October 27, 2019Konjit Sitotaw

የሲዳማን የክልል እንሁን ጥያቄን በግዴታ የሃዋሳ ህዝብ ላይ ለመጫን እየተኬደበት ያለው መንገድ ሊቆም ይገባል።- የሐዋሳ ነዋሪዎች ህብረት ተወካዮች

(ኢትዮ 360 ) – የሲዳማን የክልል እንሁን ጥያቄን በግዴታ የሃዋሳ ህዝብ ላይ ለመጫን እየተኬደበት ያለው መንገድ ሊቆም ሊቆም ይገባል ሲሉ የሐዋሳ ነዋሪዎች ህብረት ተወካዮች ጠየቁ።

ተወካዮቹ ለኢትዮ 360 በላኩት ደብዳቤ እንደገለጹት የሲዳማ የክልል እንሁን ጥያቄ የሲዳማ ዞን ብቻ እንጂ የሌላው አይደለም።

ከአራት መቶ ሃምሳ ሺ በላይ ዜጎች የሚኖሩበት የሐዋሳ ከተማ የራሱ የሆነ ምክር ቤትና የራሱ አስተዳደር አለው ያላሉ።

ይሄ ባለበት ሁኔታ ታዲያ እንዴት ነው በሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ህዝበ ውሳኔ ላይ በግዴታ ድምጽ እንዲሰጥ የሚጠይቀው ሲሉም ይጠይቃሉ ተወካዮቹ።

የሲዳማ የክልል እንሁን ጥያቄ የብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ የሆነችውን የሐዋሳ ከተማን መቀራመትና ሐብቷን መዝረፍ አላማው ያደረገ ነው ያላሉ።

የዚህ መቀራመት አንድ አካል የሆነው የማጭበርበርና ህገወጥ ስራም የከተማ ነዋሪነት መታወቂያን በገፍ በማደል ቀጥሏል ይላሉ።

ለአንድ ሰው ከ10 እስከ 15 መታወቂያ እንዲሰጠው ይደረጋል የሚሉት ተወካዮቹ መታወቂያውን ከወሰደ በኋላ ለማን እንደሚያድለው ግን የታወቀ ነገር የለም።

በተለይ ታቦር በሚባለው ክፍለ ከተማ በተለየ መልኩ ህገወጥ የነዋሪነት መታወቂያ ሲታደል እንደሚውልም እማኝነታውን ይናገራሉ።

የከተማዋ አስተዳደር ደግሞ በህገወጥ የመታወቂያ እደላው ያልተሳተፈውንና ምንም ወንጀል የሌለበትን ግለሰብ እየመረጠ ወደ እስር ቤት በማጎር ላይ ነው ብለዋል።

ይሄ ሁሉ ሁኔታ ባለበትና ነገሮች እየተወሳሰቡ በመጡበት እንዲሁም ስርአት አልበኝነት በነገሰበት ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መወሰኑ እጅግ አሳፋሪና ከአንድ ተቋም የሚጠበቅ ተግባር አይደለም ይላሉ።

ይህንን በተመለከተም ምርጫ ቦርድን ጨምሮ፣ለሕዝብና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች፣ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት፣ለሰላም ሚኒስቴር፣ለህዝብ እንባ ጠባቂ፣ለክልሉ ምክር ቤት፣ለክልሉ ብሄረሰቦች ምክር ቤት፣ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና ለክልሉ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ለሁለተኛ ጊዜ ደብዳቤ አስገብተናል።

የሰብአዊ መብት ኮሚሽን አድራሻ ቀይሯል በመባላችን ለእሱ ደብዳቤያችንን ሳናቀርብ ቀርተናል ሲሉ ለኢትዮ 360 ገልጸዋል።

መብትን መጠየቅ በራሱ የሚያስገድልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል የሚሉት ተወካዮቹ የሚሰማን እስክናገኝ ድረስ ግን ለሚመለከተው አካል የምናቀርበውን ጥያቄ አናቋርጥም ብለዋል።

የሲዳማ ዞን ተወላጅ ያልሆነውና የብሔር ብሔረሰች ስብስብ የሆነው የሐዋሳ ከተማ ነዋሪ ላይ በህዝበ ውሳኔው ተሳተፍ በሚል የሚደረግበት ጫና በአስቸኳይ ሊቆም ይገባልም ብለዋል።

ተወካዮቹ ያነሱትን ጥያቄ ይዞ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላትን ለማነጋገር ኢትዮ 360 በተደጋጋሚ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ መስጠት እፈልጋለው የሚል ማንኛውም አካል ካለ ኢትዮ 360 ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን ይገልጻል።