September 16, 2019

Source: https://mereja.com/amharic/v2/146647

እውቁ የጃዝ ሙዚቃ አቀናባሪ ሙላቱ አስታጥቄ በፈረንሳይ መንግስት ሊሸለም ነው። ( ETHIO FM 107.8 )

ፈረንሳይ ለሙዚቀኛ ሙላቱ ከፍተኛውን የጥበብ ሽልማት ልትሸልመው እንደሆነ ተሰምቷል፡፡

ሽልማቱን በመጭው መስከረም 18-19 የሀገሪቱ ባሕል ሚንስትር ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ እንደሚሰጡት አዲስ ስታንዳርድ የፈረንሳይ ኢምባሲን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

ሙዚቀኛ ሙላቱ “የፈረንሳይ ኦርደር ኦፍ አርትስ ኤንድ ሌተርስ” የሚባለውን ሽልማት እንደሚያገኝ ተገልጿል፡፡

በ1943 ዓ/ም በጅማ ከተማ ተወልዶ የልጅነት ጊዜውን በአዲስ አበባ ያሳለፈው ሙላቱ አስታጥቄ በትምህርቱ ጎበዝ ስለነበረ ቤተሰቦቹ መሐንዲስነት አንዲያጠና ወደ ታላቋ ብሪታኒያ ቢልኩትም ውስጡ በነበረው የሙዚቃ ፍቅር ተልእኮው ሙዚቃ ሆነ።

ብርቅዬው የሙዚቃ ቀማሪ ላለፉት 50 ዓመታት በ’ጃዝ’ ሙዚቃ ውስጥ ኖሯል።

ኢትዮጵያን ለዓለም በ’ጃዝ’ ያስተዋወቀው ሙላቱ የአሜሪካው የበርክሊ የሙዚቃ ኮሌጅ የመጀመሪያው ጥቁር የሙዚቃ ተማሪ ነበር።
ሙላቱ በዚሁ ኮሌጅ የአፍሪቃን ትምህርቶች ክፍል አማካሪነት ሹመት አግኝቷል። ሙላቱ አስታጥቄ «ብሮክን ፍላወር» የተባለው ፊልም ላይ ሙዚቃ በመሥራት ትልቅ አድናቆትን ማግኘቱ ይታወሳል።

ይህም ለኢትዮ ጃዝ ሙዚቃ ዕድገትና በዓለም ላይም ትልቅ ደረጃ እንዲያገኝ ረድቶታል።

ሙላቱ ለዓለም አቀፋዊ የሙዚቃ እድገት ስላደረገው ታላቅና ጉልኅ አስተዋፅፆና በቀድሞ ኮሌጁ ተማሪዎች ላይ ስላሳደረው አርአያነት በቦስቶን የሚገኘው የበርክሊ የሙዚቃ ኮሌጅ የክብር ዶክቶሬት ዲግሪ ሸልሞታል።