Source: https://mereja.com/amharic/v2/149961
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአሥሩ ማኅበራት ኅብረት በየሁለት ሳምንቱ የደረሰበትን ለምዕመናን ለማሳወቅ በገባው ቃል መሠረት ባለፉት አስር ቀናት ከመንግሥት ጋር የተወያየባቸውን ጉዳዮች በመግለጫ አሣውቋል። የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በመቃወም የሚንቀሳቀሰው የአዲስ አበባ አስተባባሪ ኮሚቴ ሒደታዊ መግለጫ፤
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት እና ምእመናን ላይ በተለያዩ አካባቢዎች የሚደርሰው ጥቃት እንዲቆም የሚንቀሳቀሰው የአዲስ አበባ ከተማ አስተባባሪ ኮሚቴ፣ መስከረም 2 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ለመስከረም 4 ቀን 2012 ዓ.ም. የጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ ከመንግሥት በቀረበለት የእንነጋገር ጥያቄ መሠረት ከሚመለከታቸው የመንግሥት ባለስልጣናት ጋር ውይይት በመጀመሩ ኮሚቴው ሰልፉ እንዲዘገይ በመወሠን በችግሮች ላይ ተወያይቶ መፍትሔ ለማሰጠት እንደወሰነ መግለጹ ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም፣ በየጊዜው የሚኖረውን የውይይት ሒደት እና ውጤት፣ ቢያንስ በየኹለት ሳምንቱ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ለማሳወቅ ቃል መግባቱም ይታወሳል፡፡
አስተባባሪ ኮሚቴው በገባው ቃል መሠረት፥ ባለፉት ዐሥር ዕለታት፣ በተመረጡ ስድስት ክልሎች እና ኹለት የከተማ አስተዳደሮች፣ ማስረጃዎችን አጠናቅሮና የውይይት አርእስተ ጉዳዮችን ለይቶ ልኡካንን በማሰማራት፣ ከርእሳነ መስተዳድሮች ጀምሮ ከሚመለከታቸው ከፍተኛ መንግሥታዊ ሓላፊዎች ጋራ ሲወያይ ሰንብቷል፡፡ በውይይቱም፣ በዋናነት ከአነሣቸው አንኳር ነጥቦች መካከል፡-
1. በጥቃት ሕይወታቸውን ላጡ ካህናት እና ምእመናን እንዲሁም ለተቃጠሉ እና ለተዘረፉ አብያተ ክርስቲያን ካሳ እንዲከፈል፤
2. ርእዮተ ዓለም መር ከኾኑ ስሑት ትርክቶች የተነሣ በሃይማኖታዊ ማንነታቸው ምክንያት ብቻ ለልዩ ልዩ አካላዊ እና ሥነ ልቡናዊ ጥቃቶች ተዳርገው፥ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ፣ ከማኅበራዊ ኑሮ የተገለሉ፣ ከሓላፊነት ቦታቸው እና ከሥራ መደባቸው የተባረሩ፣ ዛሬም በዚሁ ጫና ውስጥ የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ተገቢውን ፍትሕ እንዲያገኙ፤
3. የቤተ ክርስቲያንን ትክክለኛ ማንነት እና አገራዊ ውለታ በአገባቡ የማይገልጹ፣ ሕጋዊ እና መዋቅራዊ ድጋፍ ያላቸው የሚመስሉ፣ ሌሎች እምነቶችን ለበቀል የሚያነሣሱ በአጠቃላይ ኦርቶዶክሳውያንን ለጥቃት ያመቻቹ እና ያጋለጡ ስሑት ትርክቶች እንዲታረሙ፤
4. ለሕዝብ አገልግሎት የተሰጣቸውን መንግሥታዊ ሓላፊነት አላግባብ በመጠቀም፣ በምእመናንና በቤተ ክርስቲያን ላይ ልዩ ልዩ ስልታዊ ጫናዎችን ያደረሱ፣ ቀን ቀጥረው የተከሠቱና ለመከላከል የሚቻሉ ጥቃቶችን ያላስቆሙ፣ ይብሱኑ ጥቃቶቹን ያቀዱና ያቀነባበሩ ባለሥልጣናት፣ በገቢርም የፈጸሙ ቡድኖች እና ግለሰቦች በሕግ እንዲጠየቁ፤
5. ጥቃቶቹ እና ጫናዎቹ እንዲገቱ ለመንግሥት ጥያቄ ያቀረቡ ኦርቶዶክሳውያን፣ አቤቱታቸው ፖሊቲካዊ መልክ እና ይዘት እየተሰጠው ለእስር እና እንግልት መዳረጋቸው እንዲቆም እና የታሰሩትም እንዲፈቱ፤
6. በልዩ ልዩ ሰበቦች ሽፋን በመንግሥት ሓላፊዎች ፖለቲካዊ ድጋፍ ጭምር በሙሉ እና በከፊል የተነጠቁ የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች እንዲመለሱ፣ ለመመለስ የማያስችል ኹኔታ ካለ ደግሞ ትክ ቦታዎች እንዲሰጡ፤
7. ለዐዲስ አብያተ ክርስቲያን መትከያ፣ ለመካነ መቃብር፣ ለባሕረ ጥምቀት እና ለመስቀል ደመራ በዓል አከባበር እንዲሁም ለራስ አገዝ ልማት የሚውሉ ቦታዎች በሕግ አገባብ እንዲሰጡ፤
8. በተለያዩ አህጉረ ስብከት የሚገኙና የተወረሱ የቤተ ክርስቲያን ቤቶች እና ሕንፃዎች እንዲመለሱ፤
9. በቤተ ክርስቲያን ይዞታ ሥር ለሚገኙ፣ በቀጣይ በሚደረስባቸው ስምምነቶች ለሚመለሱ እና ዐዲስ ለሚሰጡ ቦታዎች፣ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እና/ወይም ደብተር እንዲሰጥ፤
10. በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚማሩ ኦርቶዶክሳውያን፣ በሕግ አገባብ የተፈቀደላቸውን የሥርዐተ እምነት ነፃነት በመጋፋት እየደረሱባቸው የሚገኙ ጫናዎች እንዲቆሙ፤ የሚሉት ይገኙበታል፡፡
በእነኚህ ነጥቦች መነሻነት፥ የየክልሉ ርእሳነ መስተዳድሮች፣ የሚመለከታቸው የቢሮ ሓላፊዎች፣ የዞኖች እና የልዩ ወረዳዎች አስተዳዳሪዎች በተገኙበት በተካሔዱ ውይይቶች፡-
•በቀረቡ ጥያቄዎች ላይ በስፋት በመወያየት ከሞላ ጎደል መግባባት ላይ ተደርሷል፤
•የጋራ መግባባት የተደረሰባቸውን ጉዳዮች ለመፍታት የጊዜ ገደብ ተቀምጧል፤
•አፈጻጸማቸውን በቅርበት ለመከታተልና ቀጣይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ በቅንጅት ለመሥራት ከመንግሥት እና ከየአህጉረ ስብከቱ የተውጣጡ አካላት ያሉበት የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሟል፤
•በክልሎቹ በተቋቋሙት የጋራ ኮሚቴዎች አስተባባሪነት፣ በየዞኖቹ በመንግሥት እና በቤተ ክርስቲያን ተወካዮች መካከል ጉዳይ ተኮር ጥልቅ ውይይቶች እንዲደረጉ ከስምምነት ተደርሷል፤
•ይህ እንዳለ ኾኖ፣ መግባባት ከተደረሰባቸው ጉዳዮች መካከል በመንግሥት በኩል፥ በደቡብ ክልል በሲዳማ ዞን የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያንንና የምእመናን ቤቶችን መልሶ ግንባታዎች በመጀመር፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተነጠቁ ይዞታዎችን በመመለስ እና የይዞታ ማረጋገጫ ለሌላቸው የአብያተ ክርስቲያን ቦታዎች የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ በመስጠት ተግባራዊ ምላሾች ተጀምረዋል፡፡
በአስተባባሪ ኮሚቴው የቀረቡ ጥያቄዎች የተሟላ እና ተገቢ ምላሽ እስከሚያገኙ ድረስ፣ ጥረቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ኮሚቴው ከተደረጉት ውይይቶች በፌዴራል መንግሥትም ደረጃ መታየት የሚገባቸውን ችግሮች በመለየት ከሚመለከታቸው አካላት ጋራ የሚነጋገር ሲኾን፣ ቀደም ሲል ቃል በገባው መሠረት፣ ለየጉዳዮቹ የተቀመጠውን ቀነ ገደብ ተከትሎ ዝርዝር ዘገባ የሚያቀርብ ይኾናል፡፡
በዚህ አጋጣሚ፣
• በተንቀሳቀስንባቸው ቦታዎች ኹሉ፣ ተገቢ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን በማቅረብ፣ ተወካዮችን በመመደብ፣ በውይይቶችም በንቃት እና በመሪነት በመሳተፍ አስተዋፅኦ ለአደረጉ የአህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶች፣ በተዋረድ ለሚገኙ የማህበራትና የአገልጋዮች ኅብረት፤ የውይይት መድረኮችን ከማመቻቸት ባሻገር ለልኡካኑ መልካም አቀባበል ለአደረጉ የመንግሥት አካላት ከፍተኛ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡
• ከሁሉም በላይ መላው ሕዝበ ክርስቲያን የኮሚቴውን ጥሪ በመቀበል ከኮሚቴው ጎን በመሆን ለሰላማዊ ሰልፍ ራሱን በማዘጋጀቱና፤ ሰልፉም እንዲዘገይ ኮሚቴው ያስተላለፈውን መልዕክት በመቀበል ምላሹን በትዕግስት በመጠበቁ ከፍተኛ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡ በቀጣይም መላው ሕዝበ ክርስቲያን የኮሚቴውን ሪፖርትና መልዕክት በትዕግስት እንዲጠብቅ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
መስከረም 13 ቀን 2012 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ