ ድርጅቶች መግባባት ላይ ደርሰዉ የነበረዉ የአማራን ህዝብ ሰላም፣ ፀጥታና ደህንነት በማስጠበቅ፤ የአማራን ፓለቲካ እንዲሰክንና እንዲያድግ፤ የዴሞክራሲ ስርዓቱ እንዲሰፋና የሰለጠነ ፓለቲካ እንዲተከል እንዲሁም የኢኮኖሚና ልማት ተጠቃሚነት የራቀዉን ህዝባችን የሚጠቅሙ ስራዎችን በጋራ ለመስራት ነበር፡፡
ነገር ግን ብአዴን/አዴፓ/ ልምዱ ባደረገዉ የብልጣብልጥነት ፓለቲካ በመተብተቡና ሃላፊነት በተሞላበት መንገድ በጋራ በመስራት ህዝባችንን በጋራ ከመጥቀም ይልቅ ሁሌም በማይለቀዉ አድርባይነቱና አጎብዳጅነቱ የተነሳ ግንኙነታችን የሚፈለገዉን ያህል ዉጤት አላመጣም፡፡ ከዚያም አልፎ ብአዴን-አዴፓ ለኦህዴድ-ኦዴፓ በሰጠዉ ፈቃድ ወይም ፍራቻና ቸልተኝነት የተነሳ አማራዉ በመላ አገሪቱ እንደ አዉሬ እየታደነ እየታሰረና እየተሰቃየ ነዉ፡፡ አሁን ባለዉ ሁኔታ አብን በአማራ ህዝብ ዘንድ ያተረፈዉ ከፍተኛ ተቀባይነትና አመኔታ ምክንያት በመጪዉ ምርጫ የአዴፓ-ኦዴፓ የጋራ ስጋት በመሆኑ አብን ከተቻለ እንዲጠፋ፣ ካልሆነም እንዲዳከም ካላቸዉ ፍላጎትና መግባባት ተነስተዉ እያደረጉት ያለ እስር እንደሆነ እናምናለን፡፡ ነገር ግን የአብንን አመራሮች፣ አባላት፣ በተለያየ መንገድ ለአማራ ህዝብ ጥቅም መከበር የሚንቀሳቀሱ የአማራ ልጆችን በዘመቻ በማሰር የሚቆም የአማራ ትግል የለም፡፡ ይልቁንም የአማራ ህዝብ የብሄርተኝነት ትግል ላይ ነዳጅ እያርከፈከፉ እንደሚያቀጣጥሉት ምንም አያጠያይቅም፡፡ እንኳን እንደ አማራ አይነት ፍትኃዊና ሃቅ ላይ የተመሰረቱ ጥያቄዎች ያሉትን ህዝብ እንቅስቃሴ ቀርቶ በድቡሽት ትርክት ላይ የተመሰረቱ ብሄርተኝነቶችን እንኳን በማፈን ማጥፋት እንዳልተቻለ የአገራችን የ50 ዓመት የብሔርተኝነት እንቅስቃሴዎች ማሳያ ናቸዉ፡፡ በአጭሩ የኦዲፒ መራሹ ኢህአዴግ አፈናና የብአዴን/አዴፓ የጥፋት ተባባሪነት የአማራ ልጆችን ትግል እንደብረት ያጠነክረዋል እንጅ እንደጨዉ አያቀልጠዉም፡፡

በረራ፡- ከህዝብ ጋር የምታደርጉት ግንኙነት እንደተጠበቀ ሆኖ ፣ የታሰሩ የፓርቲያችሁን አመራሮችና አባላት ጉዳይ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ለማሳወቅ እያደረጋችሁት ያለ እንቅስቃሴ አለ?

ዶ/ር ደሳለኝ፡- የታሰሩ አመራሮቻችን፣ አባላትንና ደጋፊዎችን በተመለከተ የአማራን ህዝብ በተለያዩ መንገዶች ምን እተካሄደ እንዳለ በተከታታይ ማሳወቃችን እንደተጠበቀ ሆኖ አለማቀፉ ማህበረሰብም በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ዉስጥ ከሰኔ 15 በኋላ ስለተፈጠሩ የፓለቲካ ለዉጦች፣ በአማራ ህዝብ ላይ ያነጣጠሩ እስሮችና ለኢትዮጵያ መጣኢ እጣ ፈንታ ያላቸዉን አንድምታ፣ የአለማቀፉ ማህበረሰብ ሊጫወተዉ ስለሚገባዉ ድርሻና በቀጣይ የአብን የትግል አቅጣጫዎችን ለማስረዳት ተከታታይ ግንኙነቶችን አድርገናል፡፡ አዲስ አበባ የሚገኙ ዋና ዋና አገራት ኢምባሲዎችና ተወካዮችን (delegations)፣ አምንስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዉማን ራይትስ ዋች አይነት አለማቀፍ የመብት ድርጅቶችን፣ አለማቀፍና የአገር ዉስጥ ብዙሃን መገናኛዎችን በመጠቀም በአማራ ህዝብ ላይ የተቃጣዉን የመብት ጥቃት የማሳወቅ ስራ ሰርተናል፡፡ በዉጭ አገራት ከሚኖሩ የአማራ ድርጅቶች ጋር በመተባበርም ሰፊ የአድቮኬሲና የዲፕሎማሲ ስራዎችን እየሰራን ነዉ፡፡ በነዚህ ግንኙነታችን የአማራን ህዝብ ትግል ግቦችና በአማራ ህዝብ ዙሪያ የተነዙ የተሳሳቱ ትርክቶችን እንዲሁም የአማራ ህዝብ ትግል ግቦችን ከማስረዳታችንም በላይ ብዙ የተወራለት ለዉጥ ተንገራግጮ ሊቆም መድረሱን ለማስረዳት ችለናል፡፡ ለብዙ አገራት የዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቶች ለአፍሪካና ለኢትዮጵያ ዴስኮችም «Reversal and Back-pedaling of Democratization in Ethiopia: The Conundrum of the June 22/2019 Incidents and NaMA’s Assessment» የሚል ሰፊ ፓለቲካዊ ግምገማ፣ የታሳሪ ሰዎችን ስም ዝርዝሮች እንዲሁም የአያያዛቸዉን ሁኔታና የፍርድ ሂደታቸዉን ከሚያሳይ አባሪ ጋር በዉጭ ጉዳይ ክፍላችን በኩል ተዘጋጅቶ እንዲደርሳቸዉ ተደርጓል፡፡ በጎ ግብረ-መልስም አግኝተንበታል፡፡ በተጨማሪም ለኢሰመኮ፣ ሰመጉ፣ ለህ/ተ/ም/ቤት፣ ለጠ/ፍ/ቤት፣ ጠቅላይ አቃቢ ህግና መሰል የመብትና ዴሞክራሲ ጠበቃ ሊሆኑ ይገባል ብለን ላሰብናቸዉ ተቋማትም እግረ መንገዳችን መፈተሸ ስላለብን ሰለእስሩ ህገ-ወጥነትና የአማራን ህዝብ ዒላማ ያደረገ ጥቃት መሆኑን የሚገልጡ አቤቱታዎችን አስገብተናል፡፡ እንደ አምንስቲና ሰመጉ ያሉ ተቋማትም እስሮችን ህገወጥ በማለት አዉግዘዋል፡፡

በረራ፡- የተወሰኑ አክራሪ የኦሮሞ ብሄረተኞችና ምሁራን ቤተ-አምሓራ ወሎን የመዋጥ የአደባባይ ፕሮፖጋንዳ ዘመቻዎችን ከፍተው ይታያሉ። ንቅናቄችሁ ይሄን ጉዳይ እንዴት እየተከታተለው ነው?

ዶ/ር ደሳለኝ፡- አብን እንደ ድርጅት በኢትዮጵያ የታሪክ አረዳድ ላይ ምንም አይነት ብዥታ የሌለበት ፤ እንዲሁም የፓለቲካ ግልጠኝነት (political clarity) ያለዉ ድርጅት ነዉ፡፡ ከዚህ አኳያ በተደጋጋሚ በተለያዩ መድረኮች እንደገለጽነዉ ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ርስትና ዉርስ ናት ብለን እናምናለን፡፡ ማንኛዉም ጤነኛና ንፁህ አዕምሮ ያለዉ ሰዉ ሊረዳዉ እንደሚችለዉ ኢትዮጵያዊያን የረጅም ክፍለ ዘመናት መስተጋብር ያላቸዉ ፣ ለዘመናት የዘለቀ ሰፊ የህዝብ እንቅስቃሴ፣ መስፋፋት፣ መስፈር፣ የግዛት ወሰን ማስፋት፣ መገበር – ማስገበር፣ መጋባት-መዋለድ፣ የኢኮኖሚ ምንጮችን በመቆጣጠር የበላይ ለመሆንና ስልጣንን ለመቆጣጠር ለሺህ አመታት የዘለቀ የጦርነትም የሰላምም ጊዜያት አሳልፈዋል፡፡ ዛሬ ያለቸዉ ኢትዮጵያ እንደሌሎች አገሮች ሁሉ በዚህ የታሪክ ሂደት የተፈጠረች ናት፡፡ ይህን “የታሪክ ባለሙያ ነኝ” ለሚሉት ሁሉ ማስታወስ ግድ ቢለንም እንኳ፡፡
እነዚህ ጥቂት አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች ሊገነዘቡት የሚገባቸዉ ነገር ሃቅ ከላይ የተጠቀሰዉ ሆኖ እያለ የኦሮምኛ ስም ያለዉ ቦታ ሁሉ የኛ ነዉ የሚል የመዋጥ ፣ የመሰልቀጥና ከፍተኛ የሆነ የተስፋፊነት ቅዥት ዉስጥ መሆናቸዉ ለህዝቦች በሰላምና በጋራ ተከባብሮ ለመኖር ጠንቅ ከመሆን ያለፈ ዉጤት የሌለዉ መሆኑን ነዉ፡፡ ባለፈዉ 27 ዓመት ወያኔ የፈጠረዉን «ክልል» አለም አቀፍ ተቀባይነት ያለዉና ለዘላለም ፀንቶ የኖረና የሚኖር ፣ ቋሚ የአገር ድንበር አስመስለዉ ከማቅረባቸዉም ባሻገር ሁሉም ነገር የኛ ነዉ የሚለዉ የማይጨበጥ የቀን ህልም ነዉ፡፡ ማለም አይከለከልም በተግባር ማግኘት ግን አይቻልም፡፡ ተሪክ ጠቅሰን ግን እንከራከር የሚል ካለ አይደለም ወሎ (ቤተ-አምሐራ) ይቅርና ትላንት ወያኔ «ክልል» ብሎ የሰጣቸዉ ሸዋ፣ ወለጋና ባሌ እንኳ ግማሽ ምዕተ ዓመትን ወደኋላ ብንመለስ የአባቶቻችን የአማራ ነገስታት የእነ አጼ አምደጺዮንና አጼ ዘርዓያዕቆብ ታሪካዊ ግዛቶችና የአማራ አጽመ-ርስቶች እንደሆኑ ማሳየት ከባድ አይደለም፡፡ ባለቤትነት እንጠይቅ ካልን አማራ በስነቃሉ «በሺ አመቱ ርስት ለባለቤቱ» እንደሚለዉ አማራዊ አጽመ ርስቱን ይጠይቃል፡፡ ይህ ለሕዝባችን አብሮነት ጠንቅ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ንቅናቄያችን በሙሉ የኃላፊነት ስሜት የሚንቀሳቀስ፣ ለሰከነ ፖለቲካ በሩን የከፈተ በመሆኑ ቅዥት ላይ ያሉ ኃይሎች ሰመመን ውስጥ ሆነው በቃዡ ቁጥር መልስ መስጠት አይጠበቅብንም፡፡ መሬት ላይ መሥራት ያሉብንን ሥራዎች መሥራታችንን ግን አጠናክረን እንሰራለን፡፡ ስለዚህ የሚሻለዉ ያለፈዉን ታሪካችን ጥሩዉንም መጥፎዉንም ተቀብለን፣ መላ ኢትዮጵያዊያን የኢትዮጵያ ባለቤትነታቸዉን ተረድተን ግን ደግሞ አሁን የተተከለዉን ፌደራሊዝም ህፀፁን አርመን ወደፊት መሄድ ለአብሮነታችን እንደሚበጅ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን፡፡ እርግጥ ነው ጉዳዩ የተለመደና «የሞኝ ለቅሶ፣ መልሶ መላልሶ» አይነት ቢሆንም ቅሉ ንቀን የምንተወዉና በዝምታ የምንመለከተዉ ጉዳይ ግን ፈጽሞ አይሆንም፡፡ የተበታተኑ ነጥቦችን ጭምር እያገጣጠምን የምንከታተለዉ ጉዳይ ነዉ፡፡

በረራ፡- ማንነታቸው በይፋ በማይታወቁ አካላት መሪነት አካባቢያዊነት ላይ ያተኮሩ የአማራን ውስጣዊ አንድነት አደጋ ላይ የሚጥሉ የማህበራዊ ድረ-ገፅ ዘመቻዎችን ለማክሸፍ ምን እሰራችሁ ነው?

ዶ/ር ደሳለኝ፡- ትክክል ነዉ፡፡ በዚህ ሰዓት ወደረኞቻችን የአማራ ህዝብ አስቸጋሪ ፈተና ዉስጥ የገባ ስለመሰላቸዉ የተቀናጀ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በህዝባችን ላይ ከፍተዉበት ይገኛሉ፡፡ በሳይበሩ አለም በተለያየ መንገድና በአማራ ስም ጭምር መሽገዉ አማራን ለመከፋፈል፣ ከአማራነት ባነሰ ማንነት እንዲወርድ ለማድረግ ፣ ዉስጣዊ አንድነቱን ለመሸርሸርና እርስ በርሱ እየተጠራጠረና እየተናቆረ በዉስጥ ጉዳዩ ሲጠመድ እነሱ እኩይ አላማቸዉን ለማሳካት ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፡፡ ምንም እንኳ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ጩኸት ቢፈጥሩም መሬት ላይ ያለዉ የአማራ ህዝብ ሁኔታ ግን ከምን ጊዜዉም በላቀ ሁኔታ ዉስጡንም ዉጩንም በንስር ንቃት እየተመለከተና አንድነቱን እያጠናከረ ነዉ፡፡ በርግጥ በዚህ እኩይ ስራ ዉስጥ የኛዎቹ ሰዎችም አዉቀዉም ይሁን ሳያዉቁ ለነዚህ እኩያን ትርክት እያቀበሉ ያለበትን ሁኔታ መታዘባችን አልቀረም፡፡ አንዳንዶቹ በርግጥ ተከፋይ ካድሬዎች የነበሩ እንዲሁም እኛ ያላቦካነዉ ሊጥ አንጀራ ሆኖ አይወጣም ከሚል የእቡይነት ስሜት ዉስጥም ገብተዉ ያገኘናቸዉ ወንድም/እህቶቻችን አሉ፡፡ በዚህ ሰዓት እኔ ብቻ የምናገረዉና የማዉቀዉ ነዉ እዉነት፤ አኔን ብቻ ስሙኝ፤ እኔ ምክንያታዊ ነኝ ወዘተ በሚል ማናቸዉም ሰበብ የአማራን ህዝብ አንድነት በመሸርሸር ወደ አካባቢያዊነት ለማዉረድ የሚደረግ ተግባር ነገ ታሪክና ልጆቻችን ይቅር የማይሉት የባንዳ አከል ተግባር እንደሆነ አማራዉ ሊደራዉ ይገባል፡፡ እነዚህ ስራዎች በርግጥ የሳይበር ጦርነቶች ሲሆኑ በህዝባችን ላይ የሚካሄደዉ የማዳከም አካል ነዉ፡፡ የሳይበር ጦርነቶችን በድል ለመወጣትና የአማራን ህዝብ ከሳይበር ፕሮፓጋንዳ ጥቃት ለመከላከል ግን በጣም ብዙ የተደራጀ ፣ የተናበበና የተጠና ስራ መስራት እንዳለብንም የተረዳንበት ወቅት እንደሆነ መደበቅ አልፈልግም፡፡

በረራ፡- ከማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ አንዳንድ የንቅናቄችሁ አመራሮች ሳይቀር ስሜታዊ ፅሁፎችን ሲፅፉ ተስተውሏል ። ይህን ተከትሎ አብን ለሴራ ፖለቲካና ለውንጀላ ተጋላጭ ሆኖ ይታያልና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ምን ታስቧል?

ዶ/ር ደሳለኝ፡- ማህበራዊ ሚደያ ለአማራ ህዝብ ትግልና ለአማራ ብሔርተኝነት ማበብ እንዲሁም ለአብን መፈጠር የራሱ የጎላ ድርሻ ነበረዉ፡፡ የአማራነት ንቃት እንዲያድግ፣ ወጣቱን ስለአማራ ተጋድሎ ግቦች፣ የተወላገዱ ትርክቶችን፣ ታሪክንና ፓለቲካን ወዘተ በማስተማር በጎ አበርክቶ ነበረዉ፡፡ ለአብን የፓለቲካ ስራም ማህበራዊ ሚዲያዉና የአማራ አክቲቪስት ከፍተኛ አበርክቶ ነበረዉ፡፡ የጠቀሜታዉን ያክል ድግሞ ባግባቡ ካልጠቀምንበት ከፍተኛ ጉዳትና ዕዳ ይዞ የመምጣት ዕድልም አለዉ፡፡ ነገር ግን የተጠቀምንበትን ያህል ብዙ ችግሮችም እንደፈጠረብን መካድ አይቻልም፡፡ ከዚህ አንፃር እኔን ጭምሮ እንዳንድ የአብን አመራሮችና አባላት የምንጽፋቸዉ ጽሑፍቻችን አልፎ አልፎ ችግር እንዳለባቸዉ ገምግመናል፡፡ እነዚህን ችግሮች መቅረፍ አንዳለብን በተደጋጋሚ ብንገመግምም በሚፈለገዉ ፍጥነትና ደረጃ ከችግሩ ማዉጣት አልቻልንም፡፡ በርግጥ ከአመት በፊት ከነበርንበት ሁኔታ እንጻር ስናየዉ ብዙ መሻሻሎች አሉ ፤ ነገር ግን አሁንም ቢሆን የኛ ሚና መሆን ያለበት ፓለቲካዉ ነዉ፡፡ የአክቲቪዝሙን ስራ ለአክቲቪስቱ ልንተዉለት ይገባናል፡፡ ይህን የምልበት መሰረታዊ አመክንዮ የአማራ ፓለቲካ ምልዑነትን ሰለሚጠይቅና ወደረኞቻችንም ትንንሽ ነገሮችንና ቀጥታ አገላለፆችን እያጣመሙ በመተርጎም አጋነዉ እንዲጮኹ ስለሚያደርጓቸዉ የማስረዳትና የማብራራት ሸክሙን መሸከሙ ተጨማሪ ጫና ስለሚፈጥር በሂደት ከማህበራዊ ሚዲያ በተለይም ከፌስቡክ መዉጣታችን የግድ ነዉ፡፡ ወደፊት ከፍተኛ አመራሮች የራሳችን የማህበራዊ ሚዲያ ቡድንና አማካሪዎች ኖረዉን የተጠኑና የተመጠኑ መልዕክቶችን ለደጋፊዎቻችንና ለህዝባችን የምናደርስበት ሁኔታ እስኪኖር ድረስ ተሳትፎአችን የተገደበ መሆን እንዳለበት ግን በድርጅት ደረጃ አቅጣጫ አስቀምጠናል፡፡

በረራ፡- የአማራ ብሄረተኝነት ግንባታን ሁሉን አቀፍ በሆኑ (ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ) ዘርፎች ጭምር ለማድረግ እንደንቅናቄ ምን እየሰራችሁ ነው?

ዶ/ር ደሳለኝ፡- የአማራ ብሔርተኝነት ከፓለቲካዉ በዘለለ የአማራን ህዝብ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ በሚችሉ የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች ጭምር በርካታ ስራዎች መስራት እንዳለብን አቋም ወስደናል፡፡ በብሄርተኝነቱ አራማጆች መካከል የጋራ መረዳቱና መግባባቱም ከተፈጠረ ቆይቷል፡፡ ከዚህ አንጻር ብሔርተኝነታችን ዘርፈ ብዙ ስኬቶችን በአጭር ጊዜ እያስመዘገበ ነዉ፡፡ ለምሳሌ የአማራ ብሔርተኝነት በአጭር ጊዜ ዉስጥ አብንን የመሰለ የጠራ የትግል መስመር ያለዉ ፓለቲካ ፓርቲ፣ የተለያዩ የሲቪክ ማህበራትና አደረጃጀቶች፣ ሚዲያ፣ የህዝባችን የእርስ በርስ መተሳሰብና መረዳዳት ለአማራ የሰዉ ሰራሽና የተፈጥሮ ቅርሶች መቆርቆርንና የአማራን ህዝብ ሊያስከብሩ የሚችሉ በርካታ ስራዎችን መስራቱ በጎ ጅምር ነዉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአማራ የፋይናንስና የቢዝነስ ተቋማት (የአማራ ባንክና የአማራ ኢንሹራንስ አክሲዮን መሸጥ መጀመራቸዉ፣ የመቶ ፕሮጀክቶች ዉጥን) እንዲሁም መሰል ህዝባችን የሚጠቅሙ ስራዎች እንዲሰሩ ከወንድም እህቶቻችን ጋር እንመካከራለን፡፡ አስፈላጊ ሲሆንም አቅጣጫዎችን የማስያዝ ስራ ስንሰራ ቆይተናል፡፡ ወደፊትም በተለያ የማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች አማራዉ አንዲጠናከር የማድረግ ሃላፊነት አለብን፡፡ አማራ ከፍተኛ ቆጣቢ በሆነበት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እነ አቶ ባጫ ጊኒ የቀለዱብን ቀልድ በአጭሩ እናስቀረዋለንም፡፡ አማራ ላይ ማንም “አድቫንቴጅ” ሲወስድበትና ሲዘረፍ የነበረበትን ሁኔታ በጥቂት አመታት ዉስጥ አስቀርተን የአማራን የማህበረ-ኢኮኖሚ አብዮት በድል ማጠናቀቅ የፓለቲካ ትግላችን በድል እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ እገዛ እንዳለዉ እናምናለን፡፡ ይህ ማለት ግን አነዚህ ድርጅቶች የአንድ የፓለቲካ ፓርቲ ፍላጎት ዉጤቶች ናቸዉ ማለት አይደለም፡፡ የተለያዩ የፓለቲካ ድርጅቶች አባላትና ደጋፊዎች እየተሳፉባቸዉ ያሉ “non-partisian initiatives” መሆናቸዉን መግለጽም ተገቢ ነዉ፡፡

በረራ፡- የዛሬና የነገ የአማራ ሕዝብ መሪዎችን ከመፍጠር አኳያ አብን የፖለቲካ አመራር በማብቃቱ ረገድ ምን እየሰራ ነው?

ዶ/ር ደሳለኝ፡- አብን የአማራም ህዝብም ሆነ የኢትዮጵያ የመጪዉ ጊዜ ፓርቲ ነዉ፡፡ ከዚህ አንጻር በአብን ሊቀ-መንበርነቴ ከምደሰትባቸዉ ጉዳዮች ዉስጥ አንዱ በሺዎች የሚቆጠሩ፣ መልካም ስነ-ምግባር ያላቸዉ፣ በከፍተኛ ሁኔታ የተማሩ፣ ለአማራ ህዝብ ህይዎታቸዉን ለመስጠት የማያመነቱና ህዝባችንንም ሆነ አገራችንን ወደፊት በመምራት ወደ ተሻለ ደረጃ ሊያሸጋግሩ የሚችሉ ወጣቶች በብዛት አብንን ዉስጥ መሰባሰባቸዉ ነዉ፡፡ ነገ ሁኔታዎች ከፈቀዱ አብን ዉስጥ ህዝባችን ሊመሩ የሚችሉ ብዙ ባለተስፋዎች እንዳሉት አያለሁ፡፡ ነገር ግን ከዚህ በዘለለ ወጣት መሪዎችን በልዩ ሁኔታ መለየት ፣ ማሰልጠንና መኮትኮት መቻል አለብን፡፡ ለዚህም በቅርቡ መሪዎችን የማፍራት ስራ በፕሮጀክት ደረጃ ተይዞ ሊሰራበት እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጠን እየተንቀሳቀስን ነዉ፡፡ ዉጭ አገርም ሆነ በአገር ዉስጥ በሚገኙ ተቋማት የመሪነት ተስፋና ተስጽኦ (displayed leadership promise and character) ያላቸዉን አመራሮች መለየት፣ ማሰልጠንና የማብቃት ስራ ለመስራት እናስባለን፡፡ ለዚህም ሁሉም አማራ ድጋፍ እንዲያደርግልን እንፈልጋለን፡፡

በረራ፡- በቀጣዩ ዓመት ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው አገር አቀፍ ምርጫ የአብን ዝግጁነት የት ድረስ ነው? ከወቅቱ የፖለቲካ ኃይሎች አሰላለፍ አኳያስ አጋርነት ለመፍጠር እየሰራችሁት ያለ ስራ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ደሳለኝ፡- አብን ከመጀመሪያዉ ጀምሮ አቋሙን ግልጽ እንዳደረገዉ ምርጫዉ በተያዘለት ጊዜ መካሄድ አለበት ብሎ አቋሙን አሳዉቆ ለምርጫዉም አስፈላጊዉን ዝግጅት እያደረገ ያለ ድርጅት ነዉ፡፡ አማራጭ ፓሊሲዎችን፣ የምርጫ 2012 ማኒፌስቶና የምርጫ ስትራቴጅ በምርጫ ጉዳዮች ክፍል በቁልፍ ተግባርነት ተለይተዉ የዝግጅት ስራ እየሰራን ነዉ፡፡ ለምርጫዉ በተወዳዳሪነት፣ በምርጫ አስፈጻሚነትና በታዛቢነት ሊያገለግሉ የሚችሉ አባላትንም ለመመልመል እንዲያስችለን ፕሮፋይል የማደራጀት ስራ እየሰራን ነዉ፡፡ በምርጫዉ ዉስጥ ለመሳተፍ እየተዘጋጀን ነዉ የምንለዉ ምርጫ ለማካሄድ ሊሟሉ የሚገባቸዉ ሁኔታዎች (የተቋማት ሪፎርም፡-ነጻና ገለልተኛ ምርጫ ቦርድ፣ ነጻና ገለልተኛ የፍትህና የዳኝነት ስርዓት፣ ነጻና ገለልተኛ የጸጥታና ደህንነት ተቋማት፣ ነጻ ሚዲያ፣ አገራዊ ሰላምና መረጋጋት) ተሟልተዋል ብለን ስላምናምን አይደለም፡፡ እነዚህ ሁሉ ጉዳዮች የተሟሉ እንዳልሆኑ ግልጽ ነዉ፡፡ ቢሆንም ግን ከነችግሩም ቢሆን ምርጫዉን ማካሄድ ስትራቴጅክ ጠቀሜታ እንዳለዉ ስለገመገምን ጭምር ነዉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር አጋርነት ለመፍጠርና በኢትዮጵያ የ2012 ምርጫ ዉስጥ ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆነን ለመቅረብ የጀመርናቸዉ ዉይይቶች አሉ፡፡ ዉጤት እንደተገኘባቸዉ ወደፊት ይፋ ይደረጋሉ፡፡

በረራ፡- ወቅታዊ ፖለቲካዊና ድርጅታዊ ጉዳዮችን ጨምሮ ለአማራ ሕዝብና ለትግል አጋሮቻችሁ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ ዕድሉን ልስጥዎት?

ዶ/ር ደሳለኝ፡- የአማራ ህዝብ የትህነግ/ኢህአዴግን ዘረኛና አማራ ጠል ስርዓት ለማንበርከክ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል፡፡ ከፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ እስከ አስማረ ዳኘ፣ ከምርጫ 97 ማግስት እስከ የባህረዳር የነሐሴ 1 ሰማዕታት፣ ከነጎቤ መልኬ (ዋዋ) አስከ ህጻን ዮሴፍ እሸቱ የከፈሉትን ዋጋ በጥቂቱ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከዚህም በላይ ብዙ ባለስምና ስምየለሽ የአማራ አርሶአ ደሮችና ወጣቶች መተኪያ የሌለዉን የሕይወት መስዋትነት ከፍለዋል፡፡ በነዚህና በሌሎች ኢትዮጵያወዊያን ወገኖቻችን መስዋትነት መጥቷል ተብሎ የተለፈፈለት የኢህአዴግ ተለዉጫለሁ/ራሴን አሻሽያለሁ/ ሀተታ አብይ አህመድን በኃይለማርያም ደሳለኝ ቦታ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ከማስቀመጥ የዘለለ ለአማራ ህዝብ ትርጉም ያለዉ ለዉጥ ሊያመጣ የሚችል ነገር እንደሌለዉ ህዝባችን በአግባቡ መረዳት አለበት፡፡ አሁን ግልጽ የሆነዉ ነገር አማራ ጠል የሆነዉ ኢህአዴግ ከስሩ ካልተነቀለ አማራ ህዝብ ሁሌም የህልዉና ትግል ዉስጥ ሲዳክር እንደሚኖር ግልጽ ነዉ፡፡ ትግላችን ፍትኃዊ ስለሆነ ትግላችን በሰዉም ሆነ በፈጣሪ ዘንድ የተቀደሰ ነዉ፡፡ ትግላችን ግን ዛሬ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ማንኛዉም መስዋትነት ተከፍሎ የአማራ ህዝብ ከዚህ አስከፊ ስርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ካልተገላገለ አንገቱን ቀና አድርጎ መኖር አይችልም፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ አማራ በሚችለዉ መንገድ ትግሉን መቀላቀል፣ መደገፍ፣ አስፈላጊዉን አስተዋፆ ማበርከት አለበት፡፡ ባለፉት የትህነግ/ኢህአዴግ አይነት ስርዓት ዉስጥ ድጋሚ የአማራ ህዝብ ከሚወድቅ በትግል ዉስጥ በነጻነትና በክብር መዉደቅ የክብር ረፍት ነዉ፡፡ በጠ/ሚ/ር አብይ አስተዳደር አማራ ተሰፋ ማድረጉን አቁሞ ለነጻነቱ አምርሮ መታገል አለበት፡፡ ለዚህም ጥሪ ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ መላዉ ኢትዮጵያዊያን፣ የአማራ ህዝብ አጋር የሆኑ ዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ አባላት አማራ እንደ ህዝብ የሚያደርገዉን የህልዉና፣ የእኩልነትና ፍትሃዊ ትግል በሚችለዉ መንገድ እንዲደግፍ እጠይቃለሁ፡፡

በረራ፡- ቃለምልልሱን ስለጡን በበረራ ጋዜጣ ስም እናመሠግናለን!!
ዶ/ር ደሳለኝ፡- እኔም ስለተሰጠኝ ዕድል አመሰግናለሁ!!