August 20, 2019

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 14፣ 201 1(ኤፍ ቢ ሲ) ዩኒሴፍ ከአማራ ክልል ህዝቦች ጋር የሚሠራቸውን ልዩ ልዩ ትብብሮች አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስታውቋል።
በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ አዲል ሆደር እና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በቀጣይ የትብብር መስኮች ዙሪያ በትናንትናው ዕለት በባሕር ዳር ተወያይተዋል።
ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ ለ 67 ዓመታት ሕፃናት ላይ ትኩረት አድርጎ ሠርቷል ያሉት፥ አዲል ሆደር በአማራ ክልል በአማካይ ዕድሜ 16 ዓመት የሆነውን ያለዕድሜ ጋብቻ ለማስቀረት አሁንም በትኩረት ለመሥራት ከርዕሰ መስተዳደሩ ጋር መምከራቸውን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በጤና ተቋማት የሚወለዱ ሁሉም ሕፃናት የልደት ካርድ እንዲኖራቸው፣ የንፁሕ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እንዲሻሻል ለማድረግ እና በትምህርት ተቋማት ድጋፍ የሠሯቸው ተግባራት ውጤታማ እንደነበሩ አስታውቀዋል።
በቀጣይ በክልሉ በሕፃናት እንክብካቤ፣ በትምህርት ቁሳቁስ እና ግንባታ ድጋፍ፣ በአመጋገብ፣ በንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ያለዕድሜ ጋብቻን በማስቀረት እና በበጎ አድራጎት ሥራዎች ለመሳተፍ መምከራቸውንም ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው በትምህርት ቅበላ ችግር ያለባቸው አከባቢዎች ላይ ትኩረት ለማድረግ፣ በንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እና በጤና ዘርፍ በትብብር ለመሥራት ከተወካይዋ ጋር መግባባታቸውን ተናግረዋል።
የሕዝቡ ጥያቄ ሆነው የክልሉ በጀት መሸፈን ባልቻላቸው የልማት ሥራዎች ላይ ዩኒሴፍ ትኩረት አድርጎ እንዲሠራ መምከራቸውንም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የገለፁት።
ከዚባለፈም የአቅም ግንባታ ሥራዎች ላይ እንዲሳተፉ እና በዩኒሴፍ የተጀመሩ ግንባታዎችን በወቅታቸው እንዲያጠናቅቁ መምክራቸውን አብመድ ዘግቧል።