የደመራ በዓል በሚከበርባቸው ቦታዎች ግጭት ቀስቃሽ ፅሁፎችን እና በህገ መንግስቱ ከተፈቀደው ሰንደቅ ዓላማ ውጪ የተለያዩ አርማዎችን ይዞ መገኘት አይቻልም- ፌዴራል ፖሊስ

(ኤፍ ቢ ሲ) የመስቀል ደመራ በዓል በሚከበርባቸው ቦታዎች ግጭት ቀስቃሽ ፅሁፎችን እና በህገ መንግስቱ ከተፈቀደው ሰንደቅ ዓላማ ውጪ የተለያዩ አርማዎችን ይዞ መገኘት የማይቻል መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በሀገሪቱ በየዓመቱ የሚከበረውን የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም እንዲከናወን ያደረገውን ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥቷል።
ኮሚሽኑ በመግለጫው በሀገሪቱ የሁሉም ሃይማኖት ተቋማት ተከታዮች በጋራ በመሆን ተከባብረውና አንዱ በአንዱ እምነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሳያደርግ የየራሳቸውን እምነት እንዲያስፋፉና በሀገራቸው ሰላም ላይ በጋራ በመሆን መስራት እንዲችሉ እየተሰራ መሆኑን አንስቷል።
በቅርቡ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ላነሳቻቸው ጥያቄዎች ከፍተኛ ትኩረትና አፅንዖት በመስጠት ከአስተባባሪ ኮሚቴዎች ጋር ውይይት በማድረግ ለተነሱት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ በሰላማዊ መንገድ በፌደራልና በክልል አዎንታዊ ምላሽ መስጠት መጀመሩም ተገልጿል።
ይሁን እንጂ መንግስት ጉዳዩ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ባለበት በዚህ ወቅት የቤተ-ክርስቲያን ጥያቄን ሽፋን በማድረግ አንዳንድ አካላት ጥያቄውን መስመር በማሳት ህዝበ ክርስቲያኑን ለማሳሳትና የእምነቱ ወግና ስርዓት ከሚፈቅደው ውጪ ወደ አላስፈላጊ አቅጣጫ ለማስኬድ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ደርሸበታለሁ ብሏል ኮሚሽኑ በመግለጫው።
ከዚህ ባለፈም በዓሉ በሰላም እንዳይጠናቀቅ የተለያዩ የግል አጀንዳዎችን አንግበው የበዓሉን ስነ-ስርዓት ለማወክ የተዘጋጁ ሃይሎች እንዳሉም ተመላክቷል፡፡
ስለሆነም ከበዓሉ ስነ-ስርዓት ውጪ፣ ግጭት ቀስቃሽ ፅሁፎች፣ አንዱን የሚያሞግስ ሌላውን የሚያንቆሽሽ ፅሁፍ፣ ብዝሃነትን የማይገልፁ ፅሁፎች በማንኛውም መንገድ ይዞ መገኘት የማይቻል መሆኑን አስታውቋል።
በተጨማሪም በህገ መንግስቱ ከተፈቀደው ሰንደቅ ዓላማ ውጪ እና የተለያዩ አርማዎችን ይዞ በዓሉ ወደ ሚከበርበት ቦታ መምጣት የተከለከለ መሆኑን ነው ኮሚሽኑ በመግለጫው ያስታወቀው፡፡
የደመራ በዓል ከሚፈቅዳቸው ስነ-ስርዓት ውጪ ሌሎች ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች ማድረግ የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ አደጋ ላይ የሚጥል ስለሆነ የሃይማኖት አባቶች፣ የየደብሩ አስተዳደሮች፣ የደመራ በዓሉን በኮሚቴነት የምታስተባብሩና የምትመሩት አካላት፣ ህዝበ ክርስቲያን እንዲሁም የሃገራችን ወጣቶች ፖሊስ የሚሰጠውን መመሪያ ከግምት ውስጥ በማስገባት በዓሉ በሰላም እስኪጠናቀቅ ድረስ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ እንዲያደረጉ ጥሪ አቅርቧል።
በሌላ በኩልም በአዲስ አበባና በተለያዩ የሃገራችን አካባቢዎች የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ዝግጅት የነበራቸው የአልሸባብና አይኤስ አይኤስ የሽብር ቡድኖች አባላት በህብረተሰቡ ከፍተኛ ተሳትፎ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።
በመሆኑም አሸባሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸው የሽብር ቡድኖቹን ያስከፋቸው በመሆኑ አሁንም አፀፋዊ የሽብር ጥቃት ለመሰንዘር አመቺውን ሁኔታ ሁሉ ለመጠቀም እንደሚፈልጉ መረጃዎች መኖራቸውን ኮሚሽኑ ጠቁሟል።
ስለሆነም ህብረተሰቡ የተለየ እንቅስቃሴ ሲመለከት በአካባቢው ላሉ የፀጥታ አካላት መረጃ እንዲሰጥ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጥሪ አቅርቧል።
በመጨረሻም የፌዴራልና የክልል ፖሊስ ኮሚሽን የመስቀል ደመራ በዓል ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ የሰላም የፍቅር የአንድነትና የደስታ እንዲሆን መልካም ምኞቱን አስተላልፏል።