September 25, 2019

Source: https://fanabc.com

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 14 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስቲያናት የመሬት የባለቤትነት የይዞታ ማረጋገጫ ሰነዶችን አስረከቡ።

ምክትል ከንቲባው ሰነዶቹን ያስረከቡት በፓትርያርክ ፅህፈት ቤት በመገኘት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ነው።

ጥያቄ ከቀረበባቸው 137 አብያተ ክርስቲያናት መካከል 15ቱ ዛሬ የባለቤትነት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተሰጥቷቸዋል።

በርክክብ ስነስርዓቱ እንደተገለፀው ከ137ቱ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ለ33ቱ በፍጥነት መመለስ እንደሚቻልና ቀሪዎቹ 71 አብያተ ክርስቲያናት በጊዜ ሂደት የሚስተናገዱ መሆናቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፥ ለቤተክርስቲያኗ የሚገባትን መስጠትና ጥያቄዋን መመለስ ከመንግስት የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል።

አያይዘውም የከተማ አስተዳደሩ ላደረገው ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበው፥ ነዋሪዎች ከቀድሞ ቀያቸው በተለያየ ምክንያት ሲርቁ የቤተ እምነት ስፍራ ፍላጎት ስለሚኖራቸው በጉዳዩ ላይ መንግስት ሊያስብበት ይገባል ብለዋል።

ከተወሰኑ ቦታዎች በስተቀር በበርካታ ቦታዎች የተነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት እየተደረገ ያለውን ጥረትም አድንቀዋል።

ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ የቤተክርስቲያኗን ጥያቄ ለመመለስ ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።

ጥያቄዎችን መመለስ የመንግስት ሃላፊነት መሆኑን ያነሱት ምክትል ከንቲባው፥ በአዲስ አበባ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት የይዞታ ማረጋገጫ አልነበራቸውም ብለዋል።

በሌሎች የእምነት ተቋማት እንደሆነው ሁሉ የቤተ ክርስቲያኗን ጥያቄዎች ለመመለስ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህንንም ቤተ ክርስቲያኗ ስለሚገባት መደረጉን አስረድተዋል።

ቀሪ ጥያቄዎችንም በህግና በስርአት ለመመለስ እንደሚሰራ እና ማሻሻል የሚያስፈልጋቸው የህግ ማዕቀፎች ላይም እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢንጂነር ታከለ ኡማ ቤተክርስቲያኗ ላደረገችው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።

በርክክብ ስነ ስርአቱ ላይ የተገኙ የኮሚቴ አባላትም የከተማ አስተዳደሩ ጥያቄዎቹን ለመመለስ ላደረገው ጥረት ምስጋና አቅርበዋል።

በሃብታሙ ተክለስላሴ