September 12, 2019

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢ ሕ አ ፓ )
Ethiopian People’s Revolutionary Party (EPRP)

No photo description available.

ለ2012 የኢትዮጵያዊያን አዲስ ዓመት ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ከተደመረው ኢሕአፓ) የተሰጠ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት

አዲስ ዓመት በየጊዜው በወርሀ መስከረም ሲመጣ ሁልጊዜም ምድራችን በክረምት በነበረው ዝናብ ለምልማና ፍሬ አፍርታ እንዲሁም በአበቦች አጊጣ ስትታይ የሰው ልጅ በደስታና በተስፋ የሚሞላበት እጅግ ደስ የሚያሰኝ ወቅት ይሆናል፡፡ በዚሁ መንፈስ የኢትዮጵ ያ ህዝብም የ2012 አዲስ ዓመትን በደስታና በተሰፋ ስሜት በዓሉን ያከብራል፣ ፈጣሪውንም ያመሰግናል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ(ኢሕአፓ) ለዚህ የደስታ እና የተስፋ በዓል የኢትዮጵያን ህዝብ እንኳን አደረሳችሁ ! ይላል፡፡

ኢትዮጵያ በአለፈው የ2011 ዓ.ም. ከፍተኛ በሆነ ፈተና ውስጥ አልፋለች፡፡ በርካታ ህዝብ የተፈናቀለበት፣ የሞተበት እና ክፋትና ጥላቻ ያጠለለበት ዓመት ነበር፡፡ የሀገራችን ዋነኛ የፓለቲካ ችግር በአንድ ወገን ሀገራችንን በብሄር/በቋንቋ ለመበታተን የተነሱ ጽንፈኞች ከምንጊዜውም በላይ ስጋት መሆናቸው ነው፡፡ በሌላ በኩል መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለሀገራዊ አንድነቱና ዴሞክራሲያዊ መብቱ ከፍተኛ ትግል እያደረገ ነው፡፡

በ2011 ከአጋጠመን የሰላም ማጣት ብዙ ልንማር ይገባል፡፡ የሰላም ዋጋው ስንት ነው ብለን ጠይቀን፣ መልሱ መለኪያ የሌለው እጅግ ውድ መሆኑን መናገር ለቀጣዩ አዲስ ዓመት ለሰላም ለመታገል ያነሳሳናል፡፡ የሰላም ማጣት መነሻዎችና መፍትሄዎች ምንድናቸው ብለን ጠይቀን፣ አለመቻቻል፣ጥላቻ፣ ጭቆናና የህግ የበላይነት ያለመከበር ናቸው ብለን አነዚህን ምክንያቶች ነቅስን አውጥተን መታገል ይኖርብናል፡፡

ኢሕአፓ በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ ሀገር ቤት ከገባ እነሆ 1 ዓመት ሊሞላው ነው፡፡ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ የፓርቲውን መዋቅሮች በመላው ኢትዮጵያ ለማዋቀር ጥረት ተደርጓል፡፡ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥም ኢትዮጵያ ውስጥ በአለፉት 27 የህወሀት የአገዛዝ ዓመታት በተዘራው የዘረኝነትና የጥላቻ እንክርዳድ ምክንያት ሀገራችን የፖለቲካ ቅርቃር ውስጥ ገብታለች፡፡

ኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ ገና የዛሬ 47 ዓመት አገር ሲመሠረት ያነሳቸው የዴሞክራሲ፣ የሕዝባዊ መንግሥት፣የመሬት ላራሹ እና የነጻነት ጥያቄዎች እስከ አሁን ያልተመለሱ በመሆኑ እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ማለት ሀገራችንን ከድህነት ለማውጣትና ዓለም ወደ ደረሰበት ብልጽግና ለማድረስ ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ስለሆነም የፓርቲያችንን ዓላማዎች ይዘው የሚቀጥሉ ወጣቶች በፓርቲው ዙሪያ እየተሰባበሰቡ መሆኑ አስደሳች ነው፡፡ የፓርቲው አመራር በመስዋዕትነት የደመቀውን የፓርቲውን ዓላማዎች ለወጣቱ ለማስረከብ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ነው፡፡
በአዲሱ ዓመት ኢሕአፓ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆን ትግሉን ይቀጥላል፡፡ ህጋዊ አቋሙን የምሥረታ ጉባዔ በማድረግ ህልውናውን ያረጋግጣል፡፡

አዲሱ ዓመት ለሀገራችን የሰላም፣ የዴሞክራሲና የነጻነት፣ የጤና እንዲሆን ኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ መልካም ምኞቱን ይገልጻል፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርካት!