15 ሴፕቴምበር 2019

የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዕምነት ተከታዮች በተለያዩ ከተሞች ሰልፍ እያካሄዱ ነው።
ደሴ፣ ጎንደር እና ደብረ ታቦር ከተሞች በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ኃይማኖት ተከታዮች ሰልፍ ከተካሄደባቸው ከተሞች መካከል ተጠቃሾቹ ናቸው።
የሰልፉ ተሳታፊዎች በቤተክርስቲያኗ፣ በኃይማኖት አባቶች እና በምዕመኖቿ ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ይቁም የሚል መልዕክት ይዘው ወጥተዋል።
• ሁለት መልክ ያለው የጅግጅጋ የአንድ ዓመት ክራሞት
• “የክልሎች ልዩ ኃይልን በተመለከተ ውይይት ያስፈልጋል” የሶማሌ ክልል ም/ፕሬዝደንት
ቢቢሲ ያነጋገራቸውና በደሴ ከተማ የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ ሲያስተባብሩ የነበሩት አቶ ሙሉጌታ አሰፋ እንደነገሩን ሰልፉ መነሻውን ከደሴ ፒያሳ በማድረግ ከሁሉም አጥቢያ ቤተክርስቲያን የተወጣጡ ምዕመናን የተለያዩ መፈክሮች እያሰሙ ወደ ደሴ መስቀል አደባባይ ጉዞ አድርገዋል።
”በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ቤተ-ክርስቲያን ያቀጠሉ እና ምዕመናንን የገደሉ ለፍርድ ይቅረቡ፣ መንግሥት ቤተ-ክርስቲያንን ሊያከብር ይገባል” የሚሉና ሌሎችም መፈክሮች ሲሰሙ እንደነበር አቶ ሙሉጌታ ነግረውናል።
የደሴው ሰላማዊ ሰልፍ ጠዋት 12 ሰዓት አካባቢ የተጀመረ ሲሆን ቀትር 6 ሰአት ላይ ተጠናቋል።
አስተባባሪው እንደሚሉት በሰላማዊ ሰልፉ ላይ በግምት እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ከ150 ሺ እስከ 200 ሺ የሚደርሱ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች የተሳተፉ ሲሆን ”ያለምንም የጸጥታ ችግር መጠናቀቁን ማረጋጋጥ እፈልጋለው ብለዋል” አቶ ሙሉጌታ።
”በሃገር አቀፍ ደረጃ በእምነቱ ተከታዮች ላይ እና በአብያተ ክርስቲያናት ላይ ከሚፈጸመው በደል ባለፈ በከተማችንም ብዙ ጥያቄዎች አሉን” ብለዋል።
”በደሴ ከተማ ህጋዊ የሆነ ካርታና ሌሎች እንደ ግንባታ ፍቃድን የመሳሰሉ ሰነዶች ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት ግንባታቸው ተከልክሏል። ህጋዊ እስከሆንን ድረስ መከልከል የለብንም። መንግስትም አፋጣኝ ምላሽና የህግ ከለላ ያድርግላቸው” የሚሉ መፈክሮች መሰማታቸውን አስተባባሪው ይናገራሉ።
ምዕመኑ ጥያቄውን ሰላማዊ በሆነ መልኩ ስላቀረበ መንግስት ቢቻል በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ምላሽ እንዲሰጥ መጠየቃቸውንም አቶ ሙሉጌታ ነግረውናል።
• “ህዝብ ከህዝብ ሊጋጭ አይችልም” አቶ ሽመልስ አብዲሳ
ሌላኛው ያነጋገርናቸው የደብረታቦር ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ደሳለኝ አባተ በበኩላቸው ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ቅዳሴ ከጨረሱ በኋላ ምዕመኑ ከየአቅጣጫው ወደ መስቀል አደባባይ ማምራቱን ነግረውናል።
” የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለሃገሪቱ ያበረከተችውን ከግምት ውስጥ በማስገባትና አስተዋጾዎችዋ ተጠብቀው እንዲቀጥሉ በቤተክርስቲያኗ እና በእምነቱ ተከታዮች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት መንገስት በአስቸኳይ ያስቁም” የሚል መልዕክት በአስተባባሪ ኮሚቴው በኩል መቅረቡን አቶ ደሳለኝ ይናገራሉ።
አቶ ብርሃኑ አየሌው ደግሞ የጎንደር ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስቲያኖች ሕብረት ጸሃፊ እና የሰልፉ አስተባባሪ ሲሆኑ፤ ዛሬ በጎንደር ስለተከናወነው ሰልፍ ለቢቢሲ ሲናገሩ “ቤተክርስቲያንን ማቀጠል ኢትዮጵያን ማቃጠል ነው!፣ ቤተ-ክርስቲያን ላይ የሚደርሰው ትንኮሳ በአስቸኳይ ይቁም፣ መንግሥት የቤተክርስቲያንን ደህንነት ማረጋገጥ አለበት፣ የተቃጠሉ አብያተ-ቤተክርስቲያናትን መልሶ መገንባት ይኖርበታል። ለተጎዱም ካሳ መክፈል አለበት” የሚሉ መከክሮች ተሰምተዋል።አቶ ብርሃኑ ዛሬ ረፋድ በጎንደር በተካሄደው ሰልፍ ላይ ከአንድ መቶ ሺህ በላይ ምዕመናን ተሳታፊ ነበሩ ያሉ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓትም “ምዕመኑ በዝማሬ፣ በእልልታ እና በሽብሻቦ ወደየመጣበት አቅጣጫ እየተመለሰ ነው” በማለት በጎንደር እየተካሄደ የነበረው ሰልፍ በሰላም መጠናቀቁን ነግረውናል።