ይሄ ጽሑፍ ኢሕአዴጎች “እናደርገዋለን!” የሚሉት ውሕደት ርዕዮተዓለማዊ ያልሆነና ተራ ማጭበርበር መሆኑን የሚያጋልጥ ጽሑፍ ነው በጥሞና ይነበብ፦
ኢሕአዴግ እንደሚዋሐድ መነገር ከጀመረ ብዙዎቻቹህ እንደሚመስላቹህ አሁን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ መታሰብ የጀመረ አይደለም፡፡ 14 ዓመት አልፎታል፡፡ ምርጫ 97 የሕዝብ ድምፅ ውጤት የወያኔ/ኢሕአዴግን የጎሳ ፌዴሬሽን አሥተዳደር የሚጠየፍ መሆኑን የተገነዘበው ወያኔ/ኢሕአዴግ ከምርጫ 97 በኋላ 1998ዓ.ም. ባሕርዳር ላይ ከተደረገው የኢሕአዴግ ጉባኤ ዋዜማ ጀምሮ ቻይናን እንደ አርአያ በመውሰድ “ቻይና 56 ብሔረሰቦችን ይዛ የተሳካለት አሐዳዊ ሥርዓትን መመሥረት ችላለችና!” የሚል ትርክትን ይዘው አርዓያ በማድረግ ነበር ማውራት የጀመረው፡፡
ያኔ እንዲያውም ይባል የነበረው የኢሕአዴግ ውሕደት ሳይሆን “ወደ አሐዳዊ የመንግሥት ሥርዓት!” ነበር ተብሎ የነበረው፡፡ ከተወራ በኋላና በባሕርዳሩ የኢሕአዴግ ጉባኤ ይታወጃል ተብሎ ሲጠበቅ እነ አቶ መለስ በጉባኤው ላይ “የኢሕአዴግ የመጨረሻ ግብ አሐዳዊ የመንግሥት ሥርዓት ቢሆንም አሁን ግን ጊዜው አይደለም፡፡ ጊዜው ሲደርስ ይበሰራል!” ብለው ላልተወሰነ ጊዜ እንዳሻገሩት ይታወሳል፡፡
አሁን ደግሞ አጀንዳውን ከአሐዳዊ የመንግሥት ሥርዓት ወደ ኢሕአዴግ ውሕድ ፓርቲነት አሳነሱትና ይሄው የተራኮቱና የተወዛገቡ እያስመሰሉ ይገኛሉ፡፡
የኔ ጥያቄ ኦሕዴድ ዛሬ (ጥቅምት 7, 2012ዓ.ም.) በብዙኃን መገናኛዎች ባስነገረው መግለጫው ከዚህ በፊትም እንዳስታወቀው በጎሳ ፌዴሬሽኑ እንደማይደራደርና ለሀገሪቱ አማራጭ የሌለው የአሥተዳደር ሥርዓት መሆኑን ገልጿል፡፡ በአንድ በኩል ስለ መዋሐድ ያወራሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የጎሳ ፌዴራላዊ ሥርዓቱን የሚደራደሩበት እንዳልሆነ ይገልጻሉ፡፡ አልተምታታባቸውም ወይ???
ከዚህ ቀደም እነ አቶ ዐቢይ ወደ ውሕድ ፓርቲነት የሚቀየሩበትን ምክንያት ሲገልጹ እንደሰማናቸው የጎሳ ፓርቲ ወይም የዘር ፖለቲካ አስፈላጊ አለመሆኑንና ለሀገሪቱ ፖለቲካዊ ቀውስ መንስኤ በመሆኑ እንደሆነ ሲገልጹ ሰምተናል፡፡ እንዲያ ከሆነ ታዲያ ማለትም የዘር ፖለቲካ ገዥው ፓርቲ ከሚከተለው ፖለቲካ እንዲቀር ከተደረገ ለምንድን ነው ታዲያ መሬት ላይ ግን ጎሳና ብሔረሰብን ወይም ቋንቋን መሠረቱ ያደረገው የክልል አከላለልና አሥተዳደሩ እንዲቀጥል የሚደረገው ታዲያ??? “አልሸሹም ዞር አሉ!” አሉ አበው ሲተርቱ!!!
ቆይ እነሱ አንድ ሆነናል ብለው ሲያበቁ በዘር የተከፋፈለውን ሕዝብ እንዴት ማሥተዳደር ነው የሚፈልጉት??? በእነሱና በሕዝቡ መሐል ያለው ቋንቋ እኮ የአንድነትና የዘር ክፍፍል ሆኖ ተለያየ ማለት ኦኮ ነው፡፡ እንዴት መግባባት ይቻላል??? ሁለት ሰዎች በተለያየ ቋንቋ ቢያወሩ መግባባት ይችላሉ ወይ??? ፓርቲው የሚከተለው ርዕዮተዓለም ሌላ ሕዝቡ ላይ የሚሠራው ርዕዮተ ዓለም ሌላ ሆኖ የመንግሥት አሥተዳደርን መመሥረት ይቻላል ወይ??? በየት ሀገር ነው ይሄ ሆኖ የሚያውቀው???
ወገኖቸ ከዚህ የምትረዱት ውሕደት የሚሉት ነገር ሕዝብን ለማጭበርበር የሚደረግ ወይም የይስሙላ መሆኑንና በርዕዮተዓለም ደረጃ ወደፊትም መከተል የሚፈልጉት የዘር ፖለቲካን መሆኑን ያሳያልና የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ እንዳትታለል!!!
ሲጀመር ሲያጭበረብሩ እንጅ የሀገሪቱን ፖለቲካ የዘር ፖለቲካ ቅኝትን እንዲይዝ ያደረገው ሕገመንግሥታቸው ሳይቀየር አራቱ የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎችና አምስቱ አጋር ፓርቲዎች አንድ ሆነው ተዋሕደው የአንድነት ፖለቲካን ሊያቀነቅኑ አይችሉም!!! በዚህ ሕገመንግሥት እናሥተዳድራለን እያሉ አንድነትን ማቀንቀን ማለት ወያኔንና ኦነጋውያኑን በአማርኛ ዘፈን ለማስደንከር፣ ለማስጨፈር፣ ለማስደሰት መሞከር ማለት ነው!!!
ግን ለምን ይመስላቹሃል ወያኔ/ኢሕአዴጎች ከዘር ፖለቲካ ጋር ቆርጠው መላቀቅ መለያየት የማይፈልጉት??? ቀላሉ መልስ ሕዝቡን በዘር ከፋፍለው እርስበርስ በማናቆር ለመግዛት ከመሞከር ውጭ በሕዝብ ዘንድ ተመራጭ ተፈላጊ የሚያደርጋቸው የፖለቲካ ፕሮግራምና አስተሳሰብ ስለሌላቸው ነው!!! ምርጫ በተደረገ ቁጥር ሁሌም ኮሮጆ እየገለበጡ “አሸነፍን!” የሚሉበት ምክንያትም ይሄው ነው!!!
ከዚህ መረዳት የምትችሉት የአገዛዙ እና የሕዝቡ ፍላጎት የተለያየ መሆኑን ነው፡፡ እነሱ አስተሳሰባቸውን በሕዝብ ላይ መጫን ይፈልጋሉ እንጅ ሕዝብ እንደሚፈልገው መሆን ወይም መሥራት መቸም ቢሆን የማይፈልጉ መሆናቸውን ነው፡፡ ውሕደት ብለው መሬት ላይ የጎሳ ፖለቲካን መጫወት የሚፈልጉበት ምክንያትም ይሄው ነው!!!
እነሱ ግን የተለያየ ነገር እያወሩ ሕዝብን ያወናብዳሉ፡፡ አንዱን ምሳሌ እንጥቀስ ካልን ወያኔ/ኢሕአዴጎችን ዘወትር ሲለፈልፉ እንደምትሰሟቸው እራስን በራስ የማሥተዳደር መብት በጎሳ ፌዴሬሽን ላይ ብቻ የሚተገበር መብት አስመስለው ይለፍፋሉ!!!
እውነቱ ግን እንዲያ ነው ወይ??? በፍጹም አይደለም!!! መንግሥት በሕዝብ ምርጫ ወይም ድምፅ እስከተመሠረተ ጊዜ ድረስ አሐዳዊ የመንግሥት ሥርዓትን ጨምሮ የጎሳ አሰፋፈርንና ቋንቋን መሠረቱ ካደረገው የፌዴሬሽን አሥተዳደር ሥርዓት ውጭ በሆነው የፌዴሬሽን አሥተዳደር ሥርዓትም እራስን በራስ የማሥተዳደር (Self administration) መብት በሚገባ አለ!!!
ጠባቦቹና የፖለቲካ ደናቁርቱ ወያኔ/ኢሕአዴጎች ይሄንን ስለማያውቁ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ከላይ እንደገለጽኩት ጥቅማቸውን ማስጠበቅ የሚችሉት ሕዝቡን በዘር ፖለቲካ ከፋፍለው በማናቆር ስለሆነ እንጅ፡፡ የወያኔ ከሥልጣን መወገድ ውሸት መሆኑን የምታውቁበት አንዱ መንገድ ይሄ ነው፡፡ ወያኔ የዘር ፖለቲካን በዚህች ሀገር የተከለበት ምክንያት ከአናሳ ጎሳ የወጣ ስለሆነ በነጻና ፍትሐዊ ውድድር (fair and free competition) መንግሥት የመሆን ዕድል እንደማይኖረው ስለሚያውቅ ነው፡፡ እያስመሰሉ እንዳሉት ኦሕዴዶች “ብዙ ቁጥር ያለው ብሔረሰብ ፓርቲ ነን!” ካሉና በራስ መተማመኑ ካላቸው የአናሳውን የወያኔን ጨዋታ ለመጫወት የሚገደዱበት አንድም ምክንያት ባልነበረ፡፡ ኦነጋዊ የመገንጠል ዓላማ ስላላቸው ካልሆነ በስተቀር፡፡
በመሆኑም ኢሕአዴጎች እራስን በራስ የማሥተዳደር (Self administration) መብት የወያኔ/ኢሕአዴጓ ኢትዮጵያ ባለችበት በጎሳ ፌዴሬሽን ሥርዓት ብቻ ያለ በሌሎቹ ሥርዓተ መንግሥቶች ግን የሌለ እያስመሰሉ ሕዝብን የሚያወናብዱትን ማወናበድ ማቆም አለባቸው!!! ይሄ ያለቅጥ ሕዝብን መናቅ ነውና!!! ለነገሩ እነሱ ለሕዝብ ክብር ኖሯቸው አያውቁም!!!
በዓለማችን ወደ 195 የሚሆኑ ሀገራት አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የፌዴሬሽን አሥተዳደር ሥርዓትን የሚከተሉት 25 ሀገራት ብቻ ናቸው፡፡ ከ24 የአውሮፓ ሀገራት ስድስቱ ብቻ ፌዴራላዊ ናቸው፡፡ እነሱም ኦስትሪያ፣ ቤልጂየም፣ ቦሲኒያ ሕርዘጎቢኒያ፣ ጀርመን፣ ስፔን፣ ስዊዘርላንድ ናቸው፡፡ ከእነኝህ በዓለማችን ፌዴራላዊ ከሆኑ 25 ሀገራት ውስጥ ደግሞ ጠንቀኛውንና ኋለቀሩን የጎሳ ፌዴሬሽን ከተከተሉት ሦስት ሀገራት ሁለቱ ፈርሰዋል አንዷ ከመፍረስ ዳርቻ ላይ ደርሳለች፡፡ እነሱም የወያኔዋ ኢትዮጵያ፣ ዩጎዝላቪያና የሶቪየት ኅብረት ናቸው፡፡ ለነገሩ የሶቪየት ኅብረት ኮንፌዴሬሽን ነው የነበረው ሥርዓቷ፡፡
አንዳንዶቹ ስዊዘርላንድንና ካናዳን ጨምረው በማንሣት በጎሳ በፌዴሬሽን እንዳሉ አድርገው ይጠቅሳሉ፡፡ የጎሳ ፌዴሬሽን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ያልገባቸው ካልሆኑ በስተቀር ላይ ላዩን ሲያዩት ይመስላል እንጅ ስዊዘርላንድና ካናዳ የሚከተሉት ሥርዓት የጎሳ ፌዴሬሽን የአሥተዳደር ሥርዓት አይደለም፡፡
ከዚህም ሌላ የወያኔዋን ኢትዮጵያ ከዓለም ሀገራት ለየት የሚያደርጋት ነገር በዘር ወይም በጎሳ ወይም በብሔረሰብ የፖለቲካ ፓርቲ የሚመሠረትባት ወይም ፖለቲካዋ በዘር ፖለቲካ የሚዘወርባት በዓለም ብቸኛዋ ሀገር መሆኗ ነው፡፡
የተለያዩ ዘሮች ወይም ብሔረሰቦች በሌሎች ሀገራት ስለሌሉ እንዳይመስላቹህ በሌሎች ሀገራት ፓርቲ በዘር ወይም በብሔረሰብ ተመሥርቶ ፖለቲካቸውን የዘር ፖለቲካ እንዲዘውረው ያልፈቀዱት፡፡ የዘር ፖለቲካ እጅግ አደገኛ፣ ሀገር አፍራሽ፣ በታኝ፣ አዋኪ፣ የሰላምና መረጋጋት ጠንቅና እግጅ ኋላ ቀር ወይም ያልሠለጠነ ስለሆነ እንጅ፡፡
ወያኔ ግን ብዝኃነት ወይም የተለያዩ ብሔረሰቦች በእኛ ሀገር ብቻ ያሉ በማስመሰል የዘር ፖለቲካን በሀገራችን ተክሎ ሲያበቃ ይሄው ሀገሪቱን በዘር ከፋፍሎ አንድ ቀን ተግባራዊ አድርጎት የማያውቀውን ወይም ሰጠሁት የሚለውን መብት አክብሮት የማያውቀውን “እራስን በራስ የማሥተዳደር (Self administration) መብት ነው!” እያለ ሀገራችንን ሊያፈርሳት እየታገለ ይገኛል፡፡
እስኪ የዓለም ሀገራት በአሁኑ ጊዜ የሚከተሉትን የአሥተዳደር ሥርዓት እንመልከት፦
በዓለማችን ካሉት 195 ሀገራት ውስጥ ከላይ እንደገለጽኩላቹህ የፌዴሬሽን የአሥተዳደር ሥርዓትን የሚከተሉት 25 ሀገራት ናቸው፡፡ 131 ሀገራት ደግሞ የሚከተሉት ወያኔ/ኢሕአዴጎች አብዝተው የሚኮንኑት አሐዳዊ የአሥተዳደር ሥርዓትን ነው፡፡ ከእነኝህ ውስጥ አምስቱ የአውሮፓ ሀገራት ናቸው፡፡ እነሱም ሰኮትላንድ፣ ሰሜን አየርላንድ፣ ጣሊያን፣ አይስላንድና ዌልስ ናቸው፡፡
የሚገርማቹህ ነገር ከእነኝህ የዓለም ሀገራት በአሁኑ ጊዜ እንግሊዝንና ጃፓንን ጨምሮ 39 ሀገራት የሚከተሉት አሁንም ወያኔና ቢጤዎቹ አጥብቀው የሚኮንኑት ጥንታዊው የአሥተዳደር ሥርዓት የሆነውን ዘውዳዊውን ወይም ንጉሣዊውን ሥርዓት ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአውሮፓ ውስጥ አምስት ሀገራት ዘውዳዊ ወይም ንጉሣዊ መንግሥት ነው ያላቸው፡፡ እነሱም ዴንማርክ፣ ሉክሰምበርግ፣ ኔዘርላንድ፣ ስዊድንና እንግሊዝ ወይም UK ናቸው፡፡ እርግጥ እንደ እንግሊዝ (UK) እና ጃፓንን የመሰሉቱ የሚከተሉት የዘውዳዊ ሥርዓት ሕገመንግሥታዊ የዘውድ ሥርዓትን (constitutional monarchy) ነው፡፡
እንግዲህ አሁን ያለው የዓለማችን እውነታ ይሄ ነው፡፡ እውነታው ምን ያስረዳቹሃል??? ሀገራችን የሰው ልጆች የየዘመኑን ሥልጣኔ በፈቀደላቸው መጠን ከጎሳ ወይም ከብሔረሰብ አገዛዝ ወደ ንጉሣዊ ወይም ዘውዳዊ አገዛዝ፣ ከዘውዳዊ አገዛዝ ወደ ጉልበተኛ ወደሚመራበት አሐዳዊ አገዛዝ፣ ከአሐዳዊው አገዛዝ በሕዝብ ቀጥተኛ ምርጫ ወደሚመሠረት የሕዝብ መንግሥት ሥርዓት እያደገ የመጣበትን ደረጃዎች ሁሉ አልፋ መጥታ መጨረሻ ላይ ግን የመጨረሻውን የሕዝብ/ሕዝባዊ መንግሥት ሥርዓት ማለትም በሕዝብ ቀጥተኛ ምርጫ የሚመሠረተውን የመንግሥት ሥርዓት ሳትመሠርት ወደ የድንጋይ ዘመኑ የጎሳ ወይም የብሔረሰብ የጎጥ አሥተዳደር መመለሷን አልተረዳቹህም ወይ??? አዎ እውነታው ይሄ ነው!!! ወያኔና ቢጤዎቹ ጠባብ ደናቁርት ወደ ድንጋይ ዘመን ነው የመለሱን!!! ዝም ብለህ አይተሃቸዋልና መጨረሻ ላይም እንደድንጋይ ዘመን ሰዎች እርስበእርስህ በጎሳ አጨፋጭፈው ያጠፉሃል!!! እንደልማድህ ተኝተህ ጠብቅ እሽ??? ኧረ ተው ንቃ ተበላህ አንተ የዋህ ሕዝብ???
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com