የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)

Ethiopian People’s Revolutionary Party (EPRP)

ስለ ወቅታዊው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ

ፓርቲ (ኢሕአፓ) የተሰጠ መግለጫ

ኢትዮጵያ በታሪክ ሂደት ውስጥ እጅግ በጣም አሳሳቢ በሆነ የፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ትገኛለች። በሀገራችን ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ያለው የኃይል አሰላለፍ የዜግነት (የአንድነት) የፖለቲካ አስተሳሰብና ፅንፈኛ የብሄረሰብ ፖለቲካ አስተሳሰብ መካከል ያለው ቅራኔ ነው። የዜግነት (የአንድነት) የፖለቲካ አስተሳሰብ የሚያራምዱ ወገኖች (ኢሕአፓን ጨምሮ) የኢትዮጵያ ህልውና ተጠብቆ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማየት ሲታገሉ፣ ፅንፈኛ የብሄርሰብ ፖለቲካ አራማጆች ደግሞ ሀገሪቱን በብሄረሰብ ከፋፍለው ለመበተን እየሠሩ ነው።

በዚህ ዋነኛ በሆነው የዜግነትና የፅንፈኝነት ፖለቲካ አስተሳሰብ ትግል ውስጥ፣ ፅንፈኛ የብሄረሰብ ፖለቲካ አራማጆች ያለማቋረጥ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ተንኳሽና ጠብ አጫሪ ተግባራትን በማድረግ፣ ለዘመናት አብሮ የኖረውን ሕዝብ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ለመክተት ጥረት እያደረጉ ነው።

ፅንፈኞች በቃላት ከሚያደርጉት ማስፈራራት አንስቶ፣ እስከ ግጭት መቀስቀስ፣ መንገድ መዝጋት፣ ዝርፊያና ግድያ ድረስ ወንጀል እፈጸሙ ይገኛሉ። በፍጹም ወደ ለየለት የፖለቲካ እብደት ውስጥ እየገቡ ከሀገራችን አልፎ ለቀጠናችን ሊተርፍ የሚችል የጦርነት ድግስ እየደገሱ ነው። ራሳቸውንም እንደ ሁለተኛ መንግሥት ቆጥረው ህገወጥ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ።

በዚህ ረገድ ሰሞኑን የኦሮሞ ፅንፈኞች በአዲስ አበባና በተወሰኑ የኦሮሚያ አካባቢዎች መንገድ በመዝጋት የሕዝቡ የዕለት ተዕለት የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲገታ እያደረጉ ነው። ሽብር በሕዝቡ ላይ እየነዙ ነው። ዝርፊያ እያካሄዱ ነው። በንጹሃን ዜጎች (ሴቶችንና ህፃናትን ጨምሮ) ግድያ እየፈጸሙ ነው። የሃይማኖንና የዘር ግጭት ለመቀስቃስ በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮችና በሌሎች ብሄረሰብ ተወላጆች ላይ ጥቃት በመፈጸም ላይ ናቸው። በዚህ ጥቃት ቆሜለታለሁ የሚሉትን የኦሮሞ ተወላጆችን ጭምር በማካተት እጅግ አደገኛነታቸውን በተግባር አሳይተዋል።

ይህ በዚህ እንዳለ የኢትዮጵያ ሕዝብ በታላቅ ትዕግሥት ፅንፈኞቹን ወደ አዕምሮአቸው እንዲመለሱ ከሚያደርገው ምክር በተጨማሪ እራሱን ከነዚህ ወንጀለኞች ለመከላከል እያደረገ ያለውን ጥረት ፓርቲያችን ያደንቃል። ተደራጅተው ጥቃቱን እንዲከላከሉ ያበረታታል። የመንግሥት የፀጥታ አካላት የሕዝቡን ደህንነት መጠበቅ አለባቸው። አንዳንድ የአዲስ አበባና የክልል ፖሊሶች ሕዝቡን ለመታደግ ያሳዩት ቸልተንነት ብሎም ከወንጀለኞቹ ጋር ያሳዩት ኅብረት በጣም አሳዛኝ ነው። እነዚህ ኃላፊነት የጎደላቸው ሰዎች ለተፈጠረው ጥፋት ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል።

በአጠቃላይ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተውን ዘረፋ፣ ድብደባ ግድያና መፈናቀል በተመለከተ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የሚከተለውን አቋሙን ይገልጻል።

1. በአክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች ቀስቃሽነት የተደረገውን ጥቃት ኢሕአፓ እያወገዘ፣ ለሞቱ፣ ለቆሰሉና ለተፈናቀሉ ዜጎች ፓርቲያችን ልባዊ ሀዘኑን ይገልጻል።

2. የተፈጸመው ጥቃት በሰዎች ላይ የተፈጸመ ወንጀል (Crime Against Humanity) ስለሆነ መንግሥት ገለልተኛ አጣሪ አካል ሰይሞ ጉዳዩ እንዲጣራ፣ ወንጀለኞቹም ለፍርድ እንዲቀርቡ፣ ተጠቂዎቹም እንዲካሱ ፓርቲያችን ይጠይቃል።

3. ዜጎች በሕይወት የመኖር፣ ተዘዋውሮ የመሥራትና፣ በሰላም ወጥቶ የመግባት መብቶቻቸው አንዲከበርላቸው እንጠይቃለን።

4. መንግሥት ሕግ የማስከበር ሥራውን በአግባቡ ያልተወጣ በመሆኑ እያወገዝነው፣ ለወደፊቱ ከዚህ ዓይነት ደካማነት ራሱን እንዲያስተካክል እናሳስባለን።

5. በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ውስጥ በኦሮሚያም ሆነ በሌሎች ክልሎች እየተሰፋፋ ያለው ኢ–መደበኛ አደረጃጀት እንዲታገድና በህጋዊ አደረጃጀት እንዲተካ እንጠይቃለን።

6. የኢትዮጵያ ሕዝብ በፅንፈኛ የብሄር ፖለቲከኞችና (አክቲቪስቶች) እየተደረገበት ያለውን የጥቃት ሁኔታ በአግባቡ ተገንዝቦ የቆየ የመከባባርና የመዋደድ ባህሉን አጠንክሮ ወንጀለኞቸን በመከላከል ሥፍራ እንዳይኖራቸው እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን።

7. ሕዝብና ሕዝብን የሚያገጩና የእርስ በርስ ጦርነት ጥሪ የሚያደርጉ የፅንፈኛ አክቲቪሰት ሚዲያዎች በህግ እንዲጠየቁ፣ ሕዝቡም ለከንቱ ፕሮፓጋንዳቸው ጆሮ እንዳይሰጣቸው እናሳስባለን።

8. በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ኃላፊነት የሚሰማቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ በዚህ እጅግ አሳሳቢ በሆነ ወቅት ከሕዝቡ ጎን በመቆም ለሰላም እንዲታገሉ ጥሪ እናቀርባለን።

ኢትዮጵያን ፈጣሪ ይጠብቃት

ጥቅምት 15 ቀን 2012 ዓ.ም

Phone :0251944223216 e-mail: eprp@eprp-ihapa.com

“በመንግሥት መዋቅር ሥር ውስጥ ሆነውም ግጭቶችን የሚያባብሱ ኃይሎች እንዳሉ እናውቃለን” ኢዜማ

ኢዜማ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከሰሞኑ የተፈጠሩ ግጭቶችን በተመለከተ ትናንት ጥቅምት 18 ቀን 2012 ዓ. ም. መግለጫ አውጥቷል። መግለጫው በተለይ ጥቅምት 13 እና 14 ለደረሰው ጥፋት መነሻ ነው ካለው እና ለመንግስት አካል ማሳወቅ ሲገባው “ተከብቤያለሁ” ብሎ ለሕዝብ መረጃ ካሳራጨው ጀምሮ ጥፋት ያደረሱ ሰዎች በሕግ እንዲጠየቁ ይጠይቃል። ስለ መግለጫውና ተያያዥ ጉዳዮች የኢዜማ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀን አነጋግረናል።

ንት ኢዜማ ያወጣው መግለጫ ይዘት ምንድን ነው?

አቶ ናትናኤል፦ ስምንት ነጥብ ያለው የአቋም መግለጫ ነው ያወጣነው። ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል በተፈጠሩ ሁከቶች የሰው ሕይወት መጥፋቱና ንብረት መውደሙ እንዲሁም የተለያየ አካል ጉዳት መድረሱን መነሻ በማድረግ የተሰጠ መግለጫ ነው። አገራችን ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረግ ሽግግር ውስጥ እንደሆነች ይታወቃል። ያ ሽግግር እና የአገር አንድነትን ለማረጋገጥ ዜጎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ፍርሀት የፈጠረባቸው ኃይሎች የመጨረሻ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ የገቡበት እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን ተረድተናል።

ለጠፋ ሕይወትና ለተጎዱ ሰዎች ሀዘናችንን ገልፀን፤ ይህንን ድርጊት በመፈፀም ከመነሻው ጀምሮ ምክንያት የሆኑና በተለያየ ደረጃ ወንጀሉን ሲፈፅሙ የነበሩ ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቀናል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በተለይ እነዚህ ግጭቶችን በማባባስ ሚና ሲጫወቱ የነበሩ የሚዲያ ተቋማት ላይ ስልጣን ያለው አካል እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀናል። በተለያየ አካባቢ የተፈፀመውን ድርጊት ተከትሎ ሰዎች ቁጭት ላይ ስለሆኑ ወደ አላስፈላጊ ድርጊት እንዲሁም የመልስ እርምጃ ለመውሰድ ፍላጎት እንዳለ የሚያሳዩ ጉዳዮች ስላሉ፤ ይህ ፍላጎት በፍፁም ተግባራዊ ሊሆን እንደማይገባውና በሰላማዊ መንገድ ችግሮቻችንን ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች አሁንም መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበናል። በአጠቃላይ በአገር ላይ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም መጪው ምርጫ ጋር በተያያዘ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ውይይት በቶሎ መጀመር እንዳለበት ገልፀን፤ እዚህ ውይይትም ውስጥ ለመሳተፍ ያለንን ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት የገለፅንበት ነው።

በመፈናቀል፣ በድርቅ እና ሰሞኑን ባጋጠመው የአንበጣ መንጋ የተመቱ አካባቢዎች እንዳሉና እነዚህ አካባቢዎች ትኩረት ማግኘት እንደሚገባቸውና ትኩረት አጥተው የበለጠ ጉዳት እንዳይደርስ በመግለጫችን ጥሪ አስተላልፈናል።

መግለጫው እንደዚህ አይነት ግጭቶች ለመፈጠራቸው ምክንያቱ ባለፉት ጊዜያት ተዘርተው ከነበሩ የዘረኝነትና የአግላይነት ፖለቲካ ለመላቀቅ ሰው በመንቀሳቀሱ ነው ይላል። እውን ምክንያቱ ይህ ነው? ለለውጥና ለአንድነት መንቀሳቀሳቸው ነው ይንን ችግር ያመጣው ብላችሁ ታምናላችሁ?

አቶ ናትናኤል፦ ባለፈው ሳምንት የተፈጠረው ነገር ከሌላው የተለየ ክስተት ነው ብለን አናምንም። ተነጥሎ የሚታይ ድርጊት ነው ብለን አናምንም። በተለያየ አካባቢ የሰው ሕይወትና ንብረት ላይ አደጋ እንዲደርስ ያደረጉ ግጭቶች ሲነሱ ቆይተዋል።

እነዚህ ሁሉ ተደምረው በአጠቃላይ ትልቁ ምስል፤ በዜጎች መካከል በዘውግ ወይም በሀይማኖት ልዩነት ለመፍጠር የሚደረገው ነገር፤ ዲሞክራሲያዊና ዜጎችን እኩል እድልና እኩል መብት የሚሰጥ ሥርዓት ለመፍጠር የሚደረገው ጉዞ ያስቀራቸው ኃይሎች በተደጋጋሚ እዚህ ጉዞ ላይ ችግር እየፈጠሩበት እንደሆነ ነው። ባለፈው ሳምንት የተከሰተው ነገር ለብቻው ተነጥሎ የሚታይ ሳይሆን የዚህ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዳንሄድ የማደናቀፍ ሙከራ አንዱ አካል ነው ብለን ነው የምናምነው።

ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ የኢዜማ መሪ ሆነው ተመረጡ

“ምን ተይዞ ምርጫ?” እና “ምንም ይሁን ምን ምርጫው ይካሄድ” ተቃዋሚዎች

መግለጫውን ለማውጣት አልዘገያችሁም?

አቶ ናትናኤል፦ መግለጫ ለማውጣት ዘግይተናል ብለን አናስብም። ጉዳዩ ተከስቶ ወዲያውኑ የሀዘን መግለጫችንን አስተላልፈናል። ጉዳዮች ላይ ተጨባጭ የሆነ ከኛ የምርጫ ወረዳ አባላት የሚመጡ ማስረጃዎችን ማሰባሰብ ነበረብን። እንዲሁ ዝም ብሎ በጨበጣ ከሚዲያዎች ላይ በሚነሱ ነገሮች ተነስተን መግለጫ መስጠት አልፈለግንም። ከራሳችን የምርጫ ወረዳዎች የሚመጡ መረጃዎችና ማስረጃዎች ለማሰባሰብ ከወሰደብን ጊዜ ውጪ ዘግይተናል ብለን አናስብም።

ኤዜማ እንዲህ አይነት ክስተቶች ሲፈጸሙመግለጫ ለማውጣት ድፍረት ያጣሲባል ይሰማል። እውን ድፍረት ታጣላችሁ?

አቶ ናትናኤል፦ እውነት ለመናገር ምንም የምንፈራው ነገር የለንም። የሚፈራው የሚመስለኝ እስር፣ መሞት ወይም ከአገር መሰደድ ነው። ኢዜማ ውስጥ ያለው ስብስብ እንደዚህ አይነት ነገሮች ይከሰታሉ ብሎ የሚፈራ እንዳልሆነ በተግባር የታየ ነው።

ከዚህ በፊት የታሰሩ፣ የተሰደዱ፣ ሕይወታቸው ላይ ከፍተኛ አደጋ የተጋረጠባቸው ሰዎች ያሉበት ነው። ለነጻነትና ለእኩልነት እንዲሁም ለዴሞክራሲያዊ ትግል ሲባል። ኢዜማ ውስጥ ያሉት በተግባር የተፈተኑ ሰዎች ናቸው። የሚነሳው ወቀሳ አግባብ ነው ብዬ አላምንም።

እኛ ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የምንሰጠው የአገር ሰላም፣ አንድነትና እኩልነትን ነው። ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የምናደርገው ሽግግር ትዕግስተኛነትና የሰከነ የፖለቲካ ጉዞ ይፈልጋል ብለን በማመን፤ ግጭትን ከሚያነሳሱ እና ኃይለኝነት ከሚያሳዩ ንግግሮች እንቆጠባለን። ያ ምናልባት በስህተት ከፍርሀት ተወስዶ ከሆነ መታረም አለበት ብለን ነው የምናምነው።

የኢዜማ መሪ ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ በተደጋጋሚ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋርተጋብዘው እንደሚወያዩና ከመንግሥት ጋር ያለው ቅርርብ ፓርቲውን ድፍረት እንዳሳው ይነገራል።

አቶ ናትናኤል፦ ፕ/ር ብርሀኑ ከዚህ በፊት የፖለቲካ ታሪካቸው ምን እንደነበረ ለሚያውቅ ሰው አንድም ውሀ የሚቋጥር አይደለም። በተደጋጋሚ እንዳልነው ኢዜማ እንደ ፓርቲ ከመንግሥት ጋርም ይሁን ከየትኛውም የፖለቲካ ኃይል ጋር አገርን በማረጋጋትና ሰላም እንዲመጣ እንዲሁም ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገው ሽግግር ሰላማዊ እንዲሆን ከሁሉም አካላት ጋር ይሠራል። የአገር አንድነት ላይ አደጋ ሲመጣ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገው ሽግግር አደጋ ውስጥ ሲወድቅ፤ ምንንም፣ ማንንም ፈርተን ወደ ኋላ የምንል አይደለም። የፓርቲያችን መሪ ፕ/ር ብርሀኑ ለዚህ ጉዳይ በተግባር የተፈተነ ተሞክሮ ያላቸው ሰው ናቸው።

አሳሳቢው የሕገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች ዝውውር በኢትዮጵያ

የባልደራስ፣ የአብን አባላትና የብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ ባለቤት ተፈቱ

በመግለጫው ላ ካስቀጣችሁት ነጥብ አንዱ “ተከብቤለሁብሎ ለሕዝብ መረ ካሰራጨው ጀምሮ ሌሎች ጉዳት ደረሱ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ ነው። እነዚህ አካላት እነማን ናቸው?

አቶ ናትናኤል፦ ይሄ ችግር ሲነሳ ከምን እንደተነሳ ሁሉም ሰው ያውቃል። በማኅበራዊ ድረ ገጽ አደጋ ሊደርስብኝ ነው የሚል መረጃ ያሰራጩ ሰው አሉ። ከዛ ግለሰብ አንስቶ ይህንን ጥሪ ተከትሎ በየደረጃው የወንጀል ተግባር የፈጸሙ በሙሉ ተጣርቶ ለፍርድ እንዲቀርቡ ነው ጥያቄ ያቀረብነው።

ይሄ ለግጭቱ መነሻ ነው ብላችሁ ታምናላችሁ?

አቶ ናትናኤል፦ ሌላ ምንም የተከሰተ ነገር የለም። ይሄ ነገር ከተከሰተ በኋላ ነው በቀጥታ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ግጭቶች የተነሱትና በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ አደጋ የደረሰው። ምንም ቢሆን ደህንነቴ አደጋ ውስጥ ገብቷል ብሎ የሚያስብ ሰው በየደረጃው ላሉ የመንግሥት አካላት ማሳወቅ እንጂ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ግጭትን በሚያነሳሳ ሁኔታ እንደዚህ አይነት ጥሪ ማድረግ አለባቸው ብለን አናምንም። ስህተት ነው። ለዛ ተጠያቂነት ሊኖር ይገባል ብለን ነው የምናምነው።

ማንን ነው የምትሉት?

አቶ ናትናኤል፦እሱ በጣም ግልጽ ነው ብለን ነው የምናምነው። ግን በተጠየቅን ጊዜ የመንግሥት አካል ማንን ነው ያላችሁት? ብሎ ካለን ከማስረጃ ጭምር ለማቅረብ ዝግጁ ነን።

አሁን ላይ ስም መጥቀስ አልፈለጋችሁም?

አቶ ናትናኤል፦ አዎ። ይቆየን።

የኢዜማ የወጣቶች አደረጃጀት አዳማ ላይ ቄሮ የተባውን ቡድን ለመመከት ጉዳት አድርሷል የሚል ክስ ይቀርባልህ አይነት አደረጃጀት አላችሁ?

አቶ ናትናኤል፦ እኛ በ400 የምርጫ ወረዳዎች በሰላማዊ መንገድ ተወዳድረው የመንግሥትን ስልጣን ለመያዝ የሚሠሩ የምርጫ ወረዳ አደረጃጀቶች አሉን። አዳማ የተለየ አይደለም። በማንኛውም መልክ ከሰላማዊ መንገድ ውጪ የሚደረጉ ነገሮች እኛ አደረጃጀት ውስጥ አይሳተፉም። ይህንን ለማረጋገጥ ደግሞ ፓርቲያችን ከመመስረቱ በፊት በ312 የምርጫ ወረዳዎች በጋራ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተፈራረሙበትን የሥነ ምግባር የቃል ኪዳን ሰነድ ጭምር አሰልጥነናል።

ኢዜማ በጣም ብዙ ነገር ነው የሚባለው። ግጭት አስነሳ የተባለው የቅርብ ክስ ከነዚህ አንደኛው ነው። መሰረተ ቢስ የሆነ ክስ ነው። ከዚህ በፊትም የተለያዩ ነገሮች የተባለ ፓርቲ ነው። ይህ ለምን እንደሆነ እናውቃለን። ምን ፈርተው እንደዚህ አይነት ክስ እንደሚያቀርቡ እናውቃለን። በዋነኛነት ማኅበረሰቡ እንዲረዳ የምንፈልገው እኛ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተወዳድረን ስልጣን መያዝ ነው አላማችን። ከዛ በፊት ቅድሚያ ሰጥተን የምንሠራው ለአገር መረጋጋትና ሰላም ነው። አባሎቻችን ለሰላምና መረጋጋት ይሠሩ እንደነበር በማስረጃ አስደግፈን ማቅረብ እንችላለን።

“በኢትዮ ቴሌኮም ኃላፊ ግድያ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለ የለም” የነቀምቴ ፖሊስ አዛዥ

“በእግር ወይም በአውሮፕላን እያሉ ወሬ ማብዛቱ ትርጉም አልባ ነው” አምባሳደር እስቲፋኖስ

ስለዚህ አልተሳተፋች?

አቶ ናትናኤል፦ በፍጹም እንደዚህ አይነት ጉዳይ ላይ ተሳትፎ አልነበረንም።

ከዚህ በፊትም እንደዚህ አይነትየሰው ሕይወት ለፈባቸውግጭቶች በተለያዩ አካባቢዎች ነበሩኢዜማለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ማነው ይላል?

አቶ ናትናኤል፦ በየቦታው ለተፈጠሩ ችግሮች የየራሱ የሆነ ተጠያቂ አካል ይኖራቸዋል። በተለይ ድርጊቱን በመፈጸም የተሳተፉ አካላት የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ። በዋነኛነት ተጠያቂ የሚሆኑት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እና ዜጎችን በእኩልነት የሚያይ የፖለቲካ ሥርዓት መመስረት ሂደት ላይ እንቅፋት ለመጣል የሚፈልጉ ኃይሎች ናቸው። መንግሥትም ይሄን ከፍ ያለ ትኩረት ሰጥቶ ተጠያቂዎችን ለሕግ ማቅረብ አለበት ብለን ነው የምናምነው።

በመግለጫውመንግሥት አለበት ያላችሁትን ክፍተት ስላነሳችሁ ነው ይህንን ጥያነሳሁት

አቶ ናትናኤል፦ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገው ሽግግርና ዜጎችን በእኩልነት የሚያይ የፖለቲካ ሥርዓት እንዳይመሰረት እንቅፋት የሚሆኑት የውጪ ኃይሎች ማለት ከመንግሥት ውጪ ያሉ ኃይሎች ብቻ ሳይሆን፤ በመንግሥት መዋቅር ሥር ውስጥ ሆነውም ግጭቶችን በማባባስ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የምናደርገውን ጉዞ ለማስተጓጎል ሙከራ እያደረጉ ያሉ ኃይሎች እንዳሉ እናውቃለን።

እነዚህ ኃይሎች ደግሞ ከዚህ በፊት ማኅበተሰቡን ሲበድሉ የነበሩና እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ቢመጣ ማኅበረሰቡ ሥልጣን እንደማይሰጣቸው ያረጋገጡ ኃይሎች ናቸው። እነዚህ ኃይሎች የሚያባብሱት ግጭት ራሳቸውን ችግር ውስጥ ከመክተቱ በፊት፣ ራሳቸውን አደጋ ላይ ከመጣሉ በፊት እንዲያቆሙ ነው መልዕክት ያስተላለፍነው።

እነዚህ ኃይሎች እነማን ናቸው?

አቶ ናትናኤል፦ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሰዎችን ጨምሮ ተጠያቂ መሆን ያለባቸው ኃይሎች ናቸው።

በመግለጫውለግጭት የሚያነሳሱ መልዕክቶች የሚተላለፉባቸውማኅበራዊ ድረ ገጾችና ሚዲያዎችን የተመለከተ ሀሳብአንስታችኋል። የለያችኋቸው ሚዲያዎች አሉ?

አቶ ናትናኤል፦ በሕግ ሥልጣን የተሰጠው አካል የእርምት እርምጃ እንዲወስድ ነው የጠየቅነው። ይህ አካል በጠየቀን ጊዜ አሁንም በማስረጃ አስደግፈን የምንሰጥ ይሆናል።

ኢዜማ መግለጫ ከማውጣት ባሻገር በተግባር ምን እየሠራ ነው?

አቶ ናትናኤል፦ በሚቀጥለው ምርጫ በሰላማዊ መንገድ ተወዳድረን አሸንፈን የመንግሥትን ስልጣን ለመያዝ አደረጃጀታችንን በማስፋትና በማጠናከር ሂደት ላይ ነው የምንገኘው። በየጊዜው በምርጫ ወረዳዎቻችን ባደራጀንባቸው ቦታዎች ላይ የተለያዩ ስልጠናዎችን እየሰጠን፤ አደረጃጀት በሌለባቸው ቦታዎች ደግሞ ተደራሽነታችንን እያሰፋን እየሄድን ነው።

የፖሊሲ አማራጭ የሆኑ ዶክመንቶችን እየቀረጽን ነው የምንገኘው። ከዚህ ባለፈ ግን ከፍተኛ ትኩረት የምንሰጠው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ነው። አባላቶቻችን እና አባላቶቻችን የሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ያሉ የማኅበረሰብ አካላትን ከማንኛውም ሰላምና መረጋጋትን ከሚያውክ ተግባር ራሳቸውን እንዲያቅቡና እንዲከላከሉ፤ ማኅበረሰቡንም አስተባብረው እንደዚህ አይነት ችግሮች እንዳይከሰቱ እያስተባበርን፣ እያስተማርን፣ እያደራጀን ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያን ለማቆየት፣ ኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ ፍላጎት ያላቸው የሙያ ማኅበራት፣ የሀይማኖት ተቋሞች፣ መንግሥት እና ሌሎችም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ውይይት ማድረግ አለብን ብለን እናስባለን። ያንን ውይይት በቅርቡ አዘጋጅተን የምናደርግ ይሆናል።

”መንግሥት ከደረሰው ጥፋት ተምሮ ሕግ ማስከበር ካልቻለ ሌላ ዙር ጥቃቶች ላለመፈጸማቸው ማረጋገጫ የለም,”የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

October 30, 2019

መንግሥት በተግባር ሕግ እንዲያስከብር ጥያቄ እየቀረበለት ነው

ሪፓርተር

በኦሮሚያ ክልል ከ350 በላይ ተጠርጣሪዎች ታስረዋል

ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል ባጋጠሙ ጥቃቶችና ግጭቶች የ67 ሰዎች ሕይወት ካለፈ በኋላ ሰሞኑን አንፃራዊ መረጋጋት በተፈጠረባቸው አካባቢዎች፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መንግሥት ሕግ እንዲያስከብር ጥያቄ እያቀረቡ ነው፡፡ መንግሥት ሕግ ለማስከበር ቃል ከመግባት ባለፈ በተግባር እንዲያረጋግጥ ጥያቄ እየቀረበለት ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጥቅምት 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ባስተላለፉት መልዕክት፣ ‹‹የሕግ የበላይነት ለማረጋገጥና አጥፊዎች በሕግ ፊት ቀርበው ተገቢውን ሁሉ እንዲያገኙ ያለማወላወል እንሠራለን፤›› ካሉ በኋላ፣ በርካቶች የመንግሥትን ዕርምጃ እየጠበቁ ነው፡፡

መንግሥት ሕግ እንዲያስከብር ጥያቄ ካቀረቡለት የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ የሐረር ከተማ ነዋሪዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ሰኞ ጥቅምት 17 ቀን 2011 ዓ.ም. በሐረሪ ክልል በሐረር ከተማ በተካሄደ ውይይት፣ ከተለያዩ የእምነት ተቋማትና የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ተሳታፊዎች ሰላም በሚያደፈርሱ አካላት ላይ መንግሥት ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድ አለበት ብለዋል፡፡ ጥቃቶች እየተፈጸሙ ያሉት ሕግ ባለመከበሩ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

የተለያዩ ሃይማኖቶችን በመወከል የተገኙ አባቶች ብሔርና ሃይማኖትን በመከለል በነዋሪዎች መካከል ለዓመታት የተገነባውን የመቻቻልና በሰላም አብሮ የመኖር እሴቶችን የሚንዱ አካላት፣ በአስቸኳይ በሕግ መጠየቅ አለባቸው ብለዋል፡፡

በሐረሪ ክልል ሰላምና መረጋጋት እንዲኖርና በተለያዩ የእምነት ተከታዮች መካከልም በሰላም አብሮ መኖር እንዲቻል፣ የሚፈለግባቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ገልጸው፣ መንግሥት ደግሞ ሕግ የሚጥሱትን ለሕግ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል፡፡ ይህንን ጥያቄያቸውንም መንግሥት በፍጥነት እንዲመልስላቸው ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አርዲን በድሪ በበኩላቸው ሃይማኖትንና ብሔርን በመከለል ሃይማኖታዊ ግጭት ሲቀሰቅሱ የነበሩ አካላት እንዳሉ አስታውቀው፣ የሃይማኖት መሪዎች የእነሱ መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ማሳሰባቸውን፣ የክልሉ መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሐረሪ፣ በድሬዳዋና በአካባቢው አንፃራዊ ሰላም መኖሩ የታወቀ ሲሆን፣ ለበርካቶች ሕልፈትና ለንብረት ውድመት የዳረጉ ጥቃቶች ካሁን በኋላ እንዳይፈጸሙ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር እንደሆነ ነዋሪዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ከደረሰው ጥፋት ተምሮ ሕግ ማስከበር ካልቻለ ሌላ ዙር ጥቃቶች ላለመፈጸማቸው ማረጋገጫ የለም ብለዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ አርሲና በባሌ ዞንም አንፃራዊ ሰላም መስፈኑ ታውቋል፡፡ ባለፈው ሳምንት በተለይ በዶዶላ፣ በባሌ ሮቤና በተለያዩ ሥፍራዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካቶች ተገድለው በንብረት ላይም ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል፡፡ በአካባቢዎቹ አንፃራዊ ሰላም ከተፈጠረ በኋላ አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ ለመንግሥት ጥሪ እየቀረበ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት በሌለበት ዋስትና እንደሌላቸው የጥቃት ዒላማ የነበሩ ወገኖች አሳስበዋል፡፡

ሪፖርተር ከባሌ ሮቤ ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በአሁኑ ጊዜ አንፃራዊ መረጋጋት በመፈጠሩ ኅብረተሰቡ በተለያዩ ቀበሌዎች ውይይት እያደረገ ነው፡፡ በውይይቱ ወቅት ከፍተኛ ትኩረት ያገኘው መንግሥት ሕግ ማስከበር እንዳለበት ነው፡፡ በተጨማሪም ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች በፍጥነት ተቋቁመው ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲመለሱ ማድረግ ይገባል ተብሏል፡፡

በሮቤ ከተማ ተዘግተው የነበሩ የንግድ መደብሮች፣ ሆቴሎችና ባንኮች ተከፍተው ሥራ መጀመራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በጥቃቶቹ ወቅት የተፈጸሙ ግድያዎችን፣ ዘረፋዎችንና የንብረት ውድመቶችን የሚያጣሩ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ሥራ እንዲጀምሩ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ከአካባቢው ምንጮች ለመረዳት ተችሏል፡፡

ሰኞ ጥቅምት 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ከኦሮሚያ ክልል አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት መሪዎችና ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክልል ተወካዮች ጋር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባደረጉት ውይይት፣ መንግሥት ሕግ ማስከበር እንዳለበት ጥያቄ መቅረቡ ተሰምቷል፡፡ በተለይ ሐሰተኛ መረጃዎች በማሠራጨት ችግር እየተፈጠረ መሆኑ ተገልጾ፣ ለአገር ደኅንነት የሚቆረቆሩ ካሉ ሕግ ማስከበር ተቀዳሚ መሆን አለበት መባሉ ታውቋል፡፡

በአዲስ አበባም ሆነ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለመገናኛ ብዙኃን አስተያየታቸውን የሰጡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ መንግሥት ሕግ እንዲያስከብር እየጠየቁ ነው፡፡ ሕግ ካልተከበረ በሰላም ወጥቶ መግባት ብቻ ሳይሆን፣ የአገር ህልውናም ለአደጋ እንደሚዳረግ ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለው በአብያተ ክርስቲያናትና በሌሎች ሥፍራዎች የተጠለሉ ወገኖች፣ መንግሥት በተጨባጭ ሕጋዊ ዕርምጃ ካልወሰደ ለሕይወታቸው እንደሚፈሩ እየተናገሩ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት መንግሥት ሕግ ያስከብራል ማለታቸውን በማስታወስ፣ በተግባር እንዲያሳዩዋቸውም ጠይቀዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን፣ በክልሉ ውስጥ አጋጥመው በነበሩ ጥቃቶችና ግጭቶች ሳቢያ 359 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል፡፡ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጠርጣሪዎች ማንነት በዝርዝር አልተገለጸም፡፡ ነገር ግን በቁጥጥር ሥር የሚውሉ ተጠርጣሪዎች ቁጥር ሊጨምር ይችላል ተብሏል፡፡ በዚህም ምክንያት የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ እየሠራ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ሰሞኑን ግጭቶችና ጥቃቶች የነበሩባቸው ሥፍራዎች ሰላም ወደነበረበት መመለሱን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

የመንግስትን ትዕግስት እንደ ፍረሃት በመውሰድ አንዳንድ ግለሰቦች እራሳቸውን እንደገዥ በመቁጠረ በበረካታ ንፁሃን ዜጎች ሞት ምክንያት ሆነዋል- የኢፌድሪ መከላከያ ሰራዊት

October 28, 2019

ከዚህ ሰዓት ጀምሮ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የኢፌድሪ መከላከያ ሰራዊት የሃይል እረምጃ እንዲዎስድ ትዕዛዝ ተሰጥቷል!

የመንግስትን ትዕግስት እንደ ፍረሃት በመውሰድ አንዳንድ ግለሰቦች እራሳቸውን እንደገዥ በመቁጠረ በበረካታ ንፁሃን ዜጎች ሞት ምክንያት ሆነዋል።ይህን የመካከለኛው ምስራቅ የሽብረ ተለዕኮ እና የጠላት ሃገረ ተልዕኮ ለማስፈፅም በሚሊዮን ዶላሮች እየተቀበሉ ሃገራችንን ሰላም ማሳጣት ተልዕኮ አድረገው ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል።

መንግስትም ጉዳዩን በህቡዕ ሲከታተለው ቆይቷል።መከላከያ ሃይል ከመላው የፅጥታ አካል ጋረ በመሆን እነዚህን አፍራሽ ተልዕኮ ያነገቡ ቡድኖችን ፍቃደኛ የሆኑትን በሰላም ለህግ ያቀረባል።ፍቃደኛ ያልሆኑትን የሃይል እረምጃ በመውሰድ ችግሮቹን ከምንጩ ለማድረቅ ይሰራል።

እስካሁን በጀሞ ፖሊስና ትቂት የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ወደላይ በመተኮስ ሰልፉ የተበተነ ቢሆንም በተለያዮ አካባቢዎችም የማያዳግም እረምጃ መውሰዱን ይቀጥላል።

መላው ሰላም ፈላጊ ህዝባችን ጥቆማዎችንና መረጃዎችን በስልክ ቁጥሮቻችንና በውስጥ መስመረ ማድረሳችሁን እንድትቀጥሉ እያሳሰብን ህብረተሰቡንና የፅጥታ ሃይሉ በመቀናጀት የምትሰሩት አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ እናሳስባለን።
በማወቅም ሆነ ባለማዎቅ በዚህ አስነዋሪ ድረጊት የተሳተፍችሁ ወጣቶች ከድሪጊቱ እንድትቆጠቡ እናሳስባለን።

የኢፌድሪ መከላከያ ሰራዊት!

መንግስት የዜጎችን ሕይወትና ደሕንነት እያስጠበቀ አይደለም ሲል መኢአድ ወቀሰ

October 29, 2019

መንግስት የዜጎችን ሕይወትና ደሕንነት እያስጠበቀ አይደለም ሲል መኢአድ ወቀሰ

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ጥቅምት 16/2012 ዓ/ም ባወጣው መግለጫ በአሁኑ ወቅት እየተፈፀሙ ያሉ ድርጊቶች ሕግና ስርዓት የሚያስከብር፣ የዜጎችን ሕይወትና ደሕንነት የሚያስጠብቅ መንግስት እንደሌለ ማሳያ ሆኗል ሲል መንግስትን ወቅሷል።

ባለፈው አንድ አመት ተኩል ብቻ ከ3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ከኖረበት ቀዬ በማንነቱ ብቻ መፈናቀላቸውን፣ በርካቶችም መገደላቸውን፣ ሀብትና ንበረታቸው መውደሙን ያወሳው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የኦዴፓ/ኢህአዴግ አመራሮች ከቀደመው የትህነግ/ኢህአዴግ ዘመን ለውጥ አድርገናል ብለው የነበር ቢሆንም የኢትዮጵያ ሁኔታ ከድጡ ወደ ማጦ ሆኗል ብሏል።

በሀገራችን ኢትዮጵያ ለተፈፀመው ማንኛው ጥፋት የአገዘዙን ተጠያቂ ያደረገው መኢአድ “አዲስ እያገረሸ ለዚህ ሁሉ መፈናቀል ፣እልቂትና ንብረት መውደም ሁለተኛው ተጠያቂ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የተቋቋሙ ሚዲያዎች 24 ሰዓት ሙሉ አንዱ የህብረተሰብ ክፍል በሌላው የአንደኛው እምነት ተከታይ በሌላኛው ላይ እንዲነሳ የሚያደርግ የጦርነት አዋጅ በሚዲያ የሚደረገው ቅስቀሳ ያስከተለው ውጤት መሆኑ ለማንኛውም ሰው የተሰወረ አይደለም።” ብሏል። መሰል ድርጊቶች ሲፈጠሩ መንግስት የዜጎችን ደሕንነት እንዲያስጠብቅ በተደጋጋሚ ወትውቻለሁ ያለው መኢአድ ሆኖም “በአገዛዙ በኩል ችግሮችን የሚያባብስ እንጂ ችግሩን ለመቅረፍ የተወሰደ አንዳች እርምጃ አላየንም።” ሲል ወቅሷል።

ከዚህ በፊት በተሰሩ ጥፋቶች በመንግስት በኩል አጥፊዎች ተለይተው በፍትህ አደባባይ ቆመው ህጋዊ ቅጣት ባለመወሰዱ ሌሎች አዲስ አጥፊዎች እየተፈጠሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሀገር ቀውስ ውስጥ እየገባች ኢትዮጵያውያን በተወለዱበት ፣ ባደጉበት፣ ሀብት ባፈሩበት ፣ ወልደው በከበዱበት በራሳቸው ሀገር በጠራ ፀሀይ በአደባባይ በዱላ ተቀጥቅጠው፣ በስለት ተቆራርጠው ሲገደሉ ህግ የሚያስከብር እና የዜጎችንን በህይወት የመኖር መብት የሚያስጠብቅ መንግስት እንደሌለ ከዚህ በላይ ማሳያ የለም ብሏል መኢአድ በመግለጫው።

በተለይ ባሳለፍነው ሳምንት በአርሲ፣ ኮፈሌ፣ ዶዶላ ሮቤ፣ በድሬደዋ፣ በሀረር፣ በናዝሬት፣ በደብረዘይት፣ በአዲስ አበባ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ ሰበታ ወለቴ አካበቢ በተፈጠረው ጥቃት በማንነታቸው ብቻ በተገደሉት ዜጎች የተሰማውን ሀዘን የገለፀው ድርጅቱ ለመከላከያና የፖሊስ አባላት፣ ለሀገር ሽማግሌዎችና ለሀይማኖት አባቶች፣ ለወጣቶች፣ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የሚገኙ ሚዲያዎች ታሪክ የጣለባችሁን ኃላፊነት መወጣት ይገባችኋል ሲል ጥሪ አቅርቧል።