October 6, 2019

(ኢዜአ) – የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ የውህደት ሃሳብ አገራዊ አንድነትን ለማስቀጠል የሚደረገውን እንቅስቃሴ የሚያጠናክር ነው ሲሉ የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ ሊቀመንበር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

Image may contain: 1 person

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ የኢህአዴግ ምክር ቤት የውህደት ውሳኔን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ቀደም ሲል ኢህአዴግ በአራት ድርጅት ላይ ብቻ የተመሰረተና አጋር ድርጅቶችን ያላካተተ እንደነበር ተናግረዋል።

“በዚህም አጋር ድርጅቶች በወሳኝ ሀገራዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የመሳተፍ እድል ተነፍገውበታል፤በድርጅቱ የሚተላለፉ ውሰኔዎችን ተረድቶ ወደ ተግባር ከመለወጥ አኳያ የራሱ የሆነ ክፍተት ነበረበት”ብለዋል።

አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር በሚደረገው ሂደት ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩንም ገልጸዋል።

ቀደም ሲል የነበረው የኢህአዴግ አደረጃጀት በብሔራዊ ማንነት ላይ ጠንካራ ስራዎች ቢከናወኑም በዚሁ ልክ በኢትዮዽያዊነት /ሀገራዊ ማንነት/ ላይ የተሰራው ስራ አመርቂ አለመሆኑንም አመልክተዋል።

ለዚህም በአራት ድርጅቶች ላይ ብቻ በመመስረቱ የአምስቱን ክልሎች ድምጽና ውሳኔ ባለመያዙ የራሱ የሆነ ተጽዕኖ መፍጠሩን አስረድተው “ውህደቱ አገራዊ አንድነትን ለማስቀጠል የሚደረገውን እንቅስቃሴ የሚያጠናክር ነው” ብለዋል።

“ኢህአዴግ ወደ አንድ ፖለቲካ ፓርቲ መቀየር በኢትዮጵያዊነትና በብሔራዊ ማንነት ላይ የሚሰሩ ስራዎችን ያጎለብታል፤በኢህአዴግና በአንድ አንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለውን የመጠራጠርና ያለመተማመን ችግሮችም ይቀርፋል” ሲሉ ገልጸዋል።

እንዲሁም አጋር ድርጅቶችና በውስጡ ያሉ ህዝቦች የወሳኝ ድርጅታዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተሳታፊነትን የሚያጎለብትና ውሳኔዎችን ተግባራዊ ለማድረግ በትጋት ለመንቀሳቀስ የሚያነሳሳ እንደሆነም አስምረውበታል።

በውህደቱ የሚፈጠረው አዲስ ፓርቲ ሁሉም እኩል የሚስተናገድበት ይሆናል ቀደም ሲል ይታዩ የነበሩ ችግሮች በህዝቡ ይሁንታ አግኝተው የሚፈቱበት ሁኔታ ይፈጥራል” ብለዋል።

“በተጨማሪም በሀገሪቱ በየትኛውም ጫፍ ላይ ያለ ኢትዮጵያዊ በሁሉም እረከኖች ላይ ተሳትፎ የመምራት እድል የሚያገኝበትና መገለልን የሚያስቀር አካታች አሰራርን የሚያሰፍን ነው” ሲሉ ጠቁመዋል።

ውህደቱን ተከትሎ በፌዴራል ስርዓቱ ላይ በተለያዩ ወገኖች የሚነሳው ስጋት ተገቢ እንዳልሆነና በምንም መልኩ ችግር እንደማያስከትል ይልቁንም የብዙሃኑን ጥቅም እንደሚያስጠብቅ ያላቸውን እምነት አስረድተዋል።

“በህገ-መንግስቱ የተቀመጡትን የብሔር ብሔረሰቦች፣ ራስን በራስ ከማስተዳደርና ከቋንቋ አኳያ የተሻለ እድል ይፈጥራል” ብለዋል።

“የኢህአዴግ የውህደት ጉዞ በደንብ ውይይት ተደርጎበት ወደ ተግባር የሚገባ በመሆኑ የጋራ ጥቅምን የሚያረጋግጥ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

(ኢዜአ)