የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)
Ethiopian People’s Revolutionary Party (EPRP)
መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ. ም
ዝም አንልም!
እንዴት ዝም እንላለን? ዝም አንልም! ማለትም የለብንም! ይህንን ዝም ብሎ ማለፍ ከኃጢያትም በላይ ኃጢያት ነው። የፍቅር ዘመን እንዲሆን የአዲስ ዓመት ምኞት ከተመኘን ገና አንድ ወር ሳይሞላን፣ ሰላምና የሕግ የበላይነት እንዲመጣ ሕዝቡ ካለው ታላቅ ምኞት የተነሳ የመስቀልን በዓል የክልልና ብሄራዊ መንግሥታቱ እንድንሆን በፈለጉን መልኩ ሆነን ካከበርን ገና አንድ ሳምንት ሳይቆጠር፣ የኢሬቻ በዓል ጉድ አሰማን። የኦሮሚያው ም/ፕሬዘዳንት የአቶ ሽመልስ አብዲሳ የጥላቻ ንግግር ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ሲያስተጋባ፣ ጭብጨባና እልልታ ሲያጅበው፣ አዲስ አበባ ስትናጋ፣ የአቶ ሽመልስ ልብ በደስታ ጮቤ ስትረግጥ የስንቱን ኢትዮጵያዊ ልብ እንዳደማ አላሰበም።
ባለፉት ዓመታት የደረሱትን ዘግናኝና ኢ–ሰብዓዊ ጥቃቶች ለኢትዮጵያ ሲባል ለመርሳት ከራስ ጋር የሚደረገው ትግል ገና ሳይደላደልና ራስን ማሸነፍ ሳይቻል፣ ከፍተኛውን የክልሉን የፖለቲካ ሥልጣን የጨበጠው አቶ ሽመልስ በኢሬቻ የበዓል አከባበር ላይ በቁስሉ ውስጥ እንጨት ሳይሆን ሰይፍ ሰነቀረበት። በርካታ የዋህ ልቦችን አደማ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት ሲሉ አደብ ለመግዛት በጥረት ላይ ያሉትን ሁሉ ከመቀመጫቸው ፈንቅሎ አስነሳቸው፣ ቀደም ሲል ባጋጠሙት ጥቃቶች ሁሉ፣ ሊነጋ ሲል ይጨልማል እንጂ ለኢትዮጵያ የተስፋ ጎህ ይፈነጥቃል፣ ብለው ሩቅ የሚመለከቱትን ሁሉ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የከተተ ንግግር! ከአንደበቱ ብቻ ሳይሆን ከገጽታው ላይ የሚንበለበለው አቶ መልስ የራሴ ያለውን ሕዝብ ለማስደሰት ሲል በጥላቻ በታጀሉ ቃላት አየሩን በከለው።
ጥላቻ መርዝ ነው!
በፍጹም ዝም አንልም! ይህ የጥላቻ መርዝ ሃላፊነት ከጎደለው አንደበት የወጣ እንጂ ከሕዝብ ወደ ሕዝብ የተወረወረ መርዝ አይደለም። በአዲስ አበባ በዓሉን ለማክበር የተሰበሰበና በደስታ ብዛት በስሜት ውስጥ ገብቶ የተሳከረ ታዳሚ አጨበጨበ እንጂ የኦሮሞ ሕዝብ ለዚህ ለሰላም ሳይሆን ለጸብ፣ ለፍቅር ሳይሆን ለጥላቻ ከተዘጋጀ አንደበት ለተሰነዘሩ ቃላት ዕውቅናና ይሁንታአይሰጥም። አብረን ተባብረን ኢትዮጵያን ለመገንባት የጀመርነውን የጠነከረ ግንብ እንዲንድብን አንፈቅድለትም፣ በውስጧም አብረን በብልጽግና ለመኖር ሩቅ እያየን የጀመርነውን ጉዞ አያጨናግፍብንም።
አሁንም ቢሆን፣ እንደበፊቱ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ኦሮሞም ሆነ አማራ፣ ትግራይም ሆነ አፋር፣ ወላይታም ሆነ ሲዳማ፣ ሶማሌም ሆነ ጋምቤላና ሌሎችም ብሄር ብሄረሰቦች፣ ለሰላም፣ ለፍቅርና ወንድማማችነት ባላቸው የማይናጋ አቋም ላይ ያለን ጽኑ እምነት አሁንም በአቶ ሽመልስ የተዛባ ንግግር ንቅንቅ እንደማይል ለአቶ ሽመልስና ለአክራሪ ጠባብ ብሄረተኞች መልሰን ልናሳውቃቸው እንወዳለን።
ሌላም ልናሳውቃቸው የምንፈልገው ትልቅ ጉዳይ አለ። ኢሕአፓና መሰል ድርጅቶች ቲም ለማ የጀመረው የለውጥ ሂደት ለአገራችንና ለሕዝቧ የተሻለ ዘመን ሊመጣ ነው ብሎ አምኖ በነቂስ በመውጣት ያሳዩትን ገደብ የሌለው ድጋፍ ባልታገተ በአንደበታቸውና በሌሎች እንደ ሕዝብ የማፈናቀል ዓይነት አስነዋሪ ተግባሮቻቸው ምክንያት እንድንጠራጠር እያደረገንእንደሆነ እንዲያውቁት ያስፈልጋል። የለውጡን ሂደት የመቀልበስ ሙከራ ከህወሓት እንጠብቅ ነበር እንጂ ከለውጥ አራማጁ ወገን ይመጣል ብለን አላሰብንም። አሁን ያለው ሁኔታ ይህን አንፀባራቂ በመሆኑ በጣም አስጊና አስፈሪም ነው።
በዚህ ሃላፊነት በጎደለው በአቶ ሽመልስ ንግግር በሕዝብ ቁስል ውስጥ የተሰነቀረው ሰይፍ ውሎ አድሮ ሳያመረቅዝ በቶሎ ህክምናው መጀመር አለበት። ህክምናውም አቶ ሽመልስ በይፋና በአደባባይ በማናለብኝነት ሕዝብ እንዲጋጭ የሚያነሳሳ ንግግር በማድረጉ ሕዝብን በአደባባይ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል። አቶ ሽመልስ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነትና አብሮነትየሚያጠናክር ሳይሆን የሚበትን፣ ሕዝብን በሕዝብ ላይ የሚያነሳሳና ሀገሪቱንም ወደ ብጥብጥ እንድታመራ የሚያደርግ ንግግር ያደረግ የኦሮሚያ ክልል መሪ ታላቁን የኦሮሞ ሕዝብ ለማስተዳደር የሞራል ብቃት የለውም። አቶ ሽመልስን ያደፋፈሩና የልብ ልብ የሰጡት የመንግሥት ባለሥልጣናትም የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል።
ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ የለገጣፎ የረዥም ጊዜ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን አስመልክቶ ሲጠየቁ እኔ ከንቲባ አይደለሁም፣ የማውቀው ነገር የለም ብለዋል። የአቶ ሽመልስ ንግግር በተወሰኑ ግለሰቦች ላይ የተነጣጠረ ሳይሆን የሕዝብን ልብ የወጋ ንግግር በመሆኑ አላውቅም ወይም አልሰማሁም በማለት የሚታለፍ ሊሆን አይችልም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁልጊዜ እንደሚሉት የኢትዮጵያውያንን አንድነት ለማጠናከርና ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት፣ ለዚህ የሕዝብ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እርምጃ በመውሰድ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ይጠበቅባቸዋል። የግፍ ጽዋ ሞልቶ ካልፈሰስኩ በሚልበት በአሁኑ ወቅት፣ እንዲህ ያለው ሕዝብን የመናቅ ተግባር ሕዝብን ሊያነሳሳ እንደሚችል አስቀድሞ መረዳት ብልኅነት ነው። ይህ ካልሆነ ለኢትዮጵያ ሲባል የተጀመረው ከራስ የመታገልና ለዘር ሳይሆን ለሀገር የመቆም ጥረት ሊቀጥል አይችልም። የሃገሪቱን ህልውና ክፉኛ የሚፈታተንና በለውጡ ሂደት የተፈጠረውን መልካም ተስፋ ሰጪ የሕዝብ ግንኙነትን የሚንድ ይሆናል።
-
ይህ ደግሞ ለማንም አይበጅም።
አሁንስ ዝም አንልም!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
