September 12, 2019 – BBC Amharic

የሥነ ህዋ ተመራማሪዎች በአንዲት ፕላኔት ላይ ውሃ ማግኘታቸውን ይፋ አድርጉ።
ከመሬት ውጪ በፕላኔት ከባቢ አየር ላይ ውሃ ሲገኝ ይህ የመጀመሪያው መሆኑን ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል።
• ናሳ ህዋ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ወንጀል ተፈጸመ አለ
• ኢትዮጵያ ሳተላይት ማምጠቅ ለምን አስፈለጋት?
ግኝቱን በበላይነት የመሩት ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጂኦቫንያ ቲኔቲ፤ K2-18b የተባለችው ፕላኔት ላይ ውሃ የመታየቱን ዜና “እጅግ ድንቅ” ብለውታል።
“በፕላኔት ላይ ውሃ ስናገኝ ይህ የመጀመሪያው ነው። ሙቀቱም የሰው ልጅ ሊኖርበት ከሚችለው የሙቀት መጠን ጋር የሚመጣጠን ነው” ብለዋል።
K2-18b የተባለው ፕላኔት ከመሬት 650 ሚሊየን ማይል ይርቃል። ከመሬት ሥርዓተ ጸሐይ ውጪ ያሉ ፕላኔቶች ኤክሶፕላኔት ይባላሉ።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2020 ይሠራል ተብሎ በሚጠበቅ ቴሌስኮፕ፤ ፕላኔቷ ላይ ሕይወት ባላቸው ነገሮች የሚወጣ አየር ስለመኖሩ እንደሚፈተሽ ተመራማሪዎች ገልጸዋል።
“በህዋ ውስጥ ያለነው የሰው ልጆች ብቻ ነን? የሚለው በሳይንስ ውስጥ ካሉ ጥያቄዎች ዋነኛው ነው” ሲሉ ፕሮፌሰር ጂኦቫንያ ተናግረዋል።
የምርምር ቡድኑ ግኝቱ ላይ የደረሰው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2016 እስከ 2017 በሚገኙት ወራት በተደረገ ጥናት ነው። ከK2-18b ክፍል 50 በመቶው በውሀ የተሸፈነ እንደሆነ የሚታመን ሲሆን፤ ምናልባትም ለሰው ልጆች ምቹ መኖሪያ ልትሆን እንደምትችል መላ ምቶች አሉ።
ፕላኔቷ ከመሬት ሁለት እጥፍ የምትበልጥም ናት።