

National Electoral Board of Ethiopia- NEBE -የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ጥያቄ 1 – የምርጫ ስርአቱ ለምን አልተቀየረም ?
መልስ – የምርጫ ስርአት አይነቱ በህገ መንግስቱ ተወስኖ የተቀመጠ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም አብላጫ ድምጽ ያገኘው አሸናፊ የሚሆንበት ስርአት በህገ መንግስቱ የተቀመጠ በመሆኑ በአዋጅ መሻር ስለማይቻል የህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠው የምርጫ ስርአት እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡ የፓለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ስርአቱ እንዲቀየር የጠየቁ ቢሆንም ህገ መንግስቱ እስካልተሻሻለ ድረስ በአዋጅ መቀየር አልተቻለም፡፡
ጥያቄ 2- የፓለቲካ ፓርቲዎች ለምስረታ ለአገራዊ ፓርቲ 10 ሺህ የድጋፍ ፊርማ እና ለክልል ፓርቲ ምስረታ 4 ሺህ የድጋፍ ፊርማ እንዲያሰባሰቡ በረቂቅ ህጉ ውስጥ ለምን ተካተተ ?
መልስ – የፓለቲካ ፓርቲዎች ህዝባዊ መሰረት እንዲኖራቸው ከመፈለግ አንጻር፣ ከአገሪቷ ህዝብ ቁጥር አንጻር እንዲሁም የሚወክሉት ህዝብ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ከማጥበቅ አንጻር 10 ሺህ እና 4 ሺ የድጋፍ ፊርማ እንዲያሰባስቡ መደንገጉ የተጋነነ ቁጥር አይደለም፡፡ በአንዳንድ ፓርቲዎች የሚነሳው አሁን ካለው የጸጥታ ችግር አንጻር 10 ሺህ ሰው ማስፈረም አንችልም የሚለው ሃሳብ የሚያሳምን ቢመስልም መታወስ ያለበት ግን አንድ ህግ ሲወጣ ለአንድ አመት ብቻ ተብሎ አለመሆኑን ነው፡፡ ህግ የሚወጣው ለረጅም ጊዜ ከመሆኑ አንጻር የህጉን መርሆ በጊዜያዊ ሁኔታ ብቻ ማየት አይገባም፡፡
ጥያቄ 3 – በረቂቅ ህጉ ላይ የመንግስት ሰራተኞች ለምርጫ ውድድር ሲቀርቡ በጊዜያዊነት ከስራ ቦታቸው እንዲለቁ የሚደረግበት ምክንያት ምንድነው ?
መልስ – ከዚህ በፊት ከፍተኛ አቤቱታ የሚቀርብበት የመንግስትን ሃብት ለፓርቲ ስራ ማዋል ለመቀነስ የመንግስት ሰራተኛ እጩዎች ከስራ ቦታ እንዲርቁ የሚያደርገው ድንጋጌ አላማው የፓለቲካ ፓርቲ ስራን ከመንግስት ስራ መለየት ነው፡፡ በመጀመሪያው ረቂቅ ላይ የመንግስት ሰራኞች ያለምንም ጥቅማ ጥቅም ከስራ ለጊዜው እንደሚርቁ ቢገልጽም ከፓለቲካ ፓርቲዎች በተገኘ ግብአት መሰረት በማድረግ እጩ ተወዳዳሪ የመንግስት ሰራተኞች እስከ ሁለት አመት የሚደርስ የአመት ፍቃዳቸውን እንዲጠቀሙ የሚያስችል ሆኖ ተሻሽሏል፡፡ በመሆኑም የአመት ፍቃዳቸውን ሲጠቀሙ ደምወዝ የሚያገኙ ቢሆንም የስራ ገበታቸው ላይ መገኘት እንደማይገባቸው ግን ህጉ ይደነግጋል፡፡ እጩ ተወዳዳሪው የመንግስት ሰራተኛ ከምርጫ ውድድሩ በኋላ ወደስራው የሚመለስበት እና ተገቢው ጥቅሙ መጠበቅ እንዳለበት ህጉ ጥበቃ ይሰጣል፡፡ በተጨማሪም ከመንግስት ለፓርቲ የሚሰጥ ድጋፍ ውስጥ ለምርጫ የመንግስት ሰራተኛን ያቀረቡ ፓርቲዎች በተጨማሪ መስፈርትነት እንዲታይላቸው ሆኖ ተጨምሯል፡፡ዋናው ግን የድንጋጌው አላማ የመንግስት ሃብትና ንብረት ለፓርቲ መገልገያነት እንዳይውል መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ ሊገባ ይገባል፡፡
ጥያቄ 4 – ለእጩነት ከቀረቡት መስፈርቶች መካከል ለሁሉም እጩዎች የደጋፊ ፊርማ እንዲያሰባስቡ ማድረግ ለምን አስፈለገ ?
መልስ – ከዚህ በፊት የነበረው የእጩነት መስፈርት በቁጥር (12) እና በእሱም በእጣ እንዲወሰን ሆኖ ገዳቢ የነበረ እና ብዙ አቤቱታዎች ሲቀርቡበት የነበረ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም በአዲሱ ረቂቅ ገደቡ ተነስቶ ለእጩነት ጥረት አድርገው የሚመጡ ፓርቲዎችና ግለሰቦችን ሁሉንም ለማስተናገድ ያለመ ነው፡፡ ለእጩነት የደጋፊ ፊርማ በምርጫ ወረዳው የሚያሰባስብ ሰው በሂደቱ ከማህበረሰቡ ጋር ራሱን የሚያስተዋውቅ ሲሆን ለምረጡኝ ዘመቻውም ቅድመ ዝግጅት የሚያደርግበት ይሆናል፡፡ በዚያውም በብዙ መራጮች ዘንድ የሚነሳውን የሚወክለን ግለሰብ ማን እንደሆነ እንኳ ሳናውቅ ድምጽ ስጡ እንባላለን የሚለውንም አቤቱታም ያስቀራል፡፡ እጩዎችና የሚወክሉት ህዝብ በግልጽ የሚተዋወቁበት እና የምርጫ ሂደቱን በቁም ነገር (seriously) የሚይዙ እጩዎችን ወደ ድምጽ መስጫ ወረቀት የሚያመጣ አሰራር ነው፡፡
ጥያቄ 5 – ዕጩዎች በግንባር ቀርበው መመዝገብ አለባቸው የተባለው ለምንድነው ?
መልስ – ከዚህ በፊት ከነበሩ ልምዶች በመነሳት እጩዎች ይኑሩ አይኑሩ ሳይታወቅ ስማቸው ብቻ ለምርጫ የሚቀርበብት አሰራርን ለማሻሻል የተካተተ ሲሆን የፓርቲም ሆነ የግል እጩዎች የእጩነት ምዝገባ በግንባር ቀርበው ማድረጋቸው ማጭበርበርን ይቀንሳል ተብሎ ይታመናል፡፡
ጥያቄ 6 – የፓለቲካ ፓርቲዎች ቢያንስ በ3 አመት አንድ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ ያለባቸው ለምንድነው ?
መልስ – የፓለቲካ ፓርቲዎች በሶስት አመት አንድ ጊዜ ከአባላት ጋር በመገናኘት ውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ አሰራራቸውን የሚያረጋግጡበት መንገድ ነው፡፡ ሶስት አመት ለጠቅላላ ጉባኤ አጠረ የሚባል አይደለም፡፡ አንድ ፓርቲ ከሶስት አመት በላይ ጠቅላላ ጉባኤ ሳያደርግ ከቆየ ውስጠ ፓርቲ አሰራሩ ላይ ያሉ ችግሮችንም በፍጥነት የመፍታት እድሉ ይጠባል፡፡ የአዋጁ አላማ ፓርቲዎችን አሰራር ማጠናከር፣ ውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲያቸውን ማበረታታት እና መቆጣጠር እንደመሆኑ መጠን ይህ አነስተኛ መስፈርት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ጥያቄ 7 – በቀድሞ ህግ የተመዘገቡ የፓለቲካ ፓርቲዎች በዚህ ህግ እንዴት ይገዛሉ ?
መልስ – ቀድመው የተመዘገቡ የፓለቲካ ፓርቲዎችን አስመልክቶ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ከተቀመጠው መስፈርት ጋር የሚጣጣሙበትን መንገድ አስመልክቶ ምርጫ ቦርድ መመሪያ እንዲያወጣ ህጉ ያስገድዳል፡፡ በመሆኑም ተመዝግበው የሚገኙ ፓርቲዎች በሂደት መስፈርቱን የሚያሟሉበትን ዝርዝሩን ከቦርዱ ከፓርቲዎች ጋር በመመካከር በሚያወጣው መመሪያ የሚያሳውቅ ይሆናል፡፡
የተሳሳቱ መረጃዎች
1. 10 ሺህ ደጋፊ ፊርማን ማሰባሰብ እንዲ 10 ሺህ አባላት በምስረታ እለት በግዴታ ፓርቲዎች ይኖራቸው ይገባል የሚል ግዴታ አላስቀመጠም፡፡ 10 ሺህ የፈረሙ ደጋፊዎችና ቢያንስ ከዚያ ቁጥር ውስጥ 5 በመቶ የሚሆኑት በመስራች ጠቅላላ ጉባኤው እንዲገኙ ነው የሚጠበቀው
2. ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ የሚያደርጉት ቢያንስ በ3 አመት ከመሆኑ ውጩ ስለጉባኤውም ሆነ ስሌሎች ውስጠ ፓርቲ ጉዳዮች የሚወስኑት ራሳቸው ፓርቲዎች ናቸው፡፡ቦርዱ በፓርቲዎች ውስጠ አሰራር ላይ ጣልቃ አይገባም፡፡
3. የአባላት ስም ዝርዝርን በየአመቱ ሪፓርት የማድረግ ግዴታ ህጉ አያስቀምጥም፡፡ ህጉ የሚያስቀምጠው የአባላት ቁጥርን የጾታ የእድሜንና የመኖሪያ አካባቢ( ክልል ከተማ …ወዘተ) ተዋእጾ ፓርቲዎች ሪፓርት እንዲያደርጉ ብቻ ነው፡፡ ይህም የፓርቲዎች ዳታ ለማደራጀትም ሆነ ድጋፍ ለመስጠት ስለሚረዳ ነው፡፡
4. በህጉ ላይ የተሰጡ ግብአቶች ከአገረ አቀፍና አለም አቀፍ ልምዶች ጋር ታይተው ተካተዋል፡፡ የህግ አርቃቂ ኮሚቴው ግብአቶችን አልወሰደም የሚለው የተሳሳተ መረጃ ነው፡፡ አርቃቂ ኮሚቴው ሙሉ ለሙሉ የተጠቀማቸው፣ በከፊል የተጠቀማቸው ወይም አሻሻሎ እንደግብአት የወሰዳቸው ሃሳቦች ከፓለቲካ ፓርቲዎች፣ ከምሁራን እንዲሁም ከተለያዩ ጥናቶች የተገኙ ናቸው፡፡
ስለህጉ ጥያቄ አለዎት ? እባክዎን በኮመንት መስጫው ሳጥን ይጻፉልን፡፡