
6 October 2019
በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካይነት የፀደቀውን የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምርጫ አዋጁን የተቃወሙ 70 የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ አዋጁ ከመፅደቁ በፊት ለመንግሥትና ለሚመለከተው አካል ያቀረቡት የተቃውሞና የእንወያይ ጥያቄ ምላሽ ባለመግኘቱ ለሁለት ቀናት የረሃብ አድማ እንደሚያደርጉ አስታወቁ፡፡
ፓርቲዎቹ ይኼንን ዕቅዳቸውን ያስታወቁት ረቡዕ መስከረም 21 ቀን 2012 ዓ.ም. በመላው ኢትዮጵያና አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ዋና ጽሕፈት ቤት ለአገር ውስጥና ለውጭ የመገናኛ ብዙኃን መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡
በተደጋጋሚ ለሚመለከተው አካል ጥያቄ እንዳቀረቡ የገለጹት የ70 ፓርቲዎች ስብሰብ ተወካዮች እንዳስታወቁት፣ ሰኞ መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም. መደበኛ ሥራውን የሚጀመርው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄያቸው ከግምት አስገብቶ ዳግም ለውይይት የማይጠራቸው ከሆነ ጥቅምት 5 እና 6 ቀን 2012 ዓ.ም. የረሃብ አድማ ያደርጋሉ፡፡
ከረሃብ አድማው በማስከተልም ከጥቅምት 7 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ በመላው አገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምርጫ አዋጁን በመቃወም ፊርማ የማሰባሰብ እንቅስቃሴ እንደሚጀምሩም አስታውቀዋል፡፡
የረሃብ አድማውን ተፈጻሚ የምታደርጉት እንዴት ነው በሚል ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ የመኢአድ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙሉጌታ አበበ፣ ‹‹አመቺ በሆነ ሥፍራ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አመራሮች ተሰብስበን አድማውን እናደርጋለን፡፡ ይኼም የመገናኛ ብዙኃን በተገኙበት የሚፈጸም ይሆናል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምርጫ አዋጁን በመቃወም ላይ የሚገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የተለያዩ ጥያቄዎችንና ተቃውሞዎችን ሲያቀርቡ ነበር፡፡ በተለይ ጳጉሜን 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ሰጥተውት በነበረው መግለጫ፣ ‹‹ድምፃችን ይሰማ›› የሚል ሕዝባዊ እንቅስቃሴ እንደሚጀምሩ አስታውቀው የነበረ ሲሆን፣ ለማካሄድ ያቀዱት የረሃብ አድማና የተቃውሞ ፊርማ ማሰባሰብ ዕቅድ የዚሁ እንቅስቃሴ አካል እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪም ‹‹በሕዝብ ትግል የተገኘ ውጤት በጥቂቶች ሊቀለበስ አይገባውም›› በሚል በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹የዛሬ አንድ ዓመት ተኩል ገደማ በአገሪቱ የተከሰተውን የለውጥ ሁኔታ በአንድ ቡድን ወይም በተወሰኑ ቡድኖች መስዋዕትነት የመጣና ለሕዝብ በስጦታ የተሰጠ ሳይሆን መላው ሕዝብ የደም፣ የአካልና የሕይወት መስዋዕትነት ከፍሎ ያመጣው ለውጥ ነው፤›› በማለት በአገሪቱ የተከሰተውን ፖለቲካዊ ሁኔታ ገልጸውታል፡፡
ፓርቲዎቹ ወቅታዊውን ፖለቲካዊ ሁኔታ እንዲህ ባለ መልኩ ከመግለጽ ባለፈ፣ ‹‹አሁን እየታየ ያለው ሁኔታ ዛሬም የተጀመረውን ለውጥ ወደፊት እንዲሄድ ከማድረግ ይልቅ እንደባለፉት በርካታ የአገራችን የለውጥ ሒደቶች ሁሉ ተደናቅፎ እንዲቀርና ለውጡ በጥቂት አምባገነኖች እጅ ተጠልፎ የአምባገነኖችና የብልጣብልጦች መጠቀሚያ ሆኖ እንዲቀር የሚያደርግ አዝማሚያ ነው፤›› በማለት ሥጋታቸውንም ገልጸዋል፡፡