August 17, 2019

Source: https://fanabc.com

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 11፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኬንያው ፕሬዚደንት ኡሩ ኬንያታ ጳጉሜ 2 እና 3 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሚካሄደው የሰላም ፌስቲቫል ላይ ይሳተፋሉ፡፡

ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ከሀገር አቀፍ የአንድነት፣ ይቅርታና ሰላም ኮሚቴ የበላይ ጠባቂ የቀድሞ ፕሬዚደንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እና ከኮሚቴው አባላት ጋር ተወያይተዋል፡፡

በዚህ ወቅት ኢትዮጵያውያን በምንም ሁኔታ ውስጥ ሆነው የማይለወጡ እና ለድርድር የማይቀርቡ የኬንያውያን ወዳጆች ናቸው ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።
ኢትዮጵያ ከቅድመ-ነጻነት ጊዜ ጀምሮ የኬንያ የቁርጥ ቀን ወዳጅ እንደሆነች የገለፁት ፕሬዚዳንቱ በሀገር አቀፍ የአንድነት፣ ይቅርታና ሰላም ፌስቲቫል ላይ እንደራሳችሁ እንደ ኢትዮጵያውያን ሆኜ እገኛለሁ ብለዋል።

የኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ኬንያ የኢትዮጵያ ወዳጅ ሀገር መሆኗን በመግለፅ የኬንያን ግጭትን የማስወገድ ተሞክሮ እንዲያጋሩ እንደሚፈልግ ገልፀዋል።

ከፕሬዚደንቱ በተጨማሪ ለቀድሞ የኬንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ራኢላ ኦዲንጋ በፌስቲቫሉ ላይ እንዲሳተፉ ግብዣ የቀረበላቸው ሲሆን ለመሳተፍ ቃል ገብተዋል።

ጳጉሜ 2 እና 3 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሚካሄደው የሰላም ፌስቲቫል የሩዋንዳው ፓልካ ጋሜና የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡