September 12, 2019

“ባሳለፍነው ወርም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተቃጣው ሃይማኖትን የመከፋፈል ሴራ ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው እና መንግስት ከእምነቱ ተከታዮችና ከመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመሆን በጋራ ልንመክተው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ”

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ የ2012 አዲስ ዓመት ዋዜማ ልዩ ዝግጅት መልዕክት

ሙሉ መልዕክቱን ያንብቡት

የተከበራችሁ የአማራ ክልል ህዝቦች፤
የተከበራችሁ መላው የአገራችን ህዝቦች፤
ክቡራን የሃይማኖት አባቶች፤
የተከበራችሁ የፌዴራልና የክልል የስራ ኃላፊዎች፤
የተከበራችሁ የዞን፣ የከተማ፣ የወረዳና የቀበሌ አመራሮች፤
ክቡራን የባህር ዳር ነዋሪዎች፤
ክቡራን ጥሪ የተደረገላችሁ ምሁራንና ባለሃብቶች
ክቡራትና ክቡራን

በቅድሚያ ሁላችንንም እንኳን ከዘመን ዘመን በሰላም አሸጋገረን፡፡ መልካም አዲስ ዓመት፤ እንኳን አደረሳችሁ አደረሰን ለማለት እወዳለሁ፡፡ በዚህ አይነቱ ለየት ባለ ሁኔታ በተዘጋጀ የአዲስ ዓመት ዋዜማ ዝግጅት ተገኝቼ መልዕክት ማስተላለፍ በመቻሌ የተሰማኝ ደስታ እጥፍ ድርብ መሆኑን እየገለፅኩ ‹‹ማቅ አውልቀን፤ ግምጃ እንልበስ›› በሚል መሪ ሃሳብ በተዘጋጀው በዚህ የዋዜማ ክብረ በዓል ላይ ጥሪ ስናስተላልፍላችሁ ፈቅዳችሁ የአዲስ ዓመት ዋዜማ ክብረ በዓላችን ተካፋይ ለመሆን በመምጣታችሁ በክልሉ መንግስት፣ በህዝቡና በራሴ ስም ላቅ ያለ ምስጋናዬን እያቀረብኩ የአማራ ክልል ርዕሰ መዲና ወደ ሆነችው ውቢቷ ከተማችን ባህር ዳር እንኳን ደህና መጣችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡

ክቡራትና ክቡራን፡-
ኢትዮጵያ የፍጥረታት ሁሉ መነሻ ምድረ ቀደምት፣ የጥንታዊ ታሪክ ባለቤት፣ የገናና ስልጣኔ አምባ፣ የአኩሪ ተጋድሎ እና ድል ባለቤት ሀገር ስትሆን ኢትዮጵያዊነት ደግሞ የኩራት ምንጭ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የኩራት ምንጭ ነው ስንል ሀገሪቱ ጥንታዊነት እና የገናና ስልጣኔ ባለቤት የነበረች መሆኑ ብቻ ሳይሆን የበርካታ ውብ ባህሎች ሀገር በመሆኗም ጭምር ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን ባሕሎች ዘርፈ ብዙ እና ውቦች ናቸው፡፡ ከባሕላችን መገለጫዎች መካከል አንዱ የበዓል አከባበር ስርዓታችን ነው፡፡ በዓላት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ልዩ ቦታና ትርጉም አላቸው፡፡ በተለያዩ በዓላቶቻችን እንደ ሕዝብ ትዝታችን ተጽፎባቸዋል፤ ህብረታችን ታትሞባቸዋል፣ ማህበራዊ ትስስራችን ተገምዶባቸዋል፤ ተስፋችን ተበስሮባቸዋል፡፡ የዘመን መለወጥን ማብሰሪያው የአዲስ ዓመት በዓልም ሁላችንም ኢትዮጵያውያን በጋራ የምናከብረው፤ ከከረምንበት ጭጋጋማ ብርዳማ ክረምት፣ ተስፋን ወደምትፈነጥቀው የጸደይ ፀሀይ፤ ማብሰሪያ ወቅት የሚከበር በመሆኑ፤ ልዩ ስሜት ይሰጣል፤ ለዚህም ነው ብዙዎቻችን የአዲስ ዓመት በዓል ትዝታ የሚናፍቀን፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ የተገነባችበት ሁኔታ፤ እንደ ታሪኳ ሁሉ ረዥም ጊዜ የፈጀ፣ በጥልቅ ጥበብ የተበጀ ነው፡፡ ይህቺ ድንቅ አገር የተገነባችው በቅድመ አያቶቻችን ብርቱ ታታሪነት፣ደም እና አጥንት ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር እና ክብሯን ለማስጠበቅም፤ የአማራ ክልል ሕዝቦች ከሌሎች እህት እና ወንድም ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ሳይሰስቱ ፊት ለፊት ግንባራቸውን ሰጥተዋል፡፡ ለዚህም ቅዱስ ተግባራቸው ለዘላለም ስናከብራቸው፣ ስናመሰግናቸው እና ስንመካባቸው እንኖራለን፡፡
ዓለም የሚመሰክረው እኛም የምናውቀው ሀቅ የአማራ ክልል ሕዝቦች መነሻ እና መድረሻቸው፤ የኢትዮጵያ ጥንካሬ እና ታላቅነት ነው፡፡ ይህም ዕውን የሚሆነው፤ በሁሉም የኢትዮጵያውያን ሕብር እና እኩልነት እንደሆነ በጽኑ ያምናሉ፡፡ የአማራ ክልል ሕዝቦች፤ በኢትዮጵያ አገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የተለያዩ ፈተናዎችን አልፈዋል፡፡ በተለይም ኢትዮጵያን ለማፍረስ የፈለገ ጠላት ሁሉ፤ የመጀመሪያ ኢላማ አድርጎ ግፍና መከራ የሚያደርስበት፣ ባህሉን ለማጥፋት የሚረባረብበት፤ ወጉን ለማኮስመን የሚታትርበት የአማራ ክልል ሕዝቦችን ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህ የሆነበት አበይት ምክንያ የአማራ ክልል ሕዝቦች ለኢትዮጵያ እና ለህብረ ኢትዮጵያዊነት ቀናኢ በመሆናቸው ነው፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ለመካድና ለመርሳት ወይንም ለመጥራት እና በውስጣቸው ለመኖር መስጋት፤መጠራጠር፤ መዘንጋት ለሚሹ አካላት ከላይ የጠቀስኳቸውን የኩራት ምንጮች የሆኑ ውብ የአባቶቻችን ባህል፣ ወግ፣ ወኔና ጀግንነት አለማወቅ፤ ወይንም እያወቁ ሆነ ብሎ ማጥፋት በመሆኑ የእንዲህ አይነት አባዜ የተጠናወታቸው አካላት ሁሉ፤ በአዲሱ ዓመት ፈጣሪ ቅን ልቦና እንዲሰጣቸው እንመኛላቸዋለን፡፡

ክቡራንና ክቡራት፡-
ባለፉት በርካታ ዓመታት በመጣንበት ጉዞ ውስጥ ያጋጠሙ ፈተናዎች እና ሳንካዎች እጅግ ብዙ እና ውስብስብ ቢሆኑም ከፊሉን ተገዳድረን እያለፍን ብዙውን ግን በአሸናፊነት እየተወጣን እዚህ ደርሰናል፡፡ በየጊዜው ያጋጠሙንን ፈተናዎች እንዴት ማለፍ እንደቻልን ልምድ እና ተሞክሮ ያለን ህዝቦች ስለሆን፤ ባለፉት ጊዜያት በአገራችን በተለይም በክልላችን ያጋጠሙንን ፈተናዎችም፤ በአሸናፊነት መወጣት ጀምረናል፡፡ ችግር ሲያጋጥመን እንዴት መፍታት እንዳለብን የተማርነው፤ ከቀደምት አባቶቻችን ነው፡፡ እኛ የጠበብት አባቶች ልጆች ነን፡፡ አይደለም በጥንታዊቷ ይቅርና በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እንኳ የኢትዮጵያንም ሆነ የአማራን ሕዝብ በእጅጉ ህልውናውን የሚፈታተኑ፣ አያሌ ጉድጓዶች ተምሰዋል፡፡ ይሁንና፤ በፈተና ወቅት ወደ ኋላ መንደርደር ማለት ለባለ ራዕይ ወደ ፊት እንዴት እንደሚያስወነጭፍ አባቶቻችን አስተምረውናል፡፡ እኛም የአባቶቻችን ልጆች ነንና፤ ዛሬም ብዙ የችግር አረንቋዎች አልፈን እዚህ ደርሰናል፡፡ አበው እንደሚሉት ችግር ሲገጥመው የሚደነግጥ ከዚህ ቀደም ያለ ችግር የኖረ ሰው ነው፡፡ በብዙ ችግር ያለፈ ሰው ግን የሚያጋጥመውን ፈተና በብቃትና በአሸናፊነት ይወጣዋል፡፡ እኛም እንደ ሕዝብ የብዙ ተግዳሮቶች ውል የሚፈታበትን ጥበብ የያዝን ስለሆነ ባለፈው ጊዜ በክልላችነ አጋጥሞን የነበረውን አስጨናቂና ከባድ ጊዜ ተቋቁመን ይኸው እዚህ ደርሳል፡፡ ይህ ክስተት ያደረሰብን የህይወት የንብረትና የስነ ልቡና ጉዳት ከባድ ቢሆንም በደረሰብን ሀዘን እየቆዘምን እንደ ዶሮ አንገት ደፍተን መሬት ስንጭር የምኖር ደካሞች አይደለንም፡፡

ክቡራንና ክቡራት፡-
አጋጥሞን የነበረው ጉዳት ጥልቅ ሀዘን ውስጥ ቢያስገባንም ለሕዝባችን ስንል ከሀዘን ቶሎ መውጣት ነበረብን፡፡ ሀዘን ማብዛት ትረፉ የበለጠ ለችግር መጋለጥ ነው፡፡ መሪ በደስታ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በሀዘን ጊዜም ጭምር ሕዝቡን እየመራ ማሻገር አለበት፡፡ በሀዘን በመቆዘም የምናተርፈው ነገር የለም፡፡ የሚሻለን የወንድሞቻችንን ህልም እውን ማድረግ ነው፡፡ ስለሆነም ያጋጠመን ጉዳት ወደ ባሰ ችግር ሳይሸጋገር ከሕዝባችን ጋር ሆነን በጥበብ በመወጣት ከማቅ ወደ ግምጃ ከምንሻገርበት ቀን ደርሰን፤ ይኸው ዛሬ በእናንተ ፊት ግምጃ ለብሰን መቆም ችለናል፡፡
የማያሳፍረንና የማያሳንሰን የክልላችን ሕዝብ፤ ከጎናችን ሁኖ ስለደገፈን በሕዝባችን አይዞህታ ተረጋግተንና ተበረታተን፤ ይኸው ዛሬ ማቅ አውልቀን ግምጃ ለብሰን ለተጨማሪ ተስፋ እና ድል ወደ መጪው ብሩህ ዓመት እንሸጋገር ዘንድ ቆርጠን ተነስተናል፤ አዲሱን ዓመት ስንቀበል ከሕዝባችን ጋር ጣትና ጥፍር ብቻ ሳይሆን ደምና የደም ስር ሆነን የምናከናውናቸውና ውጤት የምናስመዘግብባቸው በርካታ ተግባራት ሰንቀናል፡፡ በአዲሱ ዓመት “ማቅ አውልቀን ግምጃ እንለብሳለን” ስንል ከመቼውም ጊዜ በላቀ መንገድ ለሁለንተናዊ ልማትና ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንሰራለን ማለታችን ነው፡፡
በአትክልት እና ፍራፍሬ እንዲሁም የእንስሳት ሀብት ላይ ያተኮረ በመሆኑ የአመጋገብ ስርዓታችንንም ለማሻሻል ይረዳናል፤ ሰላማችሁን ነቅታችሁ ጠብቁ፡፡ አዳዲስ የአሰራር ዘዴዎችን ጠቃሚነት ተረድታችሁ ተግብሩ፡፡ የመንግስት ድጋፍ በመጪው አመት ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ አደራ የምላችሁ ነገር ትርፍ አምርቱ፤ እናተ እያላችሁ ክንዳችሁ ሳይዝል ኢትዮጵያውያን መራብ የለባቸውም፡፡
እናንት የአማራ ክልል ምሁራን፡- የክልላችንን ኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን ለመደገፍ የምሁራን ሚና የማይተካ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ስለሆነም የክልሉን ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ እንድትደግፉ ፣ችግር ፈቺ የሆኑ ጥናት እና ምርምሮችን እየሰራችሁ ፣ሳይማር ያስተማረ ወገናችሁን ወደ ብልጽግና ለማሻገር፣የመፍትሔ አካል ሆናችሁ እንድታገለግሉና የማህበረሰብ አገልግሎት ኃላፊነታችሁን በተግባር እና በቅርበት እንድትወጡ ጥሪ አቀርብላችኋለሁ፡፡
የክልላችን ባለሀብቶች፣ ዳኞች፣ የፍትህ እና የጸጥታ አካላት፣የመንግስት እና የግል ዘርፍ ሙያተኞች፣የሚዲያ አካላት፣ የሲቪክ ማህበራት፣ባለጥበቦች፣የማህበረሰብ አንቂዎች፣ተማሪዎች በጥቅሉ ሁላችሁም ወገኖቻችን በየተሰማራችሁበት ሙያ በኃላፊነት መንፈስ ፣ በንጹህ ሰብዕና፣በተቆርቋሪነት እና በቁጭት ለሰላም፣ለዕድገት እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ታገለግሉ ዘንድ ጥሪ አቀርብላችኋለሁ፡፡ በምታደርጉት ህግ እና ስርዓትን የተከተለ እንቅስቃሴያችሁ ሁሉ ለሚያጋጥማችሁ ተግዳሮት የክልሉ መንግስት በየትኛውም ቦታና ሰዓት ከጎናችሁ መሆኑን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡

ክቡራት እና ክቡራን፡-
የአማራ ህዝብ ከጥንት ጀምሮ በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢዎች በብዛት እንደሚኖር ይታወቃል፡፡ ተጋብቶ እና ተዋልዶ እንደጠፍር አልጋ ከሁሉም ጋር ተጋምዶ ይኖራል፡፡ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሜ ጥሪ ማቅረብ የምፈልገው ለመላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የአማራ ህዝብ በየአካባቢያችሁ የሚኖረው አንድም ሀገሩ ስለሆነ እንደ ኢትዮጵያዊነቱ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እናንተ ወንድሞቹ እና እህቶቹ ስለሆናችሁ፣ እንደ ትናንቱ ነገም አብራችሁ ተሳስባችሁ በፍቅር እንደትኖሩ፣ በመካከላችሁ የሚገባውን አሜካላ ጊዜ ሳትሰጡ እንድትነቅሉ እያሳሰብኩ ከእናንተ በላይ ስለእናንተ መስተጋብር የሚያውቅ እና የሚረዳ የሌለ መሆኑን ተረድታችሁ በቆዬው የኢትዮጵያዊነት መንፈስና ስሜት በሰላም እንደትኖሩ ጥሪዬን አቀርብላችኋለሁ፡፡

ክቡራን እና ክቡራት
እናንት የምወዳችሁ እና የማከብራችሁ የአማራ ክልል ህዝቦች፤ ዛሬ በዚህ ልዩ ‹‹የማቅ ማውለቂያና ግምጃ መልበሻ ቀን›› በአዲሱ አመት የሚኖረኝ የመልዕክት ማሰረጊያ የሚከተለው ነው፡፡ ኑ የተስፋችንን ጥጥ በጋራ እንዳምጠው፣ በአንድነት እናዳውረው፣ በህብረት እንፍተለው፣ በሕብራዊነት እናቅልመው፣ በፍቅር እንሸምነው፣ በያገባኛል ስሜት እንስፋው፣ በባለራዕይነት እንቋጨው፣ ኑ የጋራ የሰላምና እድገት ግምጃችንን በጋራ እንልበሰው፡፡ የእኛ ተስፋ እኛው ራሳችን እንጂ ማንም የሚሰጠን ወይም ማንም የሚነሳን አይደለም፡፡
በመጨረሻም ለዚህ የደመቀ፣ የአማረ እና የተሳካ የበዓለ ዋዜማ የሃሳብ ጠንሳሾች እና በዝግጅቱ ላይ ለተሳተፋችሁ አካላት ሁሉ በክልሉ መንግስት፣ ህዝብና በራሴ ስም ላቅ ያለ መስጋናዬን አቀርብላችኋለሁ፡፡

በድጋሚ እንኳን ለ2012 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል ከመላው ቤተሰቦቻችሁና ወዳጅ ዘመዶቻችሁ ጋር በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን፡፡

መጭው ዘመን የሰላም፣ የፍቅር፣ የመቻቻል፣ የብልፅግናና የአንድነት ዓመት ይሁንልን!

አመሰግናለሁ

AMMA