
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር የአባይ ወንዝ ለተፋሰሱ ሃገራት የጋራ ሃብት እንጂ የፍጥጫ ምንጭ ሊሆን እንደማይገባ አሳሰቡ።
ፕሬዝዳንቷ በ74ኛው የድርጅቱ ጉባኤ ላይ በአማርኛ ባደረጉት ንግግር ላይ ኢትዮጵያን በተመለከተ የተለያዩ ጉዳዮችን ያነሱ ሲሆን በማጠቃለያቸው ላይ የግብጹ ፕሬዝዳንት ከእርሳቸው ቀደም ብለው አባይን በተመለከ ለገለጹት ስጋት ምላሽ ሰጥተዋል።
የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባለፈው ረቡዕ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ያለችውን ግድብ በተመለከተ የሚደረገው ድርድር ውጤት ላይ አለመድረሱ በአካባቢው ላይ አለመረጋጋትን ሊያስከትል እንደሚችል መናገራቸው ይታወሳል።
• አል ሲሲ ግብፅ በአባይ ላይ ያላትን ጥቅም ለማስጠበቅ ቃል ገቡ
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ለዚህ የግብጹ ፕሬዝዳንት ንግግር ምላሽ በሚመስል ሁኔታ “የአባይ ወንዝ ለተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ሃብት እንጂ የጥርጣሬና የውድድር ምንጭ ሊሆን አይገባም” በማለት ሃገራቱ የወንዙን ውሃ በጋራ መጠቀም እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ፕሬዝዳንቷ አክለውም የተፋሰሱ ሃገራት “የአባይን ወንዝ የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ ለመጠቀምም በትብብርና በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ” በንግግራቸው ላይ አንስተዋል።።
የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ በተለያዩ አጋጣሚዎች ኢትዮጵያ ከሰባት ዓመት በፊት በአባይ ወንዝ ላይ መገንባት የጀመረችውን ግዙፉን የህዳሴ ግድብ በተመለከተ ቅሬታና ተቃውሞ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
• ክፍል 2 ፡የህዝብ ብዛት መጨመርና የአካባቢ ብክለት ሌሎቹ የዓባይ ስጋቶች
• ክፍል 3 ፡የዓለማችን ረጅሙ ወንዝ መፃኢ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን?
አሁንም የዓለም ሃጋራት መሪዎች ስለሃገራቸውና በተለይ እንዲሁም ስለዓለማቀፋዊ ጉዳዮች ንግግር በሚያደርጉበት ዓመታዊው የተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ ላይ የግድቡን ጉዳት አንስተውታል።
በዚህ ንግግራቸውም ፕሬዝዳንቱ በሚገነባው ግድብ ዙሪያ ለዓመታት እየተካሄደ ያለው ውይይትና ድርድር ውጤት አለማስገኘቱ እንዳሳሰባቸው አመልክተዋል።
አክለውም ከግድቡ ግንባታ ባሻገር ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚጀመረውን የውሃ አሞላልና አያያዝን በተመለከተ ለዓመታት የተደረጉትን ውይይቶች አንስተው እንደተፈለገው ውጤታማ ሊሆኑ እንዳልቻሉ ለጉባኤው ታዳሚዎች ተናግረው ነበር።
ይህም በዚህ ከቀጠለ በሃገራቸው መረጋጋትና ልማት ላይ እንዲሁም በአካባቢው ሃገራት ላይ ከፍ ያለ ተጽእኖን እንደሚያስከትል አሳስበዋል።
ፕሬዝዳንት ሲሲ በንግግራቸው እንዳሉት ኢትዮጵያ ግድቡን ያለ በቂ ጥናት ለመገንባት መነሳቷን አመልክተው በዚህም ሃገራቸው ቅሬታ እንዳልነበራት ቢገልጹም በወቅቱ በስልጣን ላይ ከነበሩት የግብጽ ፖለቲከኞች ከፍተኛ ተቃውሞ ተነስቶ እንደነበር አይዘነጋል።
ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ፣ የግብጽና የሱዳን ባለስልጣናት ካይሮ ላይ የግድቡን ውሃ አሞላል በተመለከተ በተከታታይ የሚያደርጉት የሦስትዮሽ ውይይት ካይሮ ላይ የተካሄደ ቢሆንም ያለስምምነት መጠናቀቁ ይታወሳል።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በ74ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ከዚህ ከአባይ ጉዳይ ባሻገር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ንግግር አድርገዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተም ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብር በመቅረፅ አበረታች ስራ መስራቷን ገልፀዋል።
አፍሪካ በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክርቤት ቋሚ መቀመጫ አንዲኖራትም ጠይቀዋል።