
በመላው ዓለም የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ዓለማችን በአየር ንብረት ለውጥ እየተጎዳች መሆኑን በማስመልከት በትናንትናው እለት ሰላማዊ ሠልፍ አካሂደዋል።
ሠልፉ የተጠራው በአየር ንብረት ለውጥ የመብት ተሟጋቿ ግሬታ ተንበርግ ሲሆን፤ ከአውስትራሊያ እስከ ኒው ዮርክ፣ ከእስያ እስከ አፍሪካ ከሊቅ እስከ ደቂቅ እንደተሳተፉበት ተነግሯል።
ሠልፈኞቹ መፈክሮችን ይዘው የወጡ ሲሆን፤ በአንድነት ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ የተለያዩ መፈክሮችን ሲያሰሙ ተስተውለዋል።
ይህ ሠልፍ፤ የሠው ልጅ ያስከተለውን የዓለም ሙቀት መጨመር በመቃወም የተደረገ ትልቁ ሠልፍ ነው ተብሏል።
ግሬታ በሰልፉ ላይ “ቤታችን በእሳት እየነደደ ነው” በማለት ” እንደዘበት ቆመን በዝምታ አንመለከትም” ስትልም አክላለች።
ሠልፉ የተጀመረው በፓሲፊክና እስያ ሲሆን፤ በኒው ዮርክ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሠልፈኛ ወጥቶ ተቀላቅሏል።
የሚቀጥለው ሳምንት የተባበሩት መንግሥታት በማንሀተን ከሚያካሄደው ጉባዔ ቀደም ብሎ ነው ሠልፉ የተካሄደው። የመብት ተሟጋቾች ጉባዔው የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችሉ ወሳኝ ውሳኔዎች እንዲተላለፉበት ጥሪ አቅርበዋል።

ግሬታ ከዚህ በፊትም በ2018 ተቃውሞዋን ያሰማች ሲሆን፤ በወቅቱ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ላይ እንዲቀሩ በማድረግ ነበር ጥያቄዋን ለዓለም ሕዝብ ያሰማችው።
ይህ ድርጊቷ ተማሪዎችን እና ሌሎች ግለሰቦች ትግሏን እንዲቀላቀሉ አነሳስቷል።
ትላንት የሆነው ምን ነበር?
ሰላማዊ ሠልፉን የጀመሩት በውቅያኖስ ውሃ መጠን መጨመር የተጎዱት በኪርባቲ፣ በሰለሞን ደሴቶች እና በቫኑአቱ፣ የሚገኙ የፓሲፊክ ደሴት ነዋሪዎች ናቸው። እነዚህ ነዋሪዎች በድረገጾች ላይ የለጠፏቸው መልዕክቶች እንደሚያሳዪት “እየሰመጥን አይደለም፣ እየታገልን ነው” ይላል።
በአውስትራሊያም 35 ሺህ የሚሆኑ ሠልፈኞች እንደተቀላቀሉ ተገምቷል።
አውስትራሊያ በሙቀት መጨመርና የባህር ውሃ መሞቅ በከፍተኛ ሁኔታ ከሚሰቃዩ አገራት መካከል አንዷ ነች።
ከእነዚህ አገራት ሠልፉ ወደ እስያ፣ አውሮጳ፣ እና አፍሪካ እንዲሁም አሜሪካ ተስፋፍቷል።
• በኦሮሚያ ብክለት አስከትለዋል በተባሉ ፋብሪካዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ
• ኢትዮጵያ የአሜሪካን የፕላስቲክ ቆሻሻዎች እንደማትቀበል ገለፀች
በአፍሪካ በጋና የሚገኙ ተማሪዎች ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን፤ በባህር ዳርቻ የሚኖሩ ዜጎች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በተከሰተ ጎርፍ እየተጎዱ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው ግን በጋና 44 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ስለ አየር ንብረት ለውጥ ሰምቶ አያውቅም።
በታይላንድ እና በሕንድ የሚገኙ ሠልፈኞች፤ የሞቱ በማስመሰል መሬት ላይ በመውደቅ መንግሥታቱ ወሳኝ የሆነ ምላሽ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል።
በጀርመን በ500 ትላልቅና ትናንሽ ከተሞች ሠልፉ ሲካሄድ፤ የአገሪቱ ጥምር መንግሥት ግሪን ሀውስን ለመቀነስ ያለመ የ54 ቢሊየን ዮሮ ፓኬጅ አስተዋውቋል።
በዩኬ በአራት አገራት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሰልፉን መቀላቀላቸው ተነግሯል።
የሚቀጥለው ሳምንት የተባበሩት መንግሥታት ጉባዔ ሲካሄድም ሌላ ሠልፍ ይኖራል ተብሏል።
ግሬታ ተንበርግ ምን አለች?
አዳጊዋ የመብት ተሟጋች ግሬታ፤ አርብ ዕለት እንደ ዝነኛ አርቲስት ነው ከሠልፈኞቹ ሠላምታ የቀረበላት። በኒው ዮርክ ባተሪ ፓርክ የተሰበሰቡ ሠልፈኞች ስሟን ደጋግመው ሲጠሩ ተሰምተዋል።
“በታሪክ ከተደረጉ የአየር ንብረት ለውጥ ሠልፎች ሁሉ ይህ ትልቁ ነው፤ እናም ሁላችንም በራሳችን ልንኮራ ይገባናል፤ ምክንያቱም ይህንን ማድረግ የቻልነው በጋራ ነው” ስትል ለሠልፈኞቹ ተናግራለች።
• “የከተማ መስፋፋት የኢትዮጵያን ብዝሀ ሕይወት አደጋ ላይ ጥሏል” ዶ/ር መለሰ ማርዮ
በዓለማችን ላይ በአጠቃላይ ሠልፉን የተቀላቀሉት ግለሰቦች አራት ሚሊየን ይሆናሉ ያለችው ግሬታ “አሁንም እየቆጠርን ነው” ስትል ቁጥሩ ከዚህ እንደሚልቅ ፍንጭ ሰጥታለች።
“ይህ የአደጋ ጊዜ ነው፤ ቤታችን በእሳት ተያይዟል። ቤቱ ደግሞ የእኛ የአዳጊዎች ብቻ አይደለም፤ ሁላችንም የምንኖረው እዚህ ነው፤ ስለዚህ ሁላችንንም ይጎዳናል” ስትል ለሠልፈኞቹ ተናግራለች።
በሄደችበት የዓለማችን ክፍል ሁሉ “ውጤት አልባ ቃል ኪዳኖች ሁሉ ተመሳሳየይ ናቸው፣ ውሸቶቹ ተመሳሳይ ናቸው፣ ተግባር የማይታይባቸው እንቅስቃሴዎች ተመሳሳይ ናቸው” ስትል ትናገራለች።
• ትላልቅ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦች “አዋጭ አይደሉም”
የዓለማችን አይን የተባበሩት መንግሥታት የሚሰበሰቡ መሪዎች ላይ ሊሆን ይገባዋል፤ እናም “እንደሰሙን ለማረጋገጥ የመሪነት ሚናውን የመውሰድ እድሉ በእጃቸው ነው” የምትለው ግሬታ፤ “በእኛ ድርጊት ስጋት የገባው ካለ፤ የሕዝብ ኃይል ይህንን ነው የሚመስለው” ብላለች ንግግሯን ከማጠናቀቋ በፊት።
“ይህ ገና የመጀመሪያው ነው” በማለትም ” ፈለጉትም አልፈለጉት ለውጥ ይመጣል” ብላለች።
ግሬታ ተንበርግ ማን ነች?
ስውዲናዊቷ ግሬታ ተንበርግ ለመጀመሪያ ጌዜ ተቃውሞ ያደረገችው በትምህርት ቤቶች ነው። ባለፈው ዓመት በነሐሴ ወር ላይ በአገሯ የሕዝብ እንደራሴ ምክር ቤት ፊት ለፊት “ለአየር ንብረት ለውጥ፤ ከትምህርት ቤት መቅረት” በማለት ተቃውሞዋን አካሂዳለች።
ይህ ድርጊቷ ሌሎች ተማሪዎችንና ሰዎችን በመላው ዓለም ያነሳሳ ሲሆን፤ እርሷንም ለኖቤል የሰላም ሽልማት እንድትታጭ አድርጓታል።
ግሬታ የሚቀጥለው ሳምንት ለተባበሩት መንግሥታት ከምታደርገው ንግግር ቀደም ብሎ፤ የአሜሪካ ባለስልጣናትን የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት የተሻለ ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርባለች።
“እናንተ ምንም ሳትሠሩ፤ እኛ ምን ያህል እንዳነሳሳናችሁ ልትነግሩን አትጥሩን” ብላለች።