October 16, 2019

Source: https://fanabc.com

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባውን በማካሄድ ላይ ይገኛል።

ማእከላዊ ኮሚቴው ስብሰባውን በአዲስ አበባ ከተማ ነው በማካሄድ ላይ የሚገኘው።

የኦዲፒ ማእከላዊ ኮሚቴ በስብሰባውም የፓርቲውን እና የክልሉን መንግስት የስራ አፈፃፀም በመገምገም አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ይጠበቃል።

በዚህም ኮሚቴው የነበሩ ጥንካሬዎችን እና ድክመቶችን በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ነው የተባለው።

እንዲሁም ማእከላዊ ኮሚቴው በወቅታዊ ሀገራዊ እና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ተጠቁሟል፡፡

የኦዲፒ ማእከላዊ ኮሚቴ በስብሰባው የፓርቲው የውስጥ አንድነት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሪፎርምንም በአጀንዳ መያዙን ተነግሯል።

ከዚህ በተጨማሪም ማእከላዊ ኮሚቴው እንደ ሀገር እና እንደ ክልል የተጀመሩ ለውጥ እንቅፋቶችን በመለየት አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ነው የሚጠበቀው።

ጉባኤው በጀመረበት ወቅት የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማትን በማግኘታቸው ደስታቸውን በመግለፅ ስጦታ አበረክተውላቸዋል፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስተሩ ሽልማቱን የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር እና የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ለማ መገርሳ አባላቱን በመወከል አበርክተዋል፡፡

በዚህ ወቅት አቶ ለማ ባደረጉት ንግግር ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተበረከተው ሽልማት ለኢትዮጵያ ህዝብ ትግል እውዕና የሰጠ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከነበረችበት ደረጅ አንድ ደረጅን ከፍ ብላ ተቀባይነት ያገኘችበት ሽልማት መሆኑን ነው አቶ ለማ መገርሳ ያነሱት፡፡

የሽልማቱን አውቅና ማቆየት የሁላችንም ሃላፊነት ነው ሲሉ አቶ ለማ መገርሳ ተናግረዋል፡፡

የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው ሰላም ወዳድነታችን ድንበር ተሻግሮ እውቅና እግኝቷል ብለዋል፡፡