ወጣቱ በህጋዊ መንገድ ጥያቄ ማቅረብን ባህሉ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አሳሰበች

ወጣቱ ምንም አይነት ቅሬታና ጥያቄ ቢኖረው በሰለጠነ እና ህጋዊ በሆነ መልኩ ሃሳብን መግለጽ እንደሚገባው የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አሳስባለች።
በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት እና የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ሰብሳቢ ብርሃነየሱስ ”ባለፉት ቀናት በተፈጠሩ ሁኔታዎች ምክንያት የተፈጠረው የዕምነት ተቋማት ስጋት የእኛም ስጋት ነው” ብለዋል።
የስራ አጥነት ችግር ባለበት አገር ድርጅቶች ስራ ለማቆም መገደዳቸው በሃገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷልም ብለዋል።
ከዚህ ጥቃትና አመጽ ጀርባ “ስር የሰደደ የሞራል ውድቀት አለ” ያሉት ካርዲናል ብርሃነየሱስ፤ የዕምነት ተቋማት ዜጎችን በጥሩ ስነ ምግባር በማነጽ ሃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
ወላጆችም ልጆቻቸውን ሰው አክባሪና አገር ወዳድ እንዲሆኑ በመምከርና በጥሩ ግብረገብነት ኮትኩተው በማሳደግ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
እያንዳንዱ ዜጋ የጋራ ሰላምና ጥቅም ላይ በማተኮር አገሩን መጠበቅ እንዳለበትም አሳስበዋል።
ቤተ ክርስቲያኗ በሀገሪቷ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባወጣችው መግለጫም ወጣቱ ምንም አይነት ቅሬታና ጥያቄ ቢኖረው በሰለጠነና ምንም አይነት ጉዳት በማያደርስ መልኩ ሃሳብን መግለጽ እንደሚገባው ነው ያሳሰበችው።
በማከልም ወጣቶች በራሳቸውም ሆነ በሌሎች ዕምነት ተቋማት ላይ ምንም አይነት ጥቃት አለማድረስና እንዲህ ዓይነቱን ዕኩይ ተግባር ማውገዝ እንዳለባቸውም አሳስባለች።
የጸጥታ አካላትም በቂ ዝግጅት በማድረግ ህጋዊ ያልሆኑ ድርጊቶችን በንቃት በመቆጣጠርና በማስቆም ሃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ አጥብቀው አሳስበዋል።
ምንጭ፡- ኢዜአ