
ትናንት ሌሊት በአክቲቪስት ጀዋር መሃመድ መኖሪያ ቤት አጋጠመ የተባለውን ክስተት ተከትሎ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች በርካታ ሰዎች ለተቃውሞ ሰልፎች አደባባይ ወጥተዋል።
የተቃውሞ ሰልፍ ከተደረገባቸው ከተሞች መካከል አምቦ፣ አዳማ እና ሻሸመኔ ከተሞች ይጠቀሳሉ። በዚህም በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ቢቢሲ ያነጋገራቸው መንጮች ጠቁመዋል።
አምቦ
በአምቦ በተቀሰቀሰው ግጭት ቢያንስ ስድስት ሰዎች በጥይት የተመቱ ሲሆን ሦስቱ ህይወታቸው አልፏል።
ዛሬ ጠዋት በአምቦ በተቀሰቀሰው ግጭት ነዋሪዎች አምስት ሰዎች በጥይት መመታታቸውን ለቢቢሲ ተናግረው የነበረ ሲሆን፤ የሆስፒታል ምንጮች በበኩላቸው ሦስት ሰዎች ለሕክምና ወደ አምቦ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠው ነበር።
የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ሌሊቱን በአክቲቪስት ጀዋር መሃመድ መኖሪያ ቤት ተፈጸመ የተባለውን ክስተት ተከትሎ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ አደባባይ ወጥተው ነበር።
ለተቃውሞ የወጡትን ሰዎች ለመበተን የጸጥታ ኃይሎች አስለቃሽ ጭስ ከተኮሱ በኋላ ተቃዋሚዎች ፖሊሶች ላይ ድንጋይ መወርወር እንደጀመሩ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ያስረዳሉ።
ዛሬ ጠዋት የነጋገርናቸው የአምቦ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ደበበ ፈጠነ ሦስት ሰዎች በጥይት ተመተው ለህክምና ወደ ሆስፒታላቸው መምጣታቸውን ነግረውን ነበር።
ዛሬ ከሰዓት በስልክ ደግመን ያገኘናቸው የአምቦ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዛሬ ረፋድ ላይ በጥይት ተመተው ህይወታቸው ያለፈ የሦስት ሰዎች አስክሬን ወደ ሆስፒታላቸው መምጣታቸውን ነግረውናል።
አቶ ደበበ ጠዋት ላይ በጥይት ተመተው ለህክምና ስለመጡት ሰዎች ሲያስረዱ፤
“እድሜያቸው ከ17-28 የሚገመቱ ሦስት ወጣቶች ወደ ሆስፒታላችን በጥይት ተመተው መጥተዋል። አንዱ ሆዱ ላይ የተመታ ሲሆን ከፍተኛ ጉዳት አጋጥሞት የቀዶ ህክምና ተደርጎለታል። ሁለተኛው መራቢያ አካሉ ላይ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን በአሁኑ ሰዓት የቀዶ ህክምና እየተካሄደለት ነው። ሦስተኛው ትከሻው አካባቢ ቀላል የሚባል ጉዳት የደረሰበት ሲሆን ለእርሱም ህክምና ተደርጎለታል” በማለት አስረድተዋል።
ግጭቱ የተከሰተው ከኦሮሚያ ፖሊስ ጋር መሆኑን ያስረዱት ነዋሪዎቹ፤ አንድ የፖሊስ መኪና ሙሉ ለሙሉ በቃጠሎ መውደሙን ጨምረው ተናግረዋል።
ግጭቱን ተከትሎ በከተማው የንግድ እንቅስቃሴ መቆሙን እና ከተማውን አቋርጦ የሚያልፈው መንገድ ዝግ መሆኑን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አዳማ
በተመሳሳይ መልኩ በአዳማ ከተማ የተቃውሞ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው። ሰልፎቹ ባህርያቸውን በመቀየር በሁለት ጎራ በተከፈሉ ሰዎች መካከል ግጭት መከሰቱን በሥፍራው የሚገኘው ሪፖርተራችን ተመልክቷል።
“ቄሮ ሌባ” በሚል ቡድን እና ለጀዋር መሐመድ ድጋፍ ለማሳየት በወጡ ወጣቶች መካከል ግጭት እንደተፈጠረ ሪፖርተራችን ከሥፍራው ዘግቧል።
የሃገር መከላከያ ሠራዊት እና ኦሮሚያ ፖሊስ በሁለት ቡድን ተከፍለው ወደ ግጭት ባመሩ ኃይሎች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ዘጋቢያችን ተመልክቷል።
እስካሁን በአዳማ በተከሰተው ግጭት በሰው እና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት በግልጽ ማወቅ ባይቻልም የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን የከተማው ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአዳማ ከተማ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ራውዳ ሁሴን የአንድ የዱቄት ፋብሪካ ጥበቃ ተኩሶ ሁለት ሰዎችን መግደሉን እና በዚህ የተበሳጩ ሰልፈኞ በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ውስጥ የነበሩ 15 መኪኖችን ማቃጠላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ግልጽ ባልሆነ ምክንያት የአፍሪካ ዱቄት ፋብሪካ ጥበቃ ሰልፈኞች ላይ ተኩሶ ሁለት ሰዎች ገድሏል። ጥበቃው ስለሚገኝበት ሁኔታ ምንም መረጃ የለኝም” ያሉት የከተማው ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ፤ የሃገር መከላከያ ሠራዊት በስፍራው ደርሶ ነገሮችን በቁጥጥር ሥር እንዳለዋለ ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በሥፍራው የሚገኘው ሪፖርተራችን በከተማዋ የተቃውሞ ሰልፉን ተከትሎ ሱቆችን የመዝረፍ፣ የሥርዓት አልበኝነት ተግባራት ሲፈጸሙ ታዝቧል።
ይህንን ተከትሎም የንግድ እንቅስቃሴዎች የቆሙ ሲሆን ወደ ከተማዋ የሚያስገቡ መንገዶች ዝግ መሆናቸውን መረዳት ችለናል።
ሻሸመኔ
በሻሸመኔ ከተማም በተመሳሳይ ሁኔታ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል።
የተቃውሞ ሰልፉ ተሳታፊ የሆነ አንድ ወጣት ለቢቢሲ “በጀዋር መሃመድ ላይ የሚደረገው ማስፈራሪያ መቆም አለበት” በማለት ተናግሯል።
ይህ ወጣት የተቃውሞ ሰልፉ ከሌሊቱ 10፡30 ጀምሮ ሲካሄድ እንደነበረ ያስረዳል።
ምንም እንኳን ወደ ሻሸመኔ የሚያስገቡ መንገዶች ሙሉ ለሙሉ ተዘግተው ቢገኙም፤ የተቃውሞ ሰልፉ በሰላም እየተከናወነ እንደሆነ ሌሎች የተቃውሞ ሰልፉ ተሳታፊዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አወዳይ
በምስራቅ ሃረርጌ የአወዳይ ከተማ ነዋሪ የነበረ ወጣት በጥይት ተመትቶ ስለመገደሉም የአወዳይ ከተማ ክንቲባ ጃፋር ሙሐመድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከንቲባው ወጣቱ የተገደለው አወዳይ እና ሃረር ከተሞች መካከል ሃማሬሳ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ከመከላከያ ሠራዊት አባል በተተኮሰ ጥይት መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።

ጀዋር ምን ይላል?
ጃዋር እንደሚለው ከሆነ ማክሰኞ ዕኩለ ሌሊት አቅራቢያ ሁለት መኪኖች ወደሚኖርበት ቤት አካባቢ በመምጣት ጥበቃዎቹን “እኔ ሳላውቅ እቃቸውን ይዘው ቤቱን ለቀው እንዲወጡ” እንደተነገራቸው በፌስ ቡክ ገጹ ላይ አስፍሯል።
በጥበቃዎቹ ላይ ግፊቱ ሲበረታ ከእንቅልፉ ቀስቅሰው ሁኔታውን እንደነገሩትና እሱም ወደ ጥበቆቹ አዛዥ ጋር ደውሎ ማብራሪያ እንደጠየቀና በመጀመሪያ ላይ “የተለመደው ጥበቃዎችን የመቀየር ሂደት መሆኑን” እንደተነገረው፤ ከዚያም ኃላፊው የተሰጠውን ትዕዛዝ ብቻ እያስፈጸመ መሆኑን ጽፏል።

ፌደራል ፖሊስ ምን አለ?
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽር እንደሻው ጣሰው፤ ጃዋር መሀመድ ለተከታዮቻቸውና ለደጋፊዎቻቸው ልታሰር ነው፣ ጥቃት ሊደርስብኝ ነው በማለት ያስተላለፉት መልዕክት ስህተት ነው ብለዋል።
“በፖሊስ ተወሰደብኝ ያሉት እርምጃ ስህተት ነው” ካሉ በኋላ “በመንግሥትም በፖሊስም በኩል ምንም ዓይነት እርምጃ አልተወሰደባቸውም” ሲሉ ተናግረዋል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር፤ ለውጡን ተከትሎ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች በሚንቀሳቀሱበትና በሚኖሩበት ስፍራ ችግር እንዳያጋጥማቸው የጥበቃ ከለላ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው “የግል ጥበቃዎችን የማንሳት ሥራ ስንሰራ ቆይተናል” ብለዋል።