August 18, 2019

ማንነቱን የማያውቅ የሌላውን ማንነት ሊያውቅ አይችልም፤የወሎ ማንነት ኢትዮጵያዊነት ነው!

ከወሎ የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማህበር የተሰጠ መግለጫ ነሃሴ 11 ቀን 2011 ዓም(16-08-2019)

ወሎ የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማህበር ከተመሠረተበት እለት አንስቶ ስለወሎ ክፍለሃገር ታሪክ፣ መልክአምድራዊ አቀማመጥ፣የተፈጥሮ ችሮታ(ሃብት)፣በኤኮኖሚያዊ ዘርፍና ማህበራዊ እንቅስቃሴ እንዲሁም የሕዝቡን በኢትዮጵያዊነት ላይ ያረፈ ፣ የተለያዩ ጎሳዎችን አቅፎ በተውጣጣ ባህልና እምነት የዳበረ ማንነት ባለቤት መሆኑን ለመተንተን ሞክሯል።

ይህንን የአንድነት ምሳሌና ናሙና የሆነ የሚያኮራ ክፍለሃገር ከሃያ ስምንት ዓመት ወዲህ የተፈጠሩ ቡድኖች ሌላ መልክና ስም እዬሰጡ፣ለዘመናት በቤተሰብነት ደረጃ ተዋልዶና ተዛምዶ የኖረውን ሕዝብ ጭራሽ በማያምንበት የሴራ ገመድ እዬተበተቡ እርስ በርሱ እንዲጋጭና ኢትዮጵያን ከማፈራረስ ዓላማ በመነሳት ለኢትዮጵያ ዋልታና ማገር የሆነውን በተለይም የአማራውን ህብረተሰብ ነጥሎ በማጥቃት፣መሬቱን በመንጠቅና በማፈናቀል የክተት አዋጅ ከታወጀ ዓመታት አልፈዋል።ሕዝቡ በመቻቻልና በትዕግስት ማለፉ እንደፍርሃት ተቆጥሮ የጥቃቱ መጠን እዬጨመረ መጥቷል።

በዘመነ ወያኔ የሰፈነው የጎሰኞች ስርዓት ተዋንያን በመቀያዬር እዬተቀባበለ ጸረ አትዮጵያዊነቱን ይፋ በማድረግ የክተት አዋጅ ካወጀባቸው ክፍላተ ሃገር አንዱ ወሎ ክፍለሃገር ነው።የዚህን ክፍለሃገር አዋሳኝ ከባቢዎች በመዋጥ ይዞታቸውን ለማስፋት በሰሜን በኩል የትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር፣ በመሃልና በምስራቃዊ ደቡብ በኩል የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር (ኦነግ)ሃይላቸውን አሰማርተው ጥቃት በማድረስ ላይ ናቸው።

ለሚያደርሱት ጥቃት የሚሰጡት ምክንያትና መነሻ በክፍላተ ሃገር ውስጥ የሚገኙ ጥቂት የትግርኛና የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑትን የክፍላተሃገር ኑዋሪዎችን እንወክላለን፣ተገደው የተያዙ ዜጎቻችንና ቦታውም የእኛ ይዞታ የነበረ ነው በማለት ነው።በወሎና በሌላውም ክፍላተ ሃገር ውስጥ ግን የዚህና የዚያ ጎሳ መሬት ተብሎ ተሸንሽኖ የተቀመጠበት ታሪክ የለም።ሁሉም በአንድ አገር ዜግነት፣ በኢትዮጵያዊነት እውቅና ኖሮት የሚኖርባቸው ክፍላተሃገር ነበሩ፣ናቸውም።

የሌሎቹን ክፍላተሃገር የሕዝብ ስብጥርነት እውቅና ሰጥተን በተለይ ግን አሁን የይገባናል ጩኸትና የጥቃት እርምጃ የሚታይበት የወሎ ክፍለሃገር ስለሆነና እኛም በዚህ ክፍለሃገር ስም ተደራጅተን የምንንቀሳቀስ ስለሆነ የከፍለሃገሩን ታሪካዊ ይዘትና መልክ ለማሳዬት ብሎም ለማስከበር፣አስፈላጊም ከሆነ በታታኝና አፍራሽ ሃይሎች በመጡበት መንገድ ለመመለስ የምንገደድበት ወቅት ላይ መሆናችንን ለመግለጽ እንወዳለን።

ወሎ እንደተቀሩት የኢትዮጵያ ክፍላተ ሃገር ብዙ ጎሳዎች ተስማምተውና ተቀላቅለው የሚኖሩበት ለመሆኑ የታሪክን ገጽ ላገላበጠ ሰው እንግዳ ሊሆን አይችልም።እንኳንስ ኢትዮጵያዊ ቀርቶ የውጭ ወራሪዎች ሳይቀሩ የሚመሰክሩት ሃቅ ነው።

ገጣሚ ስለወሎ ከገጠመው መሃል እነዚህን ቦጭቀን እናቀርባለን።

ከቶ አይሰለችም ስሙ ቢደጋገም

ወሎ ያገር ዋልታ ወሎ ያገር ቅመም።

ያይማኖት ንትርክ፣ የዘር አምባጓሮ ወሎ መች ለመደ፣

ስሙ ምስክር ነው ፋጤ ገ/ማርያም፣ሰለሞን እንድሪስ ፣አሰገደች አሊ ሙሃመድ ከበደ

የሆነውን ሆኖ ፣

ያመነውን አምኖ

የሸጠውን ሸጦ ፣የገዛውን ገዝቶ

አቅሙ እንደፈቀደ አምርቶና ሰርቶ

ህዝብ የሚኖርበት ተግባብቶ ተስማምቶ

ዘር ሃይማኖት አይልም ወሎና መርካቶ።

ዘር ሳይመለከት ከሁሉም ተጋብቶ

የህብረብሔር ድር ቤተሰብ መሥርቶ

ወሎዬ ይኖራል ከሁሉም ተስማምቶ።

በኢትዮጵያዊነቱ፣ ሁሉንም አክብሮ፣ሁሉንም አፍቅሮ፣

ወሎዬ ይኖራል ከሁሉም ተባብሮ፣

የናት ኢትዮጵያን ድንበር አስከብሮ።

ክራር ቢደረደር፣ዋሽንት ቢነፋ ፣ ማሲንቆ ቢመታ፣

አንቺ ሆዬ ለእኔ ፣ አረ ባቲ ባቲ፣አምባሰል፣ ትዝታ፣

የቀኝቱ ጳጳስ የኪነቱ ጌታ ፣

ወሎ ባህሉ ነው እንግዳ መቀበል ቁም ነገር ጨዋታ።

የዘመዶቹ እምነት ክርስትናና እስላም፣

በፍቅር ኖረዋል ባንድነት በሰላም።

መስጊድና ደብር ባንድ ሰፈር ሲኖሩ፣

ፋሲካና አረፋ ባንድ ላይ ሲያከብሩ፣

የምነት አክራሪዎች ከወሎ ይማሩ።

በወሎ መሬት ላይ በሰላሙ ቦታ፣

ተቀባይ የለውም የምነትና የዘር አክራሪ በሽታ።

በወለጋ አሩሲ በከፋ ሲዳሞ፣

በሸዋ ፣በትግራይ፣በሓረር በባሌ፣

ወሎ ክፍለሃገር ይቅረብ በምሳሌ።

እራያና አዘቦ ቆቦና ሰቆጣ

ግንባሩን አያጥፍም የመጣው ቢመጣ፣

መሞቱን ይመርጣል በዘር ተሸንሽኖ ኢትዮጵያን ከሚያጣ።

በኢትዮጵያዊነቱ ዝምድናው ቢነሳ፣

ቅድም አያቱ ጎይቶም አጎቱ ዲሳሳ

የጋርዮሽ አገር የክርስቲያን የእስላም፣

ክፉ ነገር እንጂ፣ዘረኝነት እንጂ ወሎ ሰው አይጠላም።

የዚህን ግጥም ሙሉ ይዘት በወሎ የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ድረገጽ ላይ ያገኙታል

www.wollo.org

በቀድሞ ጊዜ በነበሩት ስርዓቶችና የአስተዳደር አወቃቀር ወሎ 12 አውራጃዎች ነበሩት።እነሱም ዋድላና ደላንታ፣አንባሰል፣የጁ፣ላስታ፣አውሳ ፣ራያና ቆቦ፣ደሴዙሪያ፣ወረይሉ፣ወረሂመኖ፣ቃሉ፣ባረናና ዋግ ነበሩ።ከእነዚህ አውራጃዎች አንዳንዶቹ ከግራኝ አህመድ ጥቃት ጋር ተያይዞ በመጣው የኦሮሞ ጎሳ ወረራና መስፋፋት የተነሳ የቀድሞ ስማቸው እየተለወጠ ቢጠሩም ማህበረሰብአዊ ግንኙነቱና የሕዝቡ ማንነት፣ቋንቋና ባሕሉ ሳይበረዝ፣ለደረሰበት ጉዳት ካሳ ሳይጠይቅ በይቅርታ ከመጤው ጋር ባህል እየተወራረሰ አዳብሮ የዘለቀ ሕዝብ ነው።ሌላው ቀርቶ ላኮመልዛ ወይም የአማራው ማህበረሰብ ይዞታ በመሆኑ ቤተአማራ የሚለው የክፍለሃገሩ ስም ተቀይሮ ወሎ ለመባል የበቃው ከዚሁ የኦሮሞ ጎሳ መስፋፋት በዃላ ነው።የወሎ ሕዝብ ግን የመጣውን ማሰተናገድና እንደ እራሱ ቆጥሮ መቀበል ከተፈጥሮ ያገኘው ሰብአዊ ባህሪው ስለሆነ በክፋት አላዬውም ነበር።ነባሩ ሕዝብ በወራሪው የኦሮሞ ጎሳ ግፊትና አስገዳጅነት ብሎም በመዋለድና አብሮ በመኖር የኦሮሞ ቋንቋ እንዲናገር መብቃቱ ነባሩን ሕዝብ የኦሮሞ ጎሳ ነው ብሎ ለማለት አያስደፍርም።የአውሮፓ ወራሪ ሃይሎች የሌላውን አገር ወረው ሕዝቡ ቋንቋቸውን እንዲናገር በማድረጋቸው የተወረረው ሕዝብ የወራሪውን ቋንቋ በመናገሩ የወራሪውን አገር ማንነት ያዘ ማለት አይደለም።ማንነት የማይቀየር በትውልድ ሃረግ የሚቀባበሉት፣በደምና በሥጋ የተሳሰረ፣ከከባቢው የተፈጥሮ ጸጋ ጋር የተቆራኘ፣በስነልቦና፣በታሪክና በባህል የታጀበ እንጂ በቋንቋ ብቻ የሚገለጽ አይደለም።የአንዱ ከባቢ ተወላጅ ወይም ጎሳ ከሌላው ጋር በጉርብትናና ወይም ኑሮ ባስገደደው የመዘዋወር ሂደት አንዱ ለሌላው እያቀበለ በመቀላቀል ዘመን የተሻገረየቋንቋና የባህል ውህደት ይፈጥራል። ይህንን ለዘመናት የዘለቀ የሕዝብ መስተጋብር በመካድ ነባሩን የቤተአማራን ሕዝብ ጭራሽ እንዳልነበረና ባይተዋር አድርጎ መጤውንየኦሮሞ ጎሳ ነባርና ባለቤት ለማድረግ በኦነግና ተባባሪዎቹ የሚከናወነው ድርጊትና የታሪክ ግድፈት በምንም መልኩ ተቀባይነት የለውም።ከታሪክም ሆነ ከሕግና ከሰብአዊ አመለካከት ጋር የሚጋጭ ብቻ ሳይሆን እርኩስ ተግባር ነው።

በ1991 እ.አ.አ. ወያኔ መራሹ የኢህአዴግ ጎሰኛ ስርዓት ሲሰፍን የኢትዮጵያን ሕዝብ በጎሳ ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያመቸው አዲስ አወቃቀር ዘረጋ።በዚህ ሳቢያ እያንዳንዱ ጎሳ የራሴነው የሚለው ክልል እንዲኖረውና በመሬት ድርሻ እርስ በርሱ እንዲጋጭ፣ብሔራዊ አንድነቱ እንዲፈራርስ እቅድና ሕግ ወጥቶ ተግባራዊ ሆነ።በዚህም መሰረት በወሎና በሸዋ ክፍላተ ሃገር ውስጥ ባቲ፣ሃርቡ፣ከሚሴ፣ሰንበቴ(አጣዬ) የሚኖሩ ኦሮሞ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ጥቂት ነዋሪዎች ከኖሩበት ክፍለሃገርና ሕዝብ ተቆርጠው የኦሮሞ ክልል ይዞታ እንዲሆኑ ተፈረደባቸው።የራያና አዘቦ ሕዝብና መሬት ለወያኔ አገዛዝ ተላልፎ ተሰጠ።እምቢ ያለው ሕዝብ በጠራራ ጸሃይ በጥይት ተደበደበ፣በጨለማ ቤት ታጎረ።ለዘመናት ተቃቅፎ የኖረው ሕዝብ የጎሰኝነት ጎራ ለይቶ እንዲጋጭ ከውጭና ከውስጥ ያሉ ጸረ ኢትዮጵያና ጸረ አንድነት ሃይሎች ስልጣንና ሃይልን ተገን አድርገው በንጹሃን ላይ የእልቂት ዘመቻ ፈጸሙ፣አሁንም በመፈጸም ላይ ናቸው።በሥልጣን ላይ የተቀመጠው ቡድንም አይቶ እንዳላዬ በመሆን አጋርነቱን አበሰረላቸው።ይባስ ብሎም ለመብታቸው የሚታገሉትን በሽብርተኛነት እየፈረጀ ማዋከቡን ሥራዬ ብሎ ተያያዘው።ጌታዋን የተማመነች ጥጃ ጅራቷን ከውጭ ታሳድራለች እንዲሉ በዚህ የመንግሥት ወገንተኝነት የጥፋት ሃይሎቹ ይበልጥ የልብ ልብ እዬተሰማቸው ሄደ።ለፍላጎታቸው መልክና ገደብ አጡለት።በከተማም ሆነ በገጠር ጭራሽ ስግብግብነት አሳበዳቸው።

በወሎ ክፍለሃገር በተለይም በነዚህ በተጠቀሱት ቦታዎች የሕዝቡን ስብጥርና ቁጥር ለማወቅ በ1994እ.አ.አ. በተደረገው ቆጠራ 60% ኦሮሞ ነህ ተብሎ የተመዘገበ ፣36% አማራ፣2.5መሆናቸው ታውቋል።

በነዚሁ አካባቢዎች 40% ኦሮሞኛ ተናጋሪ ሲሆን 60% አማርኛን በመደበኛ ቋንቋነት የሚናገር ሕዝብ ነው።ሌላው ወሎንና ቀሪዎቹን ክፍላተ ሃገር የማመናመኑና የማዳከሙ ስልት ደቡብና ሰሜን የሚለው የልዩነት መስመር መዘርጋቱ ነው።በዚህም አንድ የነበረው ወሎ ደቡብና ሰሜን ተብሎ እንዲራራቅና በልዩነት እንዲተያይ ብሎም ለወረራ ምቹ እንዲሆን ተደርጓል።በ1994 ቆጠራ በመላው የወሎ ክፍለሃገር 92,68% አማራ፣6,78% ኦሮሞ፣0,54% ሌላ ጎሳዎች የነበሩ ሲሆን 96,45% አማርኛ ተናጋሪ፣3,13% ኦሮሞኛ፣0,42% ሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎች እንዳሉ ጥናቱ ያመለክታል።

በ2007 ቆጠራ የደቡብ ወሎ የመሬት ስፋት 17,067.45km2(6589,78sq.mile) ሕዝብ ቁጥር 2,518,862 ሲሆን ይህም በ1994 ከተደረገው ቁጥር በ18% አድጓል። ከዚህ ውስጥ የወንዱ ቁጥር 1,270,164፣የሴቱ 1,270,164 ነበር።በ2012 በተደረገው ቆጠራ የሕዝቡ ቁጥር 2,758,199 እንደሆነ ተገልጿል።በደቡብ ወሎ 94.33% አማራ፣ 5.67%ሌሎች ጎሳዎች ሲኖሩ አማርኛ ቋንቋ በ98.65 % ሲነገር 1.35%የሚሆኑት ሌላ ቋንቋ የሚናገሩ ናቸው።

ሰሜን ወሎ የመሬት ስፋት 12,172,50 km2(4699,83 sq mile)፣የሕዝብ ብዛት በ2007 1,500,303 የነበረው በ2017 ቆጠራ 1,639,151 በመሆን በ19,04% ጨምሯል። ወንድ 752,895 ፣ሴት 747,408 መሆኑን የብሔራዊ ስታስቲክስ ቢሮ ጥናት ያሳያል።በሰሜን ወሎ 99,38% አማራ፣0,62% ሌሎች ጎሳዎች እንደሚኖሩና 99,28% አማርኛ ተናጋሪ፣0,72% ሌሎች ቋንቋዎች ተናጋሪ እንደሆነ ተመዝግቧል።

ታዲያ ይህንን በማስረጃ የቀረበና እራሱ ኢሕአዴግ ጥናት አካሂዶ ያመነበትን ዝርዝር ወዴት አስቀምጠው ነው አሁን ወሎን የኦሮሞና የትግሬ ጎሳ ይዞታ ነው ብሎ መሬቱን ለመቀራመት ጦር የሚሰብቁት?የአስራሰባተኛውን ክፍለዘመን የዘመነ መሳፍንትን ስርዓትና የኦሮሞን ወረራ ለመድገም የሚከጅሉትን ጽንፈኞች ለማለት የምንሻው ነገር ቢኖር አርፋችሁ ተቀመጡ፣ለታሪክና ለሃቅ ተገዙ ነው።በወሎዬነቱና በኢትዮጵያዊነት ማንነቱ አምኖ ተዋልዶ የኖረውን የተለያዩ ጎሳዎች ተወላጅ ለጥፋት አትቀስቅሱት ነው።ሕዝብን ለማጋደልና አገር ለመበታተን የምትሸርቡት ሴራና የፈጠራ ታሪክ ነጻ እናወጣሃለን በማለት በምትነግዱበት ሕዝብ ክንድና ትብብር ይከሽፋል ።ያ የጊዜ ጉዳይ ነው።የክፍለሃገሩ ባለቤት የሆነው በተለይም የአማራው ጎሳ ተደራጅቶ እንኳንስ የራሱን በተመሳሳይ መንገድ በኦሮሞ ነውጠኞች በመፈናቀል ላይ ላሉት ለሌሎች ጎሳ ተወላጅ ለሆኑት ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ መከታ ይሆናል።ለዚያም ፍራቻ ነው አሁን መረባረቡ የበዛበት።

በሚሰበከው የነውጠኞችና የቅጥረኞች ዲስኩር ተታለው በወገኖቻቸው ላይ ጥቃት ለማድረስ የተሰለፉትን የኦሮሞ ጎሳ ተወላጆች ወገኖቻችን ለማሳሰብ የምንወደው ከባዕዳን ወራሪዎች ቅጥረኞች ጎራ ወጥታችሁ ወደ ኢትዮጵያዊነት ጎራ ተመለሱ ።ለኢትዮጵያዊ ማንነታችሁ ቁሙ ።ሌላው ቢቀር ወደ ሰውነታችሁ ተመልሳችሁ እንደሰው አስቡ። ምክራችንን የማትቀበሉ ከሆነ ለሚደርስባችሁ ጉዳትና የታሪክ ተጠያቂነት ምክንያቱ እራሳችሁ እንደምትሆኑ ልትገነዘቡት ይገባል።

የወሎ ክፍለሃገር ተወላጆች የሆናችሁም ሁኔታውን በቸልታ ከማዬት ይልቅ በመሰባሰብ በወሎና በኢትዮጵያ ላይ በተለይም በአማራው ማህበረሰብ ላይ የተነሳውን የጥፋት ሃይል ለመከላከል በምትችሉት ሁሉ የድርሻችሁን እንድታበረክቱ የወሎ ውርስና ቅርስ ማህበር ጥሪ ያደርጋል።በወሎ ስም የሚንቀሳቀሱትንም የጥፋት ሃይል ተላላኪዎችን ቦታና ዕድል እንዳይኖራቸው የማድረጉ ተግባር ከሁሉም ወሎዬ ይጠበቃል።በጎሳ፣በቋንቋና በሃይማኖት ሰበብ ገብተው ሊያበጣብጡን በሚሞክሩት ላይ የተባበረ ክንዳችንን እናንሳባቸው!

የሌላው ክፍላተ ሃገር ተወላጅ የሆነው ኢትዮጵያዊ ዛሬ በወሎና በሌሎቹ ላይ በተለይም የአማራ ክልል ተብሎ በሚጠራው ክፍላተ ሃገር የተከፈተውን የጥቃትና የመሬት ነጠቃ በጋራ ተሰልፋችሁ እንድትከላከሉና የነበራችሁን አንድነትና አብሮነት እንድታስከብሩ ጥሪ እናደርጋለን።ዛሬ በወሎና በቤጌምድር ላይ የተሰነዘረው ጥቃትና የይገባኛል ጥያቄ ነገ በየተራ በሁሉም ላይ የሚሰነዘር መሆኑን አትርሱ። ቀደም ሲልም ኦነግ መራሹ ጽንፈኛ በህወሃት እየታገዘ በኦጋዴን ተወላጅ በሆነው የሶማሌ ጎሳ፣በደቡብ ደግሞ በኮንሶና በጌዶ ሕዝብ ላይ የደረሰው የሕዝብ ግድያ፣ማፈናቀልና የመሬት ዘረፋ እንደትምህርት ሊወሰድ የሚገባው የመከራ ጽዋ ነው።በቸልታ ከታለፈ ነገ ባለተራው የጋምቤላው፣የትግራይ፣የጎጃም፣የአፋርና የጎንደር ክፍላተ ሃገር ይሆናሉ።አሁን ለአገር አንድነት ግንባር ቀደም በሆነው የአማራ ማህበረሰብ ላይ የተከፈተውን የማጥቃት ዘመቻ በመከላከል አብሮነታችሁን ግለጹ!በሌሎች አገሮች የደረሰው የመበታተን አደጋ እንዳይደርስ በአስቸኳይ ግንባር ፈጥራችሁ ለጋራ አገራችሁ ህልውና ተሰለፉ! የአሁኑ ኦነግ መራሹ የኦሮሞ ጎሳ መስፋፋት በዚህ ብቻ አያቆምም፤እንደመሪዎቹ ቅዠት ከሆነ የምሥራቅና ደቡብ ምዕራብ ያፍሪካ አገሮችም ሳይቀሩ የቄሮ ቆንጨራ ደም የሚያፈስባቸው ቀጠናዎች ይሆናሉ።

በአማራ ሕዝብ ስም የክልሉ ባለሥልጣናት የሆናችሁ የኢሕአዴግ ሹመኞች በወሎና በጎንደር እንዲሁም በጎጃምና በሸዋ ውስጥ በኦነግና በተባባሪዎቹ የሚደረገውን ወረራና ዘመቻ የማትከላከሉና የማታወግዙ ከሆነ የአማራው ሳይሆን የአማራው ጠላት የሆነው የወያኔና የኦነግ እንደራሴዎች መሆናችሁን አትዘንጉ!እርግጥ ነው የኢሕአዴግ አካል በመሆናችሁ ኢሕአዴግ ሲወገድ አብራችሁ እንደምትወገዱ ሊያሳስባችሁ ይችላል።ቁም ነገሩ ግን በእናንተ ላይ የሚደርሰው ሳይሆን ለተተኪው ትውልድና ለልጆቻችሁ የማያሳፍር ታሪክ ጥሎ ማለፉ ነው።ከአሁኑ ሰልፋችሁን ካስተካከላችሁና ሕዝቡን ይቅርታ ጠይቃችሁ ወገንተኝነታችሁን በተግባር ካሳያችሁ የአማራ ሕዝብ ይቅር ባይ ነው።ሌላው ቢቀር ግፍ እንዳይፈጸምባችሁና በሕግ አግባብ እንድትያዙ ያደርጋል። በአማራው ስም የተቀመጣችሁበትን ወንበርና የተሰጣችሁን ሥልጣን አማራውን መጥቀሚያ እንጂ መጠቀሚያ አታድርጉት።በተሾማችሁበት ክልል ውስጥ ሕዝብ የበደሉትን፣ወንጀል የፈጸሙትን ቡድኖችና ግለሰቦች ለፍርድ ለማቅረብ እንጂ የሥልጣናችሁ መደራደሪያ አታድርጉ።

ሁሉም ሕዝብ የሚፈናቀልበት፣ኢትዮጵያ ፈራርሳ ሁሉም አገር አልባ የሚሆንበት የኢሕአዴግ የጎሳ ፖለቲካና የሚመራበት እራሱ ያረቀቀው “ሕገመንግሥት” ተብዬው የግጭት ሰነድ ተወግዶ የሥርዓት ለውጥ እስኪመጣ፣፣በሕዝብ ለሕዝብ የሕዝብ የሆነ በኢትዮጵያዊነት ካስማ ላይ የቆመ አገር ወዳድ መንግሥት እስኪመሰረት ድረስ ትግላችን መቀጠል አለበት።አሁን ሥልጣን ላይ የተቀመጠው ቡድን ያው የቀድሞው ኢሕአዴግ አባላትና ከጎሳ የተውጣጣ መሆኑን አትርሱ። የጎሳ መተካካትና የግለሰቦች መቀያዬር መፍትሔ እንደማይሆን በገሃድ እዬታዬ ነው።በባዶ ቃላት መጭበርበር ይብቃ!በጆሯችን ሳይሆን በአይምሯችን እንመራ!

ቤተአማራን(ወሎን) ከወረራ ማዳን ኢትዮጵያን ማዳን ነው!

ኢትዮጵያ በሕዝቧ የተባበረ ትግል በነጻነትና በአንድነት ለዘላለም ትኖራለች!

ወሎ የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማህበር