21 ኦገስት 2019
የሃገሪቱ ፖለቲካዊ ሁነቶች በአልባሳት አሰያየም ላይ

ከሰሞኑ ምናልባት ትግራይ ሄደው በአንደኛው ልብስ መሸጫ መደብር ውስጥ ‘ደብረጽዮን’ አለ? ሲባል ሲሰሙ ምናልባት የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት እዚህ ሱቅ ውስጥ እንዴት ይኖራሉ? የሚል ስሜት ሊፈጥርብዎት ይችላል።
ነገር ግን የሃገር ባህል ልብስ መሆኑን ሲሰሙ ይገረሙ ይሆን? እንዴት ነው ስያሜውን ያገኘውስ የሚል ጥያቄን ይጭርብዎት ይሆናል።
በየአመቱ ከነሐሴ 14 ጀምሮ ለሶስት ቀናት በአማራ ክልል በሰቆጣና በላሊበላ ሻደይ፣ አሸንድየ፤ በትግራይ ክልል አሸንዳ ክብረ በዓል ሴቶችን ማዕከል በማድረግ ይከበራል።
በዚህም ክብረ በዓልም ዋነኛው ትኩረት አልባሳት ሲሆን በየአመቱም አዳዲስ የልብስ ዲዛይኖችም የሚታዩበት ነው።
በዚህ አመትም በትግራይ ክልልና በኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ህብረ ቀለም ያሸበረቁ ልብሶች ቀርበዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የሃገሪቱ ወቅታዊና የፖለቲካ ግለቶች የተንፀባረቁባቸው የአልባሳት ስያሜዎችም ተሰጥተዋቸዋል።
በመቐለ ከተማ የሃገር አልባሳትን በመስፋት ሽርጉድ ሲል ቢቢሲ ያገኘው የማነ ለቢቢሲ እንደገለፀው በዚህ አመት ዋነኛ ተፈላጊው ልብስ ደብረፅዮን የሚል ስም ተሰጥቶታል።
ደብረፅዮን የሚባለው ልብስ የትግራይ ክልል ሰንደቅ አላማ በዋነኝነት ይዟል።
“ዘንድሮ በጣም ተፈላጊ የሆነው ይሄው ‘ደብረጽዮን’ የሚባለውነው። ብዙዎቹም እየሸመቱት ነው። የትኛው ነው ደብረጽዮን እያሉ ይጠይቁንና ይወስዱታል” ብሏል።
ትግራይ በዚህ አመት ህይወታቸውን ያጡ ጄኔራሎችን በአልባሳት ስምም እየዘከረቻቸው ነው።
ከዚህ በተጨማሪ በቀድሞው የመረጃና ደህንነት ኃላፊ ጌታቸው አሰፋ፣ በዚህ አመት ህይወታቸውን ባጡት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የተሰየመው ሰዓረ መኮንን እንዲሁም ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራ እና ጌታቸው ረዳ በመሳሰሉት የተሰየሙ አልባሳትም ለገበያ ቀርበዋል።
በባለፉት ስምንት አመታት የአሸንዳን በዓል ያከበረችው መርሂት ገብረ አሸንዳ “የነጻነት ቀኔ ናት” ትላለች
ለአሸንዳ ለየት ያለ ፍቅር ያላት መርሂት በተለይ ደግሞ አሸንዳ ስትመጣ በየዓመቱ አዳዲስ አልባሳትና ዲዛኖች ይዛም ስለምትመጣ፤ እንዲሁም ከጓደኞቿ ጋር በደስታ ፈንጥዘው የሚያሳልፉባቸው ቀናት በመሆኑ እንድትናፍቃት አድርጓታል።
በየአመቱም ከጓደኞቿ ጋር ዋነኛ መወያያቸው በዓሏ ምን አይነት አዲስ ዲዛይን ይዛ ትመጣ ይሆን የሚለው ነው።
በዓሏ በቡድን በቡድን ተለይተው የምትከበር በመሆኑ ደግሞ፤ የእያንንዱ የቡድኑ አባላት አንድ ዓይነት ምርጫ ላይ ለመድረስ ሁሌም እንደሚቸገሩ መብርሂት ትናገራለች።
ምንም እንኳን በመጨረሻ አንድ ዓይነት ቀለም እና አሰራር ምርጫ ላይ መድረሳቸው እንደማይቀር መብርሂት ትናገራለች። አሁን አሁን ይሄው ምርጫቸውን የሚያወሳስበው ደግሞ ሌላ ጉዳይ ታነሳለች።

“በተለይ በቅርቡ ዓመታት የምንመርጠው ጨርቅና አሰራር ዘዴ ብቻ ሳይሆን ለአልባሳቱ የሚሰጠው ስያሜም ፤ ‘ይሔ ይሻለናል’ ‘ይሄ ይሻላል’ ስንባባል ክርክሩ እንደሚቀጥል” ትናገራለች።
የአሸንዳ ልብስ ስያሜውን ከማን ነው የሚያገኘው?
በመቐለ ከተማ ዓዲ ሓቂ ለረዥም ዓመታት በልብስ ስፌት ስራ የተሰማራው ጀማል ወሃቢ ረቢ የአሸንዳ በዓል ከፍተኛ ገበያ የሚያገኝበት ጊዜ ነው።
በልጃገረዶቹ ምርጫ የተለያዩ ልብሶች ሰርቶ የሚያቀርብ ሲሆን የአልባሳቱ ስያሜዎች ብዙዎቹ ከአምጪዎች እንደሚያገኝ ይገልፃል።
• ሜድ ኢን ቻይና- የሀገር ባህል አልባሳቶቻችን
አንደኛው ደረጃ ልብስም በሜትር 170 ብር እየተሸጠ እንደሆነ ሪፖርተሮቻችን ታዝበዋል።

ቀደም ሲል የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ የመጡበት ወቅት ስለ ነበር ‘ኦባማ’ የሚባል ልብስ አንደኛ ሆኖ ሲሸጥ ነበር።
ከእሱ በኋላም በቃና የቴሌቪዥን ጣብያ ‘ቃና’ የሚል ልብስ ተወዳጅ ሆኖ ገበያውን ተቆጣጥሮት እንደነበርም ቢቢሲ ያናገራቸው ግለሰቦች ተናግረዋል።
ልጃገረዶቹ ብቻ ሳይሆን በሚዲያዎችም ባህላዊ ልብሳቸውን አሸንዳን እንዲያከብሯት በሚድያ ቅስቀሳ ሲደርግ ተስተውሏል።
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ምክትል ሐላፊ ወ/ሮ ዘነቡ ሓለፎም ገበያው በየዓመቱ ‘ዘንድሮ ምን ተባለ’ በሚል ወቅታዊ ሁኔታዎች ከፍተኛ ተፅእኖ ውስጥ እንደሚወድቅ ተናግረዋል።
“አሸንዳ ባህላዊ ትውፊት አላት። በየዓመቱ የምትቀያየር ባህል መሆን የለባትም። በተለመደውና የቀደመው አለባበስ ዘይቤን ጠብቃ ነው መከበር ያለበት”ይላሉ።
“አሸንዳ ፋሽን አይደለችም። በየዓመቱ ልብሱ መቀያየር አለበት ብለን አናምንም። የልብሱ አሰራርና ዲዛይን በየግዜው ሊለያይ ይችላል። መከበር ያለባት ግን በአገር በቀል ጥበብ ልብስ ነው። ምክንያቱም አንደኛ ጥበቡ የራሳችን ለስንት ዘመን ከተውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ የመጣ ነው። ሁለተኛ በርካታ የስራ ዕድልም ይፈጥራል።” ይላሉ
“ዘንድሮ ለኪሳራ ተዳርገናል”

በልብስ ስፌት የተሰማሩት ጀማልና የማነም በዓሏ ባህሏን ጠብቃ ብትከበር ያምናሉ።። ሆኖም፤ ባለፉት ዓመታት በአሸንዳ ጥሩ ትርፍ ያገኙ እንደነበር ዘንድሮ ግን ለኪሳራ እንደተዳረጉ ነው የሚናገሩት።
“ጨርቁ አምጥተኗል። የሚድያ ቅስቀሳ መደረግ የነበረበት መጀመርያ ነበር። እኛም አንከስርም ነበር። ይዘነው ቁጭ ብለናል። ቀድመው ይህንን በሚድያ ቢያደርጉት ጥሩ ነበር” ይላል የማነ።