ፕሮፌሰር ዐሥራት ወ/ኢየሱስ ይመሩት ከነበረውና በወያኔ/ኢሕአዴግ የውንብድና ጥቃትና አማራው የመአሕድ ጥሪ የማንቂያ ደወል ሳይገባው በመቅረቱ ፈጣን አወንታዊ ምላሽ ስላልሰጠው ከከሰመው የመአሕድ እንቅስቃሴ በኋላ አማራ ተነግሮ የማያልቅ ግፍ፣ መከራ፣ ስቃይ፣ ሰቆቃ፣ እልቂት፣ የዘር ፍጅት ለዓመታት ካስተናገደ በኋላ ለመቀስቀስ እጅግ አድካሚና ተስፋ አስቆራጭ በሆነ ጥረት ነው በግድ ተቀስቅሶ በጋለ የአማራ ብሔርተኝነት ስሜት ለህልውናው፣ ለነጻነቱ፣ ለመብቱና ለጥቅሙ እንዲታገል እንዲቆም ሌላው ቢቀር አቋም እንዲይዝና እንዲነቃ ማድረግ የተቻለው፡፡
በአሁኑ ጊዜ በአማራ ሕዝብ ዘንድ ሌላው ቢቀር አማራ የህልውና አደጋ እንዳለበትና ከዚህ የህልውና አደጋ ለመውጣት አንዳች ነገር መደረግ እንዳለበት የማይገነዘብ አማራ የለም ማለት ይቻላል፡፡
አሳዛኙ ነገር ግን አማራ እስከአሁንም ድረስ ካለበት ፈተና ታግለው በማታለል ሊታደጉት የሚችሉ ብሔርተኞች፣ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የምሁራን የመማክርት ስብስቦች ሊያገኝ አለመቻሉ ነው፡፡
በተለይም በአሁኑ ሰዓት “ለአማራ ህልውና፣ ነጻነት፣ መብት፣ ጥቅም ቆመናል!” እያሉ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ ብሔርተኞች፣ አክቲቪስቶች በሙሉ ሊባል በሚያስችል ደረጃ ከታች የተዘረዘሩት አሳሳቢና አንገብጋቢ ችግሮች ያሉባቸው ናቸው፡፡
1ኛ. የአማራ ፈተና፣ ችግር፣ አደጋ ምን እንደሆነ በትክክል ጠንቅቀው አያውቁትም!!!
2ኛ. የአማራ ጠላቶች እነማን እንደሆኑና በምን ምክንያት ጠላት እንደሆኑት፣ አሁንም ጠንቅቀው አያውቁም!!!
3ኛ. የጠላቶቹ ፍላጎትና ዓላማ ምን እንደሆነ ይሄንንም ጠንቅቀው አያውቁም!!!
4ኛ. የጠላትነታቸው መጠን ምን ያህል እንደሆነና እንዴት ሊወገዱ እንደሚችሉ በትክክል የሚያውቁት ነገር የለም!!!
5ኛ. የአማራ ጠላቶችን ፍላጎትና የጥፋት ዓላማ እንዴት መከላከል፣ ማክሸፍና አማራን መታደግ እንደሚቻልና እንደሚገባም የሚያውቁት፣ የነደፉትና ለሕዝብ ያደረሱት ስትራቴጂ (ስልት) የለም!!!
6ኛ. የአማራ ሕዝብ ፍላጎት፣ ጥቅምና ምኞት ምን እንደሆነ አጥርተው አያውቁም፡፡ አንዳንዶቹማ ጭራሽ የራሳቸውን ጭንጋፍ አስተሳሰብ የአማራ ሕዝብ እንደሆነ አድርገው ሳያፍሩ በድፍረት እስከመናገር የሚደርሱም አሉ!!!
7ኛ. የአማራ ጠላቶች የጥፋት ዓላማቸውን በአማራ ላይ ለመፈጸም የሚጠቀሙትን ስልት (ስትራቴጂ) እና አፈጻጸም ጨርሶ አያውቁትም፡፡ ስለማያውቁትም አስቀድመው ለመከላከል የሚያደርጉት ጥንቃቄና ጥረት የለም!!!
8ኛ. አንካሶች ናቸው!!! አንካሳ ስለሆኑም መሰናክል ሲያጋጥማቸው ከመሰናክሉ ስር ሲልሞሰሞሱ ሲንከላወሱ ይገኛሉ እንጅ መሰናክሉን ዘለው ማለፍ አይችሉም!!!
9ኛ. የሚከተሉት የትግል ስልታቸውና ትልማቸው የተገደበና የአማራን ትግል ለድል ወይም ለስኬት የማያበቃ፣ ነባራዊውን ሐቅ ያላገናዘበ ነው!!!
10ኛ. እንደአስፈላጊነቱ በግንባር ቀደምትነት ዋጋ ከፍሎ መሥዋዕት ሆኖ ትግልን ለስኬት የማብቃት ፍላጎትና ቁርጠኝነቱ ጨርሶ የላቸውም!!! አስቂኝ በሆነ ሁኔታ ፍላጎታቸውና ሕልማቸው ዋጋ ሳይከፍሉና መሥዋዕት ሳይሆኑ ለድል መብቃት ነው፡፡ a great victory comes a great sacrifice! የሚለውን የማይለወጥ ነባራዊ ሐቅ ያልተረዱና ጨርሶ የማያውቁ ናቸው!!!
11ኛ. በጥቅም የሚደለሉ፣ ለግል ጥቅም ሯጮችና እራሳቸውን አምላኪዎች ናቸው!!! በዚህም ምክንያት ብዙዎቹ እራሳቸውን ሸጠው ለብአዴን አድረዋል፡፡ ይሄ ጉድ በተለይ ደግሞ አገዛዙ ባሕርዳር ላይ ከፈጸመው የግፍ ግድያ በኋላ በሚገባ ግልጽ ሆኖ ታይቷል!!!
12ኛ. የጠራ አቋም የላቸውም!!! ብዙ ሳይሆን አምስት ደቂቃ ያህል ብቻ በአማራ ትግል ዙሪያ ሲያወሩ ብትሰሟቸው በሚያወሩት ወሬያቸው ውስጥ እርስ በርሱ የሚጣላና የሚጋጭ ሐሳብ ታጭቆ ታገኛላቹህ፡፡ የብአዴንን ፀረ አማራነት ይነግሯቹህና እዚያው ላይ ደግሞ “ብአዴንን ከመደገፍ ውጭ አማራጭ የለንም!” ብለው አንካሳነታቸውንና ጥገኛነታቸውን ያሳዩዋቹሃል ወይም ደግሞ ይሄንን ማለት ከፈሩም “አንድ አማራ!” እያሉ በሚለፍፉት ስውር ዓላማቸውን የማስፈጸሚያ ሽፋን በአማራ ትግል ውስጥ ብአዴንንም አጋር ማድረግ የሚገባ መሆኑን በመናገር ለብአዴን ሲወይሉ ወይም ሲደልሉ ታገኟቸዋላቹህ፡፡ በመሆኑም ቅጥረኞች፣ ጥገኝነት የተጠናወታቸውና አንካሶች ናቸው፡፡ እራሳቸውን ችለው በመታገል ለድል መብቃት ይቻላል ብለው አያምኑም፡፡ ስለማያምኑም የድሉ መንገድ አይታያቸውም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ የሚመስለኝ የብአዴን ምንደኞች በመሆናቸው አንዱ ሲሆን ሌላው ደግሞ መሥዋዕት እስከመሆን ድረስ ለመታገል ባለመፈለጋቸው ወይም ባለመቁረጣቸው ነው!!!
13ኛ. አማራ ያለበትን እጅግ አሳዛኝና አስደንጋጭ ተጨባጭ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እውነታ አምነው ተቀብለው ይሄንን ተጨባጭ እውነታ ባገናዘበ፣ በሚመጥንና ሊቀርፍ በሚያስችል መልኩ የመፍትሔ እርምጃና አቅጣጫ አይተልሙም፡፡ ከዚህ ይልቅ የአማራን የቀደመ ገናና ታሪክ በመተረክና “እንዲህ ነህ!” እያሉ በመንገር እንዲዘናጋ፣ ያለበትን እጅግ አሳዛኝና አስደንጋጭ ውርደት የተሞላ ማኅበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ተመልክቶና አውቆ እንዳይነቃ ነቅቶም ወደ ገናና ክብሩና ማንነቱ ለመመለ፣ ከአሳዛኝና አስደንጋጭ ውድቀቱና ውርደቱ ለመውጣት እንዳይተጋ ያደርጉታል፡፡ አማራ ያለበትን ፈተና፣ የገባበትን ማጥ፣ የተጋረበትን ሥጋት በሩቁ ይሸሹታል እንጅ አይቀርቡትም፡፡ የሚሸሹበትም ምክንያት መፍትሔው የሚፈልገውን ጠንካራ አቋም፣ ጽናት፣ ቁርጠኝነት፣ የትግል ስልትና ዓይነት መከተልና መፈጸም ስለማይፈልጉ ወይም አቅሙ፣ ጽናቱ፣ ቁርጠኝነቱ፣ ድፍረቱ፣ ወኔው ስለሌላቸውና አልጫ፣ ስልብ፣ ድውይ ስለሆኑ ነው!!!
እናም በመድረኩ ላይ ሲወራጩ ሲራወጡ የምታዩዋቸው “የአማራ ፓርቲ ነኝ፣ የአማራ ፖለቲከኛ ነኝ፣ የአማራ ምሁር ነኝ፣ የአማራ ብሔርተኛ ነኝ፣ የአማራ አክቲቪስት ነኝ፣ የአማራ ምንንትስ ነኝ!” የሚለው ሁሉ በዚህ ሁሉ ችግር የተተበተበ ድውይ፣ ዘገምተኛና ድኩም ስለሆኑ እንደምታዩዋቸው በአማራ ላይ ተጨማሪ ችግር ሆነውበት ቁጭ አሉ እንጅ ፈጽሞ ለአማራ ችግር መፍትሔ የሚያመጡና አማራን የሚታደጉ ሊሆኑ አልቻሉም!!!
ይሄንን ሳስብ “የአማራ መዳን ከወዴት፣ መቸና በማንስ ይመጣል ታዲያ???” የሚለው ጥያቄ ዘወትር በእጅጉ ያስጨንቀኛል!!!
የሚያሳዝናቹህ ነገር ሌላ ምን አለ መሰላቹህ ደግሞ በብአዴንና በጌቶቹ ወያኔና ኦነጋውያን በትጋት በሚሠራ የመከለል፣ የመሸፈን፣ ትኩረት የማሳጣት፣ መንገድ የመዝጋት የተቀናጀ ሥራ እነኝህ ከላይ የገለጽኳቸው ችግሮች የሌሉባቸው እኔን ጨምሮ ሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ያሉ ጥቂት ቁርጠኛ የአማራ ብሔርተኞች ምንም እንኳ በአማራ ሕዝብ ልብ ያለን ብንሆንም መድረኩ ሙሉ ለሙሉ በአንካሶች በጥገኞችና በቅጥረኞች ወይም በምንደኞች ስለተያዘና የአገዛዙ ፖለቲካዊ ምኅዳርም ለእነኝህ ጥቂት ቁርጠኛ የአማራ ብሔርተኞች የማይፈቀድ ወይም ዕድል የሌለ በመሆኑ ከሕዝቡ ጋር በቀጥታ መገናኘት መድረስ እንዳንችል መደረጉ ነው!!!
ለውጥ የተባለውን የአገዛዙን ድራማ እውነት ለማስመሰል በተፈጠረ ክፍተት ዕድሉን አግኝቶ የነበረውን ጀግናውን አሳምነው ጽጌንና ጓዶቹንም “ሳይቀድመን እንቅደመው!” በሚል ድራማ አዘጋጅተው በፈጠራ ክስ በመወንጀል እንዴት እንደመቷቸው የምታውቁት ነው፡፡
ችግሩ ጥጃዋ አለመለቀቋ ነው እንጅ ጥጃዋ ብትለቀቅ ወይም ነጻ ምኅዳር ቢኖር ኖሮ ጥጃዋ ሳታመነታ እናቷን ከብዙ ጥገቶች መሀል ፈልፍላ የምታወጣና የምትወስድ መሆኗ እሙን በመሆኑ አገዛዙ የአገዛዝ ዘመኑን ለማራዘም ጥጃዋና ጥገቷ (የአማራ ሕዝብና እውነተኛ ልጆቹ) እንዳይገናኙ ማድረግን ሁነኛ መላው አድርጎ መያዙ ነው፡፡
በመሆኑም የሚከፈለው ዋጋ ሁሉ ይከፈላል እንጅ ግፋ ቢል ምስለኔ እየቀያየረ አማራን “ይሄው ድርጅትህ!” እያለ የተለያየ ለእሱ ታማኝ የሆኑ ምንደኛ የአማራ ድርጅቶችን እየፈጠረ ይሰጠዋል እንጅ ወያኔ/ኢሕአዴግ በቁም እያለ የፈለገ ተአምር ቢፈጠር አማራ ከእጁ ወይም ከቁጥጥሩ እንዲወጣና ከቆራጥ ልጆቹ ጋር እንዲገናኝ ወይም በእነሱ እንዲመራ ፈጽሞ አይፈቅድም!!!
እርግጥ ነው ጀግና ማለት መንገድ በሌለበት መንገድ ፈጥሮ የሚታደግ ማለት ነውና እነኝህ ጥቂት የአማራ ቁርጠኛ ብሔርተኞች የፖለቲካ ምኅዳሩ የማይፈቅድ፣ ዕድሉም የሌለ ቢሆንም ይሄንን ፈተና በማለፍ ወይም በችግሩ ሳንበገሩ አንዳች እመርታ ማስመዝገብ ይጠበቅብን ይሆናል፡፡ ይሁንና በጣም ጥቂት ከመሆናችን አኳያ የችግሩ መወሳሰብ፣ ግዝፈትና ክብደት አቅም ስላሳጣን ብዙ ጥረት ብናደርግም በፈጠነ ሰዓት እመርታውን ማስመዝገብ እንዳንችል አድርጎናል!!!
እናም አማራና ፈተናው ወይም አማራና ትግሉ እንዲህ የተወሳሰቡ ናቸው፡፡ አማራ ሆይ! “የወላድ መሐን ሆነሃልና ሁሉንም ነገር ትተህ ፈጣሪህን ብቻ ለምን ተማጸን!” ብየ እንዳልመክር ሰው ከራሱ የሚጠበቅበትን የቤት ሥራ ሳይሠራ፣ ሳይፈጽም፣ ሳይለፋ፣ ሳይጥር፣ ሳይደክም እግዚአብሔር ማንንም እረድቶ፣ ታድጎና አድኖ እንደማያውቅ ቅዱሳት መጻሕፍቱ ይናገራሉና አንተን ከንቱ ቅዠት ውስጥ መክተት ነው የሚሆነው፡፡ ቃሉም የሚለው “የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፥ እኛም ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን!” ነህ. 2:20 ነውና፡፡ ተኝተን ወይም እጅ እግራችንን አጣምረን ወደ ሰማይ በማንጋጠጥ አላለም!!!
“ፈረስ ለጦርነት ቀን ይዘጋጃል፤ ድል ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው!” ምሳሌ 21:31 ይላል፡፡ ድል ከእግዚአብሔር ቢሆንም ድል ለማግኘት የጦር ሰልፍ ግን የግድ መሆኑን ልብ በሉ፡፡ ለጦር ያልተሰለፈ ድል ሊያገኝ አይችልምና!!! ስታስቡት ጦርነት ያልወጣ እንዴት ጦርነት ሊያሸንፍ ይችላል???
“ሊሠራ የማይወድ አይብላ!” 2ኛ ተሰሎንቄ 3:10
“የሚደክመው ገበሬ ፍሬውን ከሚበሉት መጀመሪያ እንዲሆን ይገባዋል!” 2ኛ ጢሞቴዎስ 2:6
“ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ!” ዘፍ. 3:19
ከእነዚህ የእግዚአብሔር ቃሎች የምንረዳው ቁምነገር ቢኖር እግዚአብሔር የሚያደርገው ነገር ቢኖርም ያን የሚያደርገውን ነገር እንዲያደርግ ግን ሰው የድርሻውን መወጣቱ ግዴታው መሆኑን ነው፡፡ አዳሜ የእግዚአብሔር ቃል ባልተናገረው በራስህ የስንፍና አስተሳሰብ እየተመራህ እጅና እግርህን አጣምረህ ወደ ሰማይ ብታንጋጥ ተጨፍጭፈህ ለማለቅ ካልሆነ በስተቀር አንጋጠህ ትቀራለህ እንጅ ማንጋጠጥህ ምንም የሚያተርፍልህ ነገር የለም!!! ወያኔ እኮ የመንግሥት ሥልጣንን ለመጨበጥ የበቃው ታግሎ ነው፡፡ እግዚአብሔር ወርዶ ደርግን አባሮ እነሱን ኑ ብሎ ጠርቶ ሥልጣን የሰጣቸው ይመስላቹሃል???
ከዚህ የተለየ እውነት የለምና ወገን ሆይ! የድርሻህን ከአንተ የሚጠበቀውን በሚገባ ሳትወጣ እግዚአብሔር እግዚአብሔር ብትል ወይም ወደሰማይ ብታፈጥ ጠብ የሚልልህ ነገር እንደሌለ ተረድተህ ጊዜ ሳታባክንና በጅልነት አስተሳሰብህ እንደተያዝክ ሳታልቅ በፊት ንቃና ቆርጠህ ታገል!!!
ድል ለአማራ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com