ለሠላምና መረጋጋት መስፈን የፖለቲካ ኃይሎች ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋቸዋል – ፕሮፌሰር መረራ
ኢዜአ – ሠላምና መረጋጋት እንዲመጣ የፖለቲካ ኃይሎች የሚጋጩ ሕልሞቻቸውን አስቀምጠው ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚያስፈልጋቸው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩና ፖለቲከኛው ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ገለጹ።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ጉልህ ስፍራ ያላቸው ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ሠላም ሊረጋገጥ የሚችለው በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ መስማማት ሲኖር እንደሆነ ይናገራሉ።
“ስብሰባ ስለበዛ ሠላም አይረጋገጥም” የሚል አቋም ያላቸው ፕሮፌሰር መረራ ብሔራዊ መግባባትን የሚያመጣ ተግባር መፈጸም እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።
በተደጋጋሚ በሚካሄዱ ስብሰባዎች የራሱን የሚናገር እንጂ የሌላውን የሚያዳምጥ ተሳታፊ እንደሌለ ጠቁመውይህ ደግሞ የሚፈለገውን ሠላም ሊያመጣ እንደማይችል አክለዋል።
መግባባት ሳይኖር የሚወጡ ፖሊሲዎችም ከአንድ ቀውስ ወደሌላ ቀውስ የሚያሸጋግሩ በመሆናቸው ብሔራዊ መግባባት ቅድሚያ ማግኘት ይገባዋል ባይ ናቸው።
ሠላምና መረጋጋት፣ ዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደርና ልማት እንዲመጣ የፖለቲካ ኃይሎች የሚጋጩ ሕልሞቻቸውን አስቀምጠው ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚያስፈልጋቸውም ተናግረዋል።
የአገሪቱን ችግር ለመፍታት የፖለቲካ ኃይሎች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ የገለጹት ፕሮፌሰሩ ይህግን “ኪሳቸው ውስጥ የፖለቲካ ድርጅት ተሸክመው የሚሄዱትን አይመለከትም” ብለዋል።
በሂደቱ መሳተፍ ያለባቸው ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ ያላቸው የፖለቲካ ኃይሎች መሆን እንዳለባቸው በመጠቆም።
ወደስልጣን ለመምጣት የሚደረገውን ጥረት የሰለጠነ ማድረግ ሠላምን እንደሚያረጋግጥ ተናግረው፤ በጉልበት ስልጣን መያዝና ጉልበተኛ ሲመጣ ከስልጣን መውረድ ማብቃት እንዳለበት መክረዋል።
ይህን ሁኔታ የመቀየር ሂደት የተለየ ቀመር የሌለው በመሆኑ የሰለጠነ ፖለቲካ ለማራመድ የፖለቲካ ኃይሎች መወያየትና መተማመን ላይ መድረስእንዳለባቸውም አመልክተዋል።
በሕዝብ ፍላጎት ላይ ያልተመሰረተና ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ የሚተገበር አሰራር ቢዘረጋ መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ የቀውስ አዙሪት ውስጥ የሚያዳክር በመሆኑ የሕዝብን ፍላጎት ማክበር ተገቢ እንደሆነ አስገንዝበዋል።