ሁሌ እናስታውሳቸው
ተቀብሮ እንዳይቀር
አኩሪ ታሪካቸው!!!
መርድ ሽፈራውና መሰረት ሽፈራው እነማን ናቸው??


በጓዱ አብሮ አደጉ አብዱልዋሂድ መሃመድ እንደተነገረው፤…
ከአንድ ቤት ሁለት ከአንድ ቤት ሶስት እንደሚባለው የደርግ ግፍ፤ ሁለቱም ወንድምና እህት የፋሺስቱ ድርግ አስከፊ ስርአት ሰለባ በመሆን በትግል የተሰዉ ወጣቶች ናቸው።
የመሰረት ሽፈራው ታናሽ ወንድም መርድ ሽፈራው ከአባቱ አቶ ሽፈራው ከእናቱ ከ ወይዘሮ አበበች ተስፋዬ በ ሃምሌ 16/ 1949 በድሬ ደዋ ከተማ ተወለደ። መርድ ሽፈራው የመጀመርያ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ትምህፍቱን በ ብስራተ ገብርኤና በ እመቤታችን ት/ቤት ( Notre Dam School) ገብቶ ተከታትሏል።
እንደሌሎቹ ተማሪዎች የደርግ የእድገት በህብረት ዘመቻ ይመለከተው ስለነበር፤ በድሬ ደዋ አውራጃ በአይሻ ወረዳ ተመድቦ፤ ዘመቻውን ከሚቃወሙት አንዱ ስለነበር ሳይጨርስ ወደ ድሬ ደዋ ተመልሷል።
ከዘመቻም መልስ በ 1969 መጀመርያ፤ በ በህቡዕ ይካሄድ የነበረውን ኢሕአፓን ድርጅት በመቀላቀል ለዴሞክራሲና የህግ የበላይነትና ለጊዜያዊ ህዝባዊ መንግስት ሲታገል ከቆየ በኋላ ሰኞ ነሃሴ 23/1969 በጥቆማ ህዝብ ድርጅት በሚባለው የፋሺስት ወንጀለኞች ስብስብ ተይዞ ወደ ፖሊስ ጣብያ ተወስዶ ለእስር ተዳርጓል። በዚያን ወቅት እኔና ነብዩ በላቸውም ተይዘን እሱ ወደ ታሰረበት ድሬ ደዋ ወደሚገኘው አንደኛ ፖሊስ ጣብያ ተወሰድን።
ከአንድ ወር የእስር ቆይታ በኋላ እሁድ እለት መስከረም 15/1970 መርድ ሽፈራውን ጨምሮ 59 ጓዶቻችንን መርጠው ወደ ወህኒ ከወሰዷቸው በኋላ፤ ሰኞ እኩለ ሌሊት በኋላ፤ ማክሰኞ መስከረም 17/1970 ሁሉም ወጣቶች መልካጀብዱ መንገድ ተወስደው በጅምላ በግፍ ተረሽነዋል።
በድሬ ደዋ የ እመቤታችን ት/ቤትታ( Notre Dam School ) ከዚያም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ አመት ተማሪ የነበረችው ታላቅ እህቱ መሰረት ሽፈራውም በከፋ ክፍለ ሃገር ቦንጋ ወረዳ ጭሪ ዘመቻ ጣብያ ተመድባ ምንም ተከላካይና በቂ የመንግስት ጥበቃ በሌለበት፤ ጥቅማቸው በተነካ የመሬት ባላባቶች በዘመቻው ጣብያና በወጣቶቹ ላይ በተካሄደ ጥቃት፤ ከዚያም በሳር ጎጆአቸው ላይ በለቀቁት እሳት ከሌሎች ወጣቶች ጋር ተቃጥላ ተሰውታለች።
መሰረት ሽፈራው በተማሪው ትግል ንቁ ተሳትፎ የነበራት፤ ቆራጥና ሁሌም በ አላማዋ ፀንታ የቆመች ድንቅ ወጣትና የህዝብ ልጅ ነበረች። ለዚያም በጎህ መፅሄት በ 1968 እትሙ ላይ የተገጠመላት አነቃቂና አታጋይ ግጥም ምስክር ነው።
ክብር የህዝብን ጥያቄ አንግቦ ግንባሩን ለጥይት ለሰጠ ጀግና ትውልድ !!
ለህግ የበላይነት፤ ለሰላም ለዴሞክራሲና ለእኩልነት..
ሁሉንም ያካተተ የሽግግር መንግስት!!!
የተለያዩ የህዝብ ልጆችና ሰማዕታት አጭር ታሪክ (BIO)ይቀጥላል !!!