እንደሚታወቀው ቤተክርስቲያን ሦስት የማተብ ክር ቀለማት አላት፡፡ ሕፃናት ክርስትና ሲነሡ ካህናት ከአንገታቸው ላይ ሲያስሩላቸው ትመለከታላቹህ፡፡ ይህ ሦስት የክር ቀለማት ምንጩ በዘፍ. 98-17 ያለውን ቃለንባብ መሠረት ያደረገ ነው፡፡ እግዚአብሔር ቀለማቱን በቀስተ ደመና ላይ ሥሎ የድኅነት ወይም የምሕረት የቃልኪዳን ምልክት ነው!” ብሎ ሠይሞታልና ሊቃውንቱ በምሥጢር የምሕረት ወይም የድኅነት ምልክቱን ድኅነት ከምናገኝበት ጥምቀቱና የክርስትና ምልክቱ ማተብ ጋር አገናኝተው ቀለማቱን ቤተክርስቲያን ለማተብ ክር ቀለማት እንድትጠቀምበት አደረጉ፡፡

አሁን ችግሩ ያለው ለማተብ ቀለማት እየተጠቀምንበት ያለው የክር ቀለማት በትክክል ቀስተደመናው ላይ ያለውን ቀለማት ነው ወይ??? የሚለው ላይ ነው፡፡ መልሱ ማናችንም በግልጽ መረዳት እንደምንችለው አይደለም የሚለው ነው፡፡ ስሕተቱ የተፈጠረው የቀለማትን ሥያሜ ለየቀለማቱ ለያይቶ ካለመጠቀም የተነሣ ነው፡፡

ነገሩ እንዲህ ነው የቀድሞ አባቶች ጠቆር ያሉ ቀለማትን ለምሳሌ አረንጓዴን፣ ሰማያዊን፣ ቡኒን የመሳሰሉ ቀለማትን በጥቅሉ ጥቁር ሲሏቸው፡፡ ነጣ ያሉ ቀለማትን ለምሳሌ ቢጫን፣ ብርቱካንማን፣ ውኃ ሰማያዊን፣ ግራጫን፣ ቡላን ወዘተረፈ. ደግሞ በጥቅሉ ነጭ የሚሉት መሆኑ ነው ስሕተቱን የፈጠረው፡፡ ቀይን፣ ነጭን፣ ጥቁርን ግን በስም በስሙ ነው የሚጠሩት፡፡

በዚህ ምክንያት የቀስተ ደመና ቀለማትን በጽሑፍ ሲያስቀምጡ አረንጓዴውን ጥቁር ብለው፣ ቢጫውን ነጭ ብለው፣ ቀዩን ቀይ ብለው አስቀመጡት፡፡ ይሄንን የቀስተደመና ቀለማትን አገላለጽ ቀስተደመና በተጠቀሱባቸው የቤተክርስቲያናችን የትርጓሜ መጻሕፍት ላይ ታገኙታላቹህ፡፡

ለምሳሌ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ ዘረቡዕ ላይ አንቲ ዘበአማን ደመናን ሲተረጉም ደመና ኖኅ አንች ነሽ!” በሚለው ስር ተገልጾ ታገኙታላቹህ፡፡ አባቶቻችን የቀስተደመና ቀለማትን በጽሑፍ ላይ እንዲህ ብለው ያስቀምጡት እንጅ በብራና ላይና በቤተክርስቲያን ግድግዳ ላይ ኃረጋትንና ቅዱሳት ሥዕላትን ሲያስቀምጡ ግን የቀስተደመናውን ማለትም የቃልኪዳን ምልክቱን (ትእምርተ ኪዳኑን) እራሱን ቀለሙን በትክክል ማለትም ቀይ፣ ቢጫ፣ አረንጓዴውን ወይም አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩን ነበር ያስቀምጡት የነበረው፡፡

ቀስተደመና እንደምታውቁት የቀለም አቀማመጡ ከላይ ወደታች ቀይ፣ ቢጫ፣ አረንጓዴ ነው፡፡ ቤተክርስቲያንም ይሄንን የቃልኪዳን ምልክቷን ስትጠቀምበት የነበረችው በዚህ አቀማመጡ ነበር፡፡ አሁን ወዳለው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ አቀማመጥ ሊቀየር የቻለው ዐፄ ምኒልክ ይሄንን ንዋየ ቅዱስ አድዋ ድረስ አብሮ ተጉዞ ከነበረውና በድንኳን ይንቀሳቀስ ከነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ወስደው በዓላማ ወይም አጠና ላይ ሰቅለው ከዛሬ ጀምሮ ይሄ ሰንደቅ የሀገሪቱ ሰንደቅ ይሁን!” ብለው ባወጁ ጊዜም የቀለማቱ አደራደር እንደ ቀስተ ደመናው ቀይ፣ ቢጫ፣ አረንጓዴ ነበር፡፡ እንደ ዐፄ ምኒልክ በአዋጅ አይሁን እንጅ ይሄንን ሰንደቅ ዐፄ ቴዎድሮስም ዐፄ ዮሐንስ 4ኛም ይጠቀሙበት እንደነበር ይታወቃል፡፡ በዚያ ዘመን ከተነሡ የጥቁርና ነጭ ፎቶዎችና ስለ አድዋ ከጻፉ የምዕራባውያን ጸሐፍት ከጻፏቸው መጻሕፍት መመልከትና መረዳት እንደሚቻለው የሰንደቁ ቀለም አቀማመጥ ቀይ፣ ቢጫ፣ አረንጓዴ ነበር፡፡ በኋላ ላይ ግን እንዳጋጠመ ቀይ፣ ቢጫ፣ አረንጓዴ ወይም አረንጓዴ ቢጫ ቀይ እየሆነ ሲሰቀል ቆይቶ በመጨረሻ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ በሚለው ጸንቶ ሊቀር ቻለ፡፡

እንደምታውቁት ሳይንስ የቀለማቱ መጋጠሚያ መጋጠሚያ ላይ ቀለማቱ ሲገናኙ የተፈጠሩ ሌሎች ቀለማትን ጨምሮ ቆጥሮ የቀስተደመና ቀለማት ሰባት ናቸው!” ይላል፡፡ በዓይን ለማየት የማይቻል ሆኖ ነው እንጅ በየቀለማቱ መጋጠሚያ መጋጠሚያ ላይ ቀለማቱ ሲጋጠሙ ወይም ሲገናኙ የሚፈጠሩ ቀለማትን ጨምረን እንቁጠር ከተባለማ የቀስተደመና ቀለማት ቁጥር ሰባት ብቻ ሳይሆን የትየለሌ ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም ቀለም ከቀለም ጋር ሲገናኝ የሚፈጠረው ቀለም እንደገና ከጎኑ ካለ ቀለም ጋር ሲገናኝ ሌላ አዲስ ቀለም ይፈጥራልና ነው፡፡ ያ የተፈጠረው ደግሞ እንደገና ሌላ አዲስ ቀለም ይፈጥራልና ነው፡፡

ይሄንን በመንፈስቅዱስ የተረዱ አባቶቻችን የቀስተደመናን ቀለማት ሲያስቀምጡ ለዓይን በቀላሉ ጎልተው የሚታዩትን ሦስቱን ቀለማት ማለትም ቀይ፣ ቢጫና አረንጓዴውን ወይም አረንጓዴ ቢጫና ቀዩን ብቻ ወሰዱና እግዚአብሔር እንዳዘዘ የቤተክርስቲያኗ ትእምርተኪዳን (የቃል ኪዳን ምልክት) አደረጉት፡፡እኛ የኋለኛው ዘመን ሰዎች ግን ምን አደረግን አባቶች በዘልማዳዊ የቀለም ሥያሜ አጠቃቀም አረንጓዴውን ጥቁር ማለታቸውን፣ ቢጫውን ነጭ ማለታቸውን ሳንረዳ ጥቁር፣ ነጭና ቀይ ብለው የገለጹትን የቀለም ዓይነት እንዳለ ወስደን የማተብ ክር ቀለሙን በትክክለኛው አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ማድረግ ሲኖርብን እንደቃልቻ ቀለም ጥቁር፣ ነጭና ቀይ አድርገነው አረፍንንና የቃልቻ ቀለምን ሕፃናትን ክርስትና ሲነሡ አንገታቸው ላይ እያሳሰርን እንገኛለን!!!

ማኅበረ ቅዱሳን ደግሞ እሱማ እንዲያውም የቀለማቱን አደራደር ከጥቁር፣ ነጭ፣ ቀይ ወደ ጥቁር፣ ቀይ፣ ነጭ ቀይሮ ዋናውን የዋቄፈታ የባዕድ አምልኮ ማለትም የቃልቻ መለያ ቀለም አስይዞ የአቡነ ጎርጎሪዮስ ተማሪዎች የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) ላይ አስቀምጦት አርፎታል፡፡ ይሄ ግን የእነእንትና እጅ የለበትም ትላላቹህ???

በነገራችን ላይ ከላይ የገለጽኩላቹህ የውዳሴ ማርያም ትርጓሜ ክፍል የተስፋ ገ/ሥላሴ ማተሚያ ቤት ከጃንሆይ ዘመን ጀምሮ ሲያሳትመው በቆየው የውዳሴ ማርያም ትርጓሜ መጽሐፍ ላይ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በጉባኤ ቤት ወይም በወንበር ትምህርት ነጭ ያሉት ቢጫውን መሆኑን ሳይረዱ ቀስተደመናው ላይ ጎልቶ የሚታየው ቢጫው ቀለም አለመጠቀሱ አስከፍቷቸው ይመስለኛል ቢጫን አራተኛ አድርገው ጨምረው ጠቅሰዋል፡፡

ቢጫን ጠቅሰው አራት ቀለማት አደረሱትና አራቱ ቀለማት የአራቱ ባሕርያተ ሥጋ የውኃ፣ የመሬት፣ የነፋስ፣ የእሳት ምሳሌ ነው!” ብለው ተረጎሙት፡፡ ይሄም “‘ከእንግዲህ ወዲህ ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ እና ከአምስተኛ ባሕርየ ነፍስ የተፈጠረ የሰውን ልጅ በንፍር ውኃ አላጠፋውም!’ ሲል ነው!” ብለው ተርጉመውታል፡፡

ነጩን የውኃው፣ ቢጫው የመሬት፣ ጥቁሩ የነፋስ፣ ቀዩ የእሳት ምሳሌ ነው አሉት፡፡ አክለውም “…. ከእመቤታችን ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ አምስተኛ ባሕርየ ነፍስ ደማዊት ነፍስን ነሥቶ የመዋሐዱ ምሳሌ ነው!” ብለውታል፡፡ አንድም አሉና ነጩን የውኃ፣ ቢጫው የሥጋ፣ ጥቁሩ የደሙ፣ ቀዩ የመንፈስቅዱስ ምሳሌ ነው!” አሉት፡፡

የጥንቱ ሦስቱን ቀለማት ብቻ የሚጠቅሰው በሊቃውንቱ አንደበት የሚነገረው ትርጓሜ ግን ሦስቱን ቀለማት ይጠቅስና አነኝህ በአንድ የሆኑት ሦስቱ ቀለማት የአንድነቱ የሦስትነቱ ምሳሌ ነው!” ይሉታል፡፡ አክለውም ቀዩ በኋለኛው ዘመን ደማዊት ነፍስን ነሥቶ የመዋሐዱና በደሙ ዋጅቶ የማዳኑ ምሳሌ ነው!” ይላል፡፡ ነጭ ያሉት ቢጫው ቀለም ደግሞ የብርሃነ መለኮት ወይም የግርማዓ መለኮት ምሳሌ ነው!” ይላል፡፡ ጥቁር ያሉት አረንጓዴው (ቅጠልያው) ደግሞ የልምላሜ ገነት መንግሥተሰማያት ምሳሌ ነው!” ይልና በኋለኛው ዘመን ሰው ሆኖ ተወልዶ በአማናዊው በግ በክርስቶስ ቤዛነት አዳምንና የልጅ ልጆቹን ወደገነት መንግሥተሰማያት የሚያስገባቸው የሚመልሳቸው መሆኑን ሲያጠይቅ ነው!” የሚል ትርጉም ይሰጡት ነበር፡፡

የተስፋ ገ/ሥላሴ ማተሚያ ቤት ተርጓሚዎች ቢጫውን ቀለም ቀርቷል ወይም ተረስቷል ብለው አራተኛ አድርገው ጨምረው ሲጠቅሱ ለምን በግልጽ የሚታየውን አረንጓዴውንም ተረስቷል ሳይሉ እንደተውት ነው ያልገባኝ፡፡ ጥቁር የተባለው አረንጓዴው መሆኑ ከገባቸው ደግሞ ነጭ የተባለው ቢጫው እንደሆነስ እንዴት ሳይገባቸው ቀረ ታዲያ??? ምናልባት ቀለማቱ አምስት ከሆኑ የሚሰጡት ምሳሌ ቸግሯቸው ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን “…. ከእመቤታችን ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ አምስተኛ ባሕርየ ነፍስ ደማዊት ነፍስን ነሥቶ የመዋሐዱ ምሳሌ ነው!” ያሉትንና “‘ከእንግዲህ ወዲህ ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ እና ከአምስተኛ ባሕርየ ነፍስ የተፈጠረ የሰውን ልጅ በንፍር ውኃ አላጠፋውም!’ ሲል ነው!” ያሉትን አስተካክሎ ይተረጉምላቸው ነበር፡፡ የአምስቱ አዕማደ ምሥጢራት ምሳሌ ነው ማለትም አይችሉ ነበር!!!

ይሄ ማተሚያ ቤት እንዲህ ዓይነት የድፍረት ሥራዎችን መሥራት መለያ ጠባዩ ካደረገው ቆይቷል፡፡ ከቤተክርስቲያኗ አስተምህሮ ጋር የሚጻረር ነገር በእመቤታችን ተአምር ስም ከቤተክርስቲያኗ ተአምረ ማርያም ላይ ጨማምሮ ያተመውን ተአምረ ማርያም መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሚሊዮን!” የሚል የእንግሊዝኛ የቁጥር ስምንም በግእዝ መጽሐፍ ላይ እስከመጠቀም የደረሰ የድፍረት ስሕተትም እየፈጸመ ይገኛል፡፡ ሌላም ሌላም ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ማተሚያ ቤቱ የግል ስለሆነ በልቡ አዳሪ ነው፡፡ ማተሚያ ቤቱ እነኝህን ስሕተቶቹን አርሞ በርካታ የሠራቸውን መልካም ሥራዎቹን እንደጠበቀ ቢዘልቅ ለራሱም ሆነ ለቤተክርስቲያን መልካም ነው!!!

ሲጠቃለል በላይ በተጠቀሰው መልኩ ቤተክርስቲያንን አሳስተን እየተጠቀምንበት ያለው ሦስቱ ማለትም ጥቁሩ፣ ነጩና ቀዩ የማተብ ክር ቀለማት ከላይ እንደገለጽኩት የተሳሳተ ስለሆነና መታረምም ስላለበት ስሕተቱ እንዲታረም ከካህናትና እስከ ምእመናን ያለን ሁላችንም የየበኩላችንን ኃላፊነት እንድንወጣ አጥብቄ ለማሳሰብ እወዳለሁ!!!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል፣ ወለመስቀሉ ክቡር አሜን ወአሜን ለይኩን ለይኩን!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው