23 ኦክተውበር 2019

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽር እንደሻው ጣሰው
አጭር የምስል መግለጫ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽር እንደሻው ጣሰው

የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ዳይሬክተር ጃዋር መሀመድ በመንግሥት ተመድበውለት የነበሩት የደህንነት ጥበቃ አባላት በምሽት እንዲነሱብኝ ታዘዋል በሚል በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያስተላለፈው መልዕክት ቁጣና ተቃውሞን ቀሰቀሰ።

በዚህም ሳቢያ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የተቃውሞ ሰልፎች ያጋጠሙ ሲሆን በርካታ ወጣቶችም ድርጊቱን በመቃወም አዲስ አበባ በሚገኘው የጃዋር መሀመድ ቤት አቅራቢያ ተሰብስበዋል።

የጸጥታ ኃይሎችም በአካባቢው ተሰማርተው እንዳሉ የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽር እንደሻው ጣሰው በሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ላይ ቀርበው እንዳስረዱት፤ ጃዋር መሀመድ ለተከታዮቻቸውና ለደጋፊዎቻቸው ልታሰር ነው፣ ጥቃት ሊደርስብኝ ነው በማለት ያስተላለፉት መልዕክት ስህተት ነው ብለዋል።

“በፖሊስ ተወሰደብኝ ያሉት እርምጃ ስህተት ነው” በማለትም “በመንግሥትም በፖሊስም በኩል ምንም ዓይነት እርምጃ አልተወሰደባቸውም” ሲሉ ተናግረዋል።

ፖሊስ እንደወትሮው የየእለት ተግባሩን እያከናወነ እንደሚገኝም ጨምረው አመልክተዋል።

ፖሊስ ለውጡን ተከትሎ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች በሚንቀሳቀሱበትና በሚኖሩበት ስፍራ ችግር እንዳያጋጥማቸው የጥበቃ ከለላ ሲያደርግ መቆየቱን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በሀገር ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስተዋለ የመጣውን ሰላምና መረጋጋት ከግንዛቤ በማስገባት እንደማንኛውም ግለሰብ በሰላም ተንቀሳቅሰው መኖር እንደሚችሉ ስለታመነበት “የግል ጥበቃዎችን የማንሳት ሥራ ስንሰራ ቆይተናል” ብለዋል።

ወደፊትም ያሉትን ሁኔታዎች በማየትና አስፈላጊ የሆኑና ያልሆኑትን በመለየት የማንሳት እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የተዘጉ መንገዶች እንዲከፈቱና መደበኛ እንቅስቃሴዎች እንዲቀጥሉ ጥሪ ያስተላለፉ ሲሆን ፖሊስ የሕግ ማስከበር ሥራውን እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

“አሁን ያለው ሁኔታ ከቀጠለ ነገ ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንደሚገባ ግልጽ ነው” አቦይ ስብሃት

በዓለማችን የተበራከቱት የተቃውሞ ሰልፎች የሚያመሳስላቸው ነገር ይኖር ይሆን?

“ለውጡ ሐዲዱን ስቷል ብዬ ነው የማምነው” አርቲስት ታማኝ በየነ

ጃዋር መኖሪያ ቤት አቅራቢያ የተሰበሰቡ ግለሰቦች

ጃዋር እንደሚለው ማክሰኞ ዕኩለ ሌሊት አቅራቢያ ሁለት መኪኖች ወደሚኖርበት ቤት አካባቢ በመምጣት ጥበቃዎቹን “እኔ ሳላውቅ እቃቸውን ይዘው ቤቱን ለቀው እንዲወጡ” እንደተነገራቸው በፌስ ቡክ ገጹ ላይ አስፍሯል።

አክሎም ጥበቃዎቹ ለምን እንዲወጡ እንደጠየቁና ለስልጠና እንደሆነ እንደተነገራቸው እነሱም እንዳልተቀበሉ፣ ከዚያም ስልክ ተደውሎላቸው በአስቸኳይ ቤቱን ለቀው ካልወጡ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ጠቅሷል።

በጥበቃዎቹ ላይ ግፊቱ ሲበረታ ከእንቅልፉ ቀስቅሰው ሁኔታውን እንደነገሩትና እሱም ወደ አዛዡ ጋር ደውሎ ማብራሪያ እንደጠየቀና በመጀመሪያ ላይ “የተለመደው ጥበቃዎችን የመቀየር ሂደት መሆኑን” እንደተነገረው፤ ከዚያም ኃላፊው የተሰጠውን ትዕዛዝ ብቻ እያስፈጸመ መሆኑን ጽፏል።

ጃዋር ቀጥሎም ጉዳዩን የበለጠ ለማወቅ ከፖለቲካና ከጸጥታ አመራሮች ጋር መነጋገሩን እነሱም የተከሰተውን ነገር ከስር መሰረቱ ለማወቅ ቃል እንደገቡለት ገልጿል።

ይህንንም ተከትሎ በቤቱ አካባቢ በርካታ ደጋፊዎቹ መሰብሰባቸውንና በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በጃዋር ላይ የሚገጥሙ ማንኛውንም ነገሮች በመቃወም ሰልፎች እየተካሄዱ ነው።

በአንዳንድ ቦታዎችም መንገዶች መዘጋታቸውንና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ መገታቱን በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በአካባቢያቸው ያለውን ሁኔታ በተመለከተ የሚገልጹ ሰዎች በፎቶ ጭምር እያመለከቱ ነው።