September 7, 2019
Source: https://fanabc.com

አዲስ አበባ ፣ ጳጉሜን 2 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 74ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።
ምክር ቤቱ በሆርቲካልቸር፣ የቁም እንስሳት እና ቆዳና ሌጦ ዘርፎች ግብይትን በተመለከተ በአስፈጻሚ አካላት ስልጣንና ተግባር አዋጅ ላይ ለውጥ ለማድረግ በተዘጋጀ ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቷል።
በዚህም ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ተሰጥተው የነበሩ የሆርቲካልቸር ዘርፍ ልማትና ግብይትን የተመለከቱ ስልጣንና ተግባራት ለግብርና ሚኒስቴር እንዲሰጡ ወስኗል።
እንዲሁም ለግብርና ሚኒስቴር ተሰጥተው የነበሩ የቁም እንስሳት የቆዳና ሌጦ ግብይትን የሚመለከቱ ስልጣንና ተግባራት ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዲሰጡም ተወስኗል።
ከዚህ ባለፈም በሰላም ሚኒስቴር በቀረበውና በሳይበር ሰራዊት ማፍረሻ ረቂቅ ደንብ ላይም ተወያይቶ ረቂቅ ደንቡ ተግባራዊ እንዲሆን ውሳኔ አሳልፏል።
ኢንስቲቲዩቱ እንዲያከናውናቸው የተዘረዘሩ ተግባራት በሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሊከናወኑ የሚችሉ መሆኑና በኢንስቲቲዩት ደረጃ መቋቋሙና ትምህርትን በዚህ ደረጃ መስጠቱ ሃገሪቱ ላይ የበጀት ጫና የሚፈጥር መሆኑ ለኢንስቲቲዩቱ መፍረስ ምክንያት ነው ተብሏል።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በቀረበውና የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የገቢ ማስገኛ ድርጅቶችን ለማስተዳደር በተዘጋጀ ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ ማሻሻያ በማከል እንዲጸድቅ መወሰኑን ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በመጨረሻም ምክር ቤቱ በማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር በቀረቡት አባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማህበር ከፍተኛ ደረጃ የሸክላ አፈር፣ የጂፕሰም እና ላይምስቶን ማዕድን ማምረት ፈቃድ ስምምነቶች ላይ በመወያየት ስምምነቶቹ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል እንዲፈረሙ ይሁንታ ሰጥቷል።