October 12, 2019
Source: https://www.zehabesha.com/amharic/archives/97453
የኖቤል ሽልማቱ የኢትዮጵያ ሰዎች ፣ ሰው መሆናቸውን ለጨቋኝ ገዢዎች ለማሥገንዘብ ላደረጉት ተጋድሎ የተሰጠ ሽልማት ነው።
ክብሩ ጠቅላይ ሚኒሥቴር ፣ዶ/ር አብይ አህመድ ፣የ2019 ዓ/ም የዶ/ር አልፍሬድ ብርን ሃርድ ኖቤልን የሰላም ሽልማት በመሸለሟ እንኳን ደሥ አለዎ። ሽልማቱ የኤርትራ ና የኢትዮጵያ ሰዎች ሽልማት በመሆኑም ደሥታችን እጥፍ ድርብ ነው።የሞት ድግሥ የሚደገሥባትን የኤርትራን ምድር የሰላም፣የልማትና የብልፅግና ድግሥ እንዲደገሥባት እና ወንድምና እህቶቻችን ” እፎይ” እንዲሉ አድርገዋልና ሽልማቱ ይገባወታል። ክቡሩ ጠቅላይ ሚኒሥቴር፣ በመጀመሪያው የሥልጣን ዓመትዎ የፈፀሙት ፖለቲካዊ ተግባር በአምሥትና በአሥር ዓመት ውሥጥ ይፈፀማል ተብሎ ያልተገመተ ነበርና ከሊቅ እስከደቂቅ እስከ ዓመቱ ማገባደጀ ድረስ እጅግ በሚሥገርም መልኩ ደግፎወታል። ዛሬ ግን እንደግለሰብ እርሶ የዘር ና የቋንቋ ክፍፍልን ለሥልጣን መደላድላቸው የሚያቀነቅኑትን የፍቅርና የአንድነት ጠላቶች፣ ባይደገፉም ፣ በመሪነትዎ ፣ ከሁሉም ጋር በመወያየት ” ሁላችንንም ወደሚጠቅመን የብልፅግና መንገድ ፣ ወደ አንድነት እንምጣ።…” በማለት ፣ሁሉንም ላለማሥቀየም የሚያዱርጉትን ጥረት ባለመገንዘብ ፣ከፅንፈኛ የቋንቋ አክራሪዎች ምክር ይቀበላሉ ብሎ በማመን(ይማክሯቸዋል እንጂ እንደማይመክሯት በግሌ ባምንም) በቋንቋዊው ሥርአቱ ፣ድብልቅ የሆነው የከተማ ኗሪ ፣ነፃነቱን በማጣቱ ሰበብ አመራርዎን በጥርጣሬ እያየ ነው። “ቀድሞ በሥርዓቱ ውሥጥ ያሉ ሌቦች ፣ዛሬም በቋንቋ ሥም ለግል ምቾታቸው ዘላቂነት እስከነ ግብረአበሮች ጋር ይጮሃሉ እንጂ እኛ ጠብ ያለልን ነገር የለም።በየጊዜው ኑሯ እያማረረን ፣ መኖር ከአቅማችን በላይ እየሆነ መጥቷል። በለውጡ ቢያንሥ የከተማው ነዋሪነታችን አልተረጋገጠልንም።ዜግነታችንም አደጋ ላይ ወድቋል።ባዩ ጥቂት እንዳይደለ ከእርሶ የተሰወረ አይደለም እና በጥናት ላይ የተመሰረተ ለውጥና ቢያንስ በየክልሉ አማርኛን ተጨማሪ የሥራ ቋንቋ ማድረግ የወደፊት የቤት ሥራዋ ይመሥለኛል።ይኽንን ካላደረጉ የቋንቋ አፓርታይድ ይህቺን ሀገር እያተራመሰ መቀጠሉ አይቀሬ ነው። በፓርላማ አማርኛን እስከተጠቀሙ ድረስ በክልል እንደ ሁለተኛ ቋንቋነት አማርኛን መጠቀም ምን ይገዳቸዋል ??? ቋንቋ መግባብያ እንጂ የመጨቆኛ እና ሰውን ከሰው መለያ መሣሪያ አይደለም። ይሁን እንጂ የቋንቋ አረቄ ጭንቅላታቸው ላይ የወጣ በህገመንግሥቱ የተቀመጠው መብት እንኳ ተግባራዊ እንዳይሆን እያገዱት ነው።የአዲሥ አበ ነዋሪ ድብልቅ ነው። የአፍመፍቻ ቋንቋውም ብዙ ነው።በአንድ የሚያግባባው ቋንቋ ግን አማርኛ ነው።እንደ አዳማ፣ሻሸመኔ ፣ቢሾፍቱ፣አዋሳ፣ወላይታ፣መቀሌ፣አሰላ፣ድሬደዋ፣ሐረረ፣ጅጅጋ፣ወዘተ በመሣሠሉ በአደጉና በማደግ ላይ ያሉ፣ ከተሞች ሁሉ፣ እናም ለምንድነወ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳያደርግ የተከለከለው? ሰዎች ጠመንጃ ይዘናል ብለው ፣እስር ቤት አለን ብለው ዛሬ ቢመኩ ነገ የቀኃሥ፣የደርግ ና የወያኔ ዕጣ እንደሚያጋጥማቸው ሣይታለም የተፈታ ነው።እኔ እያዘንኩ ያለሁት ማመዛዘን በጎደላቸውባለሥልጣናት ሰበብ ሰው መሆኑን በሚያምነው ዜጋ ተሰሚነትዋ እየቀነሰ መምጣቱ ነው። እውነቴነው ለሀገሬ አለቀሥኩላት። ክብሩ ጠቅላይ ማኒሥቴር ፣ የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት ለእርሶ መሰጠቱ ፣ከኖቤል አለማ አንፃር በጣም ትክክል ና ተገቢ ነው። ለመሆኑ አልፍሬድ ብርን ሃርድ ኖብል ማነው? ዶ/ር አልፍሬድ ብርንሃርድ ኖቤል፣ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ጥቅምት 21 ቀን 1833 ተወልዶ ትህሳስ 20 ቀን ዓለምን የተለያት ሲዊዲናዊ የታወቀ የጦር መሣሪያ ነጋዴ (ኢንጂነር አባቱ ፣ ኢማኑኤል ኖቤል የጦር መሳሪያ ፋብራካ የነበረው ነጋዴ ነበር።) ፣ኬሚሥት፣ኢንጂነር፣የብዙ ፈጠራ ባለቤት በመጨረሻም የበጎ አድራጎት ሰው ነበረ። ኖብል የ355 የግል ፈጠሬዎች ባለቤት ነው።ከፈጠራዎቹ ትልቁ ዳይናሚት እና ከዳይናማይት አሻሽሎ የሰራው ለማዕድናት ፍለጋ የሚያገለግለው ጂሊግናይት(gelignite) ቦፎርስ(bofors) የተባለው ግኝቱም ለመድፍ እና ለአየር ሙቃወሚያ ጥይቶች መሥሪያ የሚያገለግል ነው። በኬሚሥትሪ ኤለመንቶች ውስጥ አንድ ኤለመንት “ኖቤል ኤለመንት” ተብሎ ተሰይሞለታል። ዶ/ር አልፍሬድ ብርንሃርድ ኖቤልን ፣ኖቤል የሽልማት ድርጅትን ለመመሥረት ና በምድር ላይ ለሚከናወን በጎ የሣይንሥ ተግባር ፣ለሱው ልጅ ጠቃሚ ለሆኑ የኬሚሥትሪ ፣የህክምና ፈጠራዎች እንዲሁም የመላው ዓለምን አሥተሣሠብ የሚያንፅ ፣ሥነፅሁፍ ለፃፉ እና ድንበር ተሻጋሪ የሆነ ተጨባጭ የሰላም ተግባር ላከናወኑ ለመሥጠት ያነሳሳው አጋጣሚ እአአ አቆጣጠር በ1888 የተከሰተ አጋጣሚ ነው። ይህ አጋጣሚ የወንድሙ ሉዱየይግ ኖቤል መሞትና አንድ የፈረንሳይ ጋዜጣ በአሥደንጋጭ መልኩ ያልሞተውን አልፍረሬድ ኖብልን ሞቷል ብሎ ሥሙን በሚያጠለሽ መልኩ በመፃፉ ነው። ፅሁፉ እንዲህ ይላል “Le marchand de la mort est mort” (the merchant of death is dead) ” የሞት ነጋዴው ሞተ።” “Dr Alfred nobel ,who become rich by finding ways to kill more people faster than ever before ,died yesterday.” “ዶ/ር አልፍሬድ ኖቤል ከመቼውም ይልቅ በዓለማችን ብዙ ሰዎች በአንድ ጊዜ የሚገድል የጦር መሣሪያ ፈለሰፎ በመሸጥ ሀብታም የሆነው ትላንት ሞተ” ይህን ፅሁፍ ሢያነብ ፣ ልጅ የሌለው አልፍሬድ ኖብል በጣም አዘነ። ከፈለሰፋቸው አውዳሚ ጦር መሣሪያዎች ይልቅ ሥሙ በመልካም እንዲጠራ 94% ሀብቱን(1, 687,837 ፓውንድ በ2012 ይህ የሽልማት ብር 472 ሚሊዮን መድረሱ ይታወቃል።) ለሰው ለጆች፣ዕድገት፣ልማት ብልፅግና እና ሰላም የጎላ አሥተዋፆ ለሚያደርጉ ምርጥ የዓለም ሰዎች ይበርከትልኝ በማለት ህዳር 27/1895 ይህንን የሽልማት ድርጀት አቋቁሞ። በነገራችን ላይ ፣ይኽ ሽልማት በ 1901 እኤአ ነው የተጀመረው። የ2018 የሠላም የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች ኮንጎዊው የመሐፀን ሀኪም ዴኒስ ሙክወንጋ እና በአይስስ ታፍና የነበረቺው ናድያ ሙራድ ነበረች።ለሁለቱ ነበር ሽልማቱ የተበረከተው። የ 2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት ተሸላሚ ደግሞ ዶ/ር አብይ የኢትዮጵያ ጠ/ሚ ብቸኛ ተሸላሚ ናቸው። ይህ ሽልማት የኢትዮጵያ ህዝብ ሽልማት ነው።( የመናገር፣የመፃፋ፣ሃሳባቸውን ያለአንዳች ፍርሃት የመግለፅ፣የፈለጋቸውን ፓርቲ የመደገፍ፣የመቃወምና የመተቸት መብቶቻቸው ያልተከበረላቸው፣ ሆኖም ግን በአሸባሪነት፣ በሰላም አደፍራሺነት ተጠርጥረው፣ያለአንዳች ክስ እሥር ቤት የታጎሩ ፣” አሳብያን” መኖራቸውን በበቂ ማሥረጃ አስደግፈው አያሌ ምሁራን በየቀኑ ይጮኸሉ ና እኔም በአሥቸኳይ ይፈቱ እላለሁ። እነዚህ አሳብያን እንዲፈቱ ጠ/ሚ ጣልቃ እንዲገቡም በማክበር እጠይቃለሁ።…) ይኽ ሽልማት በዋናነት የኢትዮጵያ ህዝብ ጭቆና ይብቃ።እሥር ይብቃ።ዘረፋ ይብቃ።የኃይል አገዛዝ ይብቃ። የድብቅ ግድያና ቶርቸር ይብቃ ብሎ ለሰው ነፃነት ና ፍትህ በመታገሉ የተገኘ ሽልማት ነው። ሽልማቱ ፣የህዝቡ ትግል ተገቢ ና ትክክኛ ጥያቄ የያዘ መሆኑን ፣ የእርሶ ፓርታ ቁንጮ አመራሮች ፤ የአቶ ደመቀ መኮንን ፓርቲ አመራሮች ፤ የደቡብ ህዝቦች ፓርቲ መሪ በቆራጥነት ” የብዝበዛ ተባባሪ ሆኜ አልቀጥልም። የይስሙላ ጠቅላይ ሚንሥቴርነት ይብቃኝ።” በማለታቸው የተገኘ ፣ ነው። ሽልማቱ የኢትዮጵያ ሰዎች ሽልማት ነው።ሽልማቱ በቋንቋው፣በዘሩ፣በኃይማኖቱ ሰውን አውቀዋለሁ እንጂ በሌላ አላውቀውም የሚሉ ሰዎች ሽልማት አይደለም።እነዚህማ ፀረ-ሠላም ናቸው።እነዚህማ የሰው ፈጣሪ አንድ መሆኑን የማያምኑ ናቸወ። “ዋቃ” አልነው፣” አላህ “አልነው፣”እግዛብሔር” አልነው ፣”GOD” አልነው፣ ፈጣሪ አንድ ነው። የማይጨበጥና የማይዳሰሥ ከሰባት ቢሊዮን የበለጠውን የዓለም ሰው በተመሳሳይ ሰዓት፣ባሉበት ሥፍራ እና ሁኔታ ውሥጥ የሚያሥተውል፣ልባቸውንም የሚመረምር ነው ፣የሰው አእምሮ በማሰብ ብዛት የማይደርሥበትም ኃያልና ሁሉን ቻይ አምላክ ነው።ፈጣሪያችንን በየማይክሮ ሰኮንዱ በሚከናውነው ታለቅ ሥራ ና ተአምራቱ ፣ እሥከ እሥትፋሳችን ማክተም ድረሥ ማደነቅ ደግሞ የእኛ የሰዎች የዘወትር ተግባር ነው።እርሶም ክብሩን ለፈጣሪ እንደሚሰጡ አምናለሁ።
ክብር ለፈጣሪ ፣ ለእግዚአብሔር አምላክ ይሁን።አሜን!!