-
Phone: 251 944 223 216 e-mail: eprp@eprp-ihapa.com
ቅጽ 47፣ ቁጥር 2 ጳጉሜን 2011 ዓ. ም
ለውጡ የት ገባ?
የዛሬ አንድ ዓመት ተኩል ድፍን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊባል በሚችል ደረጃ፣ ለውጡንና ለውጡን የሚመራውን ኃይል ደግፈው የዘመናት ስቃያቸው ማብቂያው አድማሱ ላይ እየታያቸው፣ ተስፋን በመሰነቅ ደስታቸውን የገለጹበት ወቅት ነበር። የለውጡ ኃይል ኢትዮጵያዊነትን አግንኖ ከፍታ ላይ ሲያስቀምጥ፣ ከለውጥ ኃይሉ በፊት ገዥ የነበረው በራሱ አንደበት “የበሰበስኩ” ያለው ህወሓት/ኢህአዴግ ኢትዮጵያዊነትን ምን ያህል ያዋርድ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታ መሆኑም ጭምር ነበር ደስታውን እጥፍ ድርብ ያደረገው።
የለውጥ ኃይሉ አከታትሎ በወሰዳቸው እርምጃዎች (የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት፣ ከውጭ ወደ ሀገር እንዳይገቡ የታገዱ ድርጅቶችን እገዳቸውን ማንሳት፣ ፀረ–ዴሞክራሲ የነበሩ ሕግጋትን መለወጥ መጀመሩ…ወዘተ) ከራሱ ዜጎች አልፎ የውጭ አገር መንግሥታትም በከበሬታ እንዲያዩትና ተስፋ እንደጣሉበት ታይቶ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት በተቃዋሚ ፓርቲዎች ሲገፋ የነበረው የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋምና ይኸው አጭር ዕድሜ ያለው መንግሥት ህገ–መንግሥታዊ ጉባዔ ሰይሞ አብዛኛው ሕዝባችን የሚስማማበት አዲስ ህገ–መንግሥት እንዲረቀቅና ምርጫ ተደርጎ ቋሚ መንግሥት እንዲመሠረት የሚል ነበር።
ምንም እንኳን የሽግግር መንግሥት አስፈላጊነት በብዙዎች ዘንድ ታምኖበት የነበረ ቢሆንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋግመው ያነሱትን ኢትዮጵያዊነትና የወሰዷቸውን እርምጃዎች ግምት ውስጥ በማስገባትና የእሳቸውን በአደባባይ “እኔ አሸጋግራችኋለሁ” ማለትን ተከትሎ እሳቸው አሽጋጋሪ እንዲሆን ያልተጻፈ ስምምነት ላይ የተደረሰ መሰለ።
በእርግጥ ማንኛውም ለውጥ መንገዱ አልጋ በአልጋ እንደማይሆን በሰው ልጅ ታሪክ የታዩት መንግሥታዊና ኅብረተሰባዊ ለውጦች ቋሚ ምስክሮች ናቸው። በተለይም አብዮታዊ ተብለው የሚታወቁ ለውጦች፣ ለምሳሌ እንደ ፈረንሳይና የሩሲያ አብዮቶች ያሉት ኅብረተሰቡን ያናጉና መንግሥታዊ ታቋማትን ከመሠረቱ የለወጡ ናቸው። የ1966 አብዮት ተብሎ የሚታወቀው የእኛም አገር አብዮት የገጠር መሬትን ላራሹ ከማወጅ ባሻገር፣ ደርግ ባደረገው ከፍተኛ ኢ–ሰብዓዊ ጭፍጨፋ ለአንድ ትውልድ እልቂት ምክንያት ሆኗል። ምናልባትም ከነዚህ ከአገራችንና ከውጭም ከተገኙት አሉታዊ የአብዮት ተመክሮዎች በመነሳት በአገራችን እየታየ ያለው የለውጡ ኃይል የመረጠው ጉዞ ዘገምተኛ ከሚባሉት ለውጦች ውስጥ የሚመደብ ነው። ዘገምተኛ ለውጥ ከአብዮታዊ ለውጥ የሚለየው፣ ስሙ እንደሚያመለክተው፣ ዘገምተኛ መሆኑና በለውጡ ሳቢያ የሚወሰዱት እርምጃዎችም ሥር–ነቀል ሊባሉ የማይቻላቸው፣ በአንፃሩ ግን ጥቂት የማይባል የሰው ሕይወትና ንብረት የሚጠፋበት ሂደት መሆኑ ነው። በፍልስፍና ላይ ተመሥርቶ አብዮታዊ ወይም ዘገምተኛ ለውጥ ከመምረጥ ባሻገር፣ የኢትዮጵያው የለውጥ ኃይል ዘገምተኛ ለውጥ ለመምራት የተገደደው የለውጥ ኃይሉ ራሱ የወጣው ከዚያው ከጨቋኙ ገዥ ፓርቲ እቅፍ ከኢህአዴግ ውስጥ በመሆኑም ጭምር ነው።
ዘገምተኛ ሆነ አብዮታዊ ለውጥ ግቡን ለማሳካት ስትራቴጂና ታክቲክ እየነደፈ ለውጡን በሃዲዱ ላይ ማስኬድና ማራመድ ይጠበቅበታል። በተለይ ዘገምተኛ ለውጥ፣ አደብ የመግዛትና ጊዜን በአግባቡ የመጠቀም ፋታ ስለሚያገኝ፣ ለውጡን በሃዲዱ ላይ ለማቆየትና የለውጡን ደጋፊ ቁጥር እያበረከተ የመሄድ ሰፊ ዕድል አለው። ከዚህ አንፃር ሲታይ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድንና የአጋሮቻቸውን የለውጥ ጉዞ ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ስንመረምር፣ ምንም እንኳን ዘገምተኛ ለውጥን የተከተለና ፋታ የማግኘት ዕድልን ሊጠቀም ይችል የነበረ ቢሆንም፣ በአግባቡ ስላልተደረገ ዛሬ በሚያሳዝን ሁኔታ ያ ሁሉ ድጋፍ እንደ ጤዛ ረግፎ ወደ ተቃውሞ ተለውጧል ባይባልም፣ አብዛኛው ዜጋ በለውጡ አካሄድና በለውጥ ኃይሉ ግራ ተጋብቷል ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ይህ የሀገራችን ሁኔታ አንድ ዶክተር የበሽተኛውን ህመም ከምልክቶቹ በመነሳትና ምርመራ በማድረግ በሽታውን ለይቶ እንደሚያውቀውና ለበሽታው ፈውስ እንደሚሰጥ ሁሉ እኛም ሳይንሳዊ መንገድ ተከትለን የለውጥ ኃይሉንና የለውጡን ጉዞ እንዲህም የገጠመውን ችግር በመተንተን፣ እንደ ተቆርቋሪ ዜጎች የመፍትሄ ሃሳባችንን እናቀርባለን። ለመሆኑ
የሀገራችን ሁኔታ ምን ይመስላል?
1. የለውጥ ኃይሉ መነሻውንና መዳረሻውን (ፍኖተ–ካርታ የሚባለውን) እስካሁን ለማቅረብ አለመቻሉ አንዱ ችግር ነው። በራሱ ውስጥ ይህ ፍኖተ–ካርታ ሊኖረው ይችላል፣ ይህን ራዕዩን ግን ለለውጥ ደጋፊው ሕዝብ ባለማካፋሉና ለውጡ የኔ ነው የሚል ዜጋ በርካታ ዜጎችን ባለማፍራቱ አብዛኛው ሕዝብ ከዳር ሆኖ ግራ በመጋባት እየተሞከረ ያለውን የቅልበሳ ሙከራ ከንፈር በመምጠጥና ተስፋውን በማሟጠጥ የሚታዘብበት ሁኔታ ተፈጥሯል። የለውጥ ኃይሉ ራዕይና ፍኖተ–ካርታ ካለው ለምን ለሕዘብ እንደማያቀርበው ግምቶች ቢኖሩንም ከግምት ያለፈ ዋጋ ስለማይኖራቸው ዘርዝሮ ማቅረቡ ጠቀሜታ የለውም።
2. የለውጥ ኃይሉን የገጠመው የመጀመሪያ ፈተና በአዲስ አበባ አካባቢ (ቡራዩ፣ ለገጣፎ፣ ሱሉልታ፣ ሰበታ…ወዘተ) የተደረገው፣ ኦሮሞ ባልሆኑ ኢትዮጵያውያን ላይ ያተኮረ የሚመስል የቤት ማፍረስና የማፈናቀል ህገ–ወጥ ድርጊት ነበር። በአመዛኙ ተፈናቃዮቹና ነፃው ሚዲያ ባደረጉት ርብርቦሽ የቤት ማፍረሱ ሂደት የቆመ መስሎ ነበር። ከስድስት ወራት በኋላ ነሃሴ 2011 ላይ ሂደቱ እንደገና ቀጥሏል። ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለመፈናቀሉ ተጠይቀው ስለ ሁኔታው አለማወቃቸውን መናገራቸው፣ በሕዝቡ ዘንድ ትልቅ አግራሞት ፈጥሮ እንደነበረ ይታወሳል። አሁን ደግሞ አዲስ የፀረ–ቤት ማፍረስ ሕግ ወጥቷል፣ የክልል መሪዎች ያላፀደቁት መፈናቅልም አይኖርም ተብሎ፣ ነሃሴ ላይ በማን ፈቃድ ቤቶችን ማፍረሱ እንደቀጠለ መታወቅ አለበት። መቆምም አለበት። ኢሕአፓ እንደ ሶሽያል ዴሞክራቲክ ፓርቲ፣ የዜጎች ፍትኅ መጓደል ያንገበግበዋል፣ ዜጎችን ተለዋጭ መጠለያ ሳይሰጡ ማፈናቀል ሕገ–ወጥ እንዲሆንም ይታገላል።
3. በአዲስ አበባ ዙሪያ የተጀመረው መፈናቅል፣ ወደ ክልሎችም ገፍቶ “መጤ”ና “ተወላጅ” በሚል ጎሠኝነትን ማጠየቂያ ባደረገ አሳፋሪ የሕዝብ መፈናቀል እስከ ሦስት ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎቻችን በሶማሌ/ኦሮሚያ፣ በጌዲኦ/ኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል/አማራ…ወዘተ፣ የዓለምን ክብረወሰን በሰበረ ደረጃ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፣ የሞቱም አሉ። ምንም እንኳን አሁን አብዛኞቹ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው የተመለሱ ቢሆንም፣ የአገሪቱ ጎሠኛ ሕገ–መንግሥት እስካልተለወጠ ወይም እስካልተሻሻለ ድረስ፣ አዳዲስ መፈናቀሎች እንደሚከሰቱ፣ ሲዳማን አዲስ ክልል ለማድረግ በሚደረገው ትርምስ እየተጎዱ ያሉትን ሲዳማ ውስጥ የሚኖሩትን ሲዳማ ያልሆኑ ብሄረሰቦች ማየቱ በቂ ነው።
4. የለውጥ ኃይሉ የጀመረው የዴሞክራሲ ምህዳሩን ማስፋት ጅምር እየቀጠለ አይደለም። በዚህ ረገድ ምርጫ ቦርድ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የጋራ ምክር ቤት አቋቁሞ ሁሉም ባለድርሻዎች በጋራ የሚወስኑበት ሂደት ገና ከጅምሩ ፈተና ጥሞታል። ገዥው ፓርቲ በቅርቡ በፓርላማ ያስፀደቀው የምርጫ ሕግ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አካሄድ የጋራ ምክር ቤቱን እሰጥ አገባ ውስጥ የከተተ ሲሆን፣ የለውጡን ደጋፊም ያሳዘነ ሂደት ሆኗል። በተጨማሪም የነፃ ሚዲያ መበረታታት ሲገባው አንዳንድ ጋዜጠኞችን ማስፈራራትና ፍርድ ቤት በመውሰድ ማንገላታት ጋዜጠኞች ራሳቸው ላይ ማዕቀብ/ሳንሱር ወደ ማድረግ እንዳይገፉ ሥጋታችንን እንገልፃለን።
5. በኦሮሚያና በትግራይ ክልሎች ውስጥ ያሉት ሁኔታዎች በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይነት አላቸው። እነዚህ ሁለት ክልሎች ያሉበትን ሁኔታ በዝርዝር ማየቱ ለለውጡ ከመስመሩ መውጣት ግዙፍ ማስረጃ ይሆናል። በኦሮሚያ፣ እንደ ትግራይ ሙሉ በሙሉ ፖለቲካው ለተቃዋሚዎች የተዘጋ አይደለም፣ ቢያንስ የኦሮሞ ድርጅቶች ከሞላ ጎደል በአንፃራዊ ነፃነት ይንቀሳቀሳሉ። ኅብረብሄር ድርጅቶች ግን ኦሮሚያ ውስጥ መንቀሳቀስ ሊታስብ ፈፅሞ አይቻልም። ቄሮ የተባለ ቡድን ውስጥ በኢ–መደበኛ አደረጃጀት የተሰለፉ ወጣቶች በድብደባና በማስፈራራት የተሞከሩ ስብሰባዎችን በትነዋል። ትግራይ ራሱን የቻለ አገር እስኪመስል ድረስ ሌላ ተቃዋሚ ጨርሶ የለም። የፖለቲካ እስረኞችም የፌዴራል መንግሥቱ ባደረገው
ምህረትና በሌሎች ክልልሎች እንደተፈቱት፣ በትግራይ መፈታታቸው አጠራጣሪ ነው።
የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የለውጡ ኃይል የወሰዳቸውን ዴሞክራሲያዊ እርምጃዎች እግር በእግር እየተከታተለ አንድ በአንድ እየተቃወመና ተቃውሞ እያደራጀ መጓዙ የአደባባይ ሚስጥር ነው። የለውጥ ኃይሉ የህወሓትን ሸርና ተንኮል ዓይቶ እንዳላየ መሆኑ፣ ይህ ለውጥ ሲበዛ ሊቀለበስ፣ ሲያንስ ደግሞ በቋሚነት ሲታወክ እንደሚኖር ማስረጃው ፍንትው አድርጎ ያሳያል።
በወንጀል ተጠርጥረዋል ብሎ ፍርድ ቤት የእስር ትዕዛዝ ያወጣባቸው ተጠርጣሪዎች ከሕግ በላይ በመሆን ትግራይ ውስጥ መሽገው የአገሪቱን ከፍተኛ የሕግ አካል አንቀበልም ብለው መቀመጥ ከፌደራል መንግሥቱ ያፈነገጠ የመንግሥት አካል መኖሩን ያሳያል።
ይህ ደግሞ ነገ ሌሎች ክልሎች እንዲያደርጉት የሚያበረታታ ሂደት ነው። ኦነግ ወደ ሀገር ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ለውጡን ሲያሰናክል ቆይቷል። ምዕራብ ወለጋ ውስጥ ባንኮችን ዘርፏል፣ ንፁሃን ዜጎችን ገድሏል። የለውጡ ኃይል ሲያቸንፈው የኦነግ አመራር አዲስ አበባ ቁጭ ብሎ ትግላችን ሰላማዊ ነው ብሎ፣ ነገር ግን ሸኔ የተባለው ጦረኛ ድርጅት በእሱ ዕዝ ሥር እንዳልሆነ አውጆ፣ ለውጡን በጦር ሳይሆን በፖለቲካ (በፖለቲካ ሳይሆን በጦር ለማለት ነው?) ማድማት ቀጥሏል። በኦሮሚያ አክቲቪስት የተባሉ ባለሙሉ ሥልጣን የለውጥ አደናቃፊዎች ለውጡን እንዳሻቸው ሲቃወሙ፣ የለውጥ ኃይሉ እስካሁን በዝምታ እየተመለከታቸው ይገኛል።
ይህ የለውጡ ኃይል ዝምታ ለለውጡ ደጋፊ ኢትዮጵያዊ ምንን ያሳያል? እንግዲህ ትግራይና ኦሮሚያ ውስጥ ያለው ዝግ የፖለቲካ ሁኔታ እንደዚህ እየታየ ነው አገራዊ ምርጫ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ይካሄዳል እያለ ኢህአዴግ ምርጫውን ለማሸነፍ የሚዘጋጀው።
6. አዲስ አበባ – አምስት ያህል የኦሮሞ ድርጅቶች (ገዥውን ፓርቲ ኦዴፓን ጨምሮ) ከአንድ ዓመት በፊት “ኦሮሚያ አዲስ አበባ ላይ ያላትን ልዩ ጥቅም በጋራ እናስከብራለን” የሚል የጋራ መግለጫ ካወጡ በኋላና የአዲስ አበባንና የኦሮሚያን ድንበር የሚያካልሉ የሁለቱም ወኪሎች የኦዴፓ አባላት በመንግሥት መሾማቸው ሲታወቅ፣ ይህንን አካሄድ የሚቃወም በነእስክንድር ነጋ የሚመራ “የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት” የተባለ የሲቪክ ድርጅት ተመሠረተ።
የለውጥ ኃይሉም ለኦሮሞ አክቲቪስቶች የሚያሳየውን ትዕግስት ለነእስክንድር ማሳየት አቃተው። ቄሮ የተባለው የወጣቶች ቡድን እነእስክንድር አዲስ አበባ ውስጥ ስብሰባ እንኳን እንዳያደርጉ ማወክ ቀጠለ። በመጨረሻም፣ ጥቂት የእስክንድር ባልደረቦች ሰኔ 15 ባህር ዳር በተፈጠረው የአዴፓ አመራር ግድያ ጋር በተያያዘ “በሽብርተኝነት ጠርጥሬያቸዋለሁ” ብሎ መንግሥት በቁጥጥር ሥር አዋላቸው። የነእስክንድርን እንቅስቃሴ የማይደግፉ እንኳን በመንግሥትና በቄሮዎች እነእስክንድር ላይ የሚደርሰውን ወከባ ይቃወማሉ። በሰላማዊ መንገድ እስከታገሉ ድረስ መደራጀታቸውን ይደግፋሉ። ቀላል የማይባል በተለይ የአዲስ አበባ ኗሪና ለውጥ ደጋፊ፣ በነእስክንድር ላይ በሚወሰደው ኢ–ፍትሃዊ እርምጃ ምክንያት ለውጡን በጥርጣሬ እንዲያይ ተገዷል።
7. በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሕግ የበላይነት ሲደፈር፣ የለውጥ ኃይሉ ዝምታን በመምረጡ ብዙ የለውጥ ደጋፊዎች “ሕግ ይከበር” እያሉ በለውጥ ኃይሉ ላይ ማማረር ያዙ። “በሕግ አምላክ!” ብሎ ሕግን የማክበር የዘመናት ልምድ ያለው
ሕዝባችን መንግሥታዊ ድጋፍ በሌለበት ሁኔታ በጨዋነት እየተረዳዳ ይህን ክፉ ጊዜን ለማሳለፍ ችሏል። የለውጥ ኃይሉ ከብዙ ትችት በኋላ ሕግን ማስከበር መጀመሩ ቢያስደስተንም አሁንም ክፍተቶች ስላሉ መሙላትን ይጠይቃሉ።
8. የሰኔ 15ቱ ግድያ በለውጡ ደጋፊዎች ላይ ብዥታ የፈጠረ ክስተት ነው። በባህር ዳር ከተማ የአዴፓ ባለሥልጣኖች ሲገደሉ፣ አዲስ አበባም ሁለት ጄኔራሎች (ኤታማዦር ሹሙን ጨምሮ) መገደላቸውንና ሙከራውም “መፈንቅለ መንግሥት” እንደነበረ መንግሥት አስታወቀ። የግድያው አቀናባሪ ጄነራል አሳምነው ፅጌ (እሱም የተገደለ) እንደሆነ መንግሥት ገልጾ፣ በተከታታይ ቀናት የአብንን ጥቂት አመራሮችና ደጋፊዎችን በቁጥጥር ሥር አዋለ።
በብዙ ሰዎች ዘንድ የሰኔ 15ቱ ክስተት ከመለሳቸው ይልቅ ያስነሳቸው ጥያቄዎች የተበራከቱ ናቸው የሚል ግምት እንዲኖራቸው አደረገ። በተለይም በአማራ ክልል ውስጥ ብዙ ሊባሉ የሚችሉ ሰዎች በመንግሥት ላይ ጥያቄ አነሱ። በመንግሥት በኩል በሌሎች ቦታዎች፣ ለምሳሌ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ልክ እንደ አማራው ክልል እስርና እርምጃ መውሰዱን በሚገባ ስለማይገልጽ፣ የአማራ ክልል ነዋሪዎች በእነርሱ ላይ ብቻ የተነጣጠረ ማሳደድ እንደሆነ አድርገው ያዩታል። በለውጡ ላይ እምነት የነበራቸው ዜጎች እምነታቸው እየተሸረሸረ የሚሄድበት ሁኔታ በመፈጠሩ፣ መንግሥት ስለጉዳዩ እርስ በርሱ የሚጣረስ መግለጫ ከመስጠት ይልቅ፣ ጉዳዩን፣ በተለያዩ ክፍሎች እንደተጠየቀው፣ በገለልተኛ ቡድን ተጣርቶ ውጤቱ ለሕዝብ ቢቀርብ፣ መንግሥትንና ሕዝብን የሚያቀራርብ ድርጊት ይሆን ነበር። ከዚህ ጋር በተያያዘ “በሽብርተኝነት” የተከሰሱ፣ በርካታ ዜጎች “ቀድሞ ወያኔ እንደሚያደርገው የውሸት ክስ ምሥረታ እየተመለስ ነው” ማለት ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ በሚባልም ህወሓት፣ በይፋ አዴፓ ላይ “የትምክህት” ክስ አሰምቶ፣ ከአዴፓ ጋር አብሮ መሥራትም እንደሚቸገር ገለፀ።
አዴፓም ለዚህ የአፀፋ መልስ በመስጠት ህወሓት በአማራ ክልል ውስጥ ሰላም የሚነሱ የአሻጥር ሥራዎችን በተደጋጋሚ መሥራቱን አዴፓ መረጃ እንዳለው ይሁን እንጂ ለሰላማዊ ኑሮ ብሎ በማሰብ ይፋ እንዳላደረጋቸው ገልጾ፣ ህወሓት ፈውስ ሊያገኝና ሊማር የማይችል ድርጅት ነው በማለት ምላሽ ሰጥቶ ሁለቱ ድርጅቶች በአደባባይ ተዘላልፈዋል።
9. ሌላው የለውጥ ደጋፊውን ያቀዛቀዘ ክስተት፣ በፊት የነበረው የህወሓት የበላይነት አሁን በኦዴፓ የበላይነት ተተክቷል የሚል እምነት በሕዝቡ ውስጥ በሰፊው መኖሩ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይህ ክስ ትክክል እንዳልሆነ ደጋግመው ቢያስረዱም፣ ክሱ በቀላሉ የሚሄድ አልሆነም። በማስረጃነትም አንዳንዶቹ በሚሠሩበት መሥሪያ ቤት ውስጥ የታዘቡትን በአሃዝ አስደግፈው ሲያቀርቡ (ለምሳሌ ከጉምሩክ የቀረበውና መሥሪያ ቤቱን በስጋት የለቀቀው ዜጋ) በሽብርተኝነት ተከስሶ እስር ቤት ውስጥ ይገኛል። ሌሎች ደግሞ ያገሪቱን መረጋጋትና ሰላማዊ ኑሮ በሚያውኩትና በአደባባይ የምንፈልገውን በጉልበታችን እናመጣዋለን እያሉ በሚፎክሩት በነጃዋር ዓይነቶቹ ላይ እርምጃ አለመወሰዱን ለዚህ ማስረጃ አድርገው ያቀርባሉ።
የኦዴፓ የተለያዩ መዋቅሮች በተለያየ ጊዜ እንዳመኑት የከተሞችን የሕዝብ ስብጥር ቁጥር ለመለወጥ ከስደተኛ ሠፈራ ጣቢያ የሚመለሱ ኦሮሞዎች በከተሞች እንዲኖሩ የመታወቂያ ካርድ ከመስጠት እስከ ሌሎች እገዛዎች እንደሚደረግላችው ተነግሯል። የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ ለሌላቸው ወጣቶች ሥራ ለመፍጠር በሚሰጠው የብድር ድጋፍ ብሄረሰብን መሠረት ያደረገ አድሎ ተስትውሏል የሚል ክስ መኖሩም ይህን ጥርጣሬ አጠንክሯል።
10. የህወሓት አመራር የለውጡ ግምባር ቀደም ተቃዋሚ ሆኖ በፊታውራሪነት መሰለፉ የአደባባይ ሚስጥር ነው። የኢትዮጵያን ሕዝብ በስፋት የመዘበሩና ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈፀሙ እንደ ጌታቸው አሰፋ ዓይነት ተፈላጊ ወንጀለኞችን “ያሉበትን አላውቅም” በማለት የፌዴራል መንግሥቱም ለፍርድ እንዳያቀርባቸው ተከላካይ ከመሆን ጀምሮ፣ ሲያሻው ደግሞ ሲረግጠው የነበረው ህገ–መንግሥት ድንገት ትዝ ብሎት “ህገ–መንግሥቱ ይከበር፣ ፌዴራሊዝማችን ይከበር” እያለ የአዞ እንባ የሚያነባ ድርጅት ሆኗል። በተያያዥም የፌዴራል መንግሥቱ ያፀደቀውን ወስንና ድንበር አጥኚ ኮሚሽን እንደማይቀበለው ይፋ ያደረገ ብቸኛ ክልልና ድርጅት ነው። አልፎ ተርፎም የለውጡን ተቃዋሚዎች መቀሌ እየጋበዘ በለውጡ ላይ በይፋ እያሤረ ያለ ድርጅት ነው። በነጄነራል ሰዓረ መኮንን የመቀሌ ቀብር ሥነ ሥርዓት፣ በስመ–ቀብር የለውጡን ኃይሎች ለማዋረድና ለመዝለፍ ዕለቱን የተጠቀመ ድርጅት ነው። ይህ እንግዲህ በስውር ከሚያደርጋቸው ሤራዎች በተጨማሪ በይፋ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ነው። የዘረፈውን ገንዝብና ያደራጀውን የስለላ መዋቅር በመጠቀም፣ በአገሪቱ ሰላም እንዳይኖርና ዜጎች በለውጡ እንዲማረሩ የተቻለውን ሁሉ እየሠራ ይገኛል። በሶማሌ ክልል በተደረገው የሚሊዮኖች መፈናቅልና የቤተ ዕምነቶች መቃጠል አሻራው እንዳለበት ተረጋግጧል። አዴፓ በአማራ/በቤኒሻንጉል ክልሎች ለደረሰው ጥፋት የህወሓት እጅ እንዳለበት ማስረጃ አለኝ ብሏል።
ይህን ሁሉ ጥፋት እያደረሰ ያለው ህወሓት ዝም በመባሉ የድፍረት ድፍረት እየተሰማውና የለውጡን ኃይል እየናቀ አሻጥሩንና ፀረ–ለውጥ እርምጃውን በእጥፍ ድርብ ጨምሯል። እንዲያውም “ለውጡን እኛ ነን ያመጣናው ቲም እገሌ የሚባል የለም” በሚል ድፍረት ከለውጡ በፊት ለውጥ ፈላጊውን ሕዝብ ሲጨፈጭፉና ሲያስጨፈጭፉ የነበሩት ዛሬ መድረክ አይብቃን ሲሉ እየታዘብን ነው።
11. የኑሮ ውድነት እየጨመረ መሄዱም የለውጥ ደጋፊውን ሕዝብ የሚያረጋጋና ተስፋ የሚሰጥ ክስተት አልሆነም። የሥራ አጡ ወጣት ቁጥር አለመቀነስ አሁንም ለሕይወት አስጊ የሆነ ስደትን መምረጥ፣ በአጠቃላይ የኑሮ ውድነት ሕዝቡንማሰቃየቱ በለውጡ ላይ ካሉት ከሌሎች ቅሬታዎች ጋር ተጋምዶ ጨለምተኝነትን አንግሷል።
12. የፌዴራል ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ትምህርት ሚኒስቴር በነሃሴ ወር 2011 ዓ. ም ካወጣው ፖሊሲ አንደኛው ብዝሃነትንና ኅብራዊነትን የሚያጠናክር የሥራ ቋንቋ የሆነው አማርኛ ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ በሁሉም ክልሎች ውስጥ እንዲሰጥ የሚያሳስብ ፖሊሲ ነበር። ይህ ፖሊሲ በትምህርት ፖሊሲ ጠቢባን የሆኑ አገር–በቀል ምሁራን የተሳተፉበትና ክልሎችም በሚገባ ግብዓት የሰጡበት ሲሆን ፖሊሲው ይፋ ሲሆን ማን ተቃወመው? እንደተለመደው ህወሓትና ኦነግ በሚገርም ሁኔታና ያገራችንን አንድነት እንደማይፈልጉ በሚያሳጣ መልኩ ተቃውመውታል።
ሌላው ያልተጠበቀውተቃዋሚ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ነው። ተቃውሟቸው ሌላም ተጨማሪ ፌዴራላዊ የሥራ ቋንቋ ይጨመር የሚል ቢሆን፣ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ኃይሎች ለዘመናት የታገሉለት ግብ ስለሆነ እንደ ተራማጅ እርምጃ ይታይ ነበር።
እነዚህ የጥፋት ኃይሎች ግን ድብቅ አገር የማፈራረስ ዓላማ እንዳላቸው የሚያሳየው ማንም እንደ አገር የቆመ መንግሥት ያለውን የጋራ ቋንቋ በሚጣረስ መልኩ “በጋራ መነጋገር” አንፈልግም ይሉናል። የትምህርት ሚንስቴርም የነዚህን አክራሪ ድምፆች በመስማት ሸብረክ ብሎ “ምክረ–ሃሳብ” እንጂ አስገዳጅ ፖሊሲ አይደለም ይለናል። ታድያ “ለውጡ የት ገባ”? ብለን ከመነሻው ላነሳነው ጥያቄ ባመዛኙ መልሱ በአክራሪዎች ተጠለፈ፣ የለውጥ ኃይሉም እንደ ታዛቢ ቆሞ የሚያይበት ሁኔታ ጠለፋውን አፋጠነው በማለት ልንመልሰው እንችላለን።
የለውጥ ኃይሉ ከቁጥጥሩ ውጭ የሆኑ የገጠሙትንም ችግሮች ማውሳት ፍትኅ ያለው አካሄድ ነው። በተለይ በአብዛኛው ውጭ የሚኖሩ ጥላቻን የሚሰብኩ በማኅበራዊ የመገናኝ ብዙሃን አሉታዊ ሚና የሚጫወቱ ክፍሎችም ለውጡን በመጉዳትና ሕዝብን ከሕዝብ በማቃቃር አሉታዊ ሚና እየተጫወቱ ነው።
ለውጡን ለመታደግ
ከላይ እንዳየነው፣ ለውጡ ሃዲዱን ስቶ አድራሻው የት እንደሆነ እንኳን ከማናውቅበት ደረጃ ላይ ደርሰናል ብንል ማጋነን አይሆንም። ኢሕአፓ ለውጡን ፈልጎ ማግኘትና መልሶ መስመሩ ላይ መመለስ አሁንም ይቻላል ብሎ ያምናል።
ለዚህም እንዲረዳ የመፍትሄ ሃሳቦችን እንደሚከተለው ያቀርባል።
1. የለውጥ ኃይሎችና የለውጡ ተቃዋሚዎች በአንድነት ሊቀጥሉ አይችሉም። የለውጡ ተቃዋሚዎች ሕግ ሲጥሱ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድና አሻጥራቸውን በማጋለጥ የመግታት እርምጃዎች በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል።
2. የለውጥ ኃይሉ አክራሪ ብሄርተኞችን እስከ አሁን እንደሚደረገው በመለማመጥ መቀጠል ሳይሆን፣ እነሱም የቅርብ ወራት ልምዳችን በማስረጃነት እንደሚያሳየው “ አንደረግም” በማለት በእብሪት በእኩይ ተግባሮቻቸው እንዳይገፉበት እንዳስፈላጊነቱ ሕጋዊ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል።
3. የሀገራችን የችግሮች ሁሉ ምንጭ የሆነውን የህወሓትን ህገ–መንግሥት በአስቸኳይ ለሕዝብና ለፖለቲካ ድርጅቶች ውይይት አብቅቶ፣ በብሄራዊ እርቅ ማዕቀፍ ሕዝባችን ብያኔ እንዲሰጥበት ማድረግ ተቀዳሚ ሥራ ነው። ይህ ተግባር እስኪከናወን ድረስ ህገ–መንግሥቱን መሠረት በማድረግ የክልል ጥያቄ የሚያነሱ ዞኖች የህገ–መንግሥቱ መጨረሻ እስኪወሰን ድረስ ጥያቄያቸው በይደር እንዲቆይ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ ካልሆነ፣ በተለይ በደቡብ ክልል እንደተጀመረው ጥያቄው መስተናገድ ከቀጠለ ማቆሚያ ስለማይኖረው የሀገሪቱን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል ፖለቲካዊ ሂደት ነው። ኢሕአፓ በቋንቋ ላይ ብቻ የተመሠረተውን የአሁኑን የሀገሪቱን አስተዳደራዊ ክፍፍል አጥብቀው ከሚቃወሙ ድርጅቶች አንዱ ነው። የራሱን የባለ 17 ክፍለሀገሮች ፌዴራላዊ አስተዳደር እንደ አማራጭም አቅርቧል። በውይይትና በሰጥቶ መቀበል መርኅ ስምምነት ላይ ለመድረስ ዝግጁ መሆኑንም ይገልፃል። ኢሕአፓ “ለድርድር የማይቀርብ” የሚል የፖለቲካ ቀኖና አያምንም።
4. ምርጫ አንድን አገር ካለመረጋጋት ወደ ሰላምና መረጋጋት እንደሚወስዳት ይታመናል። ይህም ምርጫው ነፃና ርቱዓዊ ከሆነ ብቻ ነው። ከላይ እንዳሳየነው ትግራይና ኦሮሚያ በአጠቃላይ ለፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በተለይ ለሀገርአቀፍ ፓርቲዎች እሾህና አሜከላ ሆነው፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ባልተረጋጋና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ሥር ባለበት ሁኔታ፣ በአጠቃላይ ሕዝባችን በለውጡ ሂደት ግራ በተጋባበት ወቅት ምርጫ ማካሄድ ሰላምና መረጋጋት ከማምጣት ይልቅ ያሉብንን
ችግሮች የበለጠ እንዳያባብስና ለአክራሪዎች ይበልጥ አቅም እንዳይሰጥ ጥንቃቄ በማድረግ፣ ህገ–መንግሥቱ “በየአምስት ዓመቱ ምርጫ ይደረግ” ይላል የሚለውን ቀኖና ትቶ በሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ብቻ የተመሠረተ ትንተና አድርጎ ውሳኔ
መስጠት ተገቢ ነው እንላለን።
5. ጠቅላይ ሚንስትሩ የጀመሯቸው አካባቢን የመለወጥ ተነሳሽነቶች፣ ለምሳሌ የአዲስ አበባ ወንዞችን ማሳመርና ሕይወታቸው እንዲታደስ ማድረግ እንዲሁም የዓለምን ክብረወሰን የሰበረውን በዚህ ክረምት በመላ ኢትዮጵያ የተደረገው የችግኝ ተከላ ትውልድ ተሻጋሪ በመሆናቸው ሊመሰገኑ ይገባል። ለውጡም በተመሳሳይ እንደገና ሕይወት ለመስጠት ቆራጥ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚያስፈልግ ማውሳት ተገቢ ነው።
ከላይ ከ1-5 ያነሳናቸው ጉዳዮች ትኩረት ተሰጥቷቸው ተግባራዊ ከሆኑ፣ ኢሕአፓ ለውጡን ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ወደነበረበት ቦታው መመለስና ማስኬድ ይቻላል ብሎ በፅኑ ያምናል። ድርጅታችንም ከሕዝባችን ጎን በመሆን ለውጡን ለማራመድ የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ያረጋግጣል።
-
የብሄር አክራሪነት ለውጡን እያደናቀፈ ያለ ከፊታችን የተደቀነ ከፍተኛ አደጋ ነው!
Phone: 251 944 223 216 e-mail: eprp@eprp-ihapa.com