በወቅታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የተሰጠ መግለጫ

October 30, 2019

በወቅታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የተሰጠ መግለጫ

ጋዜጣዊ መግለጫ

“በተከሰተው ሁከት በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ በጥፋቱ ተሣታፊ የሆኑ ሰዎች ሁሉ በሕግ ተጠያቂነታቸው መረጋገጥ አለበት!”

በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ እና ተሃድሶ እርምጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ተጨባጭ ውጤቶች እንዳስገኘ ሁሉ ውስብስብ ተግዳሮቶችም እየገጠሙት ይገኛል፡፡

በተለይ ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በተቀሰቀሰው ውዝግብ እና ሁከት የተሞላ ነውጥ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ከመጥፋቱ፣ የአካል ጉዳት ከመድረሱ፣ ንብረት ከመውደሙ እና የሰዎች መደበኛ ኑሮ እና ሰላማዊ ሕይወት ከመረበሹ በተጨማሪ፤ የህግ በላይነትን በእጅጉ የተፈታተነ እና መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶችን ከፍተኛ አደጋ እና ስጋት ላይ የጣለ እጅግ አሳሳቢ ክስተት ነበር፡፡

በዚህ ሁከት ምክንያት ከሚዲያዎች ዘገባ መሰረት እስከ አሁን ባለው መረጃ ከ70 – 80 የሚደርሱ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ አስር ያህሉ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በተፈጠረ ግጭት በጥይት ተመተው የሞቱ ሲሆን አብዛኛዎቹ ሰዎች በሁከቱ ተሳተፉ ሰዎች እጅግ አሰቃቂ በሆነ መንገድ በግፍ እና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በዱላ በድንጋይ እና በስለት ተደብድበው እንዲሁም በእሳት ተቃጥለው ተገድለዋል፡፡

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ የአካል እና የሥነ ልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በሚሊዮኖች የሚገመት የግለሰቦች፣ የሕዝብና የአገር ንብረት ወድሟል፡፡ እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት ሆን ተብሎ በተፈጸመ ጥቃት ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡

አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ማናቸውም ዓይነት ቅሬታ ወይም ጥያቄ በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ሊቀርብ የሚችልበት ምቹ ሁኔታ መኖሩ ይታመናል፡፡

ለዚህ ውዝግብ መነሻ በሆነው ጉዳይ ላይ በሰላማዊ መንገድ ሃሳባቸውን ለመግለጽ የሚሹ ሰዎች ቢኖሩም ሁከት የቀሰቀሱ፣ የፈጸሙ እና ያስፈጸሙ እንዲሁም ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ድጋፍ የሰጡ ሰዎች መኖራቸው ግን አይካድም፡፡

ማናቸውንም ዓይነት ቅሬታና ጥያቄ በአመፅ እና በእልቂት ማስፈራሪያ ለማስፈፀም የታየው ተግባር እና የአስከተለው ጉዳት የሕግ የበላይነትን፣ የአገር ሰላም እና ሥርዓትን በአደባባይ በመገዳደር እና በመጣስ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ቀውስ ያስከተለ በመሆኑ በየደረጃው በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ በጥፋቱ ተሣታፊ የሆኑ ሰዎች ሁሉ በሕግ ተጠያቂነታቸው መረጋገጥ አለበት፡፡

ይህን ጥፋት የፈፀሙ እና ወይም የጥፋቱን ተግባር እንደ መልካም ሥራ ያወደሱ ሰዎች ሁሉ በዱላ እና በስለት ተደብድበው በእሳት ተቃጥለው የተገደሉ ሰዎችና ቤተሰቦቻቸውን ለአፍታ እንኳን በእራሣቸውና በቤተሰቦቻቸው ተክተው አለማሰባቸው የደረሰውን ጉዳት ይበልጥ መሪር አድርጐታል፡፡

የድርጊቱ ተሳታፊዎች በደረሰው ጥፋት ማዘን መፀፀት እና ለሕግ የበላይነት መከበር የመተባበር ኃላፊነት እና ግዴታ አለባቸው፡፡

መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና አጥፊዎችን በሕግ ፊት ለማቅረብ ሳያወላውል እንደሚሠራ መግለጹ ተገቢ ሲሆን፤ ይህ የመንግስት ኃላፊነት እና ተግባር በስልታዊ የምርመራ ሥራ እና በሕጋዊ ሥርዓት በአፋጣኝ በሥራ ላይ ሊውል ይገባል፡፡

ከዚህ በመቀጠል ለሚደረገው የወንጀል ምርመራ ሥራ ማንኛውም ሰው በመተባበር እና ውጤቱን በትዕግስት በመጠባበቅ፣ በየአካባቢው የተጐዱ ሰዎችንና ቤተሰቦችን በማጽናናት በመደገፍ እና በመጠገን፤ እንዲሁም የመንግሥት፣ የፖለቲካ እና የልዩ ልዩ ቡድኖች መሪዎች የፖለቲካ ውጥረቱን ከሚያባብሱ ቆስቋሽ ንግግሮች እና ድርጊቶች እራሳቸውን በመቆጠብ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን እና ሰብዓዊ መብቶች ሁሉ

እንዲከበሩ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ እና ይህን የመሰለ ጥፋት ዳግም እንዳይፈጸም የሚመለከታቸው አካሎች ሁሎ በከፍተኛ ኃላፊነት ስሜት ሊሰሩ ይገባል፡፡

መንግስት የዜጐችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን ይወጣ!! (የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ)

October 28, 2019

መንግስት የዜጐችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን ይወጣ!!
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)

(ጥቅምት 17 ቀን 2012 ዓ/ም)

የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ክፍል አንድ አንቀፅ 14 ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሠሥ፣ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነትና የነጻነት መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት እንዳለውና በሕግ በተደነገገ ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ሕይወቱን እንደማያጣ በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 15 ላይ ሠፍሯል፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 32(1) ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ ሐገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ በመረጠው የሐገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመሥረት መብት እንዳለው በግልጽ አስቀምጧል፡፡ እንደዚሁም፣ አንቀፅ 40 (1) ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የግል ንብረት ባለቤትነት መብት አጎናጽፏል፡፡

ኢትዮጵያ የተቀበለችውና የሕጓ አካል ያደረገችው የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም ዓቀፍ ቃል ኪዳን በአንቀፅ 2 እያንዳንዱ ይህንን ቃልኪዳን የተቀበለ አገር በግዛቱ ውስጥ ለሚኖርና በሥሩ ለሚተዳደር ማንኛውም ሰው በዘር፣ በቀለም፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም ሌላ አመለካከት፣ በብሔራዊም ሆነ ማኅበራዊ አመጣጡ፣ በሀብት፣ በውልደት ወይም በሌላ መለኪያ ምንም ልዩነት ሳያደርግ በዚህ ሕግ ዕውቅና ያገኙትን መብቶችና ነፃነቶች እንዲያስከብር ግዴታ ይጥላል፡፡ በተመሳሳይ፣ ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለችው የአፍሪካ የግለሰቦችና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር አንቀፅ 1 በሠነዱ ውስጥ የተጠቀሱትን መብቶች የማክበር፣ የማስከበርና መብቶቹ የሚከበሩባቸውን ሁኔታዎች የማሟላት ግዴታ፣ በፈራሚ ሐገራት ላይ ይጥላል፡፡

እነዚህን የዜጎችን የአካል ደኅንነትና ነጻነት እንዲሁም የንብረት ባለቤትነት መብቶች የመጠበቅ ኃላፊነት በግንባር ቀደምትነት የተጣለበት መንግሥት ነው፡፡ ይሁንና እነዚህ ሐገራዊ፣ አሕጉራዊና የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች ባለመከበራቸው እና መንግስት የማስከበር ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የመብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል፡፡

~ ከጥቅምት አንድ ቀን 2012ዓ.ም ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ እስከ ጥቅምት ሁለት ቀን 2012ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት ድረስ አፋር ክልል አፋምቦ ወረዳ ‹‹ሰንጋ›› በሚባል መንደር ከሌላ አካባቢ መምጣታቸው በተገለጸ ታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት የ17 ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፣ በርካታ ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤

~ ጥቅምት 11 ቀን 2012ዓ.ም ሌሊት አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ‹‹ጥበቃ እንዲያደርጉልኝ የተመደቡልኝ የጸጥታ ኃይሎች ሊነሱብኝ ነው፡፡ ቤቴም በጸጥታ ኃይሎች ተከብቧል›› የሚል መልዕክት በማስተላለፋቸው መልዕክቱን የተቀበሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ሌሊቱን ወደ ግለሰቡ መኖሪያ ቤት አምርተዋል፤ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎችም የአክቲቪስቱ ደጋፊዎችና ተከታዮች በመሰባሰብ መንገድ ዘግተው የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል፡፡ ይህ የተቃውሞ ሠልፍ ወደ ግጭት አምርቶ የበርካታ ዜጐች ሕይወት ጠፍቷል፣ በብዙዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል፣ ግምቱ ያልታወቀ ከፍተኛ ንብረት ወድሟል፣ የዜጐች ያለሥጋት የመንቀሳቀስ መብታቸው ተገድቧል፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ባንኮች፣ የንግድ ድርጅቶችና ት/ቤቶች ተዘግተዋል፡፡

ይህ አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ እስከሚሆንበት ሰዓት ድረስ ኢሰመጉ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ ምንጮቹ በሰበሰበው መረጃ መሠረት ግለሰቡ ያስተላለፉትን መልዕክት ተከትሎ በተነሣው ተቃውሞና በተፈጸመው ብሔርና ሃማኖት ተኮር ጥቃት በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን፣ በሐረር ከተማ፣ በአወዳይ ከተማ፣ በድሬዳዋ ከተማ፣ በአዳማ፣ በባሌ ዞን ዶዶላ ወረዳ፣ በአምቦ ከተማ፣ በአርሲ ዞን ኮፈሌ ወረዳ፣ በዝዋይ ከተማ፣ አርሲ ነጌሌ፣ በባሌሮቤ በድምሩ ቁጥራቸው ከ67 በላይ ሰዎች መገደላቸውን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ በርካታ የንግድ ድርጅቶች መቃጠላቸውን፣ በብዙ ከተሞች የንግድ እንቅስቃሴና ተቋሞች ተዘግተው መዋላቸውን አረጋግጠናል፡፡ ከሟቾቹ ውስጥ በርካቶቹ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በድንጋይ እና በዱላ ተወግረው መገደላቸው ሁኔታውን ይበልጥ አሰቃቂ አድርጐታል።

ኢሰመጉ የቆመው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መዳበር፣ ለሕግ የበላይነት መስፈንና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ነው! EHRCO stands for Democracy, the rule of Law and the respect of Human Rights. በተጠቀሱት ሥፍራዎች እና በሐገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ ከሚፈጠሩ ሁከቶች ጋር ተያይዞ ብሔርን እና እምነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችና ግጭቶች በዜጎች ላይ ሲፈጸሙ ተስተውለዋል። ይሁን እንጂ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደተስተዋለው ሁሉ የዞንና የወረዳ አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም የጸጥታ አካላት በሕግ የተጣለባቸውን ለዜጎች ጥበቃ የማድረግ ግዴታ ባለመወጣታቸውና በፍጥነት ድርጊቶቹን ባለመቆጣጠራቸው ችግሩ በከፍተኛ መጠን ተባብሶ ወደ ከፍተኛ ቀውስ እያመራ ይገኛል። መንግሥት በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች መሠል ድርጊቶች ሲፈጸሙ በዝምታ መመልከቱ፣ የድርጊቶቹን አነሳሾች እና ፈጻሚዎች በሕግ ፊት ተጠያቂ ባለማድረጉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ክቡር ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ አካላቸው ጐድሏል፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተሰድደዋል፣ ዜጐች ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተዳርገዋል፣ የሕዝቡ ተቻችሎ እና ተከባብሮ የመኖር ዕሤቶችን እንዲሸረሸር አድርጓል።

ይህ መግለጫ በሚጠናቀርበት ወቅትም ዜጎችን ብሔርና ሃይማኖትን መሠረት ላደረጉ ጥቃቶችና ግጭቶች ዒላማ የሚያደርጉ መልዕክቶች በማኅበራዊ ድረ ገጾች በስፋት እየተሰራጩ ይገኛሉ።

በተጨማሪም፣ በኦሮሚያ ክልል በባሌ ሮቤ እና በዶዶላ ወረዳዎች ለኢሰመጉ በስልክ በደረሰው መረጃ መሠረት አሁንም ተጨማሪ ጥቃት ለመፈጸም በጥቃት አድራሾቹ እየተዛተባቸው እንደሚገኝ፤ በዚህም ምክንያት ለሕይወታቸው በመሥጋት ከአራት ሺ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በሁለት አብያተ ክርስትያናት ተጠልለው እንደሚገኙና በርካቶችም በቤታቸው ውስጥ በፍርኀትና በጭንቀት የድረሱልን ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡
እንዲሁም፣ በድሬዳዋ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ሃይማኖትንና ብሄርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በስፋት እየተፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ ይህ መግለጫ በሚጠናቀርበት ወቅትም የከተማዋ ነዋሪዎች በከፍተኛ ሥጋትና ፍርኀት ውስጥ እንደሚገኙ፣ ከሌላ የሐገሪቱ አካባቢዎች የመጡና ጥቃቱን የሚፈጽሙ ወጣቶች የጦር መሣሪያዎች እና ድምፅ አልባ የስለት መሣሪያዎች የታጠቁ እንደሆኑ ከአካባቢው ለኢሰመጉ እየደረሱ ያሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የሐገር መከላከያ ሠራዊትም ግጭቱን ለመቆጣጠር ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ምንጮቻችን አረጋግጠዋል፡፡

መንግሥት ለእነዚህም ሆነ ለተመሳሳይ ድርጊቶች ሕጋዊ እና የማያወላውል እርምጃ በመውሰድ የዜጐችን በሕይወት የመኖር፣ አካላዊ ደኅንነት እና በፈለጉት የሐገሪቱ አካባቢዎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው የመኖር መብታቸውን እንዲያከብር እና እንዲያስከብር ኢሰመጉ በድጋሚ ያሳስባል።

በተጨማሪም መንግሥት፡-
~በተለያዩ የብዙኃን መገናኛ ዘዴዎች አማካይነት ዜጎችን ለጥቃትና ለግጭት የሚያጋልጡ ቀስቃሽ መልዕክቶችን የሚያሠራጩ አካላትን እንዲቆጣጠር፣
~ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ድርጊቱን ባነሣሡና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በፈጸሙ ግለሰቦችና አካላት እንዲሁም ይህንን የመከላከልና የመቆጣጠር በሕግ የተጣለ
ባቸውን ኃላፊነት ሳይወጡ በቀሩ የፀጥታ ኃይሎች እና የመንግሥት ኃላፊዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ፣
~ጉዳዩ ተጣርቶ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው፣ ለሟች ቤተሰቦች፣ ቤት ንብረት ለወደመባቸውና ለተፈናቀሉ ዜጎች ካሣ እንዲከፍል እንዲሁም ሰብዓዊ ድጋፍና ርዳታ የሚያገኙበትን መንገድ እንዲያመቻች፣
~በክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በስፋት የሚስተዋለው የአክራሪ ብሔርተኛነት አስተሳሰብን መሠረት ያደረጉ ኢ-መደበኛ ቡድኖች እያደረሱ ያሉትን ጥፋት ለማስቆም የሚያስችል አስቸኳይ መፍትሄ በመስጠት ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ፣
~በፌዴራል መንግሥት አካላትና በክልል መስተዳድሮች መካከል ያለው ግንኙነት ሕግን መሠረት ያደረገና የሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት ያስከበረ መሆኑን እንዲያረጋግጥ፣
~በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አካላት ፖሊቲካዊ ቁርጠኛነቱ ኖሯቸው የዜጎችን ሕይወትና የአገርን ሕልውና አደጋ ላይ የሚጋርጡ የጅምላ የወንጀል ድርጊቶችን እንዲያስቆሙ፣
~ግለሰቦችም በተለያዩ ሚዲያ እየተሠራጩ የሚገኙትንና ሕዝብን ለግጭትና ለጥቃት የሚያነሣሡ ንግግሮችና የሐሰተኛ መረጃ ከመፈብረክና ሳያመዛዝኑ ከማሠራጨት በመቆጠብ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ፣ በየአካባቢው የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲቃወሙና ድርጊቶቹን እንዲከላከሉ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ /ኢሰመጉ/ ለሕግ ልዕልና፣ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የቆመ ድርጅት ነው፡፡
ሁሉም መብቶች ለሁሉም!!

ኢሰመጉ በአፍሪካ የሕዝቦችና የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የታዛቢነት ቦታ አለው፤ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ፌዴሬሽን (FIDH) አባል፣ የዓለም ዓቀፍ ጸረ-ሥቃይ ድርጅት (OMCT) አባልና የምሥራቅና የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ጥበቃ ኅብረት (DefendDefenders) መሥራች አባልም ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚቴ አስችኳይ መግለጫ

October 27, 2019

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚቴ አስችኳይ መግለጫ