September 10, 2019
በጅማ ከተማ አንድም የተቃጠለ ቤተክርስቲያን የለም– የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን

በጅማ ከተማ በሃይማኖት ሽፋን ብጥብጥ ለመፍጠር ሲደረግ የነበረው እንቅስቃሴ ሊከሽፍ መቻሉን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
በከተማው በሃይማኖት ሽፋን ክልሉን እና ሀገሪቱን ለማመስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አካላት በሕዝቡ እና በፀጥታ ኃይሎች ድጋፍ ሴራቸው ሊከሽፍ መቻሉን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ከፍያለው ተፈራ ገልፀዋል።
ወቅታዊ ሁኔታን በማስመልከት ለሚዲያዎች መግለጫ የሰጡት ኮሚሽነሩ፣ እነዚህ አካላት “በጅማ ከተማ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተቃጠለ” በሚል የሐሰት ወሬ ሕዝቡን በመቀስቀስ ብጥብጥ ለመፍጠር እና ክስተቱም ወደሌሎች ከተሞች እንዲስፋፋ በተቀናጀ መንገድ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር አብራርተዋል።
በጅማ ከተማ አንድም የተቃጠለ ቤተክርስቲያን እንደሌለ የገለጹት ኮሚሽነር ከፍያለው፤ ሕብረተሰቡ ከእንደዚህ ዓይነት ሐሰተኛ ወሬዎች ራሱን እንዲጠብቅ እና ለሀገር ሰላም ዘብ ሊቆም እንደሚገባ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ምንጭ: የኦሮሚያ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ