2019-08-30
የትግራይ ብሔረተኞች በአማራ ላይ ያላቸው ጥላቻ ከምን የመነጨ ነው?” (ክፍል አንድ)
አሰፋ ሃይሉ
(ጥናታዊ ጽሑፍ – በጌታቸው ረዳ)
ጥብቅ ቅድመ-ንባብ ማሳሰቢያ፦
የዚህ ጥናታዊ ፅሑፍ አቅራቢ ብዙዎቻችን በቲቪ መስኮት የምናውቀው የወያኔው ጌታቸው ረዳ አይደለም። ይሄኛው የምርምር ፅሑፍ አቅራቢ ጌታቸው ረዳ ሌላ የተከበረ ምሁር ነው። ይህ አሁን ጥናቱን የማጋራለት አስገራሚ ሰው – ይሄኛው ጌታቸው ረዳ – በእርግጥ የትግራይ ክፍለሀገር ተወላጅ ነው። ነገር ግን ይህ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ጌታቸው ረዳ ካልተሳሳትኩ እስከ ቅርብ ግዜያት ኑሮውን በሀገረ አሜሪካን ያደረገ፣ ለዓመታት በሰብዓዊ መብት ተሟጋችነቱ የታወቀ፣ “ኢትዮጵያን ሠማይ” የተሰኘው የኢትዮጵያውያን የመወያያ (http://ethiopiansemay.blogspot.com/) ድረገፅ አዘጋጅ፣ እና የሞረሽ ወገኔ መሥራች የተከበረ ኢትዮጵያዊ ልሂቅ ነው። እና ከዚህኛው ከወየነው (ከራያው) አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር ስመ ሞክሼ በመሆኑ አንባቢዎቼን እንዳያምታታ በከባድ አደራ ማሳሰብ እወዳለሁ። በመነሻዬ በማሳሰቢያዬ እንደጠቀስኩት – ይህኛው አሁን ጥናቱን በሶስት ክፍል ከፋፍዬ የማቀርብለት እውነተኛው ጌታቸው ረዳ – ላለፉት ዓመታት – በኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ለሀቅ እና ለሀቅ ብቻ ፀንቶ በመቆም – የህወኀት/ኢህአዴግን ሥርዓት አስከፊ አምባገነናዊ ገፅታ በአደባቤይ ያጋለጠ ምሁር ነው። ይህኛው ጌታቸው ረዳ – በተለይም ደግሞ – በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መንገድ – የዛሬ 20 ዓመታት ገደማ – የህወኀት የቀደሙ አመራሮች ከጎንደር ላይ የወልቃይት-ሑመራን መሬት እና ከወሎ ላይ የራያን መሬት ወደ ትግራይ “ክልል” በማካለል – ያደረጉትን ዓይን-ያወጣ የአደባባይ የመሬት ቅሚያ ወይም የመሬት ነጠቃ – ህገወጥነቱን እና በሁለቱ አጎራባች ሕዝቦች መካከል ጠብንና ጥላቻን ለመዝራት የታለመለትን አደገኛ ዓላማ – ለዓለም ሕዝብ በማጋለጡ – ለረዥም ዓመታት ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ዕገዳ የተጣለበት – ቢገባ ደግሞ ጥብቅ እርምጃ እንዲወሰድበት ሲታደን የኖረ – ሀቀኛ የኢትዮጵያ ልጅ ነው። አንድ የማይረሳኝ ነገር – እንዲያውም – ከጥቂት ዓመታት በፊት – ያኛውን የህወኀት አፈቀላጤ በመሆን በሚናገራቸው ያልተገሩ ንግግሮች ባጭር ጊዜ የሕዝብ ጥላቻንና ንቀትን ያተረፈውን – የወያኔውን የህግ መምህር (እና የእውነተኛውን ጌታቸው ስመ ሞክሼ) ተጋዳላይ ጌታቸው ረዳን – ለመጀመሪያ ጊዜ በፖለቲከኛ ወንበር ላይ እንደተቀመጠ በቴሌቪዥን ጉብ ብሎ ስናየው፣ እና ኋላም የኮምኒኬሽን ሚኒስትር እስከመሆን ደርሶ ስንመለከተው፣ እንዲሁም ከዚያ በኋላ “ጌታቸው ረዳ” የሚለው የእርሱ ስም በሀገሪቱ ሁሉ የሚታወቅ እኩይ ብራንድ እንዲሆን በየአጋጣሚው በጥሩም በክፉም ስሙ በሚዲያ ፕሮሞት ሲደረግለት ስንመለከት – አንድ የማልረሳው እና አሁን ስሙን መጥቀስ የማልፈልገው ወዳጄ – የሰነዘረው ሀሳብ ነው። ያን ሀሳብ መቼም አልረሳውም። ያ ራሱ የትግራይ ተወላጅ የሆነ ወዳጄ በወቅቱ የወያኔውን ስመ ሞክሼ ጌታቸው ረዳን በየሚዲያው መብዛት አስመልክቶ የሰነዘረልኝ ሀሳብ እንዲህ የሚል ነበረ፦ “ህወኀቶች እኮ የእውነተኛውን ጌታቸው ስመ ሞክሼ ይሄኛውን እኩዩን የመቀሌ የህግ መምህር ጌታቸው ረዳን ወደ አደባባይ ያወጡት – የዚያኛውን የእውነተኛውን ምሁር የጌታቸው ረዳን ስምና ማንነት ለማደናገርና ጨርሶ በሕዝብ ዘንድ እውነተኛ ማንነቱ እንዳይታወቅ ለማስረሳት (ወይም ለማስጠፋት) አልመው ሆነ ብለው ወደ አደባባይ ያወጡት “ኢምፖስተር” (ውሸተኛው አሳሳች ሞክሼ) ነው” ብሎ ነበረ የተነተነልኝ ያ ወዳጄ። በወቅቱ የኛ ሀገር የህወኀት/ኢህአዴግ ሴረኞች ለዚህን ያህል ያፈጠጠ (እና ረዥም ያቀደ) የአደባባይ ሸፍጥ ያን ያህል ይተጋሉ ብዬ አስቤ ስለማላውቅ ሀሳቡን በፈገግታ ቸል ያልኩት ቢሆንም – አሁን ላይ ሳስበው ግን – በዚያ ወዳጄ አስገራሚ አርቆ አሳቢ አብርሆት እስካሁንም (ለሁልጊዜም) ደጋግሜ ስደመምበት እኖራለሁ። ለማንኛውም ግን – አሁን በቀጥታ – ወደ ሀቀኛው ምሁር ወደ እውነተኛው ጌታቸው ረዳ የጥናት ፅሑፍ ልለፍ። የጥናት ፅሑፉን ሙሉውን ማንበብ ለሚፈልግ አንባቢ በዚህ ፅሑፍ ግርጌ መገኛ አድራሻውን ትቼለታለሁ። በተረፈ ግን ካለው ብዛት አንፃር – በሶስት ክፍል ከፍዬ – የመጀመሪያውን አሁን አቅርቤዋለሁ። ይህን የጌታቸው ረዳን ጥልቅ ጥናት የሚያነብ ብዙ አዳዲስ ነገሮችን ያገኝበታልና ያላነበበው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ጊዜ ዝጥቶ ያንብበው። መልካም ንባብ። የትግራይ ብሔረተኞች በአማራ ላይ ያላቸው ጥላቻ ከምን የመነጨ ነው?” (- ጥናታዊ ጽሑፍ ) በካሊፎረኒያ ስቴት በሳን ሆዘ ከተማ በሃያት ሪጀንሲ ሳንታክላራ ሆቴል በሰኔ 26/2006 (July 3/2014) በሞረሽ ወገኔ የአማራ ሲቪክ ማሕበር በተዘጋጀው ሕዝባዊ ስብሰባ በአቶ ጌታቸው ረዳ የቀረበ ጥናታዊ ጽሑፍ። ጌታቸው ረዳ የተከበራችሁ የመድረኩ አዘጋጆች እኔን ከእነዚህ የታወቁ ዓለም አቀፍ ምሁራን ጋር ሆኜ አገራችን በአሁኑ ሰዓት ስለ አለችበት ሁኔታ ለመነጋጋር ስለጋበዛችሁኝ፤ ምስጋናዬ የላቀ ነው። አመሰግናለሁ። እንዲሁም እናንተ ክቡራን እና ክቡራት ኢትዮጵያዊያን ወንድሞች እና እህቶች፤ ስለ አገራችን ጉዳይ ከእኛ ጋር ለመወያየት በመምጣታችሁ እጅግ አማሰግናለሁ። ከሁሉም አስቀድሜ አንድ ነጥብ ለማስረገጥ የምፈልገው ጉዳይ፤ በዚህ ስብሰባ በእንግድነት ስጋበዝ፤ የምሰነዝራቸው አስተያየቶች እና ትችቶች ማንም የፖለቲካ ቡድን ወይንም ድርጅት ወክዬ ሳይሆን እራሴን አንደ የኢትዮጵያን ሰማይ ድረግጽ አዘጋጅነቴ እንደ ጌታቸው ረዳ በግል የሚወክል ነው። ማንም ተቃዋሚ ወይንም ሚዲያ በምሰነዝረው አስተያየት የመከራከር የመተቸት መብቱ የተጠበቀ ነው። ከዚህ በታች የማቀርበው ጽሑፍ ለመጀመሪያ ጊዜ በስፋት ያልተመረመረ ታሪክ በኔ በትግራያዊ ነገድ በኢትዮጵያዊ ዜጋ የተደረገ የመጀመሪያ ጥናት ስለሆነ፤ የታሪክ ምሁራን ለምርምር ሊጠቀሙበት ፈቅጃለሁ። ይህ ካልኩኝ፤ ወደ ውይይታችን ልግባ ከናንተው ጋር ለመወያየት መርጫቸው የነበሩ ሁለት ርዕሶች ነበሩ። ሆኖም ሁለቱን ርዕሶችን አንስቼ ለመወያየት ከጊዜ አንጻር ማብቃቃት ስላለብኝ፤ በአንደኛው ርዕስ ብቻ በማትኰር ከናንተው ጋር እወያያለሁ። አሁን በመረጥኩት ርዕስ እና ከአዘጋጆቹ ተጠይቄ መልስ አንድሰጥበት ያዘጋጀሁትን “የትግራይ ብሔረተኞች በአማራ ላይ ያላቸው ጥላቻ ከምን የመነጨ ነው?” በሚል ጉዳይ አንስቼ ከናንተው ጋር እወያያለሁ። ትንታኔዎቼም አሁን ላለው ውዥምብር መሰረታዊ “ግንዛቤዎች” እንዲኖሩን ይረዱናል። ወደ ዝርዝር ንግግሬ ከመግባቴ በፊት፤ አንድ ነገር ለማለት እፈልጋለሁ። የመድረኩ አዘጋጆች ቀደም ብለው እንደገለጹት የጎሳ ትውልዴ ትግራይ ውስጥ ነው። ወያኔ የኔን ፖለቲካዊ ክርክር ለማፍረስ እንዲመቸው ማንነቴን እያወቀም ቢሆን “ትግሬ” አይደለም፡ በማለት የኔን ትግሬነት ለመንጠቅ በተከታዮቹ በኩል በየኢንተርኔቱ ማንነቴን ለመንጠቅ ያልጐለጐለው የሃሰት ፕሮፖጋንዳ የለም። ትግሬ ሆኖ ከአማራ ወይንም ከአገው ‘ነገድ’ ያልተዋለደ ወይንም ከሌሎች ነገዶች ያልተዋለደ ኢትዮጵያዊ የለም። ሁላችንም ተሳስረናል። በተለይም ትግሬ ሆኖ የገዛ ስሙ ወይንም የወላጆቹ እና የአያቶቹ ወይንም የቅድመ አያቶቹ ስም “የአማራ ስም” የሌለው ትግሬ በምንም መልኩ አይገኝም። ይህ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ብሔረተኛ መሳፍንቶች ‘አማርኛም’ የትግሬዎች አይደለም በማለት አፄ ዮሐንስንም ጭምር ለማሳመን ተከራክረው “ተቀባይነት እንዳጡ’ የትግራይ ታሪክ ፀሐፊዎች ነግረውናል። የተባለው ቋንቋ በትግሬ ነገሥታቶች እና የትግሬ የጥንት ሊቃውንት ከትግርኛ ቋንቋ ይልቅ ከጥንት ጀምሮ በግዕዝ እና በአማርኛ መገናኛቸው ለምን አድርገው እንደመረጡትም ለታሪክና ለነገድ ተመራማሪዎች እተወዋለሁ። ስለ እኔ ማንነት ይህ ካልኩኝ በኋላ። ትግሬ ሆኖ “ወያኔን የሚቃወም የለም” የሚል ወያኔዎችም ሆኑ ወያኔንም በሚቃወሙ ጭምር ይህ እምነት ስላለ ነው ይህንን ለመግለጽ የፈለግኩት። ትግሬዎች ለወያኔ ካለቸው ድጋፍ እና ብዛት አንፃር ስንመለከት ነገሩ እውነትነት አለው። ለዚህም ነው፤ አንድ ታዋቂ ጸሐፊ ክርክርህ ስመለከት እውነት ከትግሬ ነው የበቀለው ስለምል “እውነት ከትግራይ ትውልድ አለህ?” ብለው በኢመይል የጠየቁኝ አንድ ታዋቂ ጸሐፊ ኣሉ፡፡ አንድ የወያኔ ብሔረተኛም ‘እውነት ትግሬ መሆንህን ታምናለህ? እንዲህ ያለ ግልጽ ትግሬ አይተን አናውቅም” በማለት ግትር እውነታየን አስገርሞታል። የማከብረው ወዳጄ ዶ/ር አሰፋ ነጋሽም ያንተን ትግል ስመለከት “እስራላዊው ጋዜጠኛ “ገዴዎን ለቪ” ሆነህ ትታየኛለህ። ብሎኛል። ገዴዎን ለቪ ለማታውቁት ሰዎች፤ ገዴዎን ለቪ እስራኤላዊ ነው። እስራኤል የፓለስታይን ስቃይ ማቆም አለባት ብሎ የእስራልን ወንጀል ከሚያጋልጡ ታዋቂ ጋዜጠኛ እና ሰብአዊ ጠበቃ ነው። ወያኔዎች እኔን እና መሰል ጓደኞቼን ትግሬነታቸው የከዱ ብለው “ሽዋውያን ተጋሩ” እያሉ አንደሚጠሩን ሁሉ በእስራሎችም ገዴዎንን “ሓማሳዊ ፕሮፓጋንዲሰት” (propagandist for the Hamas) የሚል ቅጥያ ተሰጥቶታል። አንዳንድ ወገኖች ደግሞ ገዴዎንን “እስራላዊ አርበኛ” ብለው ይጠሩታል። በዚህም የ2012 የኢንተርናሺናል ሚዲያ አዋርድ ተሸላሚ ሆኗል። ትግሬዎች የጐንደሬዎች እና የወሎዎችን መሬት በጉልበት ቀምተው መኖርያቸው አንዳደረጉት ሁሉ፤ ገዴዎንም እስራሎችን የፓለስቲኒያን ‘ዌስት ባንክ’ መሬት ቀምተው ለሰፋሪ እስራሎች በመስጠታቸው፤ እዛው እየሰፈሩ ያሉት የእስራል ሰፋሪዎችም፤ “society’s of Moral Blindness” “የሞራል እውራን ማሕበረሰብ” ሲላቸው፤ የፓለስቲኒያን መሬት ነጥቆ የመኖርያ ህንፃ በመገንባት ለእስራሎች መኖሪያ ያደረገው የንጥቂያ ወንጀልም፤ the most criminal enterprise in ( Israel’s ) history ብሎታል። በዚህ ምክንያት ገዴዎን ለቪ ከእስራል ወገኖቹ ብዙ የዘለፋ እና የስም ማጥፋት ዘመቻ ተካሂዶበታል። ብዙ መገለልም ደርሶበታል። ወደ እኛው ታሪክ ስመልሳችሁ ደግሞ ብዙ ገዴዎኖች ባንኖርም፤ ወያኔን የምንቃወም ትግሬዎች ጥቂት መሆናችን እርግጥ ነው (ብዙ የቀራቸው መንገድ ቢኖርም አሁን አሁን የኔን ኮቴ ተከትለው የመጡ ጥቂቶች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል።) እየተሰደብኩም ሆነ ከሕብረተሰቡ አንድነጠል እየተደረገም ቢሆን እዚህ ድረስ ተጉዤ አሁን በርካታ ተከታዮች በማፍራቴ ኩራት ይሰማኛል። ወዳጄ ገብረመድህን እንዳለው “ባንተ ኮቴ ተከትለን እዚህ አንድንደርስ ያደረግከው የትግል አርአያ በትግራይ/የኢትዮጵያ የታሪክ መዝገብ ለወደፊቱ ይጻፋል።” ብሎ የጻፈልኝ የግል ደብዳቤ ሳስታውስ በትግሉ እንድቀጥል አበራታች ሆኖኛል። ወያኔ ትግራይ በ1983 ዓ.ም ስልጣን ከያዘ በሗላ፤ ጥቃቱ ያነጣጠረው “እንደ ሕብረተሰብ” በአማራ ሕብረተሰብ ላይ እና “እንደ አገር” በኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረ አንደሆነ ሃቅ ነው። በአማራ ላይ የደረሰው ጥቃት እዚህ ያሉ ክቡራን ሊቃውንቶች ስለገለጹት ወደ ዝርዝር ጥቃቱ አልገባም። ነገር ግን የትግራይ ብሔረተኞች በዚህ ሕብረተሰብ ላይ ጥቃቱን ለማነጣጠር ያነሳሳቸው ምክንያት ምንድ ነው? የሚለው ግን ለማብራራት እሞክራለሁ። የትግራይ ብሔረተኞች የአማራ ጥላቻቸው ከሌሎች ጎሳዎች ይልቅ ለምንድነው የበረታው? የሚለው መመለስ አለብኝ? ይህ ብቻ ሳይሆን “የትግራይ ብሔረተኛ ስሜት” መመንጨት የጀመረው መቸ ነው? የሚለውም አብረን ከመለስን ለጥላቻው መንስኤ ምዕራፉ ከየት አንደጀመረ ለመረዳት ይረዳናል። /ክፍል ሁለት … ይጥላል።ለት ክፍሎች ለማቀርበው የጥናት ፅሑፉ እና ስለ ሀቅ ሲል ለተላበሰው የሕሊና ብርታት የከበረ ምስጋናዬንና አድናቆቴን በአክብ
2019-08-31
የትግራይ ብሔረተኞች በአማራ ላይ ያላቸው ጥላቻ ከምን የመነጨ ነው?”
(ጥናታዊ ጽሑፍ | ክፍል ሁለት )
ጌታቸው ረዳ (ኢትዮጵያን ሰማይ አዘጋጅ)
በአሰፋ ሃይሉ
በካሊፎረኒያ ስቴት በሳን ሆዘ ከተማ በሃያት ሪጀንሲ ሳንታክላራ ሆቴል በሰኔ 26/2006 (July 3/2014) በሞረሽ ወገኔ የአማራ ሲቪክ ማሕበር በተዘጋጀው ሕዝባዊ ስብሰባ በአቶ ጌታቸው ረዳ የቀረበ ጥናታዊ ጽሑፍ። ጌታቸው ረዳ ( getachre@aol.com ) :- የትግራይ ብሔረተኞች የአማራ ጥላቻቸው ከሌሎች ጎሳዎች ይልቅ ለምንድነው የበረታው? የሚለው መመለስ አለብኝ? ይህ ብቻ ሳይሆን “የትግራይ ብሔረተኛ ስሜት” መመንጨት የጀመረው መቸ ነው? የሚለውም አብረን ከመለስን ለጥላቻው መንስኤ ምዕራፉ ከየት አንደጀመረ ለመረዳት ይረዳናል። /… ካለፈው የቀጠለ።/ የትግራይ ብሔረተኛነት ስሜት መታየት የጀመረው የትግራይ መሳፍንቶች እርስበርሳቸው ለስልጣን ሲሉ የአንድ አውራጃ ሕዝብ ከሌላው አውራጃ ጋር በደም፤ በአጥንት፤ በሃብት እና በሰራዊት ብዛት እየተኩራሩ በላቀ ተወልጄነት ወይንም “ትግሬነት” በመናናቅ ‘አውራጃዊ ስሜት’ በሕዝቡ ስሜት ላይ እንዲታነፅ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ለስልጣን ሲሉም የአንድ እናት ወይንም የአጎት ልጆች እርስ በርሳቸው እስከመገዳደልም ደርሰዋል። ይህ የበላይነት እና አውራጃዊ ስሜት አክሱሞች በዓድዋዎች ዓድዋዎች በአክሱሞች፤ አንደርታዎች እና ዓጋሜዎች በመላ የትግሬ እና ኤርትራ ተወልጄ ገዢዎች ላይ የበላይነት ለማረጋጋጥ ሲሉ አውራጃዊ ስሜት እንዲስፋፋ አድርገዋል። ይህ የእርስ በርስ አከባቢያዊ የመናናቅ ስሜት እንዳለ ሆኖ፤ ከሸዋ ወይንም ከጐንደር፤ ከወሎ ወይንም ከሌላው አካባቢ አዲስ ገዢ/ጉልበተኛ ሲነሳባቸው ግን ‘አውራጃዊ የመከፋፋል ስሜታቸውን ወደ ጎን በማቆየት” ሁሉም ባንድነት “የትግሬ ብሔረተኛነት ስሜት” በማሰባሰብ እንደ ባዕድ በሚመለከታቸው የሌሎች አካባቢ ነገሥታት/ጉልበተኞች ላይ ያምጻሉ። የንጉሡ ስም ካልተሳሳትኩ በአጼ አምደጽዮን ጊዜ ይመስለኛል……… በገዢነት ወደ እንደርታ በመጡበት ጊዜ () ትግራይ ውስጥ ከተወልጀዎች ውጭ የሆኑ ከድሃ መደብ ቤተሰብ የተገኙ ትግሬዎች ወይንም ከሌላ አካባቢ የመጡ በንጉሡ ስለተሾሙ “ሓለስተይቶት” አይገዙንም በማለት ጠባብ የትግራዋይነት ስሜት አንጸባርቀዋል። ሓለስተይቶት ማለት “የበታቾቻችን/ዲቃላዎች” ወይንም በአሜሪካኖቹ አሰያየም “ኔገር” አይገዛንም አንደማለት ይመስለኛል። ዛሬ የምትሰሙዋቸው አንዳንድ የወያኔ ሰዎችም ሆኑ ኤርትራዊያኖች እርስ በርሳቸው ሲነታረኩ/ሲጣሉ/ሲከፋፈሉ “እዚኦም ባ ል መንዮም!?” (እነዚህ እነማን ይባላሉ?!) በመባባል አርስበርሳቸው በመናናቅ የሚያሰምዋቸው ቃላቶች ከዚያ ዘመን የወረሱዋቸው ትምክህታዊ ባህሪያቶች ናቸው። ለምሳሌ የወያኔው ብስራት አማረ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ‘ቦሌ አይሮፕላን ማረፊያ’ አንደወረደ፤ በጸጥታ መ/ቤት ሐላፊዎች ትዕዛዝ “ወደ አገር አንዳይገባ” ታግዶ ወደ መጣበት አሜሪካ አንደተመለሰ ከታወቀ በሗላ ‘ገዛ ተጋሩ’ በሚባል አፍቃሬ የወያኔ ‘ፓል ቶክ’ መድረክ ስለሁኔታው ተጠይቆ ሲያብራራ፤ የተጠቀመበት ቃል ያንኑ ቃል ነበር። “እነዚያ ዲቃላቆች” ነበር ያላቸው። ያም ሆነ ይህ፤ ከሌላ አካባቢ የመጡ ሹመኞች በግማሽ የተወለዱ ትግሬ ገዢዎችን ‘ዲቃላዎች’ ወይንም ‘ባዕዳን’ ወይንም “ሓለስተይቶት” አይገዙንም በማለት ጠባብ የትግራዋይነት ስሜት አንጸባርቀዋል። ያም ሖኖ በሌሎቹ አከባቢ ጉልበተኞች ቢገዙም ስሜታቸውን ‘በማመቅ’ አንዳንዴም ‘በማመጽ’ እስከ አጼ ዮሐንስ ድረስ ቆይተዋል። አጼ ዮሐንስ በነገሱበት ወቅት ግን የትግሬ ሕዝብ ሰጥ ለጥ ብሎ ተገዝቶላቸዋል። እስካሁን ድረስም የልጅ ልጆቻቸውን “ደቂ ላሕምና” (የላሜ ቦራ/ የላማችን ልጆች” እያሉ ይጠሯቸዋል።ለምሳሌ የትግራይ ሕዝብ በደረግ ጊዜ “ልዑል ራስ መንገሻ ስዩምን “ወዲ ላሕምና” አናስጠቃም በማለት ስለጮኸ ደርግ እርምጃ ከመውሰድ ተገ’ዶ ነበር። ዮሐንስ ከሞቱ በሗላ ዘውዱ በምኒልክ ሲተካ፤ ትግሬዎች ከፍተኛ የሆነ “የባዶነት ስሜት” ወይንም ‘emptiness’/ a sense of generalized boredom) ተሰምቷቸዋል። የባዶነት ስሜት ለምን ሊሰማቸው ቻለ? የትግሬ ሕዝብ ለዘመናት በራሱ አስተዳዳሪዎች የመገዛት ልምድ ከዘመነ አክሱም ጀምሮ የቆየ ስለሆነ፤ የካባቢው ሕዝብ ምንም ኩፉ ስርዓት እና ጨካኝ ገዢ ቢሆንም በአካባቢ ገዢ የመገዛት ፍላጎታቸው የበረታ ነው። ለዚህም ልዩ ምክንያት አለው። ምክንያቱም ስልጣን የያዘው ሕዝቡ ሳይሆን ገዚዎቹ ቢሆኑም “ስልጣን የያዙ ገዢዎች ትግሬዎች ከሆኑ፤ የትግራዋይነት ጉልበት እና የበላይነት ስሜትን በስነ ልቦናቸው እንዲቀረጽ በማድረግ በሌሎች ጐሳ ገዢ መደቦች ላይም ሆነ በሌሎች ጐሳዎች ላይ የበላይነት ስሜት አንዲያድርባቸው ሆኗል።” እንግዲህ ከዚህ በመነሳት የትግራዋይነት ስሜት ከዘመነ አክሱም ጀምሮ እየተገነባ የመጣው የበላይነት እና የጉልበተኛነት ስሜት በሕዝቡ ስሜት በመቀረጹ ከትግሬ ሌላ ገዢ ካስተዳደራቸው፤ ጉልበታማነታችን እና እንዲሁም የትግሬነት የበላይነት ክብራችን ‘ተነጠቀ’ በሚል ስሜት በመነሳሳት የሌላው ጐሳ ንጉሥ በባዕድነት በመመልከት “ገዢዎች ኖረን ተገዢዎች አንሆንም” በሚል ስሜት “እሩቅ ትዝታ” ውስጥ በመግባት የስልጣን መለዋወጡ ጉዳይ ተፈጥሮአዊ መሆኑን ላለመቀበል ‘የተጠቂነት ስሜት’ አድሮባቸው ‘አንገዛም’ በማለት ጦርነት እና ግጭት ይፈጥራሉ። ጦርነቱ እና ግጭቱ በዛው ሳይወሰን፤ “ረዢም እና ጥልቅ የጥላቻ አጥር” በመገንባት ረዢም የሚጓዝ፤ ለልጅ ልጅ የሚተርፍ የጥላቻ ውርስ ‘የማስተላለፍ ባሕል’ እያስረከቡ አልፈዋል። ስለሆነም ነው የትግሬ ብሔረተኞች አጼ ዮሓንስ በመተማ ጦርነት ከተሰው በሗላ፤ ተከትለው የዙፋኑን መንበር የተረከቡት የሸዋው ንጉሠ ነገሥት “ምኒልክን” አንደጠላት እና ባዕድ ንጉሥ አድርገው በመመልከት፤ የትግሬ ሥልጣን ‘ወደ ሸዋ ተዛወረ’ በሚል ቁጭት የተነሱት የዘመኑ መሳፍንቶች ከንጉሥ ምኒልክ ጋር አለመጣጣም ፈጥረው “በሸዋ አንገዛም” በማለት ንትርኩ ወደ ሕዝቡ ተላልፎ መለስተኛ ጦርነት በትግራይ አካባቢ ተካሂዷል። ያ ዘመን፤ የትግሬ ብሔረተኞች በቁጭት የምኒልክን ዘመን “ዘመነ ሸ” ወይንም “ዘመነ ሸዌ” በማለት ይጠሩታል። በትግሬ ብሔረተኞች ጸሓፊዎች መሰረት፤ ‘የሸዋ እና የትግሬ መቃቃር’ “ዘመነ ሸ” የሚሉት በንጉሥ ምኒልክ ዘመን ብቻ ሳይወሰኑ የትግሬ ብሔረተኛነት በሸዋ ነገሥታት እና በትግሬ ገዢዎች ቅራኔ የተፈጠረበት ዘመን ወደ ሗላ በመጎተት ታሪካዊ እና መሰረታዊ ቅራኔዎቻችን መነሻዎች ከሚሏቸው ነጥቦች ውስጥ አንዲህ ይገልጹታል። የማነ ገብረመስቀል፤ የተባለው “ቀዳማይ ወያነ” የሚል መጽሐፍ የጻፈ ጸሐፊ በትግርኛ አንዲህ ይላል፦ “የትግሬ ሕዝብ ብረት አንስቶ ለመታገል የተገደደበት ለቀዳማይ ወያኔ አመጽ መነሻ በወቅቱ በተከሰቱ ምክንያቶች ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፤ ለዘመናት መፍትሄ ሳያገኙ በሕዝቡ “የልቦና ግምጃ ቤት” መሽገው የነበሩ “ታሪካዊ እና መሰረታዊ” ምክንያቶችም ጭምር ነው።” ዶ/ር ክንፈ አብርሃም የተባለ ሌላው የትግሬ ምሁር (ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል) እነኚህ የሚከተሉት ምክንያቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የትግራይ ሕዝብ በሸዋ ገዢ መደቦች ላይ “ጥላቻ” አሳድሮ ነፍጥ አንሰቶ ሊታገላቸው ትልቅ ምክንያት ሆኖታል የሚላቸው ምክንያቶች እንዲህ ይዘረዝራል። (ሀ) በሥልጣን ሽሚያ ምክንያት የተፈጠረው ፖላቲካዊ ግጭት በትግራይ ሕዝብ ላይ የፈጠረው ስሜት፤ የጀመረው፤- “ከአክሱም መንግሥት መዳከም ወዲህ፤ እና አንዲሁም ድንግተኛ የሆነ ያልተጠበቀ የአጼ ዮሐንስ አራተኛ ሞት ተከትሎ የመጣው የሸዋ መንበረ መንግሥት ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ “ትግሬዎች በትክክለኛ የፖለቲካ/ሥልጣን ሚዛን ላይ አይደለንም። ሥልጣናችን እና ታሪካችን በሸዋ ገዢ መደቦች ተነጥቀናል።” ክንፈ አብርሃም (2001- Ethiopia from Empire to Federation p.223) የሚል ስሜት አሳድረዋል። ቀዳማይ ወያነ የሚል መጽሐፍ ደራሲ የማነ ገብረመስቀል ድግሞ እንዲህ ይላል፡- “የሥልጣን ሥርወ መነግሥት እና ሥልጣኔ ማዕከላዊ መሰረቱ ትግራይ ውስጥ እና በትግሬዎች እጅ እያለ፤ በተንኮል ወደ ሸዋ ተወስዷል፤ ስለሆነም (ትግሬዎች) በሸዋ ገዢዎች ላይ ከፍተኛ ጥላቻን አከማችተዋል። በዚህ ሳይወሰን ቅራኔው ወደኋላ ብንሄድ የሸዋው የሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት የሆነው “ይኩኖ አምላክ” ሥልጣን ከያዘ በኋላ የእንደርታ (ትግራይ) ገዢ የነበረው ዓብየዝጊ እራሱ የሰለሞን ሥርወ መንግሥት ነኝ ብሎ በሚጠራው “ቡድን” ላይ ዓመፅ አካሄዷል። ከዛ ጊዜ ጀምሮ ትግራይ ውስጥ በሸዋዎች ላይ ብዙ ተቃውሞዎች ተቀጣጥለዋል።” (የማነ ገብረመስቀል ‘ቀዳማይ ወያነ’ ገጽ 23) እንግዲህ የትግራይ ብሔረተኞች ከሸዋ ጋር ቅራኔ የፈጠሩት ከይኩኖ አምላክ (12ኛው ምእተ እዝጊ) ዘመን የጀመረ ነው ብለው ነግረውናል። የማነ ‘ቀዳማይ ወያነ’ በሚባለው የትግርኛ መጽሐፉ በሰፊው የገለጸው ባጭሩ አሳጥሬ ነጥቦቹ ለናንተ ጀሮ እንዲመች ላቅርብ። እንዲህ ይላል፦ “የአክሱም መዳከም ተከትሎ ትግሬዎች ከተዳከሙ በኋላ፤ ትግርኛ ተናጋሪው ሕዝብ በተለይም ለሁለት ከተከፈለ በኋላ (ኤርትራ እና ትግራይ ማለቱ ነው)፤ ኩፉኛ ተዳክሟል። ትግሬዎች ለመዳከም የመጀመሪያ ተጠያቂዎች አድርጐ የሚያቀርባቸው አነዚያ አፄ ዮሓንስ ከሞቱ በሗላ የመጡ የሸዋ ገዢ መደቦች ናቸው።” ይላል። የማነ ገብረመስቀል። ይህንን በተመለከተ “ዶ/ር ክንፈ አብርሃምም” እንዲህ ይላል፤- “በእርግጥም ትግርኛ ተናጋሪ ሕዝቦች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች በተንኰል እርስ በርሳቸው በመከፋፋል እና በማዳከም በትግርኛ ተናጋሪ ሕዝቦች በኩል ሲነሱ የነበሩ ተቃውሞዎች ለመቆጣጠር ይጠቀሙባቸው ነበር።” ክንፈ አብርሃ (ዘኒ ከማሁ)፤ በመጨረሻ የማነ አንዲህ ይላል። “ የትግራይ ሕዝብ በ19ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ ጀምሮ “ብሔራዊ ማንነቱ እና የፖለቲካ መንበሩ እየተሸረሸረ በመሄዱ በተለያየ ጊዜ እና ቦታ ፀረ-ሸዋ ገዢ መደቦች ተቃውሞውን አሳይቷል። የመጀመሪያው ማለትም “የቀዳማይ ወያነ አብዮትም” ለዘመናት “ጸረ ብሔራዊ ጭቆና እና የበታችነት ስሜት” በላዩ ላይ የጫኑበትን የሸዋ ገዢ መደቦችን ለመጣል የታገለበት ሕዝባዊ አመጽ አንደነበረ ነው ብዙ ተማራማሪዎች የሚገልጹት” ሲል የማነ ገብረመስቀል፤ ለትግራይ ብሔረተኛ ስሜት መነሻው እና መቸ እንደጀመረ (ማለትም በእንደርታው አብየዝጊ እና በይኩኖ አምላክ ጀምሮ ማለት ነው) ሊገልጽልን የሞከረው። እንዲሁም የወያኔው መስራች እና የሽምቅ ተዋጊው ሃይል የጦር መሪው የነበረው ወዳጄ ዶ/ር አረጋዊ በርሄም በበኩሉ አንዲህ ሲል ያስቀምጠዋል። “የትግሬዎች ብሔራዊ ጥያቄ፦ ለረዢም ጊዜ የነበረ እና ስር የሰደደ የራሱ ተጨባጭ ምክንያቶች ይዞ ሲጓዝ ቆይቶ የተነሳ ነው። በተለይም የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ፖለቲካ ከትግራይ ከተነሳ በኋላ፤ በውስጥ መሰሪ ተንኰል (“በሸዋ ገዢዎች”) እና በውጭ ጣልቃ ገብነት፤ ከትግራይ ገዢ መደቦች መዳፍ ወጥቶ ወደ አማራ ገዢ መደቦች ከገባ በኋላ የትግራይ ገዢ መደቦች ከነበራቸው የፖለቲካ ሥልጣን እየተገፉ ከመጡ በኋላ ነው “የትግራይ ብሔራዊ ጥያቄ መነሳት” የጀመረው። ዛሬም ቢሆን ማዕከላዊ የፖለቲካ ሥልጣን አሁን ካለበት ተነሥቶ ወደ ትግራይ መዛወር አለበት የሚል እምነት ያለቸው አሁንም በርካታ የትግራይ ተወላጆች አሉ።” (Aregawi Berhe: 2008) Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975-1991): Revolt, Ideology and Mobilization in Ethiopia. P45) አንግዲህ የትግራይ ብሔረተኞች መነሻ ጥያቄ ባጭሩ፦ (1) ከዘመነ አክሱም ጀምሮ የነበረው የትግራይ የሥልጣን የበላይነት በሸዋዎች ተነጠቀ፤ (2) ከሸዋ እና ከመሳሰሉ አማራ ተወላጆች ወደ ትግራይ አስተዳዳሪ አድርገው በመሾም ጥንት የነበረ ‘ፍትሕ እና ሰናይ አስተዳዳር’ አንዲፈርስ ተደርጓል፤ (3) የትግራይ ታሪካዊ ቅሪቶች እና ባሕላዊ እሴቶች ተዳክመዋል፤ (4) ከፍተኛ የትግራይ መኳንንት እና ባላቦቶች እስር ቤት አንዲማቅቁ ወደ አንኰበር እና ጋሞጐፋ ተወስደው ለሞት ተዳርገዋል። (5) የትግራይ ሕዝብ በአማራዎች በምጣኔ ሐብት ከሌሎች ጐሳዎች በተለየ መልኩ አንዲደኸይ፤ ቋንቋው አንዲረገጥ ተደርጓል……ወዘተ….ወዘተ… የሚሉ አበይት ምክንያት የሚሏቸው አነኚህ ቢሆኑም። ለትግራይ ብሔረተኛነት ስሜት ዓይን አውጥቶ ምክንያት ሆኖ ቀዳሚ መከራከሪያቸው ሆኖ የቀረበው ግን ‘ሥልጣን ከትግራይ ማዕከል ወጥቶ ወደ ሸዋ መግባቱ” የትግራይ ብሔረተኞች ስሜት ተነክቷል። በመሖኑም በቁጭት ተመልክተው ከሸዋ/ ከአማራ ጋር ቅራኔ ያስገባቸው ዓይነተኛው ምክንያት ግን እስካሁን ድረስ ያልተፈተሸ ለመጀመሪያ ጊዜ “ወያኔዎች እና እኔ ብቻ” የፈተሽነው በአንድ የጥንት ትግሬ ጸሐፊ ተጽፎ የተገኘ ሰነድ ይህ የሚከተለው ዓብይ ምክንያት ነው። ዮሐንስ ከመቱ በሗላ በ1882 ዓ.ም ታሕሳስ ወር ውስጥ ምኒሊክ የበላይነታቸውን ለማረጋገጥ እና ትግራይን ለማረጋጋት በርካታ ሰራዊታቸውን ይዘው ወደ ትግራይ ዘመቱ። በወቅቱ በሕይወት የነበሩት የአፄ ዮሐንስ እህት የሆኑት ወ/ሮ (እቴጌ ) ድንቅነሽ የወንድማቸው ዙፋን በሸዋ እጅ በመግባቱ የሚከተለው የቁጭት እና የንቀት ግጥም በትግርኛ ገጠሙ፦ ጹሑፉ እንዳይራዘምብኝ ከትግርኛ ወደ አማርኛ የተረጐምኩትን ብቻ ላቅርብ፡ እንዲህ ሲሉ ለምኒልክ ገጠሙላቸው፡ አንደምን አለክ ንጉሥ ሆይ፤ ንጉሥ ምኒልክ ያመጡልን ነበር ቅቤ ማር በትዛዝ፤ ያመጡልን ነበር ላም በሬ በትዛዝ፤ አልነበሩም ወይ የዮሐንስ ታዛዥ? ይታዘዙ ነበር ብለው እጥፍጥፍ፤ ለጥ ሰጥ ብለው አንዳጎዛው ምንጣፍ። ዮሐንስ ግን ሲሞት አንደዋዛ፤ ተደብቀው ቆይተው በሽምዛ (ሽምዕዛ ቤተክርስትያን አካባቢዎች ትግራይ ውስጥ የሚበቅል ለመደበቅ የሚያመች አጠር ያለ ቅጠል የበዛበት ዛፍ ነው) ሰተት ብለው ገቡ አንደዋዛ። ለመሆኑ ዛሬ ምን አመጣዎት ‘ሰተት ብለው ገቡ ሰው በሌለበት ቤት?” በማለት ተቃውሞአቸውን ገልጸው ነበር። ምኒልክ በ1882 ዓ.ም ወደ ትግራይ ሲመጡ፤ የዮሐንስ ዘሮች የሆኑ መሳፍንቶች እና ተወልጄዎቹ አንዲህ ባለ ተቃውሞ ሲገልጹ፤ ሕዝቡስ ምን ዓይነት ስሜት እና ቅሬታ አንጸባርቆ ነበር? / ክፍል ሦስት … ይጥላል።/
የትግራይ ብሔረተኞች በአማራ ላይ ያላቸው ጥላቻ ከምን የመነጨ ነው?” (ክፍል ሦስት) – አሰፋ ሃይሉ–
2019-09-01
ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢ ጌታቸው ረዳ (ኢትዮጵያን ሰማይ አዘጋጅ) (Ethiopian Semay: http://ethiopiansemay.blogspot.com/ )
«የማንበብ ችሎታ እያለው ምንም የማያነብ ሰው፥ የማንበብ ችሎታ ከሌለው ሰው እኩል ተደርጎ ይቆጠራል።»
( – ማርክ ትዌይን፥ አሜሪካዊ ደራሲ) ኑ ፡ እውነትን ፡ እናንብብ ! |
{የዕለቱ መልዕክት} … ምኒልክ በ1882 ዓ.ም ወደ ትግራይ ሲመጡ፤ የዮሐንስ ዘሮች የሆኑ መሳፍንቶች እና ተወልጄዎቹ አንዲህ ባለ ተቃውሞ ሲገልጹ፤ ሕዝቡስ ምን ዓይነት ስሜት እና ቅሬታ አንጸባርቆ ነበር? /ጌታቸው ረዳ …ካለፈው የቀጠለ/ አሁን ወደ ዋናው የትግራይ ብሔረተኛነት ስሜት በግልጽ ለመጀመርያ ጊዜ በሕዝቡ ልቦና የተቀረጸበት እና የታየበት ወቅት እወስዳችሗለሁ:: አጼ ዮሐንስ ከሞቱ በኋላ ራስ መንገሻ ዮሐንስ እና የመሳሰሉት የትግራይ ገዢዎችን ከአዲሱ ጉልበተኛ እና ጥበበኛው ንጉሥ ምኒልክ ጋር በፈጠሩት ቅራኔ ‘ሥልጣኑን ትግራይ ውስጥ ለማቆየት የአካባቢው ገጠሮች ከምኒልክ ሠራዊት ጋር ያካሄዱት መጠነኛ ፍትግያ/ውግያ ሲደረግ የዓይን ምስክር የነበሩ “ይሓ” (ዓድዋ) ውስጥ የተወለዱ የትግራይ ተወላጅ የሆኑት “ታሪኽ ኢትዮጵያ” የሚል በእጅ ጽሑፍ በ1891 (ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር) በናፖሊ/ ጣሊያን አገር የተጻፈ ባለ 169 ገፅ የያዘ ብደብተራ ፍስሐ ጊዮርጊስ ዓቢየዝጊ የጻፉት በትግርኛ እንደመግቢያ አንዲህ የጻፉትን ላንብላችሁ። በአማርኛ የተረጎምኩትም አነበዋለሁ። “….ሽዕቱ ገጽ ሸወታይ ጥምት አቢልካ ናብ ገጽ ትግራዋይ ቁልሕ እንተበልካ ዳርጋ ክንዲ ናይ ለይትን ናይ ቀትርን ዚአክል ምፍልላይ ይርኤ ነበረ” (ታሪኽ ኢትዮጵያ ገጽ ፻፴፬ (134) ደብተራ ፍስሐ ዓብየዝጊ ናፖሊ/ኢታሊያ-1891/ ብአውሮጳዊያን ዘመን 1899) ወደ አማርኛ ሲተረጐም፤ “ያኔ የሸዌዎቹ ገጽታ ተመልክተህ ወደ የትግሬው ሰው ገጽታ ፊትህን ዞር ብለህ ስትመለከት የምትታዘበው የሁለቱ ሰዎች ገጽታ ልዩነት ልክ የቀን ብርሃን እና የሌሊት ጨለማ የገጽታ ልዩነት ይታይ ነበር።” (ታሪኽ ኢትዮጵያ ገጽ ፻፴፬ 134) 1891/ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር (1899/አውሮጳ ዘመን) ደብተራ ፍስሐ ዓብየዝጊ ናፖሊ/ኢታሊያ) ትርጉም (የኔ)። ከላይ የጠቀስኩት ግልጽ ስዕል ምን ማለት እንደሆነ እና በወቅቱ የታየው የወደፊት መጻኢ ባሕሪው ወዴት እንደሚወስድ እና አሁን ካለው ነባራዊ ክስተት ስታገናዝቡት የወያኔዎች የገጽታ ተማሳሳይ ቅጅ ምንጩ “ያቺኛዋ ወቅት” እነደሆነች መገንዘብ ትችላላችሁ። ከላይ የተመለከተው የታሪኩ አጭር ዝርዝሩ በአማርኛ የተረጎምኩትን እነሆ ፡- “ራስ መኮንን ለዲፕሎማሲያዊ ስራ በአፄ ምኒልክ ናፖሊ/ከጣሊያን አገር ደርሰው በምፅዋ አድርገው ወደ መቀሌ ከተማ ሲገቡ አጼ ምኒሊክም መቀሌ ከተማ ውስጥ ስለነበሩ ራስ መኮንን ለመቀበል ደራሲው ደብተራ ፍስሃም በግራዝማች ዮሴፍ ስር ስለነበሩ ከሳቸው እና ከነደጃች ስብሐት እና ከመሳሰሉት ከትግራይ መኳንንት ጋር ሆነው ራስ መኮንን ወደ መቀሌ ለማጀብ ወደ ከተማዋ የሚወስደው ቁልቁል መንገድ ሲደርሱ (የመሶቦ ዳገት/ ቁልቁለቱ ማለታቸው ነው) እንዲህ ይላሉ። “ለደጃች ሥዩም ገብተው የነበሩ የተምቤኑ ደጃዝማች ሐጎስ ከሳቸው ጋራ የነበረው ተፈሪ የተባለ ዘመዳቸው አብሯቸው በነበረበት ወቅት ‘ሁለት ሰናድር’ ይዞ ወደ ግራዝማች ዮሴፍ በመግባቱ ‘አጠፋህልኝ’ ብለው ተማጸኑት። ዳኛውም ራስ መኮንን ሆኑ። ያኔ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት አፄ ምኒሊክ ናቸው። ተማጓቾች ሁሉ በሙግታቸው ጣልቃ የተሟጋች-ቻቸውን አንደበት ስርዓት ለማስያዝ ሲፈልጉ “ዝባን ዮሐንስ ” (በዮሐንስ አምላክ)እያሉ ተቸገሩ። ሆኖም “በዮሐንስ አምላክ” እንዳይሉ ዳኛው ራስ መኮንን ሆኑባቸው፤ በሚኒልክ አምላክ እንዳይሉ ደግሞ አዲስ ነገር ሆኖባቸው ከእጅህ ለማማልጥ ሙሉጭልጭ እያለ እንደሚያስቸግርህ ዓሳ “በዮሐንስ አምላክ” እያሉ ምላሳቸው እያዳለጠባቸው ተቸግረው ነበር። ካፋቸው ሲያመልጣቸው ግን፤ ልክ አንድ ጎረምሳ ጎበዝ ጭቃ አዳልጦት ወድቆ ሲነሳ ሰው አይቶት እንደሆን ‘አካባቢው ግራ እና ቀኝ በሐፍረት እንደሚቃኝ ሁሉ’ ተሟጋቾቹም ወደ አድማጩ ዞር ዞር እያሉ የሰውን ስሜት በሰቀቀን ሲለኩ ነበር። “ፍርዱ ላይ በችሎቱ አካባቢ የነበረው ተሰብሳቢ ሕዝብም እርስ በርሱ በስሜት እየተጠቃቀሰ ይተያይ ነበር። ሁኔታው ሰውን ሁሉ በጣም አቅል የሚያሳጣ ሆነበት። ያችን ችሎት ተሎ ባለቀች እያለ ያልተመኘ አንድም ሰው አልነበረም።በውስጡ በብዙ ሃሳቦች ተውጦ ይታይ ነበር።” (ታሪኽ ኢትዮጵያ ገጽ ፻፴፪-፻፴፫/132-133 ደብተራ ፍስሐ ዓብየዝጊ ናፖሊ/ኢታሊያ-አቆጣጠር 1899/ፈረንጆች ዘመን አቆጣጠር (ትርጉም የኔ፤- ጌታቸው ረዳ)።” ደራሲው ይቀጥሉ እና “አጼ ሚኒልክ ራስ መኮነንን ሲቀበሉ” በሚል ርዕስ ሲተነትኑ (ራስ መኮንን ከናፖሊ ጣሊያን አገር ዲፕሎማሲ ስራ ሰርተው በምፅዋ በኩል ወደ መቀሌ ሲመለሱ የተደረገላቸው አቀባበል ማለታቸው ነው):- “አጉላዕ በተባለች ትንሽ መንደር ለአዳር ሰፈራ አድርገን ትንሽ ቆይታ ካደረግን በኋላ በወቅቱ መቀሌ ከተማ ይገኙ ከነበሩት ከአፄ ጋር (ምኒሊክ ጋር) ለመገናኘት ጫን ተባልን።በወቅቱ ራስ መኮንን ከሐረርጌ ወደ ዜላ ከዚያ ወደ ናፖሊ ከዚያ ወደ ምፅዋ፤ ያ ሁሉ መንገላታትና አስቸጋሪ ጉዞ እና ባሕር አቋርጦ በሰላም መመለስ የሸዋ መኳንንትም ሆኑ በእነ ራስ ሐጎስ በኩል ከፍተኛ ደስታ ነበር። ይኼ ደግሞ ግልጽ ነው። … “…ወደ መቀሌ የሚያስገባው ቁልቁሉን መንገድ እንደ ጨረስን የአፄው ብዙ ጭፍራ ቆዩን። ደጃዝማች ስብሐት ግን ለራስ መኮንን የሚከተለው ቃል ተናገሯቸው። “እኔ ቆየት ብየ እደርሳለሁ፤እርስዎ ግን ቅድሚያ ይሂዱ”አሏቸው። ራስ መኮንንም “እሺ ደግ ይኹን” ብለው በሃሰባቸው ተስማሙ። ሰው ግን “አይ ተደርበው እንዳይገቡ” ብለው ነው፤ በማለት ተረጎመው። ቁልቁለቱን ጨርሰን ታች እንደወረድን ወዲያውኑ ከሸዋ ሰራዊት ጋር ዓይን ለዓይን ተያየን። “ጸንዓ ደግለ” እያለሁ ድሮ የማውቀው የአጋሜ የአጉዕዳይ ተወላጅ የሆነው ፊታውራሪ ተስፋይ የተባለ ጎን ለጎን እንጓዝ ነበር እና “ወይኔ! ይበለን! ራሳችን ያመጣነው ጣጣ ነው፤ አስታጣቂዎች የነበርነው አሁን ታጣቂዎች ሆን!” አለ። “ከዚያ በኋላ ይህ ያዳመጡ ራስ መኮንን ለመሸኘት የተከተሉ እነ ‘ኮንቲ አንቶኖሊ’ እና ራስን አጅበው እየተጓዙ የነበሩት ትግሬዎች በሞላ ማለትም-ዓጋሜውም፤አከለ-ጉዛዩም፤ሐማሴኑ፤የአሕሳአውም፤ ተምቤንየውም ሁሉ ከሸዋዎቹ ጭፍራዎች ጋር ዓይን ላይን ተገጣጥሞ ሲተያይ ‘ኪፍ’ አለው። (ደራሲው የተጠቀሙበት ቃል “ኪፍ” የሚል ነው። “ኪፍ” ማለት ድመት ወይንም ነብር ጠላት ስታይ ‘ካንገቷ በላይ ያለው ጸጉር’ በማቆም ‘በጉብታ ስሜት’ የጥላቻ እና የመከላከል ገጽታዋ እንደሚለዋወጥ የሚታይ ስሜት ማለት ነው) ስሜቱ ሁሉ ተለዋወጠ። “…ያኔ “የሸዌዎቹ ገጽታ ተመልክተህ” ወደ “የትግሬው ሰው ገጽታ ፊትህን ዞር” ብለህ ስትመለከት የምትታዘበው የሁለቱ ሰዎች ገጽታ ልዩነት ልክ “የቀን ብርሃን እና የሌሊት ጨለማ የገጽታ ልዩነት” ይታይ ነበር። የደጃች ሐጎስ አሽከር የነበረ አንድ የተምቤን ሰው ይህ ትርኢት ሲመለከት የአፄ ዮሐንስ ሕልፈት ትዝ ብሎት “እንባው” ዘረፍ አደረገ። እውነት ለመናገር እንኳን “የትግራይ የወንዝ ልጅ የሆነ” የአከለ ጉዛይ እና የሐማሴን ሰው ሁሉ እንባ ተናነቀው። … (ታሪኽ ኢትዮጵያ ገጽ ፻፴፬ 134) 1891/ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር 1899/ፈረንጅ ዘመን ደብተራ ፍስሐ ዓብየዝጊ ናፖሊ/ኢታሊያ) (ትርጉም የራሴ፤ ጌታቸው ረዳ )። “…የትግራይ ሕዝብ ወቅቱ ንፍሮ ቆሎ የሚመገብበት እና በተቅማጥ ወረርሺን በሽታ ሲሰቃይ የነበረበት አስከፊ ወቅት ነበር። በወረራው ወቅትም ብዙ ሰው አልቋል። ወደ ትግራይ መሻገራቸውም ከሸዋ ሰራዊቶች መሃል ያልተደሰቱ ነበሩ።….ትግራይ ለምና እንዳመጣቻቸው ትግራይን መራገም ጀመሩ። “የአማራ ወታደር” ወደ አጋሜ ከዚያም ወደ አክሱም ሕዝብ እያጠፉ ለመሸጋገር አልመው ነበርና ፤ የአማራ ወታደር ወደ አጋሜ መሻገር አቀበት ሆነበት። ትግራይን መራገም ጀመሩ። ቋንቋውን ሁሉ መስማት አስጠላቸው። “ይህ እንደዚህ እያለ የራስ መንገሻ በሰላም እጃቸውን መስጠት ‘ደስታ’ ሆነ። በወቅቱ ራስ መንገሻ ዮሐንስ እጃቸው ለአፄ ሚኒልክ ሲሰጡ ራስ አሉላ እጄን ለሸዋ አልሰጥም ሲሏቸው ራስ መንገሻ ዮሐንስ ግን “ሰውና አገር ጠፍቶ እኔ ብቻየን ብቀር ምን ይረባኛል፡ እናንተ ግን የመሰላችሁን ቀጥሉበት፤እኔ ግን ገቢ ነኝ ብለው እጃቸውን ሰጡ።” ካሉ በኋላ ደራሲው በ፰መጋቢት፲፰፹፪ (መጋቢት 8/1882) ራስ መንገሻ ወደ ሚኒልክ ሲገቡ መቀሌ ከተማ የተደረገው ስነ ስርዓት በስፋት ከዘረዘሩ በኋላ፤ ያ አስገራሚ ትርኢት ባጭሩ እንዲህ ሲሉ ያሰቀምጡታል፦ “በ፰መጋቢት፲፰፹፪ (መጋቢት 8/1882) ራስ መንገሻ ወደ ምኒልክ ሊገቡ በመዘጋጀት እንዳሉ ከተነገረ በኋላ አጼው ወዲያ ወዲህ ሳትል በጥዋቱ ነገ በየአለቃህ ተሰልፈህ እንድትገኝ ብለው አዋጅ አስነገሩ። መቀሌ የሚገኙት አጼ ምኒልክ ይህን ካዘዙ በኋላ ጠዋት ጸሐይ ሰትወጣ ሰልፈኛው ከአፄው ደንኳን ጀምሮ በሁለት ረድፍ እንደ ግድግዳ ግራ እና ቀኝ ረዢም ረድፍ በመስራት ይጀምር እና ወደ ታች ራስ ስዩም ይመጡበታል ወደ ተባለው የተምቤን አቅጣጫ ሲደርስ ወደ አራት እና አምስት ረድፍ ሰልፈኛ ግራ እና ቀኝ በረዢሙ በመሰለፍ ረድፍ ያዘ። በዛው ላይ የራስ መንገሻን መልክ ለማየት እየተጋፋ በብዙ የሚቆጠር ሕዝብ እርስ በርሱ እየተጋፋፋ ነበር። “ቀጥሎም ትልልቆቹ ደጃዝማቾች እና ሹሟሙንቶች ወደ ንጉሱ ጃንጥላ ተሰበሰቡ። የንጉሡ ጃንጥላም ተዘረጋ። ከንጉሡ ዱንኳን ጀምሮ በሁለት ረድፍ ግራ እና ቀኝ እንደ ገመድ የተወጠረው የሰልፈኛው ጫፍ የት እንደ ሆነ ለዓይን እስኪያዳግት ድረስ ቀጥ ብሎ በረዢሙ እና በተንጣለለው ሰፈው ሜዳ ወደ ታች የዘለቀው ሰልፈኛ ስትመለከት በግራ እና በቀኝ በተሰለፈው እመሃል ላይ ለራስ መንገሻ ዮሐንስ መምጪያ ክፍት ቦታ ሰርቶ የተንጣለለ የማሳለፊያ ክፍት መንገድ ሰርቷል። “የአማራዎቹ ሠራዊት ብዛት ያኔ ነው ለማየት የተቻለው። ብዛታቸው የመሬት አፈር ያህል ነበር። ከዚያ በኋላ ረፋዱ ላይ ራስ መጡ። ቢያንስ ፼ (10,000) የሚሆን ሠራዊት አስከትለው መጡ። “እሳቸውን ለመቀበል ግራ እና ቀኝ በተሰለፈው ሰራዊት መሃል ለማሃል ሰንጥቀው በመጓዝ ወደ ንጉሡ ድንኳን ደረሱ። አፄ ምኒልክ ድንቅ ሰው ናቸው እና በብዙ አክብሮት ተቀበሏቸው፡መድፍ ተተኰሰ፡ ወዲያውኑ እያንዳንዱ እሳቸውን ለመቀበል የተሰለፈው ሠራዊት በነፍስ ወከፍ የደስታ መግለጫው ጥይት ወደ ሰማይ ተኰሰ። ሰማይ እና ምድር ድብልቅልቁ የወጣ መሰለ። እንዳይጠፉ ታስረው ከነበሩበት በረት ፈረሶች እና በቅሎዎች ማሰሪያቸውን እየነቀሉ እየበረገጉ እንጣጥ እያሉ ሸሹ። “በወቅቱ ራስ መንገሻ በአባታቸው (አፄ ዮሐንስ) ሞት ምክንያት ሐዘንተኛ ስለነበሩ በሰልፈኛው መሃል ሰንጥቀው ሲያልፉ የሐዘን ልብስ ለብሰው ነበር የመጡት። ይህንን ሲመለከት ሰው እንዳለ በሙሉ ምርር ብሎ ሐዘን በሐዘን ሆነ።……” “… በወቅቱ ራስ መንገሻ እጃቸው ባይሰጡ ኖሮ ካሁን በፊት ከታየው ውጊያ በከፋ መልኩ ትግራይን ያጠፏት ነበር። ራስ መንገሻ ከመግበታቸው በፊት አፄ ምኒልክ አጋሜ አውራጃን ለማጥፋት ዝግጅት አድርገው ነበር። የአጋሜ አውራጃም “ከአማራ ጋር ተናንቀን አብረን እንሞታለን እንጂ አይገዛንም” ብለው ዝግጅት አድርገው በየምሽጉ እና ጉራንጉሩ መዋጊያ ቦታ ይዘው ተዘጋጅተው ነበር። “ከደጃች ሥዩም በቀር ከሸዋ ጋር የወገኑት እና ያልወገኑት መኳንንት መሃል መጠኑ ያለፈ ጥላቻ በትግሬዎች አርስ በርስ ይንጸባረቅ ነበር። ይህ ጥላቻ የርስ በርስ ጥፋት ማስከተሉን አይቀሬ እና ትርፍ እንደሌለው ከተገነዘቡ በኋላ ሕዝቡ ካለቀ በኋላ ብቻየን ብቀር ምን ትርጉም አለው በማለት፤ እነ ራስ አሉላን የፈቀዳችሁ አድርጉ ብለው እነሱን ትተው ራስ መንገሻ ዮሐንስ እጃቸውን ለመስጠት ነበር የተገደዱት። (ታሪኽ ኢትዮጵያ ገጽ ፻፵፪-/፻፵፬ 142-144) 1899/ፈረንጅ ዘመን አቆጣጠር ደብተራ ፍስሐ ዓብየዝጊ ናፖሊ/ኢታሊያ) (ትርጉም ጌታቸው ረዳ ለወደፊቱ ከሚታተመው መጽሐፍ የተቀነጨበ)። መደምደሚያ፤ – ደብተራ ፍስሐ የምኒልክን ወታደሮች ለመግለጽ የተጠቀሙት ቃል “የአማራ ወታደር” እያሉ ነው። በዚህ ላሳርግላችሁ፡-ከወያኔዎች ጋር ያልሰመርነው “ሸዋውያን ተጋሩ” እያሉ እኛን ለመሰየም የበቁት እና ሸዋ/እና ትግሬ የሚለው የጥላቻ መነሻ ወያኔዎች ከየት እንደለቀሙት ታሪኩን እንደሚከተለው ከደብተራ ፍስሓ አብየዝጊ ባጭሩ ተመልክቱ። “…… (ምኒልክ) ዓይባ የተባለ ቦታ ከመስፈራቸው በፊት እዚያው ዙርያዋ ሜዳ በከበባት አንድ አምባ በውስጧ የተጠናከሩ ምሽጎች ላይ 7 ትግሬዎች ሆነው የሸዋዎቹን ጦር እና መድፈኛ ገትረው አቆሟቸው። መድፍ ሁሉ ተተኩሶ ፍንክች ማለት አቃታቸው። የአፄው ጋላዎች (በመስለብ) ሱሰኞች ነበሩ እና ሰውን እየሰለቡ መፈከር ጀመሩ። ንጉሡም መሳሪያ ሳይማርክ “ገዳይ“ ብሎ የፎከረ ሰው ወዮለት! በማለት አዋጅ አወጁ። ቢሆንም ስለ ሕልፈተ ትግራይ ልብ ላለው ብዙ አሳዝኗል። እነኚያ የቤገምድር አማራዎች ግን በጣም ይቆጩ እና ያዝኑ ነበር። (ጐንደሬው አማራ ለትገሬው አዛን ፤የሸዋ አማራ ግን ለትግሬው ጨካኝ እየተባለ የሚነገረው የተሳሳተ ይህ አባባል ዛሬም በእነ አቶ አብርሃም ያየህ በተደጋጋሚ ሲጠቀሙበት ተደምጠዋል። አምና ዴሰምበር 2013 ኤርትራን ከድቶ ለጂቡቲ እጁን የሰጠ ‘ሃብቶም ካሕሳይ’ መቀሌ “የዓይደር ህጻናት” በክላስተር ቦምብ ደብድቦ የፈጃቸው ኤርታራዊ ፓይለት መሆኑን እየተወቀ፤ እነ አብርሃም ያየህ ግን “ደብዳቢው የሸዋ አማራ ነው” “የጎንደር አማራ በትግራይ የወንድሞቹ ልጆች አንዲህ አያደርግም” እያሉ ኤርትራዊያንን ላለመወንጀል ሲሉ ድሮ ከእነ ደብተራ ፍስሃ የተረከቡት ትምህርት ዛሬም ሲደግሙት ሰምተናል)። /…የተመራማሪውን የመጨረሻ ክፍል ጽሑፍ በቀጣይ አቀርበዋለሁ።
የትግራይ ብሔረተኞች በአማራ ላይ ያላቸው ጥላቻ ከምን የመነጨ ነው?” ( – የመጨረሻ ክፍል – ጌታቸው ረዳ)
2019-09-02
የትግራይ ብሔረተኞች በአማራ ላይ ያላቸው ጥላቻ ከምን የመነጨ ነው?”
የመጨረሻ ክፍል
ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢ ጌታቸው ረዳ (የኢትዮጵያን ሰማይ አዘጋጅ)
«የማንበብ ችሎታ እያለው ምንም የማያነብ ሰው፥ የማንበብ ችሎታ ከሌለው ሰው እኩል ይቆጠራል!!!»– ኑ ፡ እውነትን ፡ እናንብብ ! |
{የዕለቱ መልዕክት} ይህን ጥናታዊ ፅሑፍ ሀገሩን ኢትዮጵያን የሚወድ ሁሉ፣ ስህተትን ላለመደጋገም የሚሻ ትውልድ ሁሉ፣ ከታሪካዊ ስህተቱ ለመማርና ለመለወጥ የሚፈልግ ሁሉ ደጋግሞ ሊያነበው የሚገባ ፅሑፍ ነው። መልካም ንባብ። በድጋሚ ጥብቅ ቅድመ-ንባብ ማሳሰቢያ፦ የዚህ ጥናታዊ ፅሑፍ አቅራቢ ብዙዎቻችን በቲቪ መስኮት የምናውቀው የወያኔው ጌታቸው ረዳ አይደለም። ይሄኛው የምርምር ፅሑፍ አቅራቢ ጌታቸው ረዳ ሌላ የተከበረ ምሁር ነው። /ጌታቸው ረዳ …ካለፈው የቀጠለ/ ወደ ደብተራ ፍስሃ ትረካ ልቀጥል…. “…በዛች አምባ መሽገው ብዙ “የሸዋ ሰራዊት” የገደሉት 7 የትግራይ ተዋጊዎች መከላከላቸውን ቀጠሉ። ምሽጉ በድንጋይ በደምብ የተገነባ ሆኖ ከአፋፉ ምሽግ ደጃፍ ላይ ወራሪዎቹን በዘዴ ለመሳብ ሆን ብለው ሰዎቹ አስቀድመው እህል እና ጓዝ እቃ ከምረውበታል። ሲተኰስባቸው ዝም ብለው አድፍጠው ይቆዩ እና “አማራዎቹ” እየተጠጉ እህሉን እና እቃውን ዓይተው ለመጎተት ወደ ዳገቱ ጫፍ ሲጠጉ የጥይት ዶፍ በማውረድ ከገደሉ ወደ ታች እየወደቁ ብዙ ሰው ጎዱባቸው። “ይህ እንደሰሙ ንጉሡ ወደ ስፍራው በመሄድ ሲመለከቱት አብሯቸው የነበረ ‘ኢልግ’ የተባለ የኢስፏፀራ መድፈኛ መድፉን አነጣጥሮ ዳገቱ ላይ የተገነባው ምሽግ ላይ በመተኮስ አፈራረሰው። ከዚያ በኋላ ነፍጠኞቹ ነፍጣቸውን ወደ ታች ጣሉት። ንጉሡም ደግ ሰው ነበሩ እና “ተው አትቶኩስባቸው” በማለት እንዳይተኩስ አገዱት። “ከዚያ በኋላ ንጉሡ 7ቱ ታጣቂዎች በራሳቸው መታጠቃቸው ብዙ አዘኑ። ወዲያውኑ ከአካባቢው ዙርያ ከመሸጉ ባንደኛው አምባ ላይ አስተማማኝ ቦታ ላይ ሆኖ ወደ ታች ሜዳ ድምፁን ከፍ አድርጎ አንድ የትግሬ ሰው ንጉሡን እንዲህ አላቸው፦ “አንተ ሸዌ እንተዋወቃለን እኮ! የማንተዋወቅ እንዳይመስልህ። አሁንም አንላቀቅም። ዮሐንስ ቢሞት እኛ ወጣት ልጆቹ የሞትን እንዳይመስልህ! አላቸው።” /- ደብተራ ፍስሐ ጊዮርጊስ ዓብየዝጊ – ታሪኽ ኢትዮጵያ 1899/ፈረንጅ ዘመን፤ የእጅ ፅሑፍ፤ ናፖሊ/ኢታሊያ)፤ ገፅ ፻፴፱-፻፵-(139-140) ፤ ትርጉም (የራሴ) ጌታቸው ረዳ:: ከዚህ ፓተርን/አነጋገር/ቅሬታ/ቁጭት ወይንም ዛቻ “ለእነ መለስ ዜናዊ እና መሰሎቹ” ምን የባሕሪ ለውጥ እና ግንዛቤ እንዳስተላለፈባቸው ግንዛቤ መውሰድ የናንተ ይሆናል። በእኔ በኩል የትግራይ ብሔረተኞች በአማራ ላይ ያላቸው ጥላቻ ከምን የመነጨ የሚለውን ለማመላከት መነሻ መጋረጃውን ከምንጩ ገልጬ እንድታዩት አድርጌአለሁ። ሃታተየን በዚህ መደምደሚያ ላጠቃልለው። ወያኔዎች ወደ በረሃ ከወጡ በኋላም ሁላችሁም እንደምታውቁት ለማመጻቸው መነሻ ያደረጉት እና በይፋ በጽሁፍ የገለጹት ዋናው ምክንያታቸውም የሚከተለው እንደነበር ታስታውሳላችሁ። የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ድርጅት መግለጫ የካቲት ወር 1968 ዓ.ም. ገጽ 15-16 እጠቅሳለሁ፦ “የትግራይ ህዝብ ለረዢም ዘመን ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቱ ተነፍጐ ሲጠላ እና ሲናቅ እንዲሁም አድልዎ ሲደረግበት ቆይቷል። ይህ በደል ጨቋኝዋ የአማራ ብሔር ሆነ ብላ የመንግሥት መመሪያዋ አድርጋ ስትሰራበት የቆየች ሲሆን… የ ፫ሺ ዓመታት የሚያኮራ ታሪክና ባህላችን መመኪያቸውና መፎከሪያቸው ሆኖ ይገኛል። ይህ የታሪክ ስርቆት በአንድ በኩል የአማራው ብሔር መፎከሪያ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ትግራይ ህዝብ ‘ታሪክ እንደሌለው’ ህዝብ እንዲያስቆጥረው የተደረገ የመንግሥት መመሪያ ነው። የትግራይ ሕዝብ ክብሩና መብቱ እስኪመለስለት ድረስ ትግሉ አያቋርጥም። ጨቋኝዋ የአማራ ብሔርም ጭቆናዋ እስካላቆመች ድረስ ሕብረተሰብዓዊ ዕረፍት አታገኝም።” (ምንጭ:- የወያኔ ገበና ማህደር፤ ገጽ 21፤ ደራሲ – ጌታቸው ረዳ)። ከላይ እንደተመለከታችሁት ለትግራይ ሕዝብ በባሕል፤ በታሪክ ባለቤትነት፤ በምጣኔ ሃብት እና ስነ መንግሥታዊ አስተዳደር እየተዳከመ መምጣት ወይንም የተጠቀሱ እሴቶች “ባለቤትነት መነጠቅ” ምክንያት “ጨቋኝዋ የአማራ-ብሔር” እንደሆነች ወያኔ በማያሻማ አገላለጽ አስቀምጦታል። ለዚህም ማንኛውም የትግራይ ተወላጅ ዋነኛ ጠላት አድርጎ መመልክት ያለበት “አማራ” እንደሆነ ካስቀመጠ ላይቀር የአማራው ህልውና ክር እና ድሩ ከኢትዮጵያ ጋር የተያያዘ ነው ብሎ ስለሚያምን ኢላማ ውስጥ በማስገባት “ኢትዮጵያን” በጠላቻ እይታ መነፅሩ ክብ ወግቷታል። “የአማራ ጥላቻው ከኢትዮጵያ ጋር አያይዞታል” ስል ምን ማለቴ ነው? ወደ ዋናው ማኒፌስቷቸው ስንመለከት አሁንም የሚጦቁመው ‘ጨቋኝዋ ብሔር” (አማራ) ኢትዮጵያ የምትባል አገር የተፈጠረቺው “በጨቋኝዋ ብሔር በአማራው፤ በተለይም በሸዋው አማራ በምኒልክ” እንደሆነ አስቀምጦታል። ሰለዚህ ኢትዮጵያን የፈጠረ ምኒሊክ “አማራው እና የአማራ ወታደር” የትግራይ ጠላት ስለሆነ የፈጠራት ኢትዮጵያም ከአማራው ባሕል፤ ከአማራው ታሪክ (ምንም እንኳ አማራው የራሱ ታሪክም ባሕልም ስለሌለው ከትግራይ “የተሰረቀ” ባሕልና ታሪክ እያራመደ ነው ብሎ ቢወነጅለውም) በአአጠቃላይ ከአማራው ጋር በመያያዙ “ኢትዮጵያ” የምትባል “የጨቋኝዋ ብሔር” (የአማራው) አገር ስለሆነች፤ የወያኔ ላዕላይ ግቡ የትግራይ ሕዝብ ከጠላቱ እና ከጨቋኝዋ ብሔር/አገር ለመነጠል “አብዮታዊ ትግል” (ወያኔያዊ ትግል) በማካሄድ “…ከባላባታዊ ስርዓትና ኢምፔሪያሊዝም ነፃ የሆነ” “የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ማቋቋም” እንደሆነ በ1968 ያሰራጨው ጽሑፍ አረጋግጦልናል። ስለዚህም የትግራይ ብሔረተኞች ለአማራ ጥላቻቸው መነሾው ከላይ በ“ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ” በግልጽ እንደተቀመጠው አብዛኛዎቹ የትግራይ ብሔረተኞች ነባር እና ወጣት ምሁራን ከዚህ የህወሓት ቅስቀሳ እና እንደዚሁም ከድሮ ከመሳፍንቶች እና በትዕቢት የተወጠሩ የአካባቢው ባላባቶች ሲያንጸባርቁት የነበረው፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፈ፤ ንጉሳችን ቢሞት “እኛ ልጆቹ” አልሞትንም፤ “እንተያያለን” የሚለው በዘመነ ምኒልክ ትግራይ ውስጥ ሲያስተጋቡት የነበረውን የወቅቱ የገጠር ጐሰኛ ወጣት ብሔረተኞች ፉከራ ከስንት አመት በሗላ “በዝግታ ሲከማች ከነበረው የቂም ግምጃ ቤት” በ1935 እና በ1967 ዓ.ም ይፋ ሆኖ “ንጉሳችን ቢሞት እኛ ልጆቹ አልሞትንም” የሚለው “ጸረ አማራ” (“ጸረ ሸዋ”) ጥላቻ የመነጨበት መነሻው ይህ ነው። “በይኩኖ አምላክ፤ በዘርዓ ያዕቆብ እና ከዚያም አማራዎች ወይንም የአማራ ንጉሦች ብለው በሚጠሯቸው በምኒልክ እና ሃይለስላሴ የተፈጠረቺው ኢትዮጵያ የምትባል አገር” ትግሬዎችን በድላለች በማለት ይህ መጠኑ ያለፈ የትግሬ ብሄረተኞች በአማራ ሕብረተሰብ ህልውና እና ቋንቋው ላይ ጥላቻቸው አስተጋብተውበታል። መረን ያለፈ ጥላቻቸው ለማረጋገጥ ሲሉ “ትምህርት ቤት ውስጥ በአማርኛ መናገር እና ድንጋይ መወርወር የተከለከለ ነው” ሲሉ በትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ አውጇል። ዛሬ የትግራይ ምሁራን እነ ፍስሃ ሀብተጽዮን እና እነ ዶ/ር አለምሰገድ አባይ እና ብዙዎቹ የመሳሰሉት “አማርኛን ከብሔራዊ ቋንቋነት ለማስወገድ” በእንግሊዝኛ መተካት አለበት እያሉ ይሟገታሉ። “Tigrayan Modern Elites and their bizarre Love for Colonial Language” በሚል መልስ የጻፍኩትን ብታነቡ ለአማርኛ ቋንቋ ሳይቀር ጥላቻቸው ምን ያህል መስመር እንደዘለለ መመልከት ትችላላችሁ። ዛሬ ስልጣን ከተቆጣጠሩ ከ1983 ዓ.ም በሗላም በሽግግሩ መንግሥት ወቅት አብረውት ሥልጣኑን ከተቀራመቱት የጐሳ ቡድኖች ጋር ተረባርበው በአማራው ሕብረተሰብና “አማራዎች የፈጠሯት ሰንደቃላማ” በሚሏት አርማችን ላይ ያደረሱት የጥቃት ርብርቦሽ ስናጤን “ጨቋኟ የአማራ ብሔር ሕብረተሰባዊ ሰላም አታገኝም” በማለት በማንፌስቷቸው የዘረጉትን ዛቻ እና ቂም በቀል ስንመረምረው፤ ምንጩ ከላይ በመረጃ ያስቀመጥኩት መነሻ አድርገው ነው። በኔ በኩል ዋቢ አድረጌ ያቀረብኩት ለማግኘት አስቸጋሪ የሆነ፤ በብዛት ለሕዝብ ያልተሰራጨ እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ1891 በእጅ ጽሑፍ የተጻፈ ጣሊያን አገር የተገኘ የትግርኛ መጽሐፍ እና ሌሎች መረጃዎችን ዋቢ አድርጌ ያቀረብኩትን የትግራይ ብሔረተኞች ለአማራ ያላቸው ትምክሕተኛ የጥላቻ መነሻቸው አንድታውቁት አድርጌአለሁ። ማስረጃውየን የመቀበል እና ያለመቀበል ግን የናንተ ድርሻ ነው። በጥሞና ስላዳመጣችሁኝ አመሰግናለሁ። ጌታቸው ረዳ (የኢትዮጵያን ሰማይ ድረገጽ ብሎግ አዘጋጅ) getachre@aol.com ———0—————– (ሙሉ ጥናታዊ ጽሑፉን በpdf ከዚህ ላይ ያንብቡ) https://welkait.com/wp-content/uploads/2014/07/የትግራይ__ብሔረተኞች_በአማራ_ላይ_ያለቸው_ጥላቻ_ከምን_የመነጨ_ነው.pdf ምንጭ ወ ምስጋና ፦ ይህ የጥናታዊ ጽሑፍ በካሊፎረኒያ ስቴት በሳን ሆዘ ከተማ በሃያት ሪጀንሲ ሳንታክላራ ሆቴል በሰኔ 26/2006 (July 3/2014) በሞረሽ ወገኔ የአማራ ሲቪክ ማሕበር በተዘጋጀው ሕዝባዊ ስብሰባ በአቶ ጌታቸው ረዳ የቀረበ ነው። ለሀቅ አንገቴን እሰጣለሁ ብለህ የቆምክ፥ አንተ ታላቅ የሀገሬ ምሁር፥ አንተ ኦሪጂናሉ ጌታቸው ረዳ፦ በአክብሮትና ምስጋና ከፊትህ ዝቅ ብዬ እጅ ነሳሁ! አሰፋ ሃይሉ ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ።መልካም ጊዜ።Filed in:Amharic