
የኤርትራ መንግሥት ከ18 ዓመት በፊት የሃገሪቱን ፕሬዝዳንት በመተቸታቸው ምክንያት ለእስር የዳረገቻቸውን 11 ፖለቲከኞችንና 17 ጋዜጠኞችን እንድትለቅ አምነስቲ ኢንትርናሽናል ጥሪ አቀረበ።
የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪው አምነስቲ እንዳለው እነዚህ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች የታሰሩት በ1994 ዓ.ም ላይ ነበር። ከዚያ በኋላም ግለሰቦቹ ላይ ይፋዊ ክስ ያልተመሰረተባቸው ሲሆን ታይተውም ሆነ ስላሉበት ሁኔታ ምንም የተሰማ ነገር የለም ብሏል።
አምነስቲ የህሊና እስረኞች ያላቸውን እነዚህን ታሳሪዎች የተያዙበትን 18ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ እንዲለቀቁ ለመጠየቅ ለ18 ቀናት የሚቆይ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ መጀመሩንም ገልጿል።
• በፕሮቴስታንት እምነት ተከታይነቱ ለእስር ተዳርጎ የነበረው ኤርትራዊ ህይወቱ አለፈ
• ኤርትራ፡”እያስተማሩን ሳይሆን ባሪያ እያደረጉን ነው”
አስራ አንዱ ፖለቲከኞች የታሰሩት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ምርጫ በማካሄድና ለሕግ የበላይነት በመገዛት ሕገ መንግሥቱን እንዲያከብሩ የሚጠይቅ ግልጽ ደብዳቤ በመጻፋቸው ሲሆን 17ቱ ጋዜጠኞች ደግሞ ፖለቲከኞቹ ስለጻፉት ደብዳቤ በመዘገባቸው ነው ተብሏል።
የአምነስቲ ኢንትርናሽናል የምሥራቅ አፍሪካ፣ አፍሪካ ቀንድና የግሬት ሌክስ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ሰይፍ ማጋንጎ እንዳሉት “ለታሳሪዎቹ ፍትህ ሲጠየቅ ሁለት አስርት ዓመታት ሊሆን ነው፤ ምጸት የሚሆነው ደግሞ ኤርትራ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት አባል መሆኗ ነው።”
“ይህ ከሕግ ውጪ የሆነው እስር የፕሬዝዳንት ኢሳያስ መንግሥት ተቃዋሚዎቹን ለመጨፍለቅ ምን ያህል እርቀት እንደሚሄድ የሚያመላክት ነው። በብዙ መቶዎች እንደሚቆጠሩት ሌሎች የህሊና እስረኞች ሁሉ እነዚህ 28 ታሳሪዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ መለቀቅ አለባቸው” ሲሉ አክለዋል።
• ኤርትራ፡ ”እናቶች ከህጻናት ልጆቻቸው ጋር ታስረዋል”
• ኤርትራ የደብረቢዘን ገዳም መነኮሳትን አሰረች
ዛሬ የሚጀምረውና አምነስቲ ለ18 ቀናት የሚያካሂደው የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ የኤርትራ የቀድሞ የገንዘብ ሚኒስትር የነበሩት ብርሐነ አብረሃ ከተያዙበት አንደኛ ዓመት ጋር በማያያዝ ነው። አቶ ብርሐነ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሕዝቡ ለዲሞክራሲ ሰላማዊ ትግል እንዲያደርግ የሚቀሰቅስ መጽሐፍ ካሳተሙ በኋላ የዛሬ ዓመት ነበር።
እንደ ሌሎቹ የህሊና እስረኞች አቶ ብርሐነ ከውጪው ዓለም ጋር ምንም አይነት ግንኙነት በሌለው ምስጢራዊ ስፍራ ውስጥ ተይዘው እንዳሉ ይታመናል። ቤተሰባቸውም ስላሉበት የጤንንት ሁኔታና የት እንደሚገኙ ምንም አይነት መረጃ እንደሌላቸውም አምነስቲ ገልጿል።
አምነስቲ አክሎም ፕሬዝዳንት ኢሳያስና መንግሥታቸው በእነዚህና በሌሎች የህሊና እስረኞች ላይ እየፈጸሙት ያለው ኢፍትሐዊነት እንደሚያሳስበውና “ዓለምም ከታሳሪዎቹና ከቤተሰባቸው ጎን በመቆም የኤርትራ ባለስልጣናት ያለቅድመ ሁኔታ በቶሎ ከእስር እንዲለቋቸው መጠየቅ አለበት” ብለዋል ሰይፍ ማጋንጎ።
ባለፈው ዓመት ቢቢሲ የ13 ዓመት ታዳጊ እያለ ወላጆቹ ከ18 ዓመታት በፊት ከታሰሩት ሰዎች መካከል አንዱ የሆነውን ኢብራሒም ሸሪፎን አናግሮ ነበር።
እናቱ አስቴር ፍስሃጽዮን እና አባቱ ማህሙድ አህመድ ሸሪፎ ታዋቂ ከሆኑ ኤርትራዊያን ፖለቲከኞች መካከል ነበሩ።
“ከ18 ዓመታት በፊት በዕለተ ማክሰኞ የተከሰተው ነገር እስካሁን ከህሊናዬ አልጠፋም። ያቺ ዕለት ህይወቴን እስከወዲያኛው ቀይራዋለች” ሲል ነበር የተናገረው።
“ከእንቅልፌ የነቃሁት ጎህ ከመቅደዱ በፊት ባልተለመደ የሰዎች እርምጃና ትዕዛዝ በሚሰጥ ድምጽ ነበር። ሮጬ ስወጣ እናቴ ከቤታችን በወታደሮች እየተጎተተች ስትወጣ ተመለከትኩ” ሲል ክስተቱን ያስታውሳል።