Asmara

ቢቢሲ በኤርትራ አዘጋጅነት ሲካሄድ የነበረውን ከ15 ዓመት በታች የሴካፋ ውድድርን እንድንዘግብ ፍቃድ ተሰጥቶን ወደ ኤርትራ አቅንተን ነበር። በኤርትራ በነበርን ቆይታ ያየነውን እና የሰማነውን በሦስት ክፍሎች አሰናድተናል። የመጀመሪያው ክፍል እንደሚከተለው ቀርቧል።

ማስታወሻ፡ በኤርትራ በነበረን ቆይታ የዘገባ ርዕሶቻችን እና እንቅስቃሴዎቻችን የተገደቡ ነበሩ።

በጽሁፉ ውስጥ የተጠቀሱት ዓመታት እንደ ጎሮጎሳውያኑ አቆጣጠር ነው።


መግቢያ

ከ1880ዎቹ መጀመሪያ እስከ 1914 በነበሩት ዓመታት ቅኝ ገዢዎቹ አውሮፓዊያን፤ አፍሪካን የመቀራመት እቅዳቸውን የወጠኑበት እና ያሳኩበት ዓመታት ነበሩ።

1890 ላይ ጣሊያን ኤርትራ የእርሷ ቅኝ ግዛት መሆኗን አወጀች። 1920ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሞሶሎኒ ወደ ስልጣን መምጣቱን ተከትሎ ኤርትራ ‘የአዲሲቷ ሮማ ግዛት’ አካል ሆነች።

ከአምስት አስርት ዓመታት በላይ በኤርትራ የቆየው የጣሊያን ኃይል፤ በኤርትራ ቆይታው በመንገድ፣ በባቡር እና በህንጻ ግንባታዎች ላይ ተሳትፏል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በ1941 ዓ.ም ላይ የእንግሊዝ ጦር የጣሊያን ጦርን ከረን ላይ ድል አደረገ።

አሥመራ፡ የአዛውንቶች ከተማ

ጣሊያን እና አጋሮቿ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሽንፈትን መከናነባቸውን ተከትሎ፤ ጣሊያን ኤርትራን ጨምሮ በአፍሪካ የነበሯትን ቅኝ ግዛቶች ለመልቀቅ ተገደደች።

ከጣሊያን ቅኝ ግዛት በኋላ ኤርትራ ከ1942-1953 ያሉትን 11 ዓመታት በእንግሊዝ ጦር አስተዳደር ስር ነበረች።

በወቅቱ ኤርትራዊያን ነጻ ኤርትራን ማየት ናፍቀዋል። እንግሊዝ በበኩሏ ኤርትራ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል እንድትከፈል ፍላጎቷ ነበር። አሜሪካ ግን ኤርትራ በፌዴሬሽን መልክ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትዋሃድ ምክረ ሃሳብ አቀረበች።

የኃያሏ አሜሪካ ፍላጎት ተግባራዊ ሆኖ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን መልክ ተዋሃደች።

ሉዓላዊ የሆነች ሃገር መፍጠርን ግብ ያደረጉ ኤርትራዊያን ከተለያዩ ሁለት የኢትዮጵያ መንግሥታት ጋር ለ30 ዓመታት ያክል የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ ቆይተው እአአ 1991 ላይ የኤርትራን ነጻነትን አወጁ።

ፕሬዝደንት ኢሳያስ ከሁለት አዛውንት መካከል ሆነው።
አጭር የምስል መግለጫ ፕሬዝደንት ኢሳያስ ከሁለት አዛውንት መካከል ሆነው።

የተራዘመው የኤርትራዊያን የትጥቅ ትግል በዓለማችን ከታዩ እጅግ ውጤታማ የሽምቅ ውጊያዎች አንዱ ነው ይባልለታል።

1991 ላይ ነጻነትን የተቀናጀችው ኤርትራ 1993 ላይ ሕዝብ ውሳኔ ከተካሄድ በኋላ ነበር በይፋ ነጻነቷን አውጃ በተባበሩት መንግሥታት እውቅና የተቸራት።

በተባበሩት መንግሥታት በቅርበት ክትትል የተደረገበት ሕዝበ ውሳኔ፤ 99.8 በመቶ የሚሆኑት ኤርትራውያን ነጻነትን እንሻለን ሲሉ ድምጻቸውን ሰጥተዋል።

ከመኪኖች ይልቅ ብስክሌቶች የሚበዙባት ከተማ

1998 በሁለቱም ወገን ብዙ ደም ያፋሰሰው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ተቀሰቀሰ። ለሁለት ዓመታት ገደማ በዘለቀው ጦርነት በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሁለቱም ወገን ለሞት ተዳርገዋል።

የአልጀርሱ ስምምነት በጦር ግንባር ላይ የነበረውን ጦርነት ያስቁመው እንጂ፤ ለ20 ዓመታት በሁለቱ ሃገራት መካከል ሰላምም ጦርነትም የሌለበት ሁኔታ ውስጥ ቆይተዋል።

የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ በሁለቱ ሃገራት መካከል ቆይቶ የነበረው ቁርሾ ተገፎ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ተጀምሯል።

እኛም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አሥመራ አቅንተናል።

አሥመራ ቆሻሻ የማይታይባት፤ ጽዱ ከተማ።
አጭር የምስል መግለጫ አሥመራ ቆሻሻ የማይታይባት፤ ጽዱ ከተማ።

“ፃዕዳ አሥመራ”

ሃገሬው አሥመራን “ፃዕዳ አሥመራ” እያለ ይጠራታል። “ፃዕዳ” በትግርኛ ነጭ ማለት ነው። እውነት ነው አሥመራ ንጹሕ ነች። ቆሻሻ የማይታይባት፤ ጽዱ ከተማ።

በእድሜ ጠገብ ህንጻዎች የተሞላችው አሥመራ፤ ከሁለት ዓመታት በፊት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ታሪካዊ ከተማ በመባል የዓለም የቅርስ መዝገብ ላይ ተመዝግባለች።

የኤርትራ መዲና አሥመራ ከ1890ዎቹ ጀምሮ የቅኝ ገዢው የጣሊያን ጦር መቀመጫ ሆና ማገልገል ጀምራ ነበር። ቅኝ ገዢው በአሥመራ ጣሊያናዊ በሆነ የሥነ-ሕንጻ ጥበብ ስልት ግንባታዎች ማከናወን ጀመረ።

ሰማይ ላይ ወልዳ አሥመራ የምትታረሰው ኢትዮጵያዊት

በወቅቱ ቅንጡ የሆኑ ለመንግሥት አገልግሎቶች የሚውሉ ህንጻዎች፣ አብያተ ክርስቲያናት፣ መኖሪያ ቤቶች፣ ሆቴሎች እና የሲኒማ ቤቶች ግንባታ ተከናውነዋል። ከ1893 እስከ 1941 ድረስ የተገነቡት እነዚህ ህንጻዎች ዘመን ተሻግረው ዛሬ ላይ ታሪክን ያስታውሳሉ።

የነዋሪው ቆሻሻን የመጠየፍ ባህሪ ካለው የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት ጋር ተደማምሮ ከተማዋን ንጹህ አድርጓታል። ጎዳናዎቿ ንጹሕ ናቸው። ስለዚህም የአፍንጫን ሰላም የሚነሳ ጠረን በአሥመራ ከተማ አልገጠመንም።

በጥንቃቄ በመስመር የተተከሉት ዘንባባ እና 'ሽባካ' ተክሎች ሌላኛው የከተማዋ ውበት ናቸው።
አጭር የምስል መግለጫ በጥንቃቄ በመስመር የተተከሉት ዘንባባ እና ‘ሽባካ’ ተክሎች ሌላኛው የከተማዋ ውበት ናቸው።

ቅኝ ገዢዎቹ ጣሊያኖች በአሥመራ አሻራቸውን ጥለው ካለፉባቸው ነገሮች አንዱ የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓት ግንባታ አንዱ ነው። ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች በከተማዋ ጎዳናዎች ሥር ተገንብተው እንደሚገኙ ከነዋሪዎች ሰምተናል።

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ከተማዋ ጠዋት ከሥራ ስዓት በፊት ትታጠብ እንደነበርም ተነግሮናል።

ይህ ብቻም አይደለም፤ በአሥመራ ሲጓዙ ቢያድሩ አባ ከና የሚልዎ አይኖርም። ሃገሬውም ሆነ የውጪ ዜጋው ከመሸ እንደፈቀደው በእግሩ ይጓዛል። በአሥመራ አንድ ምሽት እንዳሳለፉ ስለከተማዋ ሰላማዊነት ሌላ እማኝ አያሻዎትም።

ወደ አሥመራ ለመጓዝ ማወቅ የሚገባዎ 6 ነጥቦች

ትሮቪላ፣ ፍራንሲስኮ፣ ዳንተ፣ ቪሊያጆ፣ ሳንታ ዓና፣ ቦላጆ . . . እኚህ ስሞች በሃገረ ጣሊያን የሚገኙ የከተማ ስሞች አይደሉም፤ የአሥመራ ሰፈሮች መጠሪያ እንጂ።

የአሥመራ ሰፈሮች ብቻ አይደሉም፤ ብዙ የአሥመራ ካፍቴሪያዎችና ምግብ ቤቶች ጨምር መጠሪያቸውን ያገኙት ከጣሊያን ቋንቋ ነው።

ሌላኛው የአሥመራ ውበት በጥንቃቄ በመስመር የተተከሉት ዛፎች ናቸው። ዘንባባ እና ‘ሽባካ’ ተብሎ የሚጠራው ዛፍ ለከተማዋ ልዩ ገጽታን አጎናጽፏታል።

የብሌን ብሄርሰብ ተወላጆች (ግራ) የአፍር ወጣት እየጨፈረች (ቀኝ)
አጭር የምስል መግለጫ የብሌን ብሄርሰብ ተወላጆች (ግራ) የአፍር ወጣት እየጨፈረች (ቀኝ)

ኤርትራ

ኤርትራ በደቡብ ከኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምሥራቅ ከጅቡቲ፣ በምዕራብ ከሱዳን፣ በምሥራቅ በኩል ደግሞ ከቀይ ባሕር ጋር ትዋሰናለች።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤርትራ የህዝብ ብዛት ወደ 5 ሚሊዮን ይገመታል ይላል። ወደ 400 ሺህ የሚጠጉት ደግሞ መኖሪያቸውን በመዲናዋ አድረገዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ አሥመራ ካቀኑ እነሆ አንድ ዓመት፤ ምን ተለወጠ?

በስድስት ዞኖች የምትከፋፈለው ኤርትራ፤ ትግር፣ ትግርኛ፣ አፋር፣ ኩናማ፣ ብሌን፣ ሳሆ እና ራሻይዳን ጨምሮ እውቅና የሚሰጣቸው 9 ብሔሮች ኖሩባታል።

በኤርትራ የሚገኘው አፋር በጅቡቲ እና ኢትዮጵያ ጋር ከሚኖሩት አፋሮች ጋር ተመሳሳይ ቋንቋ እና ባህል አላቸው።

የራሻይዳ ሴት ከአምስት ዓመቷ ጀምሮ ከዓይኗ በስተቀረ የተቀረ ፊቷን በደማቅ ጨሌ ባማረ ጨርቅ ትሸፍናለች።
አጭር የምስል መግለጫ የራሻይዳ ሴት ከአምስት ዓመቷ ጀምሮ ከዓይኗ በስተቀረ የተቀረ ፊቷን በደማቅ ጨሌ ባማረ ጨርቅ ትሸፍናለች።

ከተቀሩት የኤርትራ ብሔረሰቦች በመልክ እና በአኗኗር ዘዬ ለየት የሚሉት የራሻይዳ ህዝቦች ናቸው። መነሻቸው ሳዑዲ አረቢያ እንደሆነ የሚነገርላቸው ራሻይዳዎች አረብኛ ቋንቋ ተናገራሪዎች እና የእስልምና ዕምነት ተከታዮች ናቸው።

አርብቶ አደር እና ከመካከለኛው ምሥራቅ የሚገቡ ሸቀጣ ሸቀጦችን በጭነት መኪና በመነገድ የሚታወቁት ራሻይዳዎች ቀይ ባህርን ተከትለው በኤርትራ በረሃማ ቦታዎች ላይ ይኖራሉ።

የአሥመራን ጎዳናዎች በፎቶ

የራሻይዳ ሴት ከአምስት ዓመቷ ጀምሮ ከዓይኗ በስተቀር የተቀረ ፊቷን በደማቅ ጨሌ ባማረ ጨርቅ ትሸፍናለች።

የሰዓት እና ቀን አቆጣጠር

አገልግሎት ፍለጋ አርፍደው በደረሱበት ስፍራ “ነገ ጠዋት 8 ሰዓት ላይ ኑ” ልትባሉ ትችላለችሁ። ኤርትራዊያን ሰዓት የሚቆጥሩት ልክ እንደ ምዕራባውያኑ ነው። የቀን አቆጣጠር ሥርዓታቸውም ቢሆን እንደ ጎርጎርሳዊያኑ ነው።

የኤርትራ መገበያያ ገንዘብ ናቅፋ ባለ 1፣5፣10፣20፣50 እና 100 ኖቶች አሉት።
አጭር የምስል መግለጫ የኤርትራ መገበያያ ገንዘብ ናቅፋ ባለ 1፣5፣10፣20፣50 እና 100 ኖቶች አሉት።

መገበያያ ገንዘብ

የኤርትራ መገበያያ ገንዘብ ናቅፋ ይባላል። ባለ 1፣5፣10፣20፣50 እና 100 ኖቶች አሉት። አንድ የአሜሪካ ዶላር በ15 ናቅፋ በሕጋዊ መንገድ ይመነዘራል። በኤርትራ ዶላር በጥቁር ገበያ ላይ ለመመንዘር መሞከር ቀይ መስመር እንደማለፍ ከባድ ጥፋት ነው።

ዶላር መመንዘር የሚቻለው በብቸኛው የኤርትራ ንግድ ባንክ ብቻ ነው።

በአሁኑ ወቅት በባንክ እና በጥቁር ገበያ ላይ ያለው ልዩነት ሰፊ አይደለም። አንድ ዶላር በጥቁር ገብያ ላይ 17 ናቅፋ ብቻ ነው የሚመነዘረው።

ሁነኛ የትራንስፖርት አማራጭ ብስክሌቶች ቢሆኑም፤ አውቶብሶች እና ቢጫ ታክሲዎችም ደንበኞቻቸውን ከቦታ ቦታ ያመላልሳሉ።
አጭር የምስል መግለጫ ሁነኛ የትራንስፖርት አማራጭ ብስክሌቶች ቢሆኑም፤ አውቶብሶች እና ቢጫ ታክሲዎችም ደንበኞቻቸውን ከቦታ ቦታ ያመላልሳሉ።

የትራንስፖርት አማራጮች

እንደ ዝርግ ሳህን ለጥ ባሉት የአሥመራ ጎዳናዎች ነዋሪው ብስክሌቶች እንደ ሁነኛ የትራንስፖርት አማራጭ የመረጠ ይመስላል።

ትልቅ ትንሹ በብስክሌት ሽር ይላል። ቦርሳ በጀርባቸው ያነገቡ ታዳጊዎች በብስክሌት ወደ ትምህርት ቤት ያቀናሉ። ሰራተኛው ጉዳዩን ለመፈጸም በብስክሌት ይንቀሳቀሳል።

አውቶብሶች እና ቢጫ ታክሲዎችም ደንበኞቻቸውን ከቦታ ቦታ ያመላልሳሉ።

የዛሬ 30 ዓመት… የኮ/ል መንግሥቱ አውሮፕላን ለምን አልጋየም?

በኤርትራ አነስተኛ ደሞዝ፣ ወደ ሃገር ውስጥ በሚገቡ መኪኖች ላይ የሚጫነው ከፍተኛ ግብር እንዲሁም ከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ ተደማምረው የግል መኪና ባለቤት መሆንን ከባድ ያደርጉታል።

በዚህም በከተማዋ የሚስተዋሉት የተሽከርካሪዎች ቁጥር እጅግ አነስተኛ የሚባል ነው። ለመኪኖች በቅደም ተከተል የሚሰጠውን የሰሌዳ ቁጥር ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ በኤርትራ የሚገኙ የግል መኪኖች ብዛት ከ40ሺህ እንደማይዘሉ ማስላት ይቻላል።

አሥመራ የትራፊክ መጨናነቅ የማያቃት ከተማ በመሆኗ “ትራፊክ አልባዋ መዲና” የሚል ስያሜ ተሰጥቷታል። ወደየትኛውም አቅጣጫ መኪና ይዘው ቢንቀሳቀሱ በሌሎች የአፍሪካ ከተሞች የሚያስተውሉትን አይነት የትራፊክ መጭናነቅ አይመለከቱም።

Pizza

ፒዛ ወይስ ላዛኛ?

የሚበላ ፍለጋ ወደ አንዱ ሬስቶራንት ጎራ ቢሉ፤ በምግብ ዝርዝር አማራጭ ውስጥ በቅድሚያ ተዘርዝረው የሚመለከቱት እነ ፓስታ፣ ላዛኛ እና ፒዛን የመሳሰሉ ምግቦችን ነው።

ኤርትራዊያን የሚያሰናዱት ፓስታ እና ፒዛ እጅግ ድንቅ ጣዕም አላቸው።

እንጀራ ከከጀሉ እንዲሁ በቀላሉ የሚያገኙት ሳይሆን “ባህላዊ ምግብ” የሚያዘጋጅ ምግብ ቤት መፈለግ ግድ ይልዎታል።

የአሥመራ መስህብ ስፍራዎች

እግር ጥሎዎት ወደ አሥመራ ካቀኑ ከተማዋ ለእንግዶቿ ጀባ ከምትላቸው በርካታ የመስህብ ስፍራዎች ቢያንስ የሚከተሉትን ሳይመለከቱ አይመለሱ።

የሥነ-ሕንጻ ባለሙያው ፊያትን ለመገንባት እቅዱን ለአከባቢው መስተዳድሮች ሲያቀርብ፤ '15 ሜትር ርዝመት ያላቸው ክንፎች ያለድጋፍ ማቆም አይቻልም' በማለት እቅዱን ውድቅ ተደርጎበት ነበር።
አጭር የምስል መግለጫ የሥነ-ሕንጻ ባለሙያው ፊያትን ለመገንባት እቅዱን ለአከባቢው መስተዳድሮች ሲያቀርብ፤ ’15 ሜትር ርዝመት ያላቸው ክንፎች ያለድጋፍ ማቆም አይቻልም’ በማለት እቅዱን ውድቅ ተደርጎበት ነበር።

ፊያት ታግሊኤሮ ተገንብቶ የተጠናቀቀው እአአ 1938 ሲሆን የነዳጅ ማደያ፣ ጋራዥ እና የመኪና እጥበት አገልግሎት ይሰጥበት ነበር። ከታሪካዊነቱ በተጨማሪ ይህን በአውሮፕላን ክንፍ ቅርጽ የተገነባን ግንባታ ለየት የሚያደርገው፤ ወደ ጎን 15 ሜትር የሚረዝሙት ክንፎቹ ያለ ምሶሶ መቆማቸው ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኤርትራ ውስጥ መኪና ሲያሽከረክሩ የሚያሳየው ቪዲዮ

ፊያት የተገነባው በጣሊያኒያዊው የሥነ-ሕንጻ ባለሙያ ጁሴፔ ፔታዚ ሲሆን፤ አስጎብኚዎች ስለዚህ ህንጻ ግንባታ አንድ አስደናቂ ታሪክ ይናገራሉ። የሥነ-ሕንጻ ባለሙያው ጁሴፔ ፊያትን ለመገንባት ሃሳቡን ለአካባቢው መስተዳድሮች ባቀረበላቸው ወቅት፤ ’15 ሜትር ርዝመት ያላቸው ክንፎች ያለድጋፍ ማቆም አይቻልም’ በማለት እቅዱን ውድቅ አደርገውበት ነበር ይላሉ።

በዚህ የተበሳጨው ጁሴፔ ‘ይሄ ግንባታ ከፈረሰ እራሴን አጠፋለሁ’ ብሎ ዝቶ ንድፉን ከልሶ ቋሚ ድጋፎችን ያስገባ በማስመሰል ግንታውን መጨረሱ ይነገራል።

ፊያት በወቅቱ ከአሥመራ ተነስተው ወደ ኢትዮጵያ እና የወደብ ከተሞች ለሚያቀኑ መኪኖች ነዳጅ የሚሞሉበት ብቸኛው ስፍራ ነበር። ዛሬ ላይ ከ80 ዓመታት በኋላ አገልግሎት ሳይሰጥ ብቻውን ተትቶ ቆሞ ይገኛል።

አሥመራ የቅንጡ የሲኒማ፣ የቲያትር ቤቶች፣ የሬስቶራንቶች እና ካፍቴሪያዎች መገኛ ከተማ ነበረች።
አጭር የምስል መግለጫ አሥመራ የቅንጡ የሲኒማ፣ የቲያትር ቤቶች፣ የሬስቶራንቶች እና ካፍቴሪያዎች መገኛ ከተማ ነበረች።

አሥመራ ዛሬ ላይ ሲያጤኗት ጭር ያለች ከተማ ናት። ከብዙ አስርት ዓመታት በፊት የነበራት ገጽታ ግን ሌላ ነበር።

ቅንጡ የሲኒማና የቲያትር ቤቶች እንዲሁም የሬስቶራንቶች እና ካፍቴሪያዎች መገኛ ከተማ ነበረች። ዛሬ ላይ ባዷቸውን የቀሩት እነ ሲኒማ ሮማ፣ ሲኒማ ካፒቶል፣ ኦዲዮን ሲኒማ እና ሲኒማ አሥመራ ለዚህ እማኝ ናቸው።

በ1920ዎቹ እና 30ዎቹ የተገነቡት እነዚህ ሲኒማ ቤቶች፤ በዘመናቸው አሉ የተባሉ የእንግሊዝኛ እና ጣሊያንኛ ፊልሞች የሚታዩባቸው ነበሩ።

አሁን ላይ ገሚሱ ባዶውን ቀርቷል፤ የተቀሩት ደግሞ ሃገር በቀል ፊልሞችን እና የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን ያሳያሉ።

በተለያዩ ወቅቶች በኤርትራ በተደረጉ ጦርነቶች ከጥቅም ውጪ ሆኑ የጦር ተሽከርካሪዎች በአንድ ሥፍራ ተሰብስበው ይገኛሉ።
አጭር የምስል መግለጫ በተለያዩ ወቅቶች በኤርትራ በተደረጉ ጦርነቶች ከጥቅም ውጪ ሆኑ የጦር ተሽከርካሪዎች በአንድ ሥፍራ ተሰብስበው ይገኛሉ።

በተለያዩ ወቅቶች በኤርትራ የተደረጉ ጦርነቶች ምን ያክል አስከፊ እንደነበሩ ይህን ስፍራ በመጎብኘት መገንብ ይቻላል።

በዚህ “ታንክ ግሬቭ ያርድ” (የታንክ የመቃብር ቦታ) ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በጦርነት የወደመ የጦር ተሽከርካሪ አይነት አንድም የቀረ አይመስልም። ከታንክ እስከ አየር መቃወሚያ፤ ከአውቶቡስ እሰከ መድፍ፤ ብቻ ሁሉም አይነት ተቃጥሎ እና ወላልቆ በአንድ ቦታ ላይ ተሰብስበው ይገኛሉ።

ቀረብ ብለው ሲመለከቱ የወደሙትን የተሽከርካሪ አካላት መኖሪያ ቤታቸው ያደረጉ ሰዎችን ያስተውላሉ።

የጣሊያን የመቃብር ስፍራ
አጭር የምስል መግለጫ በቅኝ ግዛት ወቅት ህይወታቸው በኤርትራ ያለፈ ጣሊያውያን ይቀበሩ የነበረበት ሥፍራ።

በቅኝ ግዛት ወቅት ህይወታቸው በኤርትራ ያለፈ ጣሊያዊያን ይቀበሩ የነበረበት ሥፍራ ነው። በጥሩ ሁኔታ ተይዞ የሚገኘው ይህ የመቃብር ስፍራ አሁንም ድረስ ከጣሊያን ድረስ እየመጡ በዘመዶቻቸው የመቃብር ላይ የአበባ ጉንጉን የሚያኖሩ ሰዎች እንዳሉ ይነገራል።

ካቴድራል ቤተክርስቲያን፣ ሲኒማ ሮማ፣ እንዳ ማርያም ቤተክርስቲያን እና ሌሎች የጣሊያን ቅኝ ግዛት ዘመን የሥነ-ሕንጻ ጥበብ ያረፈባቸው የሚጎበኙ ታሪካዊ ስፍራዎችም በአሥመራ ይገኛሉ።