
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)
Ethiopian People’s Revolutionary Party (EPRP)
ስለ ወቅታዊው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ
ፓርቲ (ኢሕአፓ) የተሰጠ መግለጫ
ኢትዮጵያ በታሪክ ሂደት ውስጥ እጅግ በጣም አሳሳቢ በሆነ የፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ትገኛለች። በሀገራችን ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ያለው የኃይል አሰላለፍ የዜግነት (የአንድነት) የፖለቲካ አስተሳሰብና ፅንፈኛ የብሄረሰብ ፖለቲካ አስተሳሰብ መካከል ያለው ቅራኔ ነው። የዜግነት (የአንድነት) የፖለቲካ አስተሳሰብ የሚያራምዱ ወገኖች (ኢሕአፓን ጨምሮ) የኢትዮጵያ ህልውና ተጠብቆ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማየት ሲታገሉ፣ ፅንፈኛ የብሄርሰብ ፖለቲካ አራማጆች ደግሞ ሀገሪቱን በብሄረሰብ ከፋፍለው ለመበተን እየሠሩ ነው።
በዚህ ዋነኛ በሆነው የዜግነትና የፅንፈኝነት ፖለቲካ አስተሳሰብ ትግል ውስጥ፣ ፅንፈኛ የብሄረሰብ ፖለቲካ አራማጆች ያለማቋረጥ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ተንኳሽና ጠብ አጫሪ ተግባራትን በማድረግ፣ ለዘመናት አብሮ የኖረውን ሕዝብ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ለመክተት ጥረት እያደረጉ ነው።
ፅንፈኞች በቃላት ከሚያደርጉት ማስፈራራት አንስቶ፣ እስከ ግጭት መቀስቀስ፣ መንገድ መዝጋት፣ ዝርፊያና ግድያ ድረስ ወንጀል እፈጸሙ ይገኛሉ። በፍጹም ወደ ለየለት የፖለቲካ እብደት ውስጥ እየገቡ ከሀገራችን አልፎ ለቀጠናችን ሊተርፍ የሚችል የጦርነት ድግስ እየደገሱ ነው። ራሳቸውንም እንደ ሁለተኛ መንግሥት ቆጥረው ህገወጥ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ።
በዚህ ረገድ ሰሞኑን የኦሮሞ ፅንፈኞች በአዲስ አበባና በተወሰኑ የኦሮሚያ አካባቢዎች መንገድ በመዝጋት የሕዝቡ የዕለት ተዕለት የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲገታ እያደረጉ ነው። ሽብር በሕዝቡ ላይ እየነዙ ነው። ዝርፊያ እያካሄዱ ነው። በንጹሃን ዜጎች (ሴቶችንና ህፃናትን ጨምሮ) ግድያ እየፈጸሙ ነው። የሃይማኖንና የዘር ግጭት ለመቀስቃስ በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮችና በሌሎች ብሄረሰብ ተወላጆች ላይ ጥቃት በመፈጸም ላይ ናቸው። በዚህ ጥቃት ቆሜለታለሁ የሚሉትን የኦሮሞ ተወላጆችን ጭምር በማካተት እጅግ አደገኛነታቸውን በተግባር አሳይተዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ የኢትዮጵያ ሕዝብ በታላቅ ትዕግሥት ፅንፈኞቹን ወደ አዕምሮአቸው እንዲመለሱ ከሚያደርገው ምክር በተጨማሪ እራሱን ከነዚህ ወንጀለኞች ለመከላከል እያደረገ ያለውን ጥረት ፓርቲያችን ያደንቃል። ተደራጅተው ጥቃቱን እንዲከላከሉ ያበረታታል። የመንግሥት የፀጥታ አካላት የሕዝቡን ደህንነት መጠበቅ አለባቸው። አንዳንድ የአዲስ አበባና የክልል ፖሊሶች ሕዝቡን ለመታደግ ያሳዩት ቸልተንነት ብሎም ከወንጀለኞቹ ጋር ያሳዩት ኅብረት በጣም አሳዛኝ ነው። እነዚህ ኃላፊነት የጎደላቸው ሰዎች ለተፈጠረው ጥፋት ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል።
በአጠቃላይ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተውን ዘረፋ፣ ድብደባ ግድያና መፈናቀል በተመለከተ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የሚከተለውን አቋሙን ይገልጻል።
1. በአክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች ቀስቃሽነት የተደረገውን ጥቃት ኢሕአፓ እያወገዘ፣ ለሞቱ፣ ለቆሰሉና ለተፈናቀሉ ዜጎች ፓርቲያችን ልባዊ ሀዘኑን ይገልጻል።
2. የተፈጸመው ጥቃት በሰዎች ላይ የተፈጸመ ወንጀል (Crime Against Humanity) ስለሆነ መንግሥት ገለልተኛ አጣሪ አካል ሰይሞ ጉዳዩ እንዲጣራ፣ ወንጀለኞቹም ለፍርድ እንዲቀርቡ፣ ተጠቂዎቹም እንዲካሱ ፓርቲያችን ይጠይቃል።
3. ዜጎች በሕይወት የመኖር፣ ተዘዋውሮ የመሥራትና፣ በሰላም ወጥቶ የመግባት መብቶቻቸው አንዲከበርላቸው እንጠይቃለን።
4. መንግሥት ሕግ የማስከበር ሥራውን በአግባቡ ያልተወጣ በመሆኑ እያወገዝነው፣ ለወደፊቱ ከዚህ ዓይነት ደካማነት ራሱን እንዲያስተካክል እናሳስባለን።
5. በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ውስጥ በኦሮሚያም ሆነ በሌሎች ክልሎች እየተሰፋፋ ያለው ኢ–መደበኛ አደረጃጀት እንዲታገድና በህጋዊ አደረጃጀት እንዲተካ እንጠይቃለን።
6. የኢትዮጵያ ሕዝብ በፅንፈኛ የብሄር ፖለቲከኞችና (አክቲቪስቶች) እየተደረገበት ያለውን የጥቃት ሁኔታ በአግባቡ ተገንዝቦ የቆየ የመከባባርና የመዋደድ ባህሉን አጠንክሮ ወንጀለኞቸን በመከላከል ሥፍራ እንዳይኖራቸው እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን።
7. ሕዝብና ሕዝብን የሚያገጩና የእርስ በርስ ጦርነት ጥሪ የሚያደርጉ የፅንፈኛ አክቲቪሰት ሚዲያዎች በህግ እንዲጠየቁ፣ ሕዝቡም ለከንቱ ፕሮፓጋንዳቸው ጆሮ እንዳይሰጣቸው እናሳስባለን።
8. በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ኃላፊነት የሚሰማቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ በዚህ እጅግ አሳሳቢ በሆነ ወቅት ከሕዝቡ ጎን በመቆም ለሰላም እንዲታገሉ ጥሪ እናቀርባለን።
ኢትዮጵያን ፈጣሪ ይጠብቃት
ጥቅምት 15 ቀን 2012 ዓ.ም