September 25, 2019

የመስቀል ደመራ በዓል በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መሰራታቸውን የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ። የደመራ በዓል ኢትዮጵያ በዓለም የቅርስ መዝገብ ካስመዘገበቻቸው ቅርሶች ውስጥ አንዱ ነው።

በዓሉ በዩኔስኮ ከመመዝገቡ በተጨማሪም መስህብ በመሆን እና ጎብኚዎችን በመሳብ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑም ይነገራል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርም በዓሉ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ባማረ እና በተሳካ ሁኔታ እንዲከበር የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን፥ የሚኒስቴሩ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ ታሪኩ ነጋሽ ተናግረዋል።

ከሚደረጉት ዝግጅቶች መካከል ከሀይማኖት መሪዎች እና ከሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ከፌዴራል እስከ ታች ካሉ የስራ ሀላፊዎች ጋር የሚደረጉ ውይይቶች ይገኙበታል።

በዓሉ አንድነትን በማጠናከር እና ህዝብን በማቀራረብ ረገድ ያለውን ፋይዳ በሚመለከትም ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው ይሆናል።

በተለይም ወጣቱ በበዓሉ አከባበር መቀራረብን እና መተሳሰብን እንዲማር የማድረግ ስራዎች እንደሚሰሩም ነው አቶ ታሪኩ የተናገሩት።

እንደ ሚኒስቴሩ መረጃ በበጀት አመቱ ከአንድ ሚሊየን በላይ የውጭ ሃገር ጎብኚዎችን ለመሳብ እና በዚህም 5 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል።

የሚኒስቴሩ መረጃ እንደሚያሳየው በፈረንጆቹ በ2017 ላይ 432 ሺህ 687 ጎብኚዎች በዓሉን ሲታደሙ፥ በ2018 ደግሞ 384 ሺህ 615 ጎብኚዎች የመስቀል ደመራ በዓልን ተንተርሰው ሃገር ውስጥ ገብተዋል።

በዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓልም ካለፉት አመታት የተሻለ የጎብኝዎች ቁጥር ይመዘገባል ተብሎም ይጠበቃል።

ለዚህ እንዲረዳም ጎብኚዎች የሚያርፉባቸውን ቦታዎች በበቂ ሁኔታ በማመቻቸት ቆይታቸውን ያማረ ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።

ከዚህ ባለፈም የበዓሉ ታዳሚ በሰላም በዓሉን እንዲያከብር እና ወደ መጣበት በሰላም እንዲመለስ ከፀጥታ ተቋማት ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል አቶ ታሪኩ።

በዙፋን ካሳሁን / ኤፍ ቢ ሲ