
አጭር የምስል መግለጫ
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክት ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በአክቲቪሲት ጀዋር መሐመድ መኖሪያ ቤት ትናንት ዕኩለ ለሊት ላይ የተፈጸመው ክስተት “መሆን ያልነበረበት ትልቅ ስህተት ነው” አሉ።
በክልሉ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው ለክልሉ ህዝብ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ከውጪ ወደ ሃገር ውስጥ ለገቡ ሰዎች የደህንነት ጥበቃ ሲደረግላቸው እንደነበረ ገልጸው “የክልሉ መንግሥትም ሆነ የፌደራል መንግሥት ደህንነቱን እንደሚያስጠብቁ በዚሁ አጋጣሚ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ” ብለዋል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል እንዳሻው ጣሰው ቀን ለመገናኛ ብዙኀን ጃዋር መሀመድ ለተከታዮቻቸውና ለደጋፊዎቻቸው ልታሰር ነው፣ ጥቃት ሊደርስብኝ ነው በማለት ያስተላለፉት መልዕክት ስህተት ነው ብለው ነበር።
በተጨማሪም ኮሚሽነሩ ጀዋር “በፖሊስ ተወሰደብኝ ያሉት እርምጃ ስህተት ነው። … በመንግሥትም በፖሊስም በኩል ምንም ዓይነት እርምጃ አልተወሰደባቸውም” ሲሉ ተናግረው ነበር።
• “ክስተቱ ‘የግድያ ሙከራ’ እንደሆነ ነው የምረዳው” ጀዋር መሐመድ
• “በመንግሥትም በፖሊስም በኩል ምንም ዓይነት እርምጃ አልተወሰደም” ፌደራል ፖሊስ
• በኦሮሚያ ከተሞች በተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች 6 ሰዎች ተገደሉ
ምክትል ፕሬዝደንቱ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ስህተት ሲሉ የገለጹት ክስተት በማን እንደፈጸመ እና ለምን እኩለ ለሊት ላይ ማድረግ እንደታሰበ የምናጣረው ጉዳይ ይሆናል ብለዋል።
ዛሬ በተለያዩ ከተሞች ተቃውሞ ለማሰማት አደባባይ ወጥተው ህይታቸው ያለፉ ሰዎችን በተመለከተም በክልላቸው ስም የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።
ዛሬ በተደረገው ሰልፍ ላይ ኦሮሚያን የግጭት አውድማ ለማድረግ የሚፈልጉ ኃይሎች ሰልፉ ላይ አስነዋሪ ተግባራትን ፈጽመዋልም ብለዋል፡፡እነዚህ ኃይሎች ጉዳዩ የሃይማኖትና የብሔር መልክ እንዲይዝ ጥረት እያደረጉ ነው ሲሉም አክለዋል።