የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)
Ethiopian People’s Revolutionary Party (EPRP)
መስከረም 27 ቀን 2012 ዓ. ም
የወንድማማቾች መገዳደል ይቁም!
ህወሓት ከሃያ ስምንት ዓመት በፊት አገራችን ላይ የጫነው ጎሣን መሠረት ያደረገ ሕገ መንግሥት አሁንም በጥፋት ላይ ጥፋት እያስከተለ ነው። ባለፈው ዓመት በቤንሻንጉል፣ በጋምቤላ፣ በኦሮሚያ፣ በሃዋሳ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በሐረር እንዲሁም በሰሜን ምዕራብ ጎንደር በተፈጠረው ግጭት በርካታ የሰው ሕይወት ጠፍቷል። ግምቱ በውል ያልታወቀ ንብረትም ወድሟል። ንጹሃን ዜጎች ሃብት ንብረት አፍርተው ከኖሩበት ቀዬ ተፈናቅለዋል። እነዚህን ግጭቶች የቀሰቀሱት ጠባብ አመለካከት ያላቸው ጥቂት አክራሪ ብሄርተኞች መሆናቸውን መንግሥት በሚገባ ያውቃል። ነገር ግን ጠንከር ያለ ሕጋዊ እርምጃ ባለመውስዱ የጥፋት ኃይሎቹ ከተደበቁበት እየወጡ ጥፋት ከማድረስ ወደኋላ አላሉም። ዛሬ በጎንደርና አካባቢዋ እየጠፋ ያለው ሕይወት ባለፈው ዓመት የነበረው የጥፋት እንቅስቃሴ ተቀጥላ ነው። መንግሥት የጥፋት ኃይሎቹን ተከታትሎ ወደ ሕግ ባለማቅረቡ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል። የዚህ ሁሉ ችግር ምንጩ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ነው፣ የሕገ መንግሥቱም መሠረት አክራሪ የብሄርተኝነት አመለካከት ነው። ይህ ባልተለወጠበት ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ የተረጋጋ ኑሮ ሊሰፍን ይችላል ብሎ ማመን አይቻልም።
በአሁኑ ሰዓት ጎንደር የጦር ቀጠና ሆናለች፣ ጎንደርን ከመተማ የሚያገኛው መንገድ ዝግ ነው። ትምህርት ቤት ወቅቱን ጠብቆ መከፈት አልቻለም። ነጋዴውና ገበሬው የዕለት ተዕለት ሥራውን ሠርቶ መኖር አልቻለም። በመተማ በኩል ሱዳንን ከኢትዮጵያ የሚያገናኘው መሥመርም ዝግ ነው። ይህ ማለት ከጎረቤት አገር ጋር የሚያገናኝ አውራ ጎዳና ተዝግቷል፣ ንግድም ቁሟል ማለት ነው። የጎንደር ከተማ ቀን ቀን በወታደር ኃይል ሰላም ትመስላለች ሌሊት ግን ጨለማን ተገን በመድረግ እንደ ሶሪያ የጥይት እሩምታ ይዘንብባታል፣ በብሄረስብ ላይ ያነጣጠረ ዝርፊያና ግድያም ሲፈጸም ያድራል። አማራና ቅማንት በቋንቋ፣ በባህልና በእምነት አንድ ሆኖ የኖረ ኅብረተሰብ ነው። ይህ ኅብረተሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ብሄረሰቦች ሁሉ ይበልጥ የተጋባና የተዋሃደ እንደሆነ ብዙ ማሳያዎች አሉ። ኢሕአፓ በምሥራቅ፣ በምዕራብ፣ በሰሜንና በማዕከላዊ ጎንደር ለረዥም ዓመታት በተንቀሳቀሰበት ጊዜ የኖረው ከአማራና የቅማንት ኅብረተሰብ ጋር ነው።
እስካሁን ድረስም በርካታ አባሎቻችን ከሁለቱም ማኅበረስቦች የተውጣጡ ናቸው። ልዩነታቸውን አላየነም። በሁለቱም በኩል ያየነው ነገር ትጉህ፣ የዋህ፣ እንግዳ ተቀባይና ጠንካራ ሠራተኞች መሆናቸውን ነው። በማኅበራዊ ኑሮ በኩል በደምና በአጥንት የተዋሃዱ መሆናቸውን ነው የተማርነው። ዛሬ ይህን አብሮነታቸውን የሚያፈርስ ችግር ከፊታቸው የተደቀነ በመሆኑ እየደረሰ ያለው ጥፋት ብዙ ርቆ ሳይሄድ የአማራና የቅማንት ማኅረሰቦች በዕድሜ ጠገብ የሀገር ሽማግሌዎች አማካኝነተ በአንድነት ሆናችሁ በባህላችሁ መሠረት ተወያይታችሁ ችግሩን እንድተፈቱት በአክብሮት ጥሪያችንን እናቀርባለን።
መገዳደልና መፈራርጅን ለማስቆምና ሁለቱን ወንድማማች ብሄረሰቦች ወደነበሩበት አንድነትና ፍቅር ለመመለስ መንግሥትና ይመለከተናል የሚሉ አካላት ሁሉ ከልብ ሊሠሩበት ይገባል። በተለይም ፀጥታ የመጠበቅና የማስጠበቅ ሃላፊነት የመንግሥት ነውና መንግሥት የድርሻውን እንዲወጣ እንጠይቃለን፣ ጉዳዩን በሙያው ላልሰለጠኑ ዜጎች መተው ሥርዓት አልበኝነትን መጋበዝ ይሆናልና። በተጨማሪም መንግሥት ከዚህ በፊት የጀመረውን የቅማንቱንና የአማራውን ማኅበረሰብ አቀራርቦ ማነጋገርና በሁለቱም በኩል ልጆቻቸውን መክረው ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንዲመለሱ እንዲያደርጉ ጠንካራ ሥራ ሊሠራ ይገባል።
በተጨማሪም አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ችግሮችን ይበልጥ ሊያውሳስቡ የሚችሉ ዜናዎችንና ቃለመጠይቆችን ከማቅረብ እንድትቆጠቡ እያሳሰብን፣ ሃላፊነት በተሞላው መልክ የሰፈነውን ውጥረት ለማርገብና ለማረጋጋት ተግታችሁ እንድትሠሩ እንጠይቃለን።
በሌላ በኩል ህወሓት ያገሪቱን ሰላምና አንድነት የማይፈልጉ ኃይሎችን መቀሌ ውስጥ በቅርቡ ሰብስቦ መምከሩ ተረድተናል። የቅማንት የማንነት ጥያቄ ኮሚቴ ከተሰብሳቢዎቹ አንዱ ሆኖ ለጥፋት ስምሪት መታጨቱ የአደባባይ ሚስጥር ሆኗል። ኮሚቴው የቅማንትና የአማራን ታሪካዊ ትስስር ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ሁለቱን ማኅበረሰቦች በማቀራረብ አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ እንዲሠራና ሃላፊነቱን እንዲወጣ እናሳስባለን።
የሞቱትን ነብስ ይማር፣ ቤተሰቦቻቸውንም መጽናናቱን ይስጥልን
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ልጆቿን ይባርክ !!!!

Ethiopian People’s Revolutionary Party (EPRP)
መስከረም 27 ቀን 2012 ዓ. ም